ይቅር ብየሃለሁ

February 2, 2025

ካንገቱ በላይ ሸፍኖ፣ እጆቹን ከጀርባው ጠርፎ፣ እየገፈተረና በያዘው ዱላ እየወቃ፤ ወደ እስር ቤቱ ከተተው። ከክፍሉ ካስገባው በኋላ፤ በሩን ቆለፈና ሄደ። እጆቹ ስለተፈቱለት፤ ራሱ ላይ አጥልቆ፣ አንገቱ ላይ ያሰረውን መሸፈኛ፣ ቀስ አድርጎ አወለቀው። አጆቹ ደቀዋል። ወገቡ ተሽመድምዷል። እግሮቹ የግድ ነው እየተገፉ እዚህ ያደረሱት። ሳያስበው ግድግዳውን ተደግፎ ከተቀመጠት እንቅልፍ ወሰደው። የሚገርም ነው! እንደዚህ ሰውነት ዝሎ፤ እንቅልፍ ይወስዳል። ረሃቡና ጥማቱ የት እንዳሉ አይታወቅም። ረሃቡ፣ ጥማቱ ከስቃዩ ጋር ተዳምረው፤ ሌላ ቦታ ወስደውታል። ሰውነቱ የሱ አይደለም። ሊያዘው አይችልም፣ አይታዘዘውምም።

ለስንት ጊዜ እንደተኛ ሳያውቀው፤ በሩ በኃይል ሲከፈትና መብራት ዓይኖቹን ሲያጥበረብራቸው፤ ነቃ። ዓይኖቹን እየፈታተገ ሁኔታውን ሊረዳ ሞከረ። ጊዜ አልነበረውም። ወዲያው እጆቹ ከኋላ በጀርባው በኩል ሲታሰሩና ራሱን በዱላ ሲመታ፤ ተዝለፈለፈና ሊወድቅ ሲል፤ የታሰሩ እጆቹን ከኋላው አንዱ አሳሪ አንጠልጥሎ አነሳው! አከታትሎም ጀርባውን ነረተው። እህ! ከሚል የሲቃ ድምጽ ሌላ፤ ከሱ የወጣ የለም። እየጎተቱ ወደ ምርመራው ክፍል ወሰዱት። እዚያ ሲደርስ፤ ራሱ ላይ ያጠለቁትን ገፈው፤ ወንበር ላይ አስቀመጡት። እሱ በሰመመን ላይ ነው። የሰዎቹን ማንነትም ሆነ ያለበትን ቦታ አያውቅም። ለማወቅም ጥረት አላደረገም። ሰዎቹ በኦሮምኛ ነው የሚነጋገሩት። አልፎ አልፎ፤ ዐማራ የሚል ቃል ሲዘንቁ ሰውነቱ ስለሱ መሆኑን ነግሮታል።

ፊት ለፊቱ የተቀመጠው መኮንን፤ “እኔ ላንተ ጊዜ አላጠፋም። ማንነትህን፣ ከነማን ጋር እንድምትውል፣ ምን እንደምትሠራ በደንብ እናውቃለን።” ካለ በኋላ፤ “በትክክል ተቀመጥና አዳምጠኝ!” በማለት ዓይኖቹን ወደሱ እንዲልካቸው አዘዘው። እሱም ፊቱን ወደ መኮንኑ አዙሮ ዓይኖቹን በድንብርብር በማጮለቅ ወደጠያቂው አካባቢ ላካቸው። ከጀርባው የመጣ አንድ ወታደር፤ ፊቱን ጯ አደረገው። በጭላንጭል ይመለከቱ የነበሩ ዓይኖቹ በሩ። የሲቃ እስትንፋስ ካፉ ወጣ። ከዚያ በኋላ፤ ጠያቂው የሚለፈልፈውን ምኑንም አልሰማም። ብቻ አሁንም እንዲነቃና መልስ እንዲሠጠው፤ ጠያቂው ሲቦርቅና ወታደሮቹ ሲደልቁት፤ እሱ ሰውነቱን፤ “ችሎቱን ይሥጥህ!” ብሎ ደነዘዘ።

ከጊዜ በኋላ፤ እየጎተቱ ወደሌላ ክፍል አስገቡት። ትንሽ ካረፈ በኋላ፤ ዓይኖቹን ክፍቶ ተመለከተ። ጨለማ ክፍል ነው። ወለሉ ላይ ነው። እጆቹ ተፈተዋል። ወለሉ ይቀዘቅዛል። ረሃብ ተሰማው። ጥማቱም ጉሮሮውን አድርቆታል። እንደሚያላምጥ ሰው አፉን ከፈት ዘጋ አድርጎ ሊያርስና ከድርቀቱ ሊገላገል ሞከረ። “ኣክ!” ብሎ ድርቀቱን አስወጥቶ ሊተፋው ሞከረ። እንዲህ ዋዛ! መውጣት ቀርቶ፤ ጉሮሮው እንኳን ማለስለስ አልቻለም። ጣራው በተወሳሰቡ የብረት ዘንጎች ወዲያና ወዲህ ተመሰቃቅሏል። ግንዶችም አሉ። በግድግዳው አለንጋዎች፣ የኤሌክትሪክ ገመዶች፣ ትልልቅ ባትሪዎችና ገመዶች ተሰቅለውበታል። በሩን በርግደው ሁለት ወታደሮች ገቡ። እጆቹንና እግሮቹን አሰሩና፤ ወደላይ አንስተው፣ እንደኳስ መጫወቻ ከተተከለው የጎል እንጨት፣ አናቱ ላይ በወረደው ገመድ አንጠለጠሉት። ከዚያ በሰለጠኑበት የማሰቃያ መንገድ፤ እንደ የሰው ልጅ ገላ ሳይሆን፤ እንደ መጫወቻ ኳስ ይነርቱት ገቡ። እሱ በሰመመን ላይ፤ የራሱን ሰውነት የሳተ በሚመስል መንገድ፤ ዝም አለ። ንዴታቸው ጣራ ነካ። ካንጠለጠሉበት ገመድ ፈቱና መሬት ላይ ጣሉት።

“እንደሌሎቹ ይሄም አይናገርም። ዝም ብለን አለቃችንን እንጥራው!” አሉና፤ ያንን መኮንን ጠሩት። ወታደሮቹ ሁለቱን ትተዋቸው ወጡ። መኮንኑ፤ እጆቹና እግሮቹ እንደታሰሩ፤ ለስለስ ባለ ንግግር፤ ሊያግባባው ሞከረ። መረጃ እንዲሠጠው ነበር ጉዳዩ። በመጨረሻም፤ “መናገር እንደምትችል አውቃለሁ። ከዚህ ሁሉ ስቃይ መዳን ከፈለግህ፤ አፍህን ክፈትና ተናገር።” አለው።

ያን ጊዜ አፉን ሊከፍት ሞከረ። መኮንኑ ወታደሮቹን ጠራና፤ እጆቹንና እግሮቹን እንዲፈቱለት አዘዛቸው። በፍጥነት የታዘዙትን አደረጉ። “ሂዱና ምግብና ውሃ አምጡለት!” አላቸው። እየጣደፉ ወጡ። መኮንኑ አሁንም ልፍለፋውን ቀጠለ። ስለ ገዢው ቡድን መሠልጠን፣ ስለልማት መስፋፋት፣ ስለሰላም መስፈን፣ ስለ ሕዝቡ ድጋፍ፣ ስለ አገሪቱ የውጪ ጠላቶች ቅናት፣ ስለ ሌላም ሌላም መናገሩን ቀጠለ። ዐማራ ለዘመናት ኦሮሞን እንደበደለ፣ በዝርዝር ተረት ተረት በሚመስል ጨዋታ፤ አልፎ አልፎ ንዴቱ እያየለ፤ ተረተረው። እሱም፤ በነገራችን ላይ እሱም የምለው ስሙ ጠፍቶኝ ነው። እሱም ትንፋሽ መግዛት ያዘ።

“እኔ አንተ የምትለኝ ሰው አይደለሁም። ዳሩ ምን ያደርጋል፤ አንተ አንተ የምትፈልገውን ማየት እንጂ፤ ከፊትህ ያለውን እውነተኛ አካል አታይም። አታውቀኝም፤ አላውቅህም። እንኳንስ በውስጤ ያለውን ይቅርና፤ በፊቴ የሚታየውን ማንበብ ተስኖሃል። እንዳንተ ሰው ነኝ። ላንተ ግን አንድ አስቃይ የተባልከውና በመጨረሻም የምትገለው የቁጥርህ አብዢ ነኝ። ይቅር ብየሃለሁ። የምታደርገውን አታውቀውምና! ይባስ ብሎ ደግሞ፤ የኔ መሰቃየትና ህይወት ደሞዝህ ስለሆነ ነው። ማታ ቤትህ ስተባ፤ ሚስትህ፣ ልጆችህ፣ ጓደኞችህ፣ ወዳጆችህ፣ ጎረቤትህ እንደኔ ሰዎች ናቸው። ላንተ ግን እነሱ የተለዩ ናቸው። አንተ የተለየህ ነህ። እኔ ደግሞ ከሰው የማልቆጠር የፈለግኸውን ልታደርስብኝ የምትችል መጫወቻህ ነኝ።

እስኪ በትክክል አጢነው። እያሰቃየኸኝ፣ ቆይተህ እንደምትገድለኝ እያወቅሁ፣ የማውቀውስ ቢኖር የምናገርበት ምን ላእርፍ ነው። ይልቅስ አፌን በመዝጋት ከስቃዬ ቶሎ ገላግለኽ እንድትገድለኝ ነው የምሻው! ስለኔ ልተውና ስላንተ ልንገርህ፤ ሰማኸኝም አልሰማኸኝም።

ዓየህ! የገዢው ቡድን አባላት አንተን መሳሪያ አድርጎ እኔን እንድትቀጠቅጠኝ አዞሃል። አንተ ያዝ እንደተባለ ውሻ፤ ምንም ጥያቄ ሳታቀርብ፤ ለምን እኔን መቀጥቀጥ እንዳለብህ ሳትጠይቅ፤ ከሕዝብ በተሰበሰብ ግብር የሚከፈልህ ደሞዝ፤ በደነደነ ክንድህ የምትችለውን ሁሉ ታደርጋለህ። አለቆችህ በየቤታቸው ሲዝናኑ፤ አንተ እዚህ እኔ ጋር ነህ! እነሱ ያግበሰበሱትን ንብረት ይዘው፤ መጫቸውን እያዘጋጁ ነው። ሕዝብ ከቆረጠ መመለሻ የለውም። ሕዝቡ ያቸንፋል። ያን ጊዜ፤ እነሱ መውጫቸውን ቀድመው አዘጋጅተዋልና፣ ንብረታቸውን ይዘው፤ እንዱን የመሰሉ አምባገነኖች ወዳሉበት ሄደው ያመልጣሉ። አንተ ደግሞ በኔ እግር ገብተህ፤ ባለተራ አንተን ይነርትሃል። እኔ ውዬ እንደማላድር አውቀዋለሁ፤ ይቅር ብየሃለሁ።” አለው።

ዝም ብሎ አንዳንድ ጊዜ ዓይኖቹን እየጨፈነ ይሰማው የነበረ መኮንን፤ ዓይኖቹን አጉረጠረጠ። ይሄ በቁጥጥሩ ያለ፣ ከግሩ ሥር የወደቀ ምናምንቴ፤ እንዴት ቢደፍር ነው ለሱ ሊያስተምር የሚቃጣው። በግንባሩ ልብ አቾፈቸፈ። እውነት ግን የነገረውን ስምቷል!

አንዱ ዓለም ተፈራ

እሁድ፣ ጥር ፳ ፭ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፯ ዓ. ም. (02/02/2025)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

”የዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ ገዳዮች የአገዛዙ ወታደሮች ናቸው” የአማራ ፋኖ በጎጃም

Next Story

ፕረዚዳንት መንግሥቱ ሀይለማርያም የት የተወለዱት??

Go toTop