መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም. /March 25, 2025
ከዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
ከአምስት ዓመት በፊት በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ 17 የአማራ ሴት ተማሪዎች በታጣቂ ኃይሎች ታግተው ተወስደው ደብዛቸው ጠፍቶ እንደቀረ ይታወቃል። በተመሳሳይ ሁኔታ ከዩኒቨርስቲ ተወስደው በጫካ ታግተው ሲሰቃዩ ከነበሩ እና ጥቃት ከተፈጸመባቸው የአማራ ሴት ተማሪዎች መካከል ብርቱካን ተመስገን ከዘግናኝና አረመኔያዊ ጭካኔ ከተመላበት ሰቆቃ በአምላክ ቸርነት ተርፋ በኢቤስ ሚዲያ በማያቋርጥ እንባ እና ውስጥን በሚያደብን ለቅሶ ታጅባ የደረሰባትን ግፍ ለህዝብ አሳውቃለች።
መቼም ይህንን ቪዲዮ አይቶ አማራን ለማጥፋት ቆርጠው ከተነሱት ኃይሎች በስተቀር ከብርቱካን ጋር አብሮ የማያነባና እና የማያዝን ሰው ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ይህንን ፕሮግራም ላዘጋጁት ጋዜጠኞችና የኤቢሲ ሚዲያ ባልደረቦች ምስጋና ይገባቸዋል። የህዝብን ደህንነት ይጠብቃል፣ ያስጠብቃል፣ ግፍ ፈጻሚዎችን ለፍትህ ያቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው አገዛዝ ግን ከህመሟ እንድታገግም እንደመርዳት ብርቱካንን በጸጥታ መዋቅሩ እያዋከባት ይገኛል። እንዲሁም ለሚፈጽመው ግፍ ተባባሪ የሆኑትን ሆድ አደር ዲጂታል ሰራዊቱን በማሰማራት ሴት እህቶቻችን ላይ ሌላ እንግልት እና የስነ ልቡና ጉዳት እየፈጠረ ይገኛል። የዚህ አረመኔ አገዛዝ ዋነኛ መሪዎች ዐብይ አህመድ ፣ ተመስገን ጥሩነህ፣ ብርሃኑ ጁላ፣ ሽመልስ አብዲሳ እንዲሁም ንጉሡ ጥላሁን ከደምቢደሎ ዩኒቨርሲቲ በታገቱት ሴት ተማሪዎች፣ ቤተሰቦች፣ በአማራው ህዝብ ብሎም በፍትህ ፈላጊው ኢትዮጵያውያን ላይ እንዴት ይሳለቁ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።
ዛሬ ደግሞ የደበቁትን እጅግ አስነዋሪና ዘግናኝ ዓለም አቀፍ ወንጀል ለምን ህዝብ አወቀው በሚል ኤቢሲ ሚዲያን በማዋከብ እና በማስፈራራት ቪዲዮውን ከዩቱብ ገፁ እንዲያነሳ ከማድረግም በላይ የተቀረፀበትን ካሜራ ሳይቀር በፀጥታ ኃይሎች እንዲወሰድ በማድረግ እንዲሁም ዝግጅቱን የመራችውን ጋዜጠኛ ለጥያቄ ወደ ፓሊስ ጣቢያ መጥራታቸው ተሰምቷል። ይባስ ብሎም የግፍ ግፍ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በኢቢሲ የቀረበውን እና በእህታችን ላይ የደረሰትንን ግፍ ያጋለጠውን ቪዲዮ ለማስተባበል ሐሰተኛ ዘጋቢ ፊልም እንዲዘጋጅ ግፍ የተፈጸመባት ብርቱካን ተመስገን በግዴታ ተይዛ ወንጀሉን የፈፀሙባት የአማራ ፅንፈኛ ኃይሎች ናቸው እንድትል እየተሰራ መሆኑ በሚዲያ ተዘግቧል።
ይህ የሐሰት ዘጋቢ ፊልም ዝግጅት የአማራ ሴት ተማሪዎች እገታና የደረሰባቸው ዘግናኝ ሰቆቃ በዐብይ አህመድ በቀጥታ ትዕዛዝ የተፈፀመ ወንጀል ለመሆኑ ደምበኛ ማረጋገጫ ይሆናል። መቼም ዐብይ አህመድና አረመኔያዊ አገዛዙ ስልጣን ከተቆናጠጡ አንስቶ በአማራው ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ ተዘርዝሮ አያልቅም። አገዛዙ ኢንጅነር ስመኘው በቀለን፣ ዶር አምባቸው መኮንንን፣ ምግባሩ ከበደን፣ እዘዝ ዋሴን፣ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌን በማስገደል አማራውን የማጥፋት ሴራ አጠናክሮ በመቀጠል በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ፣ በቤኔሻንጉል፣ አሩሲ፣ ሀረርጌ፣ በሻሸመኔ በሺዎች የሚቆጠሩ አማሮች እንዲጨፈጨፉ አድርጓል። ከአዲስ አበባ እና በቅሚያ ሸገር ተብሎ ከተሰየመው ከተማ ቤቱ እያፈረሰ የተፈናቀለው አማራ በሚሊዮን የሚቆጠር ነው። ይህ ሁሉ አልበቃ ያለው ግፈኛ አገዛዝ ከሁለት አመት በላይ አማራውን በመውረር በድሮን ንፁሀንን እየጨፈጨፈ ቤተክርስቲያንን፣ ሆስፒታሎችን፣ ትምህርት ቤቶችን እያፈረሰ ቅርስን እያወደመ የገበሬውን ሰብል እያቃጠለ ቀጥሏል። ከሰባት ሚሊዮን በላይ የአማራ ተማሪዎችንም ከትምህርት ገበታቸው እንዲለዩ አድርጓል። ወደ አዲስ አበባ መስመር የሚጓዘውን አማራ ከአውቶቡስ አስወርዶ በታጣቂ የታገተ በማስመሰል አገዛዙ በአንድ ታጋች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ካልከፈላችሁ እንገድላችኋለን በማለት ምስኪኑን አማራ እያንገላታ ይገኛል። በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የመንግሥት ሰራተኞች፣ ወጣቶች፣ ባለሃብቶች እና የፓርላማ አባላት በአማራነታቸው እና በአማራው ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ይቁም በማለታቸው ብቻ በእስር አየማቀቁ ይገኛሉ። ይህ በአገዛዙ እና ግብረአብሮቹ በአማራ ህዝብ ላይ የተፈጸመው እና እየተፈጸመ ያለው ግፍ በጥናት፣ በፖሊሲ፣ በመሳሪያ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በሴራ፣ በሐሰት ትርክት እና በጥላቻ ፕሮፖጋንዳ የተደገፈ ነው
ይህ ሁሉ መከራ በአማራው ላይ ሲደርስ ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ በአገዛዙ ላይ የሚጠበቀውን ያህል ውግዘት እያደረስ አይደለም። በዚህ አጋጣሚ ሰብዓዊነታችን፣ ኢትዮጵያዊነታችን፣ ህሊናችን አስገድዶን እንዲሁም ነግ በእኔ ነውና ይህንን በንጹሃን ላይ የሚደርሰውን ግፍ እና አረመኔያዊ ስርዓቱን በቃ እንድትሉ ለመላው ኢትዮጵያዉያን ጥሪያችንን እናቀርባልን። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም እዚህ ግባ የሚባል ተፅእኖ በአገዛዙ ላይ እያደረስ አለመሆኑ አሳዛኝ ነው። ነገር ግን ግፍ የወለደው የአማራ ፋኖ የእነ ብርቱካንን እና መሰሎቻቸውን የማያባራ እንባ ሊያብስ አማራውን ከዚህ ግፈኛ አገዛዝ በማላቀቅ ፍትህ እና ነፃነት ለአማራው ብቻ ሳይሆን ለድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያጎናፅፍ እየተዋደቀ ይገኛል።
ይህ ተስፋ ሰጪ የአማራ ፋኖ ተጋድሎ በአጭር ጊዜ ግቡን እንዲመታ የተጀመረውን የአንድነት ዘመቻ በፓለቲካው ዘርፍም በማጠናከር አንድ የአማራ ድርጅት በቅርቡ እንደሚያዋልዱ ተስፋ አለን። ይህ አረመኔያዊ አገዛዝ በድርድር ወይም ሀገራዊ ምክክር በሚል ማደናገሪያ ስልቶች ሊስተካከል ወይም የአማራ የህልውና እና ሌሎች መሰረታዊ ጥያቄዎች ሊመለሱ ስለማይችሉ መፍትሄው ስርዓቱን ማስወገድ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ የህልውና ትግሎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም መረባረብ ይኖርበታል።
በውጭ የሚኖረው አማራም በተናጠል ብዙ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። ነገር ግን አንድነት ኃይል ስለሆነ በውጭ የሚኖረው አማራ ዛሬ ነገ ሳይል ወደ አንድነት ወይም ትርጉም ያለው ትብብር በመምጣት የተጠናከረ የዲፕሎማሲ፣ የሚዲያ ብሎም የድጋፍ ማሰባስብ ዘመቻ መሬት ላይ እየተዋደቀ ላለው ፋኖ ማድረግ ይጠበቅበታል። የብርቱካን እና መሰል እህቶቻችን እንባ የሚታበሰው አማራውም ከዐብይ አህመድ እና አገዛዙ ሰቆቃ በአስቸኳይ ነፃ ሊሆን የሚችለው በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ያለው አማራ በአንድነት ወይም በትብብር ተቀናጅቶ መስራት ሲችል ብቻ ነው። ዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት ይህ የአማራው የተቀናጀ ትግል እውን እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ ቃል ይገባል። ሌሎች የአማራ አደረጃጀቶችም ለትብብሩ መሳካት የበኩላቸውን እንዲያደርጉ አስቸኳይ ጥሪ ያቀርባል።
ፍትህ ለብርቱካን እንዲሁም ፍትህ ለተነፈጋቸው ግፉዓን አማራዎች በሙሉ!
