
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ ብቻ ሳይሆን ሰዎቹ እራሳቸው ፣ እንደክሪስሜስ ዛፍ አሸብርቀው ፣ አምረው ና ተውበው ፣ ወርቅ መስለው ፣ ዝንጥንጥ ብለው በደስታ እየተፍከነከኑ አዲስ ዓመትን ተቀብለዋል ። ይህንን እውነት ዕድሜ ለሶሻል ሚዲያ በቀጥታ ሥርጭት አይተናል ። እርግጥ ነው በእኛው ሻራተንም ” በ20ሺ ብር ብቻ መፈንጠዝ ተችሏል ። ” ማን ከማን ያንሳል ? …
ሰው በመሰረቱ በቀላሉ የሚደሰት እና በቀላሉ የሚያዝን ፍጡሩ ነው ። ፍንጥዝያና ጭምትነት ፤ ለቅሶና ሳቅ ደግሞ በጉያው ያሉ የስሜት ነውጦቹ ናቸው ።
እነዚህ የስሜት ነውጥች ዘወትሮዋዊ ቢሆንም በአውሮፓው ዜጋ እና በአፍሪካው ዜጋ የሚስተዋለው የስሜት ነውጥ ግን በእጅጉ ይለያያል ።
አውሮፓዊው ዜጋ የስሜት ነውጡ ፤ ፈንጠዝያው ና ሐዘኑ ከመንፈስ ደስታ ከማግኘት ጋር የተቆራኘ ነው ። በአመዛኙ ። አፍሪካዊው ደግሞ ሐዘኑ እና ፈንጠዝያው የተቆራኘው ከዕለት ጉርሱ ከአመት ልብሱ ጋር የተቆረኘ ነው ። ያ ማለት አፍሪካዊው ገና መሰረታዊ ፍላጎቱን ያላረካ ምስኪን ሰው ነው ማለት ነው ። ለመሆኑ ይኽ ምስኪንነት ከፍ ሲል ደሞ ምንዱባንነት ( ዘመን በአዲስ እየተቀየረ የትየለሌ ደርሶ እንኳን ) እስከዛሬ እንዴት ሊቀረፍ አልቻለም ?
ይኽ ጥያቄ በጥበብ የሚመለስ ጥያቄ ቢሆንም በዋነኝነት ፖለቲካዊ ምክንያት አለው ።
መቼም የፖለቲካ ሳይንቲስቶች እንደምታውቁት ዓለምን የሚገዛው ፖለቲካ ነው ። ፖለቲካ የህዝብ የአስተዳደር ዘይቤ ነው እስካልን ድረስ ኢኮኖሚውንም ሆነ ማህበራዊ ጉዳዩን የሚያሽከረክረው እርሱ ነው ። ይላሉ የዘርፉ ልሂቃን ። )
እርግጥ ነው አለምን የሚገዛው ፖለቲካ ነው ። ይሁን እንጂ ይህ ገዢ ፖለቲካ ፈጣሪ እንዳለው አንዘንጋ ።…
“ፖለቲካው ዓለምን ይገዛል “ ስንል የፖለቲካ ፈጣሪዎች የፖለቲካውን መሪ ይቆጣጠራሉ ። እነሱ እንዳሻቸውም ይዘውሩታል ። እንደፈለጋቸውም ያሽከረክሩታል ማለታችን እንደሆነ ይሰመርልን ።
ለመሆኑ እነዚህ የፖለቲካው ዘዋሪዎች እነማን ናቸው ? መልሱ ግልፅ ነው ። በኢኮኖሚ የፈረጠመ አቅም ያላቸው አገሮች ሁላ ናቸው ።
አሜሪካ ፣ ቻይና ፣ ሩሲያ ፣ እንግሊዝ ፣ ጀርመን ፣ ፈረንሳይ ፣ ኢጣሊያን ፣ ሳውዲአረቢያ ፣ እስራኤል ፣ …ቱርክ ። ወዘተ። የፈረጠመ የኢኮኖሚ ያላቸው ናቸው ።
እነዚህ አገራት ለሀገራቸው የሚጠቅም ፖለቲካን በዴሞክራሲ ፣ በ’ሪኦተ ዓለም እና በኃይማኖት ሥም በአፍሪካ አገራት ላይ ያራምዳሉ ።
ፓለቲካቸውን የአፍሪካ መንግስታት ተቀብለው እንዲተገበሩም በሞኖፖል በያዟቸው የኢኮኖሚና የኃይማኖት ተቋማት አማካኝነት እጅ ይጠመዝዛሉ ። ( ወርልድ ባንክን እና አይ ኤም ኤፍን መጥቀስ ይቻላል ። )
ይህ ብቻ አይበቃቸውም ፣ ህዝቡም በአጠቃላይ እውቀት እንዳይበለፅግ አንድ መግባብያ ቋንቋ ኦንዳይኖረው ያደርጋሉ ። አንድ አይነት ፍጡር ፤ ያውም ክቡር ሰው ሆኖ እያለ በሚነገረው ቋንቋ እንዲጠራ በማድረግ ሰውነቱን ያስረሱታል ። እርስ በእርሱም እንዳይገባባ በቋንቋው ብቻ እንዲማር ያስገድዱታል ። ብሔራዊ ቋንቋ እንዳይኖረው ያደርጉታል ። ወደ 14ኛው እና 15ኛው ክፍለ ዘመን የወረደ አስተሳሰብን የሚያራምድ ግብዝና ተራ ሰው ያደርጉታል ። በዚህ ሰበብ እኔ ትግሬው፣ እኔ አማራው ፣ እኔ ኦሮሞው እኔ …እያለ ባላዋቂነት ውስጥ እየዳከረ ፣ቅልጥ ባለ ግብዝነት ተወጥሮ ፣ ተራ ሟችነቱን ረስቶ ሲያቅራራ እዛም እዚህም ይስተዋላል ።
አውሮፖና አሜሪካ ብቻ ሳይሆኑ ሩቅ ምሥራቅ እና የአረብ አገራት በሙሉ የሰው ማንነቱ ሰው መሆን ብቻ መሆኑንን ጠንቅቀው ያውቃሉ ። የሰውን ክቡርነትም በየህገመንግስታቸው አውጀዋል ።
ሰው የተለያየ የመግባብያ ቆንቋ ቢናገርም በተፈጥሮው አንድ ነው ። በቋንቋው ንግግርም ነባራዊ ተግባባቶች አይቀየሩም ። በፈለከው ቋንቋ ተናገረው ፤ሙገሳ ሙገሣ ስድብ ስድብ ነው ። የተለያየ ቋንቋ መናገር ተፈጥሯዊ እንጂ እርግማን አይደለም ። እርግማን የሚሆነው አንድ ሉአላዊ አገር አንድ ብሔራዊ ቋንቋ ከሌለው ብቻ ነው ።
የአንድ አገር ዜጋ እርስ በእርሱ እንዲግባባ አንድ መግባቢያ ቆንቋ መማር ያስፈልገዋል ። እንዳይግባባ ቋንቋውን ከፋፍሎ አንድ ብሔራዊ ቋንቋ በህግ ወስኖ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንዳይማር ማድረግ እርግማን ነው ። ( በበኩሌ የባቢሎን ግንበኞች ፈጣሪን እናገኛለን ብለው ወደሰማይ ግንብ መገንባታቸው ታላቅ ጅልነት እና ፍጹም ቂልነት መሆኑንን ፈጣሪ ያውቃልና እነዚህ ሰዎች በለመግባባት የተነሳ ተበታትነው በየግላቸዎ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ በመሻት ቋንቋቸውን እንደከፋፈል አምናለሁ ። )
እርግማንነቱም ዛሬ ላይ እየታየ ነው ። ኢትዮጵያ ዛሬ በማያባራ የእርስ በእርስ ጦርነት የተዘፈቀችው አንድ ብሔራዊ ቋንቋ ስለሌላት ነው ። የዛሬ ሥመ ጥር ፖለቲከኞች እኮ በአማርኛ በጣፈጠ አንደበት የሚናገሩት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የአማረኛ ቋንቋ ትምህርት ሥለተማሩ ነው ። ይህ እውነት መሆኑ ቢታወቅም ይህንን ሃቅ ማንም ትንፍሽ አይልም ።
ኃያል አገራትም ይህንኑ የትምህርት ሥርዓት ይከተላሉ ። እናም ዜጎቻቸው ሁሉ በዚህ ብሔራዊ ቋንቋቸው መግባባት ይችላሉ ። እኛም ይኽንን እውነት በጥሞና እንድገነዘብ ጥረት ሲያደርጉ ግን አይስተዋሉም ። ከራሳቸው ህገመንግስት ተመክሮ በመነሳት ሩሲያም ሆነች አሜሪካ ስለ ብሔራዊ ቋንቋ አስፈላጊነት አበክረው ሊመክሩን ይገባ ነበር ።
የእነሱ አገር ዜጎች አንድ መግባቢያ ቋንቋ ያላቸው ና ሰው መሆናቸውን የተገነዘቡ ከመሆናቸውም በላይ ፣ ነገ ተራ ሟችነታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ እንዲሆኑ በብሔራዊ ቋንቋቸው አስተምረዋል ።( ጥቂቶች ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ እና አውሮፖ የፈለሱ እና ዜግነት ያገኙ ኢትዮጵያዊያን ግን ከነድንቁርናቸው የተቀመጡ ፣ የሰውን ሰውነት የካዱ እና በሰው ደም የማቆምሩ ሆነው እናገኛቸዋለን ። )
የኢትዮጵያ ዜጎች ግን ዛሬም በቋንቋ ልዩነት ብቻ ሰው መሆናቸውን ረስተው እርስ በእርስ ሲሰዳደቡ ፣ ሲታኮሱ እና ሲገዳደሉ ይስተዋላል ። ሰው ሰውነቱን በመዘንጋት ብቻ ሳይሆን በቋንቋ ተቧድኖ አንዱ ቋንቋ ሌላውን ቋንቋ ካልገዛ የሚል አስተሳሰብ የነገሰባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ መሆኖ በእጅጉ ያስገርማል ። “ አይ ወያኔ ! “ ማሰኘቱም አይቀርም ።
ለምን ? ወያኔ ይኽንን አደረገች ? ይኽ እኮ በፈለከው ጋዜ በጊዜ መቆጣጠሪያ ተጠቅመው የምታፈነዳው ቦንቡ ነው ። ” ለምን ? ለምን ?… “ለምን የተሰኘ ጥያቄ በበስንቱ ድራማ ላይ ተደጋግሞ ቢሰማም ፤ ለምን ? የሚባል ጥያቄ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የማወቅ ጥማትን ለማርካት የሚጠየቅ ጥያቄ ቢሆን ደስ ይለኛል ።
ወያኔ ይኽንን ታይም ቦንብ ያስቀመጠችው እንደአቀደችው ቢያንስ 40 ዓመት በኢትዮጵያ የመሪነት ወንበር ለመሰኖበት አቅዳ ነውን ? ይህስ እቅዷ በአልነቃ ማህበረሰብ ውስጥ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ። ብላ መገመት ሞኝነት አልነበረም ወይ ? ዜጎች ከድህነት አንፃር ያለ ስጋት በአገራቸው ሰርተው ዳቦ ማግኘት እንጂ ከዳቦ የዘለለ ወቅታዊ ጥያቄ እንደሌላቸው እንዴት ዘነጋች ? ወይስ በሶና ስኳር እየበጠበጠች በመጠጣት ምኒልክ ቤተመንግስት እንደገባች ዘነጋችው ?
የአውሮፓ ፣ የአሜሪካ ፣ የቻይና እና የሩሲያ መንግስታት የሥጋ ጥቅምን ወይም መሠረታዊ ፍላጎታቸውን አሸነፈው በአመዛኙ ከቁሥ ሰቀቀን ወጥተው በእምሮአዊ እርካታ ላይ የደረሱት እኮ ዜጋቸውን በትምህርት አንድ በማድረግ ነው ። የተለየ የየራሱ ቋንቋ ይኑረው በአገራቸው የሚማር ዜጋ ሁሉ ብሔራዊ ቋንቋቸውን የማወቅ ግዴታ አለበት ።
ባለፀጎቹ ይህንን ያህል ለብሔራዊ ቋንቋቸው ዘብ ሲቆሙ እኛ ግን በሃሳብ የሚያግባባንን ብሔራዊ ቋንቋ ለምን ናቅን ? ለምን ? ለምን ? ለምን ?
የለምን ጥያቄ መልስን የሚሰጡን የዓለምን መንግሥታት ፖለታካ የተቆጣጠሩት ከላይ የጠቀስኳቸው መንግስታት ናቸው ። አፍሪካን ለመለወጥ ቢችሉም በእያንዳንዱ አገር ያለው የመሬት ውስጥ ሀብት ለተራ ሟቹ ግድ እንዳይኖራቸው አደርጓቸዋል ። ተራ ሟቹ አፍሪካዊ ህዝብ በቋንቋ አለመግባባት ፣ በአላዋቂነት እና አምሳያውን የነቃ ፖለቲከኛ በማመን ሰበብ ለምን ሲገዳደል ውሎ አያድርም ?
ተራ ሟቹ አፍሪካዊ እኮ ከእውቀት የራቀ ነው ። ” ለምን ” ብሎ አይጠይቅም ። ከ ለምን በፊት ዳቦ ነው ጥያቄው ። የሚያበለው ፣ የሚያለብሰው ፣ መጠለያ የሚሰጠው ካገኘ ዘንዳ የታዘዘውን ይፈጽማል ። በኃይማኖት ፣ በጎሣ እና በወንዝ ልጅነት ተቧድኖ እርስ በእርሱ ይታኮሳል ። ይገዳደላል ።
የዓለምን ፖለቲካ የሚዘውሩትም በሳተላይታቸው እንደ ድራማ ያዩታል ። ምናልባትም ከ50 ዓመት በኋላ በፊልም መልክ አቀነባብረው ቢዚነስ ይሰሩበት ይሆናሉ ። ከ50 ዓመት በኋላ የዛሬዎቹ የአፍሪካ መሪዎች አይኖሩምና ።
ከ0001 ዓ/ም እሰከ 2025 ዓ/ም በቢሊዮን የሚቆጠሩ የዓለም ህዝቦች በተፈጥሮ ፣ በጦርነት ፣ በበሽታ ፣ በአደጋ ፣ወዘተ ። መሞታቸው እርግጥ ነው ። በምትካቸው በቢሊዮኖች ተወልደው ይኸው ለዛሬው አዲስ ዘመን ትውልዳቸው በቅቷል ። ምንም በጊዜ ብዛት በ0001 ዓ/ም በየአህጉሩ የነበረውን ዝርያቸውን ቢረሱትም ፣ እጅግ ከሚያውቁት በላይ ወድማማችና እህትማማች ሆነው ለዛሬ በቅተዋል ። ይሁን እንጂ አንዱ አውሮፓ ና አሜሪካ እንዲሁም እሩቅ ምሥራቅ እና መካከለኛው ምሥራቅ በመኖሩ ብቻ ሥጋነቱን በዘመን ብዛት ረስቷል ። ወይም አላወቀም
ይኽ ብቻ አይደለም የሰው የክፋት ምንጭ አለማወቅ ነው ። የዓለም ሰው በሙሉ ከክርስቶስ ልደት በፊት 3000 ዓመት ተጉዞ በምድር ላይ ሥንት ሰው ነበር ብሎ ያለመ ጠየቀ ነው ።
የዛሬ 5025 ዓመት አፍሪካ ውስጥ 1000 እሰከ 30,000 እንደሚኖር ይገመታል ። ምክንያቱም ጎግልን ብጠይቁት በዛን ዘመን በዓለም የሚኖረው ህዝብ ከ1 ሚሊዮን እስከ 10 ሚሊዮን ነበርና የአፍሪካ ኮታ ከዚህ ቁጥር አያልፍም ። እናም ወገን ከፖለቲካው ባሻገር እውቀትን ገንዘባችን ካላደረግናት እና ከጥበብ ከራቅን አፍሪካዊያን ለዘላለም እርስ በእርሳችን መጋደላችን አያባራም ።
አውሮፓና አሜሪካም የምንተላለቅበትን ዘመናዊ መሳሪያ በገፍ እያመረቱ መሸጣቸውን ይቀጥላሉ ። በዙረቱ ሳይመጣ የማይቀረውን አዲስ ዓመታቸውን እስከ ዓለም ፍፃሜ በታላቅ ፌሽታ ይቀጥላሉ ። እኛም መልካም አዲስ ዓመት እንላቸዋለን ። ዓለም በዝንጋታ ገመድ እየጎተተች ወደ ሞት እንደምታደርስ ግን ልናስታውሳቸው እንወዳለን ።