የብርቱካን ተመስገን የግፍ በደል ታሪክ ፤ በኢቢኤስ ቲቪ ለሕዝብ ይፋ መሆኑ ተከትሎ በሥልጣን ላይ የሚገኘው። የአገዛዝ ሥርዓት ከፍተኛ ውጥረት ላይ ይገኛል ። ብርቱካን ተመስገንን በአዲስ አበባ ፌድራል ፖሊስ ቢሮ በእስር ላይ ትገኛለች ።የኢቢኤስ ቴሌቭዥን የፕሮግራሙ ዳይሬክተር ታሪኩ ሃይሌ ፣ ረዳት አዘጋጅ ህሊና እንዲሁም ቪዲዮ ኤዲተሩ ሃብታሙ በፌድራል ፖሊስ በቅድሚያ ታፈነው ተወስደው ከታሰሩ በኋላ ፤ ሌሎች ባለሙያዎች ከፕሮግራሙ ቀረጻ ጋር በተገናኘ ሙያዊ ስራቸው ያከናወኑ የቢሮ ሠራተኞች ተለይተው በፖሊስ መኪና ውስጥ እንዲገቡ ተደርጎ በጊቢው ውስጥ ታግተው ይገኛሉ።
ይህ መረጃ ይፋ እስከ ሆነበት ሰዓት ድረስ ከጠዋቱ ጀምሮ ወደ ኢቢኤስ ቢሮ እና ቅጥር ግቢ ወደ ውስጥ መገባት የሚቻል ሲሆን መውጣት ግን ክልከላ ተደርጎ የነበር ሲሆን ፤ ከምሳ ሰዓት በኋላ በጊቢው ውስጥ የነበሩ ሠራተኞች በሙሉ እንዲወጡ ተደርጎ በፌዴራል ፖሊስ እና ደህንነት የኢቢኤስ ቅጥር ጊቢ በከፍተኛ ሁኔታ ከበባ እና ጥበቃ ውስጥ ነው ያለው ። የኢቢኤስ አዘጋጅ ሉላ ገዙ ታስራለች ተብሎ የተሰራጨው መረጃ እስካሁን ሰዓት ድረስ ሐሰት ነው ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢቢኤስ የብርቱካን ተመስገንን ጉዳይ አስመልክቶ ሰጠ የተባለው መግለጫ ፤ በተቋሙ በተረጋገጠ የማኀበራዊ ትስስር ገጽ እንዲሁም በሚዲያው በግል የሰጠው አንዳችም መግለጫ እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል ። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢቢኤስ ቴሌቪዥን በዛሬው ዕለት ሶስቱም ቻናሎቹ በኢትዮ ሳት ላይ ስርጭት አቁሟል። የስርጭቱ መቋረጥ ከላይ በተገለጸው ጉዳይ ይሆን ወይም በሌላ በግልጽ እስካሁን የታወቀ የለም ።