መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
“ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ”
— መክብብ 7፥5
እስቲ ቆም ብለን በማሰብ ራሳችንን እንፈትሽ ። እንደ ሰው ፣ የምንጓዝበት መንገድ ትክክል ነውን ? ከቶስ ሰው መሆናችንን እናምናለንን ? እያንዳንዳችን ሰው መሆናችንን እስካላመንን ጊዜ ድረስ ጥላቻችን እየገዘፈ እንደሚመጣ ማስተዋልስ ለምን ተሳነን ? ኧረ እባካችሁ ከሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ለምን አንማርም ? ክብሩን ሰው በረሮ ( cockroach ) ብሎ በመበየን ፣ሰው ፣ ሰውን በጅምላ ፣ በጭካኔ መጨፍጨፉን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢሊቶች እንዴት በአጭር ዓመታት እንዴት ዘነጉት ? ( “ ቱሲዎች “ “ ለሁቱ “ ጎሣ በረሮ ነበሩ ። በዛን ወቅት ሁቱዎች 800 ሺ ንፁሐን ቱሲዎችን ጨፍጭፈዋል ። )
እኛስ ፣ ኢትዮጵያውያን ከዘመን በኋላ በሰው የተፈጠረው የጎሣ እና የዘውግ አጠራር ለምን ሰውነታችንን ያጠፋብናል ? ሰው መሆናችንን ይሰርዘዋል ? ለምን ከተሳሳተ የታሪክ ትርክት በዘመኑ ንቃተ ህሊና ዝቅተኝነት የተነሳ ከተፈጠረ ቆዳ መዋደድ ሙሉ ለሙሉ መውጣት ተሳነን ? ለምን ይሆን በሚገርም መልኩ ዛሬም በአስተሳሰብ ደረጃ ፣ አመድ በዱቄት ሲስቅ ጀንበር የሚጠልቀው ? በተግባር ውሃ ጠብ አድርገን ብንፈትሸው እኮ የአመድ ከንቱነት የዱቄት ምግብነት ይገለጽልናል ።
እውነቱ ይኽ ይሁን እንጂ ፣ በአስተሳሰብ ደረጃ ፣ ዛሬም በአገራችን አመድ በዱቄት መሳቁን ለማቆም አልቻለም ? ከቶስ አመድ በዱቄት መሳቅ አለበት ወይ ? ዱቄት እኮ ምግብ ይሆናል ። ሰውነት ያደረጃል ። እምብዛም ጥቅም የማይሰጠው አመድ ዱቄትን በመምሰሉ ብቻ እንዴት ህይወት ያለውን የዱቄት ተግባር ሊሳለቅበት ቻለ ? እንዴት ፈርሃ እግዚአብሔር ያለውን ጠቃሚ አስተሳሰብ እና አመለካከት ከልቦናችን ለማስረፅስ ብዙዎቻችን አቃተን ? ዛሬ እየተጎዝንበት ያለው ሰው መሆናችንን የመርሳት እና የመገዳደል አባዜስ እየበረታ ፣ እየጎለበተ እና እያየለ የመጣው ጥቂት የማንባለው “ በአስተሳሰብና በአመለካከት ደረጃ “ አመድ “ ሆነን ሣለ ጠቢብ በሆኑት ፣ አገርን ወደ ብልፅግና የሚወስድ አስተሳሰብና አመለካከት ባላቸው ጠቢባኖቻችን ( ልሂቃን ) መዘበታችንን በመቀጠላችን አይደለምን ?
ይህ ሁሉ ስደት ፣ መፈናቀል ፣ መጠላላት ፣ እርስ በራስ መገዳደል በዚህ ዘመን አይሎ የታየው ፣ ሁሉንም መልካም ነገር ፣ ሁሉንም የዕድገት ጉዞ ፣ በጥላቻ ጠንሳሾቹ ፤ የአይጠረቄነት መንፈስ በተጠናወታቸው ፣ የነዋይ ፍቅርም ባሰከራቸው ፣ የግብዝነት አስተሳሰብ በህሊናቸው በገዘፈ የአገር ልጆች እና ለጥቅማቸው ብቻ በቆሙ የፈረጠመ ጡንቻ ባላቸው የውጪ ኃይሎችና እንዲሁም ህሊናቸውን በሸጡ በግራና ቀኝ ባሉ ምናገበኝ ባይ ፖለቲከኞቻችን እና ልሂቃኖቻችን ተባባሪነት አይደለም እንዴ ? ይኸው ዛሬም ከዕድገትና ብልፅግና አንፀር ፣ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደኋላ እየተጓዝን ያለነው ፣ “ ከራስ በላይ ነፋስ “ የሚል መርህን ስለምንከተል አይደለምን ? ኩንን ከሆነው “ አመድ በዱቄት የመሳቅ አባዜ ያልተላቀቅነውስ ቆም ብለን “ እኔ በፍጥረት ማን ነኝ ? “ ብለን መጠየቅ ተስኖንን አይደለም እንዴ ?
ይኽ ኩንን አመድ በዱቄት ላይ የመሳቅ ተግባራዊ ሂደትስ ከ33 ዓመት በፊት አይደለም እንዴ በረቀቀ ሤራ የህገመንግስት ሽፋን ተሰጥቶ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ? (የአውሮፓ ሀብታም መንግስታት ፣ አሜሪካ ፣ ሩሲያ ፣ ቻይና እና ኤሜሪት … ለምን ወደብ ይገዛሉ ? አሜሪካስ ከናዳን እና የፓናማ ግዛት ለመጠቅለል ለምን ፈለገች ? ሩሲያስ ለምን ዩክሬንን ወረረች ? ለየአገራቸው ጥቅም አይደለምን ? )
በአፍሪካ እና በእኛ አገር ግን አገራቸውን ለመጥቀም ባላቸው ዕውቀት እና ተሰጥኦ በብርቱ እየተጉ ፣ ያለመታከት በጎ ምክር እና ተግፀስን የሚለግሱን እና ሲለግሱን የነበሩትን ሊቃውንቶች መቼ ሰማናቸው ? ቆም ብለን ብናስተውል ከ30 ዓመት በፊት የታተሙ መፅሐፍት ፣ መፅሔቶችና ጋዜጦች ሰው ጠል አመለካከትና አስተሳሰብ መጨረሻው ውድመትና ዕልቂት መሆኑንን አስጠንቅቀውን ነበር እኮ ። ሲቀጥል አራተኛው መንግስት ፕሬስስ ዛሬ የት ነው ያለው ? ብሎ መጠየቅ እጅግ አስፈላጊ ነው ።
አራተኛው መንግስት ( ከህግ አውጪው ፣ ከህግ ተርጓሚው እና ከህግ አስፈፃሚው ቀጥሎ ፕሬስ ቀና ምክር ፣ ሂስ እና ተግፃስን በማቅረብ ፣ መንግስትን አጋዥ የሆነው ፣ አራተኛው ወሳኝ የመንግስት አካል ይባላል ። ) ኢህአዴግ ሥልጣንን በያዘ ማግስት እጅግ ገኖ እንደነበር እናስታውሳለን ። ህትመታቸው አነስተኛ ቢሆንም ፣ የወቅቱን ሶሾ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የሚዘግቡና የሚተቹ የተለያዩ ጋዜጦቸ ና መፅሔቶች በየቀኑ ፣ በየወሩ እና በየሳምንቱ ለአንባቢ ይቀርቡ ነበር ። ያለፈውን የሆነ ሰገነት ዘመን ዞር ብሎ መቃኘት ጠቃሚ ነው ። በዛን ዘመን የተፃፉትን ፣ በሳል ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚየዊ እና ማህበራዊ ይዘት ያላቸውን ፅሑፎች መልሶ በማንበብ ፣ ቆም ብሎ በማስተዋል ለሀገር ታላቅነት መስራት የሚበጅ ይመስለኛል ።
በአናቱም ፣ ህሊናችንን ፈፅሞ ከማይገነባ ከከንቱ ውዳሴ ይልቅ ፣ የጠቢባንን ተግፀስ መስማት ከግብዝነት ለመፅዳትና ህይወትን በማስተዋል ለመምራት እንደሚጠቅምም እንገንዘብ ። ተገንዝበንም በማስተዋል በተሰማራንበት የሥራ መስክ እና የኃላፊነት ቦታ ብቻ ሳይሆን ለአገር ብልፅግና የምንችለውን ሁሉ መሰዋት እንክፈል ። ሁሉም ዜጋ በሰውነት እኩል መሆኑን ተገንዝቦ በከንቱ ውዳሴ ሳይፈነድቅ ፣ ገንቢ ተግፃስን እና ትችትን በጆሮው አዳምጦ ፣ አንብቦና ተመልክቶ እራሱን በመውቀስ በቀና ጎዳና ሲጎዝ አገር ልትበለፅግ ትችላለች ። ብዬ አምናለሁ ።
ጎበዝ ፣ እያንዳንዳችን ሰዎች ነን ። በአገር ደረጃ ደግሞ ዜጎች እንባላለን ። በግለሰብ ደረጃ እያንዳንዳችን ፣ የጠቢባንን ተግፃስ ሰምተን እራሳችንን እንደምንወቅስ ሁሉ መንግስትም ትችት ፣ ወቀሳና ተግፃስን የማዳመጥ ከባድ ኃላፊነት እንዳለበት እና ይህንንም ኃላፊነት የሰጠው የመረጠው ይኸው የሚተቸው ህዝብ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም ። ለዚህም ነው መንግሥት ገንቢ ትችቶችን አዳምጦ ፣ “ ዜጎች ጠንክረን እንድንሰራ የሚያሰራ ፖሊሲና የፖለቲካ መንገድ በተጠና መልኩ መቀየስ ፤ በተግባር ላይ የዋሉትንም በድጋሚ መመርመር ና ማሻሻል ይገባዋል ። “ የሚባለው ።
አዲስ ፣ ጠቃሚና ሁሉንም ዜጋ አሳታፊ ፖሊሲዎች ፣ በወጉ ተመርምረው በተግባር ላይ ከዋሉ እና የፖለቲካ ምህዳሩና የመጫዎቻ ህጉ እና የተሳታፊዎች መድረክ ግልፅ ፣ ፍትሐዊ እና ጠልፎ መጣል ከሌለበት ፤ እኛም ዜጎች ፣ ዘወትር ጠንክረን እየሰራን ጎን ለጎን ሳንታክት እንደሃይማኖታችን ለፈጣሪ በመፀለይ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ያለአንዳች ሥጋት ኑሯችንን ለመለወጥ ጠብ እርግፍ በማለት ለአገር ልማት የበኩላችንን አስተዋፆ ለማድረግ እንችላለን ። …
ሁላችሁም እንደምታስተውሉት ፣ ዛሬ እና አሁን ገሮች እየከፉ መጥተዋል ። በዓለም ዙሪያ የሚታየው ነገር ሁሉ አስፈሪ ነው ። አስደንጋጭ ነው ። በሽታ በዝቷል ። ቸነፈር በዝቷል ። ረሐብ በዝቷል ። ጦርነት በዝቷል ። በዛው መጠን ደግሞ አስረሽ ምችው በዝቷል ። ሰማይን በርግጫ የሚል ደልቃቄም ቁጥሩ ትንሽ አይባልም ። … ሰማይን በርግጫ ካላልኩ በሚለው፣ በፈጣሪ በተፈጠረው ሰው እኩይ እና ዘግናኝ ድርጊት ዓለም ዘወትር ትገረማለች ። እኩይ ድርጊቱ ሲገዝፍም ምድሪቱ ደም ታነባለች ። የሰው መጨካከን ምድሪቱን በሰው ደም እያጨቀያት ነው ። ነገሩ በማስተዋል ለተመለከተ ይዘገንናል ። አንዳንዴ ሳስበው ሰው የመጨረሻ ጅል ነው እንዴ ? እላለሁ ። ለዚች ሰባ ዓመት ለማትሞላ የምድር ቆይታው በፍቅር ከመ ኖሮ ይልቅ መገዳደልን መመረጡ ፤ ጥላቻን ገንዘቡ ማድረጉን እና አመድ በዱቄት እየሳቀ ጀንበሯ መጥለቋን ሳስተውል በሰው ሞኝነት በአያሌው እደመማለሁ ። ( ልብ አድርጉልኝ ከሰው ተርታ ሁላችንም አለን ። )
በመገረምም “ ሰው ጅል ነው ። ሲሞት አስከሬን ሲሆን ነው ጅልነቱን የነገ ሟቾቹ የሚረደቱ ። ሰውን ሞቶ ስትመለከቱት ብቻ ነው ፣ ‘ ለካ ሰው እንዲህ ጅል ነው ። ‘ የምትሉት ። ምንም እንኳን ራሳችሁን እንደንጉስ የምታዩ ብትሆኑ ፤ በህይወት ሳላችሁ ፣ ቁጡ ፣ ሀይለኛ ፣ አትኩኝ ባይ ወዘተ ። ብትሆኑም ፤ ስትሞቱ ፣ ምንም ማድረግ የማትችሉ ፣ በድን ስለምትሆን የመጨረሻ ጅል ሆናችሁ ለተራ ሟቹ የምትታዩት ።
“ ይህንን የምትረዱት ዛሬ በህይወት ሳላችሁ ማስተዋልን ገንዘብ ስታረጉት እና የጠቢባንን ተግፃስ ሥትሰሙ ብቻ ነው ።
“ የጠቢባንን ተግፃስ ሰምታችሁ ፣ ማስተዋልን ገንዘብ ካደረጋችሁት ፣ ሰው ሲወለድ ሞት አብሮት እንዳለ ትገነዘባላችሁ ። ይሁን እንጂ እስከዛሬ በህይወት ያለ ሰው ሁሉ የሚሞተው ሞቶ ያየው ሰው ብቻ ይመስለዋል ። በዚህ ጅል ዕውቀት የተነሳም ፣ ሰው ፣ አምሳያውን ሰው በጅምላ ለማጥፋት የሚችልበትን መሳሪያ ዘወትር መፈልሰፉን እንሆ ቀጥሏል ።
“ በአውዳሚ ጦር መሳሪያ ረገድ ፣ ዛሬ ፣ ዛሬ ኃያላኑ ሀገራት አንድን ከተማ ለይቶ እንዳልነበረ የሚያደርግ አውቶሚክ ቦንብ ወይም የኒኩለር ሚሳኤል አላቸው ። በፈለሰፉት ጅምላ ጨራሽ የጦር እና የባዮሎጂ ገዳይ መሳሪያዎችም ዛሬ መፈራታቸው ከወትሮ ይልቅ ዛሬ በእጅጉ አስደንጋጭ ሆኖ እናገኘዋለን ። “ እናም ለጥቅማቸው ሲሉ የትኛውንም የማደግ ፍላጎት ያለውን አገር እንዳያድግ የዕድገት መንገዱን መዝጋት ይችላሉ ። በእጅ ጥምዘዛም ” እስከምድር ፍፃሚ ይበዘብዙታል ።” እያስተዋልን ያለነውም ይህንኑ እውነት ነው ።
“ እያስተዋልን ያለነው ብዙኃኑ የማደግ ፍላጎት ያለው ሀገር ፣ በተለይም “የመብልፅግ ጥማቱ ከፍተኛ የሆነው መላው አፍሪካ ” እስከዛሬ እንኳን ሊበለፅግ ፣ በእነሱ ምፅዋት ድጋፍ ይኸው ወደ ሦስተኛው ሚሊኒየም እየገሰገሰ ነው ። “ በማለት እብከነከናለሁ ።
የአፍሪካ ሊሂቃን እና የዓለም አሳቢያን እንደሚመሰክሩት ፣ አፍሪካዊው በምፅዋት የሚኖረውም ከበቂ በላይ የሚታረስ ለም መሬት እያለው ነው ። ይኽንን ለም መሬትም የእንስሳት ፣ የእፅዋት ፓርክ እና የማዕድን አካባቢ በማለት ፣ ለብዝበዛ እንዲያመቻቸው “ወፍ ዝር የማይልበት ጥብቅ አካባቢ ” ብለው በህግ ና በመሳሪያ የሚያስጠብቁት ። በዚህ ረቂቅ ድርጊታቸውም አፍሪካዊያንን በረሃብ እና በችጋር ይቀጣሉ ። በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ታጥረው የተቀመጡ ጥበቅ ሥፍራዎቹ እጅግ ለም ናቸው ። በኢትዮጵያ እንኳን በሁሉም ክልሎች ጥብቅ ሥፍራዎች የበዙ ናቸው ። የአገርን ኢኮኖሚ በፓርክነታቸው ፣ በዕፅዋት ሥፍራነታቸው ከድህነት እያላቀቁ ግን አይደለም ።
በነገራችን ላይ ለዕፅዋት የተከለሉትን ሰፋፊ መሬቶችን አጥሮ ከማስቀመጥ ፣ ጎን ፣ ለጎን ፍራፍሬዎችን በማልማት የአገርን ኢኮኖሚ በጥቂቱ እንኳን መገንባት ይቻል ነበር ። ኢትዮጵያ በሜዳማ አካባቢዎች ፣ እጅግ ለም በሆኑ ሰፊ ለም መሬቶች ያውም ወንዞች በውስጧ እየፈሰሱ በሰፋፊ መሬቶቿ ላይ ለአገር ጠቃሚ በሆኑ የግብርና ዘርፎች መሰማራት አዋጪ ሆኖ ሆና ብታገኘውም የተከለከሉ ጥብቅ ሥፍራዎች በመሆናቸው ሰበብ በምግብ ሰብል ራሷን ለመቻል አዳግቷታል ። ።
በአገራችን ላይ ፣ በገዛ አገራችን ከስንዴ ልመና የሚያወጣንን መንገድ ወይም ፖሊሲ መቀየስ ለምን አቃተን ? የተሻለ ጥቅም የሚሰጠውን እና ከተረጂነት የሚያወጣንን የእርሻ እና የእርሻ መሬት ፖሊስ በማውጣት በለሀብቶች በዚህ አዋጪ ሥራ እንዲሰማሩ በማድረግ የምግብ ፍላጎታችንን ሙሉ ለሙሉ ለማሞላት ለምን ተሳን ? በነገራችን ላይ ፣በከርሰ ምድር ውሃችን ላይስ ለምን የተለየ ፖሊሲ አልተጠቀምንም ? ከከርሰ ምድር ውሃ በማውጣት የሚጠቀም ሁሉ የከርሰ ምድር ውሃ ተጠቃሚነት ግብር ለምን አይከፍልም ? በከርሰ ምድሩ ” የአገር ውሃ ” አምርቶ እየተጠቀመ አይደለምን ? የውሃ አቅራቢዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም የከርሰ ምደር ተጠቃሚዎች ለውሃችን የመክፈል ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል ። …
ማጠቃለያ
ቆም ብሎ ማሰብና ራስን በራስ ወቅሶ ወደጠቃሚው መንገድ መምጣት ለራስም ፣ ለቤተሰብም ፣ ለአገር ይበጃል ። ሁሉም ያልፋል ። የማያልፍ የለም ። ከማለት ፣ ከማብቃቱ ፊት ግን በትክክለኛው ፣ ሰው ፣ ሰው ፣ በሚሸተው በህይወት መንገድ ላይ መገኘት ያስፈልገናል ። የትኛውንም ያህል ሀብት ብናከማች ስንሞት ይዘነው አንሄድም ። ራቁታችንን መጥተናል ። ራቁታችንን እንሄዳለን ። ያለን ሀብት ፣ ያለን ሥልጣን ከሞት አያድነንም ። ከመቀባር በላይ በክብር ሥማችንን የሚያስጠራውና በትውልዱ ህያው የሚያደርገን መልካም ፣ ቅን እና በጎ ሥራችን ብቻ ነው ። እናም ይህንን እውነት ቆም ብለን ካላሰብን ፣ ግራና ቀኝ አይተንም ካላስተዋልን ፤ ከጠቢባኖቻችንም ለመማር አላዋቂነታችንን ካልተረዳን ፣ አገራችንን ወደ ብልጽግና መውሰድ ከቶም አንችልም ። አበቃሁ ።
የሚሰማ ጀሮ ካለ ማለፊያ ምክር ነው። ግን ሃበሻ አፍ እንጂ ጀሮ የለውም። የችግራችን ምንጭ ለእኔ ብቻ ማለት ነው። ሌላው የዘር፤ የጎሳ፤ የሃይማኖቱ ግርግር ሁሉ ግቡ አምጡ ነው። መንግስት ሂዶ መንግስት ሲተካ ረገበ ያልነው ጠብ የለሽ በዳቦ እንደገና አገርሽቶበት ይኸው እንሆ ዛሬ ላይ ቆመን የሃገራችን ሃበሳ ድጋሚ እያየን ነው። የጠባብ ብሄርተኞች ማቀንቀን፤ የክልል ፓለቲካው ሌላው ሌላውም ጥሩንባ የማባያ ሃሳብ ለማጎልበት የሚጠቀሙበት እንጂ ለህዝባችን አንድም ቀን አስበው አያውቁም። ያ ቢሆን ኑሮ 50 ዓመት ሙሉ በወያኔ የትግራይ ህዝብ ፍዳውን ባልቆጠረ ነበር። ዛሬም የእነርሱ መሻኮቻና መነገጃ ባልሆነም። ግን እብድ ድንጋይ ብቻ አይደለም የሚያቀብለው ለብቻው ስቆ ለብቻው ይኖራልና ያለ ልክ የደለቡት ስመ ጄኔራሎችና የወያኔ ካድሬዎች ዛሬም ይህን ህዝብ ለመከራ እየዳረጉት ይገኛሉ። ይህ በራሱ እብደት አይደለም የሚል ራሱ ያበደ ነው። በቅርቡ ጄ/ዪሃንስ ገ/መስቀል “አዙሪት” በሚል አርዕስት ለንባብ ያበቁት መጽሃፍ ሊነበብ የሚገባው ነው። እኔ የምትናፍቀኝ ኢትዮጵያ የሁሉ የሆነች ሰው በፈለገው ቋንቋና ባህል የሚኖርባት ነጻ የሆነች ምድር ነው። እውቁ ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ” የፒያሳ ልጅ” በሚለው መጽሃፉ ላይ ከምዕራፍ 1-3 ባሉት ያሰፈራቸው የልጅነት ትውስታዎች ኢትዮጵያን ያሳያሉ። ከየትም በየትም በመምጣት አዲስ አበባ ላይ በመሰባሰብ አብረው አድገው፤ አብረው ተምረው የኖሩባትን ዘመን ሲተነትን እንባ ያስመጣል። እኛ ላይ ምን ተደገመብን?
በእኔ እይታ አሁን ላይ ያለው የሃገሪቱ ችግር ከመንግስት ብቻ የመነጨ ነው ብዬ አላምንም። አዎን ይህን በማለቴ ድንጋይ የሚወረውሩብኝ አልፎ ተርፎም በቡጢ ሊነርቱኝ የሚሹ ይኖራሉ። ግን እውነታው እሱ ነው። በውስጥና በውጭ ለጥቅምና ለስልጣን ፍልሚያ የሚያደርጉ በሄርተኞችና ክልል አምላኪዎች ተጨማሪ የሃገሪቱ በሽታ ናቸው። የሃበሻ ፓለቲካ በገመድ ጉተታ ጫዋታ ይመሰላል። አንድ አንድን ሲጎትት የዝንተ ዓለም ፍክክርና ንትርክ፤ እልፈት የለሽ ጣርና መከራ! ራሱ የገዛ ቋንቋችን ጠላታችን ነው።
እስቲ እንዲህ ያልኩበትን ጉዳይ ላስረዳ። ለምሳሌ ክልል የሚለው ቃል በጥሬው ሲተረጎም – ቅጥር አበጀ፤ የእኔ ነው አለ ማለት ይሆናል። ይህ ሸረከታም ወያኔ ፈጠር ቃል የበለጠ እንድንከፋፈልና አልፎ ተርፎም እንድንጋደል አድርጎናል አሁንም መገዳደላችን አልቆመም። ይህ ሊቀየር የሚገባው ከፋፋይና ከጨካኙ የጣሊያን የአገዛዝ ስልት የተቀዳ ነው። ሌላው አሳዛኙ ቃል የደርግ ወታደር፤ የወያኔ ወታደር፤ የብልጽግና ወታደር የሚለው አባባል ነው። ወታደሩ “የኢትዮጵያ ወታደር” የሚሆነው መቼ ነው? ግን በተሳከረ ፓለቲካ ውስጥ ለሃገሩ የወደቀውን ወታደርና ቤተሰብ በመዘንጋት ጭንቅላቱን እንደ ተቀላ ደሮ መንደፋደፍ የዘመን ስሌታችን ሆኗል። ሌላው እንገነጠላለን በራሳችን ሃገር እንሆናለን የሚሉን ሸቀጣም ፓለቲከኞች ዛሬም አንድ እግራቸው መቃብር ላይ ቆሞ አለማረፋቸው ነው። እስቲ በእናንተ ትግል የአማራ ህዝብ፤ የኦሮሞ ህዝብ፤ የትግራይ ዝህብ ወይም ሌላው የሃገሪቱ ወገናችን ምን አተረፈ? መልሱ ባዶ ነው። ህዝብን ማሸበር ጀግንነት ነው? አይበቃም የምድሪቱ መከራ? የዚህ የሃገር ግንጠላ ነገር ሲወሳ አንድ ትዝ የሚለኝ ነገር አለ። አሁን በህይወት ይኑር አይኑር አላውቅም። የወንጌት ተማሪ ከዚያም በአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ በስታትስቲክ የተመረቀ አንድ ፍሬው የሚባል ሰው ነበር። በህዋላ ላይ ስሙን ቀየረ። በደርግና በወያኔ በእጅጉ የተሰቃየ ሰው። ታዲያ ከእነዚህ ሰው በላ ሰርአት አምልጦ ባሌ ተራሮች መሃል ከመሰሎቹ ጋር ይገናኛል። ከረጅም ቆይታ በህውላ እውቁ ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ደ/አፍሪቃ ላይ አግኝቶት ብዙ ከተጫወቱ በህዋላ “ለመሆኑ ኦነግ አሁንም የመገንጠል ጥያቄ ያነሳል” ሲለው የሰጠው የመጨረሻ መልስ ለእኔ ይመቸኛል። “ኦሮሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ግንድ እንጂ ቅርንጫፍ አይደለም። ግንድ አይገነጠልም” ይህን ያለው ኢብሳ ገዳ ነው። ዛሬ የት ይሆን? በህይወት አለ? አርቆ አሳቢዎችንና አስታራቂዎችን እያሳደድን ለሆድ ያደረውን ያለ ቦታው እየሰካን የህዝባችን መከራ ያራባነው እኛው ነን። እንግዲህ የዋሁን የትግራይ፤ የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ተምረናል ብለን መርዝ በመጋት እንዲህ የከፋፈልነው እኛ ነን። እኛ ስንናከስ አለቆቻችን ሊኖሩና ሊከብሩ። አበስ ገበርኩ! አይ የነጻነት ትግል ድንቄም ነጻ ትውጣ!
በመጨረሻም የሃይማኖት ተቋሞችና መሪዎች የቆመን ከመደገፍ ይልቅ የወደቀን ማንሳት ቢችሉ መልካም በሆነ ነበር። የሚበላውና የሚጠጣው የሚጠለልበት የሌለውን ህዝብ በባዶ ሆድ ” የሰማይ ቤት” አለህ ቢሉት አይሰማም። የሃይማኖት መሪዎች ግፈኞችን፤ ከፋፋዪችን፤ ዘረኞችንና ሴራዎችን ሁሉ ሊያወግዙ ይገባል። አቋማቸው ከብሄርተኝነት የጸዳ መሆን አለበት። ዛሬ ላይ እኔ የዚያ ወገን ነኝ፤ አያቴ ከዚህ ነው፤ አባቴ ከዚያ ነው እንባባል እንጂ ትርፍ የለውም። የሰው መመዘኛው ሰው ሆኖ መገኘቱ ነው። ወታደሩም የኢትዮጵይ ወታደር ነው። ክልሉም የሁሉም የሃገሪቱ ልጆች መኖርያና መፈንጫ ነው። ለአንድ ብሄር እንካችሁ ተብሎ የሚሰጥ ነገር በምድራችን መኖር የለበትም። የዘር አሰላለፍ ይቅር። አንድ አባቶች የሚሉት አባባል አለ። ” በየወገንህ ቢሉት የመቶ ዓመት ቆዳ ገብያ ወቶ ቆመ” ይላሉ። ዘረኛ ሆኖ ጤናማ እይታ ያለው የለም። ምቀኝነትን መጠላለፍን አስወግደን ሃገራችን በውጭም ሆነ በምድሪቱ ላይ የምንኖር በህብረት ለሰላምና ለእድገቷ እንስራ። ልብ ይስጠን!