ወዮ ለመከረኛው የአገሬ ህዝብ እንጅ  ታየማ ታየ ነው

January 21, 2025

January 20, 2025

ጠገናው ጎሹ

የአቤ ጎበኛው አልወለድም ለወገኖቹ መብት መከበር ሲል ባደረገው ጥረት ምክንያት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ይሙት በቃ በፈረዱበት ጊዜ በምላሳቸው መልካም  አድርጎ ስለ መገኘት እያወሩ በድርጊት ግን ተቃራኔውን የሚያደርጉ ሁሉ ክፉ ገዥዎች እንደሆኑ በምሬትና በአፅንኦት ከተናገረ በኋላ የዚህ ሁሉ ቅጥፈት ወለድ ሰለባ የሆነው ግን መከረኛው ህዝብ እንደሆነ ሲነግረን  ወዮላችሁ ተራ ህዝብ ለሆናችሁ ወገኖቼበጡንቻውና ባበጠ ቦርሳው የሚመካ ሁሉ ለባርነት ለሚያጫችሁ ምስኪኖች ወዮ!ይላል።

ከሰሞኑ የተከበረውን በዓለ ጥምቀት በተመለከተ የታዘብናቸው የሃይማኖትና የእኩይ ፖለቲካ  ሥርዓት የመደበላለቅ እጅግ አስቀያሚ እውነታ ነገረ ሥራችን ሁሉ ከይዘት (ከውስጠ ነፍስ) ይልቅ በቅርፅ (በውጫዊ “ድንቃድንቅነት”) የተሸነፈ በመሆኑ ልብ አንለውም እንጅ ለብዙ ዓመታት እና በተለይ ግን ከስድስት ዓመታት ወዲህ የመጣንበትና አሁንም የምንገኝበት ስለሆነ አዲስ ነገር አይደለም።

በእጅጉ የሚያሳዝነው ግን በመደበኛ ፀጥታ አስከባሪ ሳይሆን አገርን ለመከላከል ጦር ሜዳ መዋል በነረበት ወታደር እና ሲቪል ለባሽ ደህንነት ተብየ (ጥላ ወጊ) ተከበን ነፍስና ሥጋችን እያስጨነቅን የተገኘንበትን በዓለ ጥምቀት ዓለምን ባስደመመ የሰላምና የፀጥታ አየር አከበርነው በሚል ራሱ የጉዳዩ ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ እስከሚታዘበን የሄድንበት ርቀት ነው።  ከእንዲህ አይነት በዋናውና ፈታኝ በሆነው ፈተናችን ዙሪያ እየተሽከረከርን ራሳችንን  ከማታለል ክፉ አባዜ መቸና እንዴት እንደምንላቀቅ በእጅጉ ያሳስባል/ያስጨንቃል።

የሩብ መዕተ ዓመት ፈጣሪያዎቻቸውን ፣ አሳዳጊዎቻቸውንና ጌቶቻቸውን እኩያን የህወሃት ገዥ ቡድኖች  የበላይነት በማስወገድ ስያሚያቸውንና ቅርፃቸውን ብቻ በመቀየር የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓቱን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ማስኬድ ከጀመሩ 7 ዓመታት ሊሞላቸው ሁለት ያህል ወራት የቀራቸው ኦሮሙማዊያን/ብልፅግናዊያን ሃይማኖትን ከእኩይ ፖለቲካ መጫወቻ ካርዶቻቸው (ሜዳዎቻቸው) አንዱ አድርገውት ቀጥለዋል።  ይህ ሁሉ ሲሆን እንደ እውነተኛ የሃይማኖት መሪ እና እንደ እውነተኛ አማኝ ከምር ነውር ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነውና አስቀያሚ አንደበቶቻችሁንና እጆቻችሁን ሰብስቡ ለማለት ባለመቻላችን (ወኔው ስለ ከዳን) ይኸውና እጅግ የተቀደሱ (ፈፅሞ ሊደፈሩ የማይገባቸው) የአደባባይ ላይ ክብረ በዓሎቻችን እውነተኛ ትርጉም (ይዘት) በእጅጉ ፈተና ላይ ወድቋል።

ለዚህ አይነት ርካሽና አሳዛኝ ፖለቲካ ወለድ ድራማ መድረክ ተዋናይነት ወደ ጎንደር ከተላኩት ሰው መሰል አሻንጉሊቶች መካከል “ፕረዝደንት” ታየ አፅቀ ስላሴ አንዱ ነበር። በፖለቲካ ታሪካችን ሂደት ውስጥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እንደማነኛውም አገር የገጠሙን ስህተቶች እንዳሉ ሆነው ከመቶ ሚሊዮን በላይ ዜጎች እና የረጅም ታሪክ ባለቤት የሆነች አገራችን በታየ አፅቀ ሥላሴ አይነት ሥር የሰደደ የአድርባይነት አሻንጉሊትነት ደዌ ልክፍተኞች በፕረዝደንትነት (በርዕሰ ብሔርነት) ተሰይመው ክርስቶስ ይባርከዋል ብለን በምናምንበት ታላቁ የጥምቀት በዓላ ላይ ያፈጠጠውንና ያገጠጠውን መሪር እውነት ባፍ ጢሙ ደፍቶ የተላከበትን እጅግ አስቀያሚ፣ አሳፋሪ፣ ጨካኝና አደገኛ ፕሮፓጋንዳ “ሳያመልጣችሁ ተጠቀሙበት” በሚል ሊያሳምነን ሲሞክር ከመስማትና ከማየት የከፋ እንደ ማህበረሰብ (እንደ አገር) የሚያሳፍር (የሚያሸማቅቅ)  ነገር ይኖር ይሆን ?

እርግጥ ነው እንደ ታየ አፅቀ ሥላሴ አይነቶች አድርባይነት (ለጥቅም መስሎና አስመስሎ “ኗሪነት” ) ከደመ ነፍስ እንስሳት በታች ያወረዳቸው ወግኖች በእንዲህ አይነት አሳፋሪ ተውኔተ ፖለቲካ ተዋናይነት መገኘት ፈፅሞ የሚገርም አይደለም።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን በእጅጉ የሚያሳዝነውና የሚገርመው እንደ ማህበረሰብ (እንደ ህዝብ) እንዲህ አይነት ወገኖችን ከምር ከመፀየፍና በቃችሁ ከማለት ይልቅ ግማሾቻችን አጨብጫቢዎች የመሆናችን እና ግማሾቻችን ደግሞ ነገረ ሥራችን ሁሉ ከክስተቶች ጋር ከመሞቅና ከመቀዝቀዝ አስቀያሚ ማንነነትና ምንነት ለማለፍ አለመቻላችን ነው።

ታየማ ከትናንት እስከዛሬ እና እስከ ወዲያኛውም ያው ልክፍተኛው ታየ ነው።  ሥር የሰደደ (ከወጣትነት እስካሁን ) የዘለቀ (የገነገነ) ፍልስፍና እና ባህሪ (ደዌ) ነውና።

ለዚህም ነው ወዮ ለመከረኛው ህዝብ ማለት ትክክል የሚሆነው!

1 Comment

  1. በቅርቡ አንድ አምቦ ተወልዶ ካደገ አሁን ራሱን ኤርትራዊ ብሎ ከሚጠራ ጓደኛዬ ጋር ስለ ሃገር ቤት ጉዳይ እንጫወት ነበር። እባክህ ዝም ብል አለኝ ብስጭት ብሎ። ስማ እኛ አማራን እንድንጠላ የተሳሳተ ትርክት ተነግሮናል። አማራ የፍቅር ህዝብ ነው። አያቴ አሁን ሞቷል ጎጃም ኖሯልና ስለ አማራ አውርቶ አይጠግብም ነበር። እኔን የሚያሳዝነኝ ግን አማራው በኦሮሞው በትግሬው በኤርትራው አናሳ ጎሳ በሚባሉት ሁሉ ሳይቀር ያለ ግብሩ እንዲጠላ ተደርጓል በማለት ስሜታዊ ሆኖ ተናገረ። ሲያጠቃልልም በኦሮምኛ ተራግሞ ሃሳቡን ጨረሰ። እርግማኑን እዚህ ላይ አልደግመውም። አሁን ላይ የሚገጥሙኝ ኤርትራዊያን ሁሉ አይናቸው የተከፈተ ይመስለኛል። ተታለናል፤ ተሽውደናል፤ በጭፍን የአማራ ህዝብን እንድንጠላ መርዝ ተግተናል የሚሉ በተናጠልም ሆነ በቡድን ሰዎች ገጥመውኛል። ለዚህ መራራ መርዝ ሻብያንና ወያኔን ተጠቃሽ ያደርጋሉ እኔም በሃሳባቸው እስማማና የኦሮሞ ፓለቲከኞችንም እጨምራለሁ።
    አቤ ጉበኛ ፓለቲካና ፓለቲከኞች በሚለው መጽሃፉ ላይ እንዲህ ይለናል “ውሃን ማን ያናግረዋል ቢሉ ድንጋይ” የሚያናግር ልበ ክፍት ሰው ሲገኝ ተዳምጦ ያለፈውን መዝኖ የዛሬን ለመለየት መመከር አማራጭ አይገኝለትም። ባህር ተሻግረው የመጡ ቅኝ ገዥዎችና ሃገር በቀል ከሃዲዎች ዛሬ ኢትዮጵያ ለገባችበት የማጥ ውስጥ የፈጠራ ትርክት ምክንያቶች ናቸው። የሃገራችን ፓለቲካ ሰውን እየበላና እያስበላ ህዝብን እየጨቆነና እየረገጠ ሃገር፤ ነጻነት ቢሉት ዋጋ ይብሉን። አቤን ንጉሱ በግዞት ጨለማ ቤት ሲከቱት፤ ለህዝብ ቆሜአለሁ የሚለው ደርግ ደግሞ ገድሎታል። የዛሬውንና ያለፈውን የፓለቲካችን ከንቱነት ስናስተነትን ታጋይ የነበረው ሲቆለፍበት፤ ወይም ሲገደል፤ ለሃገር ለድንበሯ የተሰዋው ቤተሰቡ ሲበተንና ሜዳ ሲወድቅ፤ አይናችን አፍጠን እያየን እግዚኦ ማህረነ ብለናል እያልንም ነው። ምህረት ግን እስከ አሁን አልታየም። 17 ዓመት ሙሉ ከወያኔ ጋር አብሬ ታገልኩ የሚለን ታምራት ላይኔ በፈጠራ ክስ 17 ዓመት ነበር የተፈረደበት። ስዬ አብርሃ ስንቱን እንዳላበራየ እሱም ዘብጥያ ወረደ። ይህ ደግሞ የፓለቲካችን ከንቱነት ያሳያል። እድሜ ለአሜሪካ አሰስ ገሰሱን የምታግበሰብስ ሃገር ደም አፍሳሹን ሁሉ መጠለያ እየሰጠች ይኸው እልፍ አስጨርሰው በሚሊዪን ዘርፈው እፎይ ብለው ከስብሃት ነጋና ከመሰሎቻቸው ጋር ይኖራሉ። የትግራይ ህዝብ ግን አሁንም በመከራ ውስጥ ይገኛል።
    በአንድ ወቅት አቤ ጉበኛን ሰፊ ህዝብ ማለት ምን ማለት ነው ተብሎ ተጠይቆ ሲመልስ ” ሞቶ የማያልቅ” ማለት ነው ብሎ ነበር። አቤና መሰለቹ በዘመናቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ ብሄር፤ ሃይማኖት፤ ጎሳና ነገድ ሳይለዪ ለመብቱ ታግለዋል። የገደሏቸውና ያስገደሏቸው ዛሬ የሉም። አሉ ከተባለም መኖር አይሆንም። ዛሬ ላይ ቆመን በዚያ ዘመን የተፋለሙትን እውነተኛ የሃገሪቱን ልጆች ከወታደሩም ሆነ ከተማሪውና እንዲሁም ከሲቪሉ ክፍል ተግባራቸውን ስንመረምር ምን ያህል ከጊዜአቸው የቀደሙ እንደሆኑ ለማየት ይቻላል። እኛ ዛሬ የት ላይ ቆመናል? ማንን ደግፈን እነማንን ገፍትረናል? ኢትዮጵያን ማጥ ውስጥ ለመክተት እሳት እያቀበሉና በዓለም መድረክ እያጥላሉ ያለ ስሟ ስም የሰጧት ሁሉ ዛሬ የድንጋይ ክምር ናቸው። ሊቢያ፤ ሶሪያ፤ ኢራቅ፤ ሱዳን፤ ሌሎችም የጊዜ ጉዳይ እንጂ አይቀሬ ነው። በየሄድኩበት ሁሉ ከኢትዮጵያ ነህ ከኤርትራ ለሚሉኝ ሱማሌዎች የእጃቸውን ሊያገኙ ቀኑ ቀርቧል። እኔም በተራዬ ከመቃዲሾ ወይስ ከሃርጌሳ ልላቸው ነው። የመከፋፈል ጥቁሙ እልቂት ነው። ኢትዮጵያ ማንንም ቅኝ ግዛት አርጋ አታውቅም። ልታደርግም አትችልም። የቅኝ አገዛዝ መስፈሪያው ያልፋታልና! ግን የቱልቱላው ፓለቲካ እውነትን ለመመርመር ጊዜ አሰጥም። ከነጎደው ጋር አብሮ መንጎድ! አይ መኖር ባዶ ህይወት፤ ቅል ራስ ይዞ መወዛወዝ! ኦ ሰው መሆን፤ ስንት አይተን ስንቱን እያየን አለን። ግን አንዴ ኢትዮጵያዊ/ት ሆነን ተወልደናልና ተስፋ አንቁረጥ።

    ባዘቅት ይመሰላል የሰው ልጆች ጠባይ
    ጨለማ የሆነ ስሩም የማይታይ
    በጥልቀቱ መጠን ወደታች ሲሰጥሙ
    ያላሰቡት ነገር ይታያል በውስጡ ( ከበደ ሚካኤል)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

አማራ ፋኖ አነጋጋሪው የኤርትራ ሙዚቃ Nahom Yohannes New Eritrean Music

Next Story

ስለ ጃዋርና ኢትዮጵያ (ክፍል ሁለት)

Go toTop