በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ጥበበ ግዮን ሐኪምና ተመራማሪ የነበሩት ዶ/ር አንዷልም ዳኜ ባለፈው ቅዳሜ አመሻሽ ከሥራ ቦታ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ባልታወቁ ታጣቂዎች መንገድ ላይ በጥይት መገደላቸውን የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል፣ የባለሙያው መገደል ዩኒቨርሲቲውንና የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎችን በእጅጉ አሳዝኗል።
የዩኒቨርሲቲው የውስጥ ግኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማው አሸብር ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት መግለጫ ዶ/ር አንዷለም ዳኜ በጥይት ተመትተው የተገደሉት በተደጋጋሚ እገታና ግድያ ከሚፈፀምበት “ቆሼ” ከተባለ አካባቢ ባልታወቁ ታጣቂዎች በእለቱ ምሽት 1 ሰዓት አካባቢ ነው፡፡“ባለሙያው የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት፣ የጉበት፣ የቆሽትና የሐሞት መስመር ሰብ ስፔሻሊስት፣ ተመራማሪና መምህር ነበሩ” ብለዋል፡፡
በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና አገልግሎት ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ዳኜ ገና በ37 ዓመታቸው “አንቱ” የተባሉ ታላቅ ባለሙያ እንደነበሩ አቶ ግርማው ተናግረዋል።የዶክተር አንዷለም ዳኜ የቀብር ሥነ ሥርዓት የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕረዚደንት፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ ተማሪዎችና በርካታ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት በባሕረዳር በዓለ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ስርዓት ፍትሀትና ፀሎት ተደርጎ፣ በድባንቄ መድኃኔያለም ቤተክርስቲያን ሥርዓት ቀብራቸው ትናንት ተፈጽሟል።
የዶቼቬለው ዓለምነው መኮንን ከባህርዳር እንደዘገበው የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የባሕርዳር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊን ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ዋቢ አድርጎ “ፖሊስ ድርጊቱን ማን ፈፀመው? እንዴት ተፈፀም? የሚለውን እያጣራ መሆኑን አስታውቋል።
DW