![aklog birara 1](https://amharic.thehabesha.com/wp-content/uploads/2021/10/aklog-birara-1.jpg)
የአማራው ህዝብ ፋኖን የሚደግፍበት ዋና ምክንያት ባለፉት አምሳ ዓመታት በተከታታይ የሚዘገንን እልቂት፤ ስደት፤ ስራ አጥነት፤ ረሃብተኛነት፤ እስራት፤ ድብደባ፤ መፈናቀል፤ የስነልቦና ጦርነት ወዘተ ስለተካሄደበት ነው፡፡ ይህ ህዝብ እንዲጠፋ ተፈርዶበታል፡፡ ሁኔታው ተባብሷል፡፡
የአማራው ትግል የህልውና ትግል ነው ተብሎ የሚጠራውም ለዚህ ነው፡፡ ስርአቱ ካልተቀየረ በስተቀር፤ እልቂቱ ይባባሳል፡፡ የአማራው ምሁርና ልሂቅ ታሪካዊ ግዴታውን አልተወጣም፡፡ እንዲያውም ከጥቂቶች በስተቀር፤ ራሱን፤ እውቀቱን፤ አቅሙን፤ ቁሳቁሱን የደበቀና ያሸሸ ይመስላል፡፡
የባሰውን አንዳንድ ምሁራን/ልሂቃን/ጫና ፈጣሪዎች/ጋዜጠኞች/መንፈሳዊ አባቶች ወገንን ከሌላው እየለዩ ቢቻል ባንድነት፤ ቢያንስ እየተናበበ መስራት ያለበትን የአማራ ፋኖ እየከፋፈሉት ነው፡፡ ይህ የወገንተኛነት/ጎጠኛነት/መንደርተኛነት ድንቁርና ለአማራው ህዝብ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስክፍለው አንጠራጠር፡፡ የአማራው ትግል ተግዳሮት አማራው ሆኗል፡፡
አንድ ወዳጀ እንዲህ ብሎ ጠይቆኝ ነበር፡፡ “እንደ አማራው ምሁር፤ ልሂቅ፤ ፖለቲከኛ፤ ጋዜጠኛ በግለሰባዊነት፤ ጉረኛነት፤ እኔ ብቻ አውቃለሁ ባይነት፤ በቅናታዊነት፤ ዝናና ጥቅም ፈላጊነት፤ ጎጠኛነት፤ ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ ይብቀል’ ባይነት፤ ሃሜት ወዳድነት (gossip prone) የተበከለ ታውቃለህ?” የሚል፡፡ ይህንን ጥያቄ መላልሸ ሳስበውና በመሬት ላይ ያለውን (በተለይ በዲያስፖራው) መነታረክ ሳጤነው አማራው አንድ ሊሆን አይችልም ወደሚል ድምዳሜ ይመራኛል፡፡ ይህንን መሰረታዊ ያስተሳሰብ ድክመት አስቡበት፤ እኔ መልስ የለኝም፡፡
ታሪክ ጀምሮ ወደ መጨረሻው ምእራፍ ለመሸጋገር ማነቆው ምንድን ነው?
የአማራ ፋኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታሪክ ሰርታል፡፡ ዘግናኙን ስርአት አርበርብዶታል፡፡ ይህ ስኬት ከህዝቡ ድጋፍ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በችግሩ ነቀርሳነት እና ካንሰሩ መወገድ አለበት በሚለው ላይ ስምምነት አለ ማለት ነው፡፡ ይህንን ሃቅ ምሁሩ፤ ልሂቁ፤ ጋዜጠኛው ወዘተ ቢቻል በጋራ፤ ቢያንስ እየተናበበ ማስተጋባት አለበት፡፡
በአስኳልና መሰረታዊ ችግሩ ላይ ስምምነት ካለ መፍትሄውን ለመፈለግ ይቀላል ማለት ነው፡፡ መፍትሄው ግን መርህ፤ ተቋም፤ ድርጅት፤ አንድነት፤ አመራር፤ ስነምግባር ይጠይቃል፡፡ መንደርተኛነት/ጎጠኛነት/ ሆዳምነት/ ግለሰባዊነት ከአማራው ህልውና ትግል ጋር እብረው ሊሄዱ አይችልም፡፡ አንዱን ወደላይ አንዱን ወደታች አድርጎ ማሳየት ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡
የአማራው ህዝብ ጎንደር፤ ጎጃም፤ ሸዋ፤ ወሎ፤ ወለጋ፤ አዲስ አበባ፤ ሃረር ወዘተ ቢወለድና ቢኖርም፤ ወጣት፤ ሴት፤ ሙስለም፤ ሃብታም፤ ድሃ፤ ገበሬ፤ ቄስ፤ ፓፓስ፤ መነኩሴ፤ ጋዜጠኛ፤ ሃኪም፤ ዲያስፖራ ወዘተ ቢሆንም፤ በማንነቱ ብቻ እየተለየ ይታፈናል፤ ይታሰራል፤ ይገረፋል፤ ይገደላል፤ ይፈናቀላል፤ ይባረራል፤ ክስራው ይሰናበታል፤ ይሰደባል፤ እንዲራብ ይደረጋል፡፡
አናመንታ፤ አማራው ይህ ሁሉ ግፍና በደል የሚደርስበት በማንነቱ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ነው፤ አንድነትም ባይቻል እየተናበቡ መታገል ይቻላል የምለው፡፡ መደጋገፍ ይቻላል የምለው፡፡
የአማራው ህዝብ ከደርግ መንግሥት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተከታታይ የብሄር/ዘውግ ልሂቃን (ethno-nationalist elites) በሚያካሂዱት የተቀነባበረ ሴራ፤ መርህና ተቋም መሰረት ቁጥሩ በተከታታይ እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡ የኦህዴዱ መንግሥት ስልጣን ከያዘበት ወቅት ጀምሮ ደግሞ የአማራው ህዝብ በመሰረታትና መስዋእት በሆነላት ኢትዮጵያ አገር አልባ ሆኗል (stateless). ይህ ዘግናኝ አገዛዝ እስካልተወገደ ድረስ አማራው ፍትህ ያገኛል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ይህንን ስርአት ወለድ፤ መዋቀራዊ የሆነ ክስተት፤ በመንግሥት የተቀናጀና የውጭ መንግሥታት ለራሳችው ጥቅም ሲሉ የሚደግፉትን አገዛዝ በድል ለመወጣት የሚቻለው እንዴት ነው? ብየ ራሴን ስጠይቅ የማገኘው መልስ እንደሚከተለው ነው፡፡
አንደኛ፤ የአማራ ፋኖ መሪዎች፤ ታጋዮችና ደጋፊዎች ተገዢነታቸው ለዓላማ አንድነት መሆን አለበት፤ ማአለትም፤ ለአማራው ህዝብ የህልውናና ዘላቂ ጥቅም አገልግሎት ብቻ፡፡ ህልውናውን ያላስከበረ ህዝብ አገር ሊኖረው አይችልም፡፡ አሁን ካልሰራን፤ አሁን ለመደጋገፍ ካልቆረጥን፤ ነገ አማራው እንደ ጂፕሲዎች አገር አልባ መሆኑ አይቀርም፡፡
ሁለተኛ፤ የዓላማ አንድነቱን መርህ ከተቀበልን፤ የአማራ ፋኖ መላውን የአማራ ህዝብ ሁሉ የሚወክል፤ ልክ እንደ ብረት ጠንካራ የሆነ፤ እየተናበበ የሚሰራ፤ ወታደራዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ዲፕሎማሳዊ፤ ቁሳቁሳዊ፤ ግንኙታዊ ማእከል መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ማንም ግለሰብ ይህንን ሊተካ አይችልም፡፡ የፈለገውን ያህል ቢታገል ግለሰብ ተቋም አይደለም፡፡ የህልውና ትግል ያለ ተቋም፤ ቢቻል ያለ አንድነት፤ ያለ ጠንካራ ማእከል፤ ያለ ብልሃተኛ አመራር ስኬታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ባንድ በኩል የህልውና ትግል ማካሄድ፤ በተቃራኒው ደግሞ የፖለቲካ ሥልጣን ፉክክር፤ ግብግብ ሊታረቁ አይችሉም፡፡ የመጀመሪያው ቅድሚያ እንዲሰጠው እመክራለሁ፡፡
የፋኖ መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው ገና የህልውናው ጦርነት ሳይገባደድ እርስ በእርሳቸው የሚነታረኩና የሚዋጉ ከሆነ ሥልጣን ሲይዙ ምን ሊሆኑ ነው?
ተቋም፤ ድርጅት፤ የተደጋፈፈ አመራር ያስፈልጋል የምለው ይህንኑ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የፋኖን አንድነት፤ ተቋም፤ አመራርና ማእከል ወሳኝነት በሚመለከት ዶር ባደገ ቢሻውና እኔ ያቀረብነውን ምክረ ሃሳብ የምታስታውሱ ትኖራላችሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡
ፋኖ የህልውናውን ትግል ስኬታማ ለማድረግ ጥራት ያለው በፍኖተ ካርታ የተደገፈ፤ አንድነትን፤ ዲሞክራሳዊ አመራርን፤ መተሳሰብን፤ አብሮነትን ወዘተ የሚያንስተጋባ ህዝባዊ እንቅስቃሴ መሆን አለበት የሚል ምክር ነበር፡፡ ተቋማና ማእከል ማለት ይኼው ነው፡፡ ሰሚ ያገኘን አይመስለኝም፡፡ አንዱ የአማራው ችግር ሁሉም አዋቂ፤ ሁሉም መሪ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ የተለያየ ፍኖተ ካርታ የት ያደርሰናል? የአማራው ምሁር፤ ልሂቅ ይንን አስቸኳይ የማቀነባበር ስራ ለምን አልሰራም?
አንተስ? ትሉ ይሆናል፡፡ ከአገር ቤት የተላከ የፍኖተ ካርታ ረቂቅ ጊዜ ወስደን፤ አሻሺለን ሁሉም የፋኖ መሪዎችና ድርጅቶች እንዲመለከቱትና የራሳቸው ሰነድ እንዲያደርጉት የሚል መልእክት ልከን የውሃ ሺታ ሆኗል፡፡ አሁንም ይህ ስራ መተግበር አለበት፡፡
ህዝቡ እንዳይሰለች እፈራለሁ፡፡
የአማራ ፋኖው ደጀን ህዝቡ ነው፡፡ የአማራው ህዝብ፤ በተለይ ገበሬው አሁን የተከሰተውን አምካኝ ሁኔታ ተሸክሞ ሊቆይ አይችልም፡፡ አገዛዙ በፋኖ ስም፤ ሆነ ብሎ የፈጠራቸው የውንብድና ቡድኖች ህዝቡን እያሰቃዩት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ጦርነቱ በፍጥነት ስኬታማ መሆን አለበት የምለው ለዚህ ነው፡፡ ጦርነቱ ከአማራው ክልል መውጣት አለበት የምለውም ለዚህ ነው፡፡
የአማራው ህዝብ የህልውና ትግል በየፈርጁ መሪዎች ያስፈልጉታል፡፡ ብቃት ያላቸው መሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ለመርህና ለተቋም ተገዢ የሆኑ ማለቴ ነው፡፡ መስፈርቱን የሚያሟሉ ወጣት መሪዎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ እድል ይሰጣቸው፡፡ የአማራውን ትግል ለግል መኖሪያ የሚያደርጉትን መለየት ያስፈልጋል፡፡ መመንጠር ያስፈልጋል፡፡
የአማራ ፋኖና ደጋፊዎች፤ የአማራ ህዝብ በመላው ኢትዮጵያና ውጭ እንዲገነዘበው የማሳስበው፤ ሌላው ቀርቶ ለገዢው የኦህዴድ ፓርቲ ታማኝና አገልጋይ የነበሩ አማራዎች ቀስ በቀስ ክስልጣናቸው እንደሚባረሩ ነው፡፡ አይን ያወጣው የአምባገነን አገዛዝ ማንንም አይምርም፡፡ አንዱን የፋኖ መሪ በሌላው ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት የሚደረገው ለአማራው ታስቦ አይደለም፤ መሪ አልባ ለማዳረግ ነው፡፡
ይህ አገዛዝ እንኳን አማራውን ሊምረው በኦህዴድ ውስጥ ሚና የነበራቸውን ሁሉ በማሳደድ ላይ ይገኛል፡፡ በለማ መገርሳ ላይ የተወሰደውን አቋም ብቻ ማጤኑ ይበቃል፡፡
እየለያዩ መምታት
ይህ አገዛዝ ታጋዩን ዘመነ ካሴን፤ ታጋዩን እስክንድር ነጋን ወዘተ ለመግደል እያደነ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ለምን በሁለቱ መካከል እርቅና ሰላም እንዲፈጠር አንሰራም? አንመክርም? ትግሉ ስለ አማራው እንጅ ስለነሱ አለመሆኑን ለምን አንነግራቸውም? ለመስማማት ካልቻላችሁ “ታረቁ አለያ ልቀቁ” ለማለት ለምን አንደፍርም? የምሁሩ ሚና እዚህ ላይ ነው፡፡
የአማራ ፋኖ ታጋዮችና ደጋፊዎች እንዲገነዘቡት የምመኘው ሌላው ጉዳይ አገዛዙ የአገሪቱን ባጀት ለሥልጣን ማቆያው እየተጠቀመ በብዙ ሽህዎች የሚገመት ሆዳም አማራዎችን እንዳሰማራና አማራው እርስ በእርሱ እንዲጨራረስ እየሰራ ነው፡፡ ፋኖን የሚተካ በየቦታው ተሰግስጓል፡፡ የአገዛዙ “አማራ ፋኖ” ሆነ ተብሎ በስልት የተዋቀረ መሆኑ የአደባባብይ ምስጢር ነው፤ በተለይ በጎንደር ዙሪያ፡፡
አማራን ክአማራ ጋር ማጋጨት፤ በመንደርና በጎጥ መለያየት፤ እንዲናከስ ማድረግ፤ እንዲገዳደል ማድረግ ለአገዛዙ በጦርነት ሊያገኘው የማይችለውን እድል ሰጥቶታል፡፡
የአማራው ፋኖ አመራርና ደጋፊዎች ራሳቸውን መጠየቅ ያለባቸው አንድ መሰረታዊ ጥያቄ አለ፡፡ ይኼውም፤ ፋኖ በዱር በገደሉ እየተዋጋ ከፍተኛ ጀብዱ ያሳየውና የሚታገለው የማንን ጥቅም ስኬታማ ለማድረግ ነው? “የመጨረሻ ግቡ ምንድን ነው (what is the end game?”
ነባራዊ ሁኔታው የሚያሳየው ሃቅ አለ፡፡ የአማራው ህዝብ በኢኮኖሚው፤ በፖለቲካው፤ በአስተዳደሩ፤ በስነ ልቦናው፤ በእምነቱ፤ በቋንቋው ወዘተ የሚዘገንን ግፍና በደል እየተካሄድበት ነው፡፡ መልሶ ከማያንሰራራበት ደረጃ ተጠግቷል፡፡ ዱሮ የምናውቃት ኢትዮጵያ በአዲስ አገር እየተተካች ነው፡፡ ይህንን ሃቅ አንካድ፡፡ የዱሮዋን ኢትዮጵያ ናፋቂነት ይጎዳናል፡፡ ዋናው ትኩርት የአማራውን ህልውና ትግል ስኬታማ ማድረግ ነው፡፡ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ከሌሎች ጋር ሆነን ልንቀይሰው እንችላለን፡፡
የብሄር ፖለቲካ ስር ሰዷል፡፡
በአዲሲቷ የኦህዴድ ኢትዮጵያ ዘረኛነት መርህና አገዛዝ፤ በሁሉም ደረጃ የለየለት የአንድ ብሄር የበላይነት ስር እየሰደደ ነው፡፡ ዘረኛነት ነግሶ የዜነት መብት፤ የኢትዮጵያዊነት የዜግነት መለያ እሴት ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ ማክኗል፤ ተንዷል፡፡
ታዲያ፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚለው እሴት በተግባር ሲገመገም፤ ከምን ላይ ነው? ኢትዮጵያን ለማዳን መጀመርያ አማራውን ማዳን ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የአማራው መለያ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ አማራው ብሄርተኛ የሆነው ተገዶ እንጅ ወዶ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የናደው አማራው አይደለም፡፡ እንዲያውም አማራው በኢትዮጵያዊነቱ ተጎድቷል፤ ተገፍቷል፤ ከቀየው ተፈናቅሏል፤ በገፍ ታስሯል፡፡
ከዐብይ አህመድ ጋር እጅና ጓንቲ ሆነ የሚሰራው ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባለፈው ሳምንት የአማራ ባለ ሀብቶችን፤ የፖለቲካ መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦችን ሰብስቦ የተናገረው አማራውን ብቻ ሳይሆን ለሰው ፍጥረት ህይወት ደንታ ያለውን ሁሉ ሊረብሸውና “እልቂት በቃ፤ ዘረኛንት በቃ” ሊያስብለው ይገባል፡፡ የዜጎችን ደም መፍሰስ እንደ ተራ ነገር የሚመለከተው ይህ ባለሥልጥንና ሌሎቹ ጀኔንራሎች ለእልቂት ቀይ መስመር የላቸውም፤ ሊኖራቸውም አይችልም፡፡ “አስር ሚሊየን አማራ ቢሞት ምን ፋይዳ አለው?” የሚሉ አረመኔዎች ናቸው፡፡
ይህ ሰው አማራውን ለማስፈራራትና ለፍትህ የሚያካሂደውን የአማራ ህዝብ ትግል ወደ ጎን እንዲተው ለማስገደድ፤ “እርስ በርሳችሁ ካስጨራረስናችሁ በኋላ፤ ካሸናፊው ጋር እንሰራለን” ያለው መልእክት ልብ ላለው አማራ፤ ፋኖን ጨምሮ የህልውናው ትግል ወሳኝ ከሆነ ምእራፍ ላይ መድረሱን ያሳያል፡፡
“እርስ በርሳችሁ” ያለውን እያንዳንዱ ህሊና ያለው አማራ ሊያስበበት ይገባል፡፡ ዘግናኙና ፋሺስታዊው አገዛዝ በመሬት ላይ ፋኖን ተዋግቶ ለማሸነፍ እንደማይችል ተገንዝቦታል፡፡ ለማሸነፍ የሚችለው አማራውን ከአማራው ጋር እንዲገዳደል በማድረግ ነው፡፡ ይህንን ሴራ የሰማ አማራ የአማራ ፋኖን ትግል ካልደገፈ በራሱ ላይ ፈርዷል ማለት ነው፡፡
በተመሳሳይ፤ ይህንን የአማራ ህዝብ እልቂት ተንኮል የሰማ የአማራ ፋኖ አመራርና መሪ ከአሁኑ ጀምሮ በጋራ፤ በመተባበር፤ በመናበብ፤ በቡድን (Team). ቢቻል በአንድነት ትግሉን ለመምራት መወሰን አለበት፡፡ እርግጥ ነው፡፡ የአማራ ፋኖ እንቅስቃሴ ከተጀመረ አጭር ጊዜ ነው፡፡ የታጠቀው መሳሪያ በራሱ ህብት የገዛው፤ አብዛኛው የማረከው ነው፡፡ ይህ ተአምር የሚያስብል ነው፡፡ ሃይሉና ጉልበቱ የሰው ሃብቱ ነው፡፡ ደጀኑ፤ ደጋፊው፤ መጋቢው ተራው ህዝብና ዲያስፖራው ነው፡፡ የሚዋጋው ለፍትህ፤ ለእኩልነት፤ ለህግ የበላይነት፤ ለእውነተኛ ዲሞክራሳዊ ስርዓት፤ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ነው፡፡ ዘረኛነትን ይቃወማል፤ የሁሉንም ሰብአዊ መብት ያከብራል፡፡ ለዚህ ነው አማራ ያልሆነው ግዙፍ ሃይል የሚደግፈው፡፡
በመንግሥት ደረጃ ዘረኛነትን እንደ መርህ የተቀበለች እና በመተግበር ላይ ያለች የአፍሪካ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ ግብግቡ “የፖለቲካ ሥልጣን ፍላጎት ጉዳይ ነው” ለሚሉት ምሁራን፤ ስንት አማራ ሲጨፈጨፍ ነው ችግሩ የብሄር የበላይነት ነው ብላችሁ የምታምኑት? የሚለውን ጥያቄ አቀርባለህ፡፡ የአማራ ፋኖ የሚታገለው በአማራው ላይ እልቂት ስለተካሄደ ነው፡፡ ህገ መንግሥቱ አማራ ጠል መሆኑን መካድ ብልህነትን አያሳይም፡፡ ይህ ህገ መንግሥት እስካልተቀየረ፤ ቢያንስ እስካልተሻሻለ ድረስ ግጭትና እልቂት፤ ውንብድናና አለመረጋጋት፤ የዋጋ ግሺፈት ወዘተ አያቆምም፡፡
ዘረኛነት ለሁሉም አምካኝ መሆኑን በትግራይ የሚካሄደውን ህዝባዊ ትግል መመልከቱ ይበቃል፡፡ አንድ ሚሊየን ወገኖቻችን ተጨፍጭፈው እስካሁን በሃላፊነት የተጠየቀ አካል የለም፡፡ የትግራይ ህዝብ ሌላ ጦርነት ይደግፋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የኦሮሞው ሰፊ ህዝብም፤ አማራውም፤ ጋሞውም ወዘተ ጦርነትና እልቂት፤ እስራትና እንግልት፤ ሌብነትና ሙስና ሰልችቶታል፡ድህነት መሮታል፡፡ ግጭት ሰልችቶታል፡፡ ያልሰለቸው አገዛዙ ነው፡፡ ምክንያቱም ሥልጣኑን ለማቆየትና ለጥቂቶች ሃብት ለማካበት የሚችለው በግጭትና በጦርነት ስለሆነ ነው፡፡
ስር ነቀል ለውጥ ለምን?
በዚህ መሰረታዊ ምክንያት፤ የሚያዋጣው ሰርአቱን መለወጥ ብቻ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ጥገናዊ ለውጥ አያዋጣም፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የአማራውን ፋኖ በአንድነት እንዲሰራ ያልተቆጠብ ጥረት ማድረግ እና አማራ ካልሆኑ ወገኖቹ ጋር እንዲቀራረብ ማድረግ ነው፡፡
የመጀመሪያው ግብ አማራውን ከእልቂት ማዳን ሲሆን፤ ሁለተኛው ግብ ደግሞ ኢትዮጵያን መታደግ ነው፡፡ ለዚህ ነው፤ አማራ ላልሆኑትን የተገፉ አካላት ሁሉ የአማራ ፋኖ ትግል ስኬት ለናነተም ይጠቅማል የምለው፡፡
ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ለማዳን የሚቻለው አገዛዙን በማባበል ሊሆን አይችልም፡፡ ባድር ባህይነት ሊሆን አይችልም፡፡ አፍራሽ አገዛዝ ራሱን ለማደስ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያን በማፈራረስ ላይ የሚታየው የውጭ ሃይል አይደለም፡፡ ባለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ ያለውንን ሁኔታ ስገመግመው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ዳር ድንበር የመጠበቅ ሃላፊነቱን ሳይወጣ ትኩረት የሰጠው አምባገነኑን አገዛዝ በማገልገል ነው፡፡ የበላይ ጀኔራሎች ተጠቃሚዎችና ባለ ኃብቶች ሆነዋል፡፡ የካቢኔ አባላትም ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡ ይህ የጥቅም ቁርኝት ለአገር እና ለወገን የማሰብ እሴት የለውም፤ የሞራል ልእልና የለውም፡፡
በብዙ ሚሊየን የሚገመት ህዝብ እየተራበ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ አንድ ባለሥልጣን “ከመቶ ሃያ ሚሊየን ህዝብ አስር ሚሊየን ቢሞት ምን ይጎዳል?” ያለውን አስቡበት፡፡ በሰሜኑ ጦርነትም “ስድስት ሚሊየን ትግራይ ቢጨፈጨፍ ምን ፋይዳ አለው? “ እያሉ የሚሰብኩ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቀት አስር ሚሊየን አማራ በልዩ ልዩ ዘዴዎች ቢሞት ደንታ የሌለው አገዛዝ መሆኑን ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡
ገዢው የኦህዴድ ፓርቲ፤ መከላከያ፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት፤ የውጭ ደጋፊዎቻቸው የሚከተሉት መርህ አንድ ወጥ ሆኖ አየዋለሁ፤ የአማራውን ህዝብ ቢቻል ሙሉ በሙሉ ማጥፋት፤ ባይቻል ባሪያ ሆኖ እንዲገዛ ማድረግ፡፡ አማራው አገር አልባ ነው የምለው ለዚህ ነው፡፡
የአማራው ህዝብ ራሱን ከእልቂት ከመከላከል ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ትግሉን ማቆም ማለት ለእልቂት ራስን ማጋለጥ ማለት ነው፡፡ የአማራው ህዝብ ይህንን ራስን ማጋለጥ አማራጭ ይቀበላል የሚል እምነት የለኝም፡፡
የአማራ ፋኖ እንቅስቃሴ ስኬታማነት ለአማራው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የወደፊት እድል ይወስናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አንድ በሶሻል ሜድያ የሚተረክ ሊሆን የማይችል ጉዳይ እሰማለሁ፡፡ አማራው የሚፈልገው መልሶ ለማንሰራራትና የበላይነት ለመያዝ ነው የሚል፡፡ ይህ ሰው ሰራሽና የፈጠራ ወሬ ነው፡፡ አማራው በመላው ኢትዮጵያ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ ለብዙ ሽህዎች አመታት ከሌላው ጋር ተዋልዷል፡፡ አማራ ክልል የለውም፡፡ ብቻውን ሆኖ የገዛበት ዘመን ፈልጌ ለማግኘት አልቻልኩም፡፡ በችሎታ ሚናን መጫወትና በዘውግ አሳቦ የበላይነትን መያዝ የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ፍትሃዊ አገዛዝ ወሳኝ ነው በሚል መርህ የአማራ ፋኖ ሲታገል አማራው ብቻ ይጠቀም ማለት አይደለም፡፡ ሁሉም የሚሳተፍባትን ዲሞክራሳዊት ኢትዮጵያን መመስረትና የአንድ ብሄርን ሙሉ የበላይነት መመስረት የተለያዩ መርሆዎች ናቸው፡፡
ምን ይደረግ?
- ይህንንሁኔታ ከተቀበልን ፋኖ አንድ ፍኖተ ካርታ ያቅርብ፤ አንድ ተቋም፤ አንድ የሚሊታሪ፤ የፖለቲካ፤ የዲፕሎማሲ፤ የቁሳቁስ ቋት ወዘተ ይመስርት የሚለው ምክረ ሃሳብ ለነገ የሚባል ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡ ወቅቱ አሁን ነው፡፡ እድሉ ዛሬ ነው፡፡ ይህንን እንቁ እድል አናማክነው፡፡ ዲያስፖራው ማስተጋባት ያለበት ይህንን ነው፡፡
- የአማራ ፋኖን መሪዎችና ደጋፊዎችን አደራ የምለው እባካችሁ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር የሚለውን የአማራ ህዝብ ምክር ስራ ላይ እናውለው ነው፡፡ የአማራው የህልውና ትግል ስኬታማ ሊሆን የሚችለው በአንድነት፤ ካልተቻለ በመናበብ ሲተገበር ብቻ ነው፡፡
- ትግሉ የግለሰቦች ትግል አይደለም፡፡ የስድሳ ሚሊየን አማራ ህዝብ የህልውና ትግል ነው፡፡ በመጨረሻ፤ ድርድር አስፈላጊ መሆኑን ከዚህ በፊት ጠቁሜ ነበር፡፡ ድርድር ለማን? ድርድር ለምን? ድርድር እንዴት? ቅድመ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው፤ ከነዚህ መካከል በአማራው ህዝብ ላይ የሚካሄደው እልቂት ባስቸኳይ መቆም አለበት የሚለውን እናስቀድም፡፡
- ሁሉም መሪ ሊሆን እንደማይችል መቀበል አለብን፡፡ የራስን የጥቅም ፍላጎት፤ ዝና፤ እኔ የምለውን ብቻ ተቀበሉ የሚል አመለካከት የሚያስተጋቡ ግለሰቦች ለመምራት አይችሉም፡፡ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡ ለዚህ ነው ታጋዮቹን ዘመነ ካሴንና እስክንድር ነጋን እያመሰገንኩና እያደነቅሁ፤ መጀመሪያ ራሳችሁን ፈትሹ የምለው፡፡ የአማራውን ህዝብ ለሰራችሁት ሁሉ ስህተት ይቅርታ ጠይቁት፡፡ ይቅር ይላችኋል፡፡ ላደርጋችሁት ተጋድሎ እውቅና ስጥቷችኋል፡፡
- እናንተን የሚያለያያችሁ አላማው ነው ወይንስ ስልጣን? የሁለታችሁ ጎራ ለይቶ መንቀሳቀስ ለአማራው ህዝብ ያስከተለውን አደጋ የመገምገም ሃላፊነት አለባችሁ፡፡ አንድ ግለሰብ ለመምራት መጀመሪያ መመራትን መቀበል አለበት፡፡ ይህንን ሃቅ ከተቀበላችሁ ታሪክ ስመ ጥሩ ያደርጋችኋል፡፡ አለማወቅን ማወቅ ብልህነት ነውና፡፡
ይህንን ስል እነዚህ ታጋዮች ሚና የላቸውምት ማለቴ አይደለም፤ አላቸው፡፡ በየሞያቸው ይሳተፉ ማለቴ ነው፡፡ ለምሳሌ እስክንድር በውጭ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ሚና ሊኖረው ይችላል፡፡ ዘመነ በወታደራዊ ክንፉ ወዘተ፡፡ ሌሎች የአማራውን ፍትሃዊ ትግል ስኬታማ ለማድረግ ብቃት ያላቸው ወጣት አማራዎች በመሪነት ፊት ለፊት እንደሚመጡ ለማድረግ ድፈሩ፡፡ አጋር ሁኑ፡ አዲስ ምርጫ አስፈላጊ ከሆነ ስዲስ ምርጫ ይካሄድ፡፡
- የእላማ አንድነትን፤ ጥሩ ስነ ምግባርን፤ አንድ መርህን፤ አንድ ተቋምን፤ አንድ ቡድናዊ ወይንም በጋራ የመስራት መርህን የማይቀበሉ ግለሰቦች ሊመሩ አይችሉም፡፡ አንድ ግለሰብ ለመመራት ፈቃደኛ ካልሆነ ሊመራ አይችልም የሚለውን መስፈርት እናስብበት፡፡
- የአማራው ህዝብ ብቻውን ኢትዮጵያን ሊታደጋት አይችልም፡፡ የሚያዋጣን አማራጭ አማራ ያልሆኑትን ሁሉ–ጋሞውን፤ አኟኩን፤ ጉራጌውን፤ አፋሩን፤ ሶማሌውን፤ ወላይታውን፤ ትግራዩን፤ ኦሮሞውን ወዘተ እምቢተኛነት እንዲያሳይ መቀስቀስና እንዲታገል የማድረግ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ማስተጋባት አንዱ የወቅቱ አስቸኳይ ጥሪ ሆኗል፡፡
- የአዲስ አበባ ህዝብ የተከሰተው አደጋ በየቤቱ እንደሚመጣበት አምኖ የትግሉ አጋር እንዲሆን ሰፊ ስራ መሰራት አለበት፡፡
- የአማራው ወጣት፤ ምሁራንና ልሂቃን ዳር ቆመን የምናይበት ወቅት በታሪክ ያስጠይቀናል፡፡ ትግሉን እንደግፍ፡፡ ትምህርታዊ ዘመቻ እናካሂድ፤ የመቻቻል፤ የመደማመጥ፤ ይቅር የመባባል፤ አብሮ የመስራት ባህልን ሳንሰለች እናስተምር፡፡
- በመጨረሻ፤ የአገዛዙንአረመኔነት፤ ጭራቅነት፤ አምካኝነት፤ አማራ ጠልነት፤ ሰላምና እርጋታ አምካኝነት ሳንሰለች ለዓለም ተቋማትና መንግሥታት እናቅርብ፡፡
ለማስታወሻ፤
ባለፈው ሳምንት በተከታታይ በእስክንድር ነጋ ላይ እጅጎ የሚያሳዝን ዘመቻ ተካሂዷል፡፡ ከኢጋድ፤ ከአሜሪካ ተራድኦ፤ ከአውሮፓ አንድነት ማህበርና ሌሎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ፡፡ ከእኛ ይልቅ ጀፍ ፒርስ ያስተላለፈው መልእክት ሚዛናዊ ነው፡፡ እስክንድር በዓለም ደረጃ እውቅና ያለውም መሆኑን፤ በአማራው ህዝብ ላይ የተካሄደውንና አሁንም የሚካሄደውን ቀውስ ለነዚህ ተቋማት ማቅረቡ አግባብ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ መልእክት ነው፡፡ እኔም በመሬት ላይ ያለውን እልቂትና ውድመት ለነዚህ ተቋማት ማቅረብ ድርድር አለመሆኑን ተገንዝቢያለሁ፡፡
የሚያዋጣትን እርስ መነታረክ ሳይሆን ከላይ ያቅረቧቸውን ምክረ ሃሳቦች መተግበር ነው፡፡
February 3, 32025