አሳሳቢው ግድያና አሉታዊ ተፅዕኖው

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ከሚዲያም ከነፃነት ትግሉም ርቀው በተደበቁበት በአሁኑ ወቅት መጻፍ ብዙም ዋጋ እንደሌለው አውቃለሁ፡፡ ይሄ አቢይ የሚባል ጭራቅ ከመጣ ወዲህ አብሶ ሚዲያዎችን በተስፋ መቁረጥ ዱላ ቀጥቅጦ ገደላቸውና ለዕለት ጉርስና ላመት ልብስ ከመሯሯጥ በዘለለ ለሀገር የሚጨነቀውና የሚታገለው ዜጋ ቁጥር እጅጉን እየቀነሰ ነው፡፡ ለሀገራቸው ቅን አሳቢ ethioreference.comንና zehabesha.comን የመሰሉ ጥቂት ድረገፆች ቢኖሩንም አንባቢያን እንደዱሮው አይደሉም፡፡ ለማስታወስ ያህል ነው ያለንበትን አንዱን ገጽታ፡፡

ስለገዳዮች የምለው ስላለኝ ነው ብዕሬን አሁን ያነሳሁት፡፡

ገዳዮች ሆይ!!

አሁን ካላችሁ ዕድሜ ላይ 50 ወይ 60 ዓመታትን ደምሩበት፡፡ ያኔ በምድር ላይ የመኖራችሁ ዕድል ከዜሮ እስከ አንድ መቶኛ ቢሆን ነው፡፡ አሁን በዚህች ምድር ላይ ከምንገኝ ጎልማሦችና ወመሾች መካከል ከ50 እና 60 ዓመታት በኋላ በሕይወት የምንገኝ ካለን እንደተዓምር ይቆጠራል፡፡ የምንገኝ ብንኖር እንኳን ምግብ ከመቅመስና ልብስ ከመልበስ ባለፈ ምንም ዓይነት ሥጋዊ ፍላጎት የማይኖረንና የማንፈለግም ነን፡፡ ለዚህች ዕድሜ ነው እንግዲህ አሁን በተለያዬ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ አብደንና ሰክረን እየተፋጀን ያለነው፡፡

ከቀ.ኃ.ሥ መንግሥት አንድ ዘጠኝ ወይ አሥር ዓመታት ያህል አሉኝ፡፡ በደርግ የመጨረሻ ዓመታት ግድም ነው ለአቅመ አዳምም ለአቅመ ሥራም የደረስኩት፡፡ አቅሜ በፈቀደ መጠን በማንበብና በመስማት ግን ቅንጭላቴ ውስጥ የማላቁረው መረጃ የለም፡፡ እናም ስለግድያና ገዳዮች ታሪክ ጥቂት ነገር አውቃለሁ፡፡ …

አፄው ሺዎች ዓመታትን ይገዙ እየመሰላቸው ብዙ ተቀናቃኞቻቸውን በግልጽም በሥውርም እንደገደሉ ይወራ ነበር፡፡ ግን እሳቸውም አርጅተውም ቢሆን በሰው እጅ ተገደሉ፡፡ ያንን በትራስ ታፍኖ የመገደል የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ ቀድመው ቢረዱት ኖሮ ደህና ሰው ሊሆኑ ይችሉ ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡

መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ለሺዎች ዓመታት “ጓድ ሊቀ መንበር” እየተባለ ህመምም እርጅናም ሳይጎበኘው ዘላለም የሚነግሥ መስሎት በተለይ እነዚያን 12 ጄኔራሎች መሞታቸውን ለማረጋገጥ አገጫቸውን በጫማው እያገላበጠ ጭምር አሰቃይቶ ገደለ፡፡ እሱ አሁን ባይሞትና በስተርጅና ዕድሜው ቢገኝም በርሱ ጦስ ሀገር ተበተነች፤ ስንትና ስንት ምሁራንና የጦር ባለሟሎችም አለጊዜያቸው አለቁ፤ በትንሹ አንድ ትውልድ አለመላው ረገፈ፡፡ በሰበቡም ሀገር ባዶዋን ቀረች፡፡ ወያኔም ተስፋ በቆረጠ ሕዝብ መሃል ያላንዳች ተቀናቃኝ ተንደርድራ አራት ኪሎን ያዘች፡፡

መለስ ዜናዊ ዕድሜው ከ58 እንደሚያልፍ ቢያውቅ ኖሮ ላፈራረሳት ኢትዮጵያና ለዘራው የዘረኝነት ደዌ ንስሃ ገብቶ ከራሱና ከታሪክ ጋርም ታርቆ በሞተ ነበር፡፡ ሕይወት እንዲህ ናት፡፡ የአማራነት ዘር እንደሌለው ሁሉ “አማራ ቁጭ ብሎ ሲለምን ማየት እፈልጋለሁ” እያለ በአማራ ጸሎትና በሠራው ግፍ በቁሙ ፈራርሶ ሞተ፡፡ ኃጢኣታችን በዛና ግና ከርሱ ለከፋ የርሱ ርዕየተ ዓለም ተከታይ ተላልፈን በቁማችን እንጦርጦስ እየወረድን ነው፡፡

ለዚህ በሽተኛ ልጅ የመጋለጣችን አንዱ ታሪካዊ ምሥጢርም እነዚያ የመንግሥቱና የመለስ ዘረኛ አገዛዝ ዘመናት ሳይታከሙ ከትምህርትና ከዕውቀትም፣ ከሞራልና ከሃይማኖትም፣ ከሥነ ምግባርና ከሰብኣዊነትም ከተጣላ ትውልድ ጋር ፊት ለፊት መገጣጠማችን ነው – ይሄ ከኢትዮጵያ ጋር ዐይንና ናጫ የሆነ ኦሮሙማ የተባለ ጋንጩር ትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ – ታሪክም ይሁን ሰው – ተንቀሳቃሽም ይሁን ቋሚ – ካልጠፋ ሞቼ እገኛለሁ በማለቱ ይሄውና ከሆዳም አማሮች ጋር ተሰልፎ ሊያጠፋን ቀን ከሌት እየደከመ ነው፡፡ ዕድሜን በሚመለከት እዚህ ላይ መታወስ ያለበት ዋና ነገር ግን ጦርነትና መገዳደልም ባይኖር የዚያን ዘመን ገዢዎች ብዙዎቹ አሁን አይኖሩም፤ በበሽታ ወይም በዕድሜ መግፋት ሞተዋል፤ ቢኖሩም ካሉ አይቆጠሩም፡፡ እኔ የዚያን ዘመኑ ወጣት እንኳን ብታዩኝ ውሻ በጨው የማይበላኝ በዘመኑ ቋንቋ ቶርቶራ ሆኛለሁ፡፡ ለዚች ነው እንግዲህ…

ተመልከት፡- አንድን የጦር ጄኔራል – አንድን የህክምና ዶክተር – አንድን ፈላስፋና ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰው … ለማፍራት ሀገር ስንትና ስንት ወጪ ታወጣለች፡፡ ያ ሰው ደግሞ ለእናት ለአባቱም አይደለም፤ ለወጣበት መንደርና ጎሣና ነገድም አይደለም … አገልግሎቱ ለመላው የሰው ዘር ነው፡፡ የትም ዓለም ለሚገኝ ዜጋ የዚያ ምሁር አስተዋፅዖ ቀላል አይደለም፡፡ ልብ እንበል – አንድን ጄኔራል ለማፍራት ከ25 ዓመታት በላይ ይፈጃል፡፡ አንድን የህክምና ዶክተር ለማፍራትም እንደዚሁ ከ30 ዓመታት አይተናነስም፡፡ ለመግደል ግን አሥር ሴከንድ አይፈጅም፡፡ ሰውን ለመውለድ ከዘጠኝ ወር በላይ እናት ትሰቃያለች፤ ለማጥፋት ግን የሚያስፈልገው በዋናነት እልም ያለ ድንቁርናና የ10 ሴከንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ያልፈጠራትን ነፍስ አንድ ሰው ተነስቶ እንደቀልድ ከሥጋዋ ሲለያት ይታያችሁ፡፡ አንድ ሰው ወንጀለኛነቱ እንኳን ቢረጋገጥ ለስቃይና እንግልት እንዲዳረግ ህግ አይፈቅድም፡፡

ዶክተር ሐጎስና ዶክተር ደቻሣ እንዲሁም ያ የፈረደበት ዶክተር አንዷለም ቢገደሉ እነሱ የሚያጡት ነገር የለም – በመሠረቱና እንደአካሄድ፡፡ እንዲያውም ከዚህች ጨምላቃ ዓለም በመገላገላቸው ያተርፋሉ እንጂ አይከስሩም፤ ከረር ያለው ችግር እነሱ የሚያስተዳድሩት ቤተሰብ ካለ ነው – ሚስት – ልጅ – እናት – አባት …፡፡ በጣም የሚጎዳው ይልቁናስ ታዲያን ደንቆሮው ገዳይ ነው – ቢያንስ ከራማው ይጠለሻል፡፡ መናገር የሚችል ጨካኝ ዐውሬ ወታደራዊ ልብሰ ለብሶ ሰው መስሎ አራት ኪሎን በተቆጣጠረ ሰልቢያኖስ የሚባል ብዔል ዘቡል በመታዘዝ ይህን መሰል ግድያ ቢፈጽምና በግድያውም ቢዝናና ሌላው ተጎጂ በዋናነት ሀገር ነው፡፡ ከፍ ሲል እንደተነገረው ገዳዩ ዐውሬም አስገዳዩ ብዔል ዘቡላዊ ሰውዬም ቀናቸውን ጠብቀው በበሽታ ወይም በሰው ወይም በዕድሜ ማለቅ ይሞታሉ፡፡ እንደሚሞት የሚያውቅ ሰው ደግሞ ነገ ራሱ ለሚሞት ነገር የሰማይ ቤቱን የሚያቆሽሽ ነገር መሥራት አልነበረበትም፡፡

ባልዋን የጎዳች መስሏት ነው እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ በጥልቀት ሲታይ፡፡ ሰሞኑን ባሕር ዳር ላይ የገደሉት ዶክተር አንዷለም ዳኜም ሆነ ሌሎቹ በየጊዜው በኦሮሙማ የሚገደሉት የህክምናና የወታደራዊ ሣይንስ ባለሙያዎች የሞቱት የራሳቸውን ሞት ነው፡፡ መቼም ቢሆን መሞታቸው የሚቀር አልነበረም፡፡ ይሁንና በተማሩት ዕውቀትና ጥበብ ዘር ሳይለዩ፣ ሃይማኖትና ቀለም ሳይመርጡ፣ ድንበር ሳያግዳቸው የሰውን ልጅ በእኩልነት እንዲያገለግሉ ሰልጥነውና ቃል ኪዳን ገብተው ሣለ ኅሊናው የታወረና አእምሮው በጥላቻ የተሞላ ማይም ሰው ገጠመንና ሀገራችን ለሦስተኛ ጊዜ ባዶዋን ልትቀር ነው፡፡ አንድ ሀኪም ሰልጥኖ ሲመረቅ ከሚገባቸው ቃል ኪዳኖች አንዱ “ምንም አድልዖ ሳላደርግ የሰውን ልጅ በሞላ በሙያየ አገለግላለሁ” የሚለው ነው፡፡ ይህን የማያውቁትና በዘረኝነት ሰክረው በአማራ ጥላቻም አብደው የኢትዮጵያን መንበረ መንግሥት የጨበጡት ልበሥውራን ወንድሞቻችን አንድን ሀኪም ፋኖን አከምክ ብለው ይገድላሉ – አክሞም ከሆነ መሸለም ሲገባው፡፡ ጠላትን በመጣበት መንገድ ገጥሞ ማሸነፍ እንጂ በእናቴ መቀነት አሰናከለኝ የማይረባ ሰበብ አስባብ እህል “አብልታችኋል፣ ህክምና ሰጥታችኋል” በሚል መደረግ ግን በሚገባው ሰብኣዊ የሞራል ድርጊት ሰውን ወንጅሎ ሕይወትን እስከመቅጠፍ መድረስ የራስን የነገ የመትረፍ ዕድል ማሳጣት ነው፡፡ እናያለን ቀኑ ሲደርስ ይህን የሰይጣን መንጋ ማን እንደሚያድነው፡፡ እነዚህ ከሰብል ክምር፣ ከቤት እንስሳትና ከታጨደ የእህል ነዶ ጋር ሳይቀር የሚጣሉ አጋንንት የውድቀት ቀናቸው ሲደርስ ማን እንደሚያስጥላቸው ለማየት ያብቃን፡፡ ለማንኛውም ምሁራን አማሮችን መግደላቸው ቢያስለቅስም ዕብደታቸውና ስካራቸው ግን መላው ዓለምን በምፀታዊ ሣቅ ማስፈገጉ አይቀርም፡፡ በዘረኝነት የተጨማለቁ ኦሮሞዎች ከሙያ ሥነ ምግባር እጅግ ባፈነገጠ ሁኔታ በየእሥር ቤቱ፣ በየሀኪም ቤቱና በየፍርድ ቤቱ በአማራዎች ላይ የሚፈጽሙትን ዘግናኝ ግፍ እናውቃለን – የአደባባይ መሥጢር ነውና፡፡ ይህን የመሰለ ከፈጣሪም ከሰውም ህግጋት የወጣ ዕኩይ ተግባር ደግሞ አማራው በማንም ላይ እንዳይፈጽም ሙስሊሙ ኪታቡ፣ ክርስቲያኑም ማተቡ አይፈቅድለትም፡፡ አስተዳደግ ወሳኝ ነው፡፡ አማራ በምንም ዓይነት የጥላቻ ትርክት ተኮትኩቶ አላደገም፤ አማራ “ጠላትህን ውደድ” ተብሎ እንጂ “ኦሮሞን እረድ፣ ትግሬን ጥላ” እየተባለ የሰውነት መለኪያን እስኪስት ድረስ ዐውሬ እንዲሆን አያት ቅድመ አያቶቹ አላዘጋጁትም፡፡ ይህ የሰውነትን ልክ ይዞ የማደግ ሁኔታ ተጎጂ እንዳደረገው ብናውቅም በቅርቡ ግን መስተካከሉና ተመጣጠኝ የሆነ እርምጃ መውሰዱ የሚቀር አይደለም – ያኔ ነው ችግሩ፤ ለዚህም ነው – “በአባቱ ውድማ የተኛውን በሬ፤ ነካክተው ቆስቁሰው አደረጉት ዐውሬ” የሚባለው፡፡ አሁን ጥጋብ የሚሠሩትን ያሳጣቸው ሁሉ የዘሯትን የሚያጭዱበት ጊዜ መጥቷል፡፡ ፋኖ የፈለገውን ያህል ይከፋፈል፣ መቶ ቦታም ይሰነጣጠቅ – ያ ሌላ ጉዳይ ነው – ይስተካከልማል፡፡ አቢይም የፈለገውን ያህል በትያትር ዓለም ውሸት ቅጥፈቱን ያንበልብል፡፡ እውነት ግን ባለችበት አለችና አማራ ኢትዮጵያን የሚያስተካክልበት ወደቀደመ ክብሯም የሚመልስበት ሂደት ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ለሚታይ ይታየዋል፤ ለማይታይ አይታየውም፡፡ ሁሉም ነገር ለሁሉም እኩል ይታይ ደግሞ አይባልም፡፡ ሌባውንም፣ ቀማኛውንም፣ ገዳዩንም፣ አስመሳዩንም፣ ውሸታሙንም፣ ይሁዳውንም፣ ጴጥሮሱንም፣ ጳውሎሱንም … እንድናይና እውነቱን እንድንይዝ የሆነው ሁሉ ሆነ፤ የሚሆነውም ሁሉ ይሆናል፤ ግን ሁሉም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ያልፋል፡፡ (ሰፍ ብለህ ስትከታተለው የነበረ ‹ምስለኔህ› ምንም ሳያፍር 360 ዲግሪ ግልብጥ ይልና “እንዲህ አባላኋቸው፤ እንትናን አቅፌ እነእንትናን አጫውቼ እንትናን መቅ አወረድኩት፤ ቀድሜ ያልነካሁት ለዘዴ ነበር፤ አሁን ግን አፈር ከደቼ አበላዋለሁ፡፡ እኔ ጀግናው ገና ዱቄት አደርጋቸዋለሁ …” የሚል ዕብድ ሰው ማየት የቻልኩት ዕድሜና ጤናውን ስለሰጠኝ ነው፡፡ ገና ብዙ አያለሁ፡፡)

ገዳዮች ለገዛ ሕዝባችሁ ስትሉ መግደላችሁን አቁሙ፡፡ እምትገድሏቸው አማሮች ይህን ማለፉ የማይቀረውን የጨለማ ዘመን ሲያልፉ ወለጋና ኢሉባቦር እየሄዱ አሁን “የኔ ነው” እያላችሁ የምታፌዙበትን የዋሁን ኦሮሞ ያክማሉ፡፡ ትርሃስና ጫልቱ ጎንደርና ጎጃም ሄደው ወገናቸውን ፊዚክስና ኬሚስትሪ ያስተምራሉ፡፡ አሁን የምትገድሏት ነርስ ነገ አዲግራት ተመድባ ተጋሩ ወንድሞቿንና እህቶቿን ታክማለች፡፡ የማትጨርሱትን ጦርነት እያጋጋማችሁ የታሪክን ሆድ በማስባስ ሌላ ታሪክ እንዲከሰት አቅላችሁን ስታችሁ አትባዝኑ፡፡ በቃኝን ዕወቁ፡፡ ከገባችሁበት የቅዠት ዓለም ባፋጣኝ ውጡ፡፡ መተላለቅ ይብቃን፤ መገዳደል ይሰልቸን፡፡ ትላልቅና ተሰሚነት ያላችሁ ኦሮሞዎችና ሌሎችም ደፈር በሉና እነዚህን ዕብዶች አስታግሱ፡፡ ጥቅሙ ለሁሉም ነው፡፡ መግደል የማይፈልግ ሁሉ ሞትን መርጧል ማለት አይደለም፡፡ እየተገደለ ያለ አካል መከላከል ሲጀምር ማጥቃት መኖሩንም በእግረ መንገድ ሊገነዘብ ይችላልና ቀኝ ኋላ ዙርን መፍራት አስፈላጊም ተገቢም ነው፡፡ ሠላሣው ክልል በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሚኒሻና ወታደር ማዘጋጀቱ ደግሞ የጤና አይደለምና ዜጎችን ለምርትና ለፋብሪካ ሠራተኝነት እንጂ ለውጊያ ማሰለፉ ይቅር – የትም የሌለ ነው፡፡ አስቂኙ ሀገራዊ ድራማ ሁሉ መፍትሔ ይበጅለት፡፡ አራትና አምስት የፖሊስ ኮማንደሮች የሚበቁት አንድ ክፍለ ሀገር ከሁለትና ሦስት መቶ በላይ የጦር ጄኔራልና ኮሎኔል ማከማቸቱ በአንዲት ሀር ብዙ ሀገራት ለመኖራቸው ትልቅ ምልክት ነውና ኢትዮጵያዊ መንግሥት በቶሎ እንዲመጣና እንድንስተካከል ጠንክረን እንጸልይ፡፡ የጦር መሣሪያ ወደ ማዕከላዊ ግምጃ ቤት ወይም መጋዘን – ዜጎች ወደትምህርትና ወደግብርና እንዲሁም ወደ ኢንዱስትሪና ወደ ፋብሪካ፡፡ ያኔ እንኳን ለኛ ለሌላም እንተርፋለን፡፡ “ኦ አምላከ ኢትዮጵያ – ስምዓኒ ጸሎትየ ወኢትሚጥ ገጸከ እምነ ሀገሪትነ ኢትዮጵያ፡፡”

አንዱና ሌሎችም የጭራቁ አቢይ ሰለባዎች ሁሉ ነፍሳችሁ በገነት ትኑር፡፡ አይዞን፡፡ ነጻነት ቀርባለች፡፡

 


 

2 Comments

  1. ብዙ እውነት የተንጸባረቀበት ጽሁፍ ነው፡፡ እግዚያብሄር ፊቱን ይመልስልን፡፡ አገራችን እየጠፋች ነው፡፡ ሰውም ደነዝዟል፡፡ ምን እንደሚሻለን እንጃልን፡፡ ይጨንቃል፡፡

  2. እናመሰግናለን ይህንንም ያነበብነው አንተ ስለተረፍክ ነው። ያ ያልከው ግለሰብ ዩቲዩብ አልበቃ ብሎት እልቂቱ በጥሩ ሁኔታ እንዲፋፋምለት ቴሌቭዥን ሊከፍቱለት ነው ብዙ ክፍለ ጦር ወደ ክልሉ ከምታስገባ የሱ ሚዲያ ላይ በጀት ብትመድብ ኦሮሙማ ቀለል ባለ ወጭ አማራውን ያጠፋል። እስቲ የግኑኝነት መስመሮች ካለህ የቦርድ አባላቶቹን ተው በላቸው እነ ስታሊን፣ስብሀት ነጋ ኦሮሙማ ከሆኑ ከጀርባው ያሉት መፍትሄው ጸሎት ብቻ ነው። አሁንማ ፍሬን በጥሶ የማይደፈጥጠው አማራ የለም። ትልቅ ሰው መስሏቸው የቀረቡት እንደ ገለባ ስለቀለለባቸው ስልካቸውን አጥፍተውበታል። ያ በብልግናው ያጣው ክብር ሲያቃዠው ያገኘውን ሁሉ መንከስ ሁኗል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

አንድ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ባሕርዳር ውስጥ በታጣቂዎች ተገደሉ

aklog birara 1
Next Story

የአማራ ፋኖ የተቋምና የአመራር ድክመት ለአማራው ህዝብ ዋጋ ያስከፍላል – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

Latest from Same Tags

ወሰንየለሽ ኦሮሙማዊ ዕብደት!!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ አንድ አባውራ ምንነቱ ያልታወቀ እህል ከገበያ ገዝቶ ለሚስቱ አምጥቶ ሰጣት አሉ፡፡ ከሰጣትም በኋላ ሚስቱ ያንን እህል ፈጭታ ቂጣ ላርግህ ብትለው፣ እንጀራ

የችግሩን ሰንኮፍ ከስሩ ሳይነቅሉ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ፤ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ማስቆም አይቻልም!!!

መሰረት ተስፉ (Meserettesfu4@gmail.com) ሁላችንም እንደምናውቀው በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ሊካድ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ ጥቃት የተጀመረው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ስልጣን በያዘ
Go toTop

Don't Miss