በቅድሚያ እንኳን ለፊቼ ጨምበላላ በዓል አደረሰን! ሲቀጥል ፋና ብሮድካስቲንግ በብርቱካንና በኢ.ቢ.ኤስ ጉዳይ ላይ የሠራውን ዶክመንተሪ አይቻለሁ። በሌሎች ቻናሎችም ተላልፎ ሊሆን ይችላል። ዓላማው ህዝብ በሀሰተኛ መረጃ እንዳይደናገር እዉነትን የማውጣት ጥረት እንደሆነ ተገልጿል።
የተባለዉ ከልብ ከሆነ ለህዝብና ለእውነት በዚህ ፍጥነትና ጥልቀት መቆርቆር የጀግንነት ኒሻን ይገባው ይሆናል። ችግሩ የማጣሪያ ጥያቄዎች መኖራቸዉ ነው። በዚህ ጉዳይ እንደግልም እንደህዝብም ብዙ ማለት ይቻላል። ለአሁኑ አምስት ነጥቦችን ብቻ እንመልከት።
መጀመሪያ የጎደሉ የዶክመንተሪው ክፍሎችን መፈተሽ ነው። ብርቱካን ተመስገን ህዝብን ለማሳሳት በሴረኞች ተመልምላ የሀሰት ድራማ መተወኗን ከዶክመንተሪው ሰምተናል።
ፖለቲካ ቁማር መሆኑ በግልፅ የተነገረዉ ህዝብ ነገሩን በቀጥታ ለማመን የሚቸገር ቢሆንም ሴራዉን ሸርቧል የተባሉ ሰዎችም ተጠቀሷል። ሊመለሱ የሚገባቸዉ ጥያቄዎች ግን አሉን።
በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ በተጨባጭ ተደፍረዉ ከህይወት ጎዳና የወጡ በርካታ ሴቶች እያሉ “ሴረኞቹ” ድራማ መስራት ለምን አስፈለጋቸዉ? ድራማ ቢያስፈልግስ በተለያየ ምክንያት ህይወት ተበላሽቶባቸዉ በጎዳና የሚኖሩ ብዙ የመከራ ሰላባ ሴቶች እያሉ ባለትዳር፣ የልጅ እናትና የተመቸ ኑሮ የነበራት ብርቱካን ለትወናዉ በምን መስፈርት ተመረጠች? የኢ.ቢ.ኤስ ጋዜጠኞች የድራማዉ አካል ከሆኑ ቢያንስ ብርቱካን ከአዲስ አበባ ሳትወጣ ድራማውን ለምን በአየር ላይ አዋሉ? ከትወናው በፊት የብርቱካን ስልክ ተጠልፎ ከሆነ ለምን? ድራማው ከተጋለጠ በኋላስ የብርቱካን ስልክ እንደሚጠለፍ እየታወቀ “ሴረኞቹ” እንዴት በቀጥታ ደወለው ድምፃቸዉን አስቀዱ?
ለዶክመንተሪው ግበዓት ለመጨመር ይሆን? ብርቱካን ህይወቷ አደጋ ላይ መሆኑ ተነግሯት ስልኳን ጥላ ፋኖዎች ወዳሉበት እንድትሸሽ ሲነገራት ምንን ተማምና ሳትሸሽ ቀረች? የአካውንቲንግና የፋይናስ ድግሪ ያላት ብልህ ሴት ማምለጥ አቅቷት ይሆን? የተከበረ ትዳርና የተመቻቸ ኑሮ የነበራት ብልጧ ብርቱካን ለትራንስፖርት የሚሆን አምስት ሺህ ብር እንኳን ሳትቀበል ህይወቷን ለምን ለአደጋና ለውርደት አጋለጠች?
እነመዓዛ መሀመድ ሲደውሉላት ድምጿ እጅግ መደንገጧን የሚያሳብቅባት ብርቱካን ዶክመንተሪው ላይ እንዴት ተረጋጋች? በፊቷ ላይ ሀፍረትና ፀፀት የማይታይባት ለምን ይሆን? የነብርቱካን ቤት ውስጡ በዶክመንተሪው ታይቷል? ትወናውንና ዶክመንተሪውን በአግባቡ ለመረዳት እነዚህ ቁልፍ ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው ይመስለኛል።
ጥያቄዎቹን በትክክል መመለስ ማን ለምን ትወናውን እንደሰራ ጥቆማ ይሰጣል። ጥያቄዎቹ ካልተመለሱ ግን ዶክመንተሪው ከትወናዉ በላይ ህዝብን ያደናግራል። በተለይም በሀገራችን የተንሰራፋውን አሰቃቂ የሴቶች ጥቃትን ለመሸፈን የታሰበ ድብቅ ነገር ሊኖርም ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ በትወናው ሂደት ላይ የሚና መለዋወጥ ይኖር ይሆናል።
ሁለተኛዉ ወንጀልን መርምሮ ተጠያቂነት ለማስፈን የተደረገው ጥረትን ይመለከታል። በማንም ላይ የትኛዉም ዓይነት ወንጀል ቢፈፀም በፍጥነት መርምሮ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ውጤቱን ለህዝብ ይፋ ማድረግ ይገባል።
ከዚህ አንፃር ፖሊስና ፋና የሠሩት ይበረታታል። ውስጡን ለቄስ ብለን ብርቱካና ኢ.ቢ.ኤስ ሀሰተኛ መረጃን አሠራጭተዉ ከሆነ በልኩ ሊጠየቁ ግድ ይላል።
ዋናው ጥያቄ ግን ህዝብ እንዳይደናገር አስቦ የብርቱካንንና የኢ.ቢ.ኤስን ጉዳይ መርምሮ እዉነቱን ለማዉጣት ከብርሃን በላይ የፈጠነዉ ፖሊስና ሚዲያ በከረዩ አባገዳዎች ላይ በመንግስት የተፈፀመውን የጦር ወንጀል መርምረዉ እዉነቱን ለህዝብ ማሳወቅ ለምን አቃታቸዉ? በነገራችን ላይ ፋና በከፍተኛ ግፍ ሰለተረሸኑት የከረዩ አባገዳዎች ዜና ሰርቶ ያውቃል? በሜታ ወልቂጤ ተደፍራና ተገድላ የተሰቀለችው ህፃን ስምቦ ብርሃኑ ጉዳይ ተመርምሮ ጉዳዩ ለህዝብ ተገልጿል?
ወይዘሪት አያንቱ ተስፋሁን በቅርቡ በነቀምት ከተማ ተገድላ መገኘቷ የምርመራና የሚዲያ አጀንዳ ሆኗል? ፖለስና ፋና በሰምቦ ብርሃኑና በአያንቱ ተስፋሁን ጉዳይ ያልፈጠኑት ለምን ይሆን? ሀሰተኛ መረጃን ከማሰራጨት በላይ እጅግ የከፉ ወንጀሎች ተድበስብሰዉ አልቀሩም? የብርቱካንና የኢ.ቢ.ኤስ ጉዳይ በዚህ ልክ ፍጥነትና ግልፅነት ያገኘዉ ለምን ይሆን? ለኛ ያልተገለፀ ሌላ እዉነት ሊኖር እንደሚችል መገመት አይከፋም ለማለት ነው።
ሶስተኛዉ መታገትና መደፈር ለኢትዮጵያውያን ሴቶች አሁን ላይ እንግዳ አለመሆኑ ነው። በቅርቡ እንኳን በሰሜን ሸዋ አሊዶሮ አካባቢ ሴቶች የሚገኙበት አንድ አዉቶቢስ ሙሉ ዜጎች መታገታቸዉ በBBC ሳይቀር ተዘግቧል። እነዚህ ዜጎች ያሉበት አይታወቅም። እየተደፈሩም ሊሆን ይችላል።
ለፋናና ለፖሊስ ግን የምርመራ አጀንዳ አልሆነም። ከዚህ ቀደምም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በደቡብና በሌሎች ቦታዎችም በእህቶቻችን ላይ ዘግናኝ የመድፈር ወንጀሎች ሲፈፀሙ ነበር።
በኢ.ቢ.ኤስ የቀረበው የብርቱካን ታሪክ እንደተባለው ትወና እንኳን ቢሆን እንደሀገር አሁን ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ከእውነት የራቀ አይደለም። ከዚያ የባሱ ከባባድ ወንጀሎች በፀጥታ አካላት ሳይቀር ሲፈፀሙ አይተናል።
እንዲህ ዓይነት ኢ-ሰበዓዊና አስነዋሪ ወንጀሎችን ስንመለከት እንደህዝብ መተባበር ሲገባን በብሔር ወይም በሌላ ምክንያት ከፋፍሎ ምን ያነታርከናል? የአንዳችን ቁስል እንዴት ለሌላችን መዝናኛ ይሆናል? ደግሞ ግለሰብ ወይም ወንጀለኛ ቡድን በጭካኔ ለሚፈፅመዉ ጥፋት ብሔር በምን ሂሳብ ይጠየቃል? ከህግ አኳያ አንድ ሰዉ የሚፈፀመዉ ወንጀል ወንድሙን እንኳን እንደማይመለከት ይታወቃል።
እንደህዝብ የጅምላ ፍረጃ ላይ ራሳችንን መፈተሽ ያለብን ይመስለኛል። ባልተገባ ጉዳይ መፈራረጃችንና መነታረካችን በኪሳራችን ለሚያተርፉ ቁማርተኞች ብቻ ይጠቅማል።
አራተኛዉ ፋና ብሮድካስቲንግ በሀሰተኛ መረጃ ላይ የያዘውን አቋም ይመለከታል። በብርቱካን ጉዳይ ዶክመንተሪ የተሰራው ህዝብ በሀሰተኛ መረጃ እንዳይደናገር መሆኑ ተነግሮናል። በእውነቱ ይህ ግልፅነት የመፍጠር ተግባር እንደፋና ካሉ ሚዲያዎች ይጠበቃል።
ይሁንና ታህሳስ 01/2016 ሌሊት ከታሰርኩ በኋላ ፋና “አቶ ታዬ ደንደአ ኦነግ ሸኔን በቤቱ በመሸሸግ ሰዎችን ሲያሳግት ነበር” የሚል ሀሰተኛ መረጃን ለህዝብ አስተላልፏል። ይህ ውሸት እንደህዝብ ተወካይነቴ ስሜን ከማጠልሸቱ ባሻገር ህዝቡን አደናግሯል።
ፋና በኋላ በሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሲጠየቅ “ከፀጥታ ግብረኃይል ተዘጋጅቶ የመጣዉን አነበብኩ እንጂ ሀሰተኛ መረጃዉን እኔ አላዘጋጀሁትም ” ብሏል።
እውነቱ ከታወቀ ወድህም ማስተባበል ቸግሮታል:: ያኔ ሆን ብሎ ህዝብን ለማደናገር ሀሰተኛ መረጃን ሳያጣራ ተቀብሎ ያሰራጨውና በኋላ እንኳን ስህተቱን ለማስተባበል የተቸገረው ፋና ዛሬ ህዝቡ እንዳይደናገር ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከልና ኢ.ቢ.ኤስን ለማጋለጥ በብርሃን ፍጥነት ረጅምና ረቂቅ ዶክመንተሪ የሰራው በምን ፎርሙላ ነዉ? የራሷ አሮባት ያስብላል!
አምስተኛዉ እጅግ መሠረታዊ የጋራ ችግሮች እያሉብን መከፋፈላችንን ይመለከታል። ከብልፅግና አውሮፕላን ውጭ ያለን ሰዎች በዋጋ ግሽበቱ ምክንያት መኖር ቸግሮናል። ባለፈዉ ሳምንት ብቻ ነዳጅ በሊትር 11 ብር ገደማ ጨምሯል።
ይህ ችግር አማራ-ኦሮሞ፣ ትግራዋይ-ሲዳማ፣ ሶማሌ-አፋር፣ ወላይታ-ጋሞ ወይም ሙስሊም-ክርስቲያን ብሎ ሳይለይ ሁላችንንም ይጎዳል።
የሰላም መደፍረሱም በተመሳሳይ የሁላችንን ህይወት ይነካል። ለስድስት ዓመታት የቀጠለዉ የወንድማማች ጦርነት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቻችንን፣ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በልቷል።
ሀብታችንም በትሪሊዬኖች ባልተገባ ጦርነት ወድሟል። በተለያዩ ቦታዎች በኮሪደር ስም አያሌ ዜጎች ያለምንም ካሳ ከይዞታቸዉ ተፈናቅለዋል። የቀይ ባህር ዓሳ በየግዜዉ ችጋርን ለመሸሽ የሚሰደዱ ልጆቻችንን ይመገባል።
በእውነቱ ከሆነ እነዚህ ጉዳዮች -እነፋናን ባያሳስቡም- ሁላችንንም ያለልዩነት ሊያንገበግቡን ይገባል። ይሁንና በትናንሽ አጀንዳዎች ስንጨቃጨቅ ይታያል። ለምን እንደዚህ ይሆናል? ሊያስተባብሩን የሚገቡ ትላልቅ የጋራ አጀንዳዎችና ችግሮች እያሉን ምን ይከፋፍለናል? አሰቀድመዉ አንደነገሩን ፖለቲካ ቁማር ከሆነ እንደህዝብና እንደሀገር እንዳንበላ ራሳችንን ፈትሸን ማረም ይኖርብናል!
በድጋሚ እንኳን ለፊቼ ጨምበላላ በዓል አደረሰን!
ታዬ ደንደአ
——————————
ይቺ ሴትዬ ብርቱካን ነች እንዴ??????
ይቺ ሴትዬ ብርቱካን ነች እንዴ