
ውድ ወንድሜ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሣ ለጤናህ እንደምን አለህልኝ፡፡ ካልዘነጋኸኝ በሶሻል ሚዲያዎች እንተዋወቃለን፡፡ ዘንድሮ አዚሙ በርትቶብን በየበኣታችን ተከተትን እንጂ በፊት በፌስቡክም በኢሜልም አልፎ አልፎ እንገናኝ ነበር፡፡
ትናንት በአንድ ዩቲዩብ ያስተላለፍከውን መልእክት በቲክቶክ ቅንጫቢውን አየሁ፡፡ ስለመተታምነታችንና እያስከተለብን ስላለው መለኮታዊ ቅጣት ጥሩ ታዝበሃል፡፡ እኔም ሁሌም በተለያዩ አጋጣሚዎችና መጣጥፎቼ የምጮህበት ነው፡፡ ልጅ ባባቱ፣ እናት በልጇ፣ ወንድም በወንድሙ፣ እህት በወንድሟ፣ አክስት ባጎት… መተት የሚያሠራባት ብቸኛዋ ሀገር የኛዋ ስለመሆኗ ጥናትና ምርምር የማያሻው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ እንዳልከው የአምላክ ቸርነት ታክሎበት እንጂ እንደክፋትና ኃጢኣታችን ቢሆን ኖሮ ከዚህ መንግሥትም የከፋ ዐውሬ መንግሥት በተላከብን ነበር – ከዚህ የሚከፋ ካለ ማለቴ ነው – ይኖራል ብዬ አላምንም እንጂ፡፡ አንተ ያልከው እንዳለ ሆኖ ምናልባት አልሰማሁህ ከሆነ እንጂ በሌሎች ኃጢኣቶችና ክፋቶችም ሪከርድ ሳንሰብር አንቀርም፡፡
ከሃይማኖቶቻችን የላይኛው አመራር ጀምሮ እስከፖለቲካችን አመራር ድረስ የሚታየው የገንዘብ አምልኮ ላይ የተመሠረተ ኢሉሚናቲያዊ ሦዶማዊነት፣ ሙስና፣ የፕሮጀክት በጀትና የሀገር ሀብት ዝርፊያ፣ የሞራል ዝቅጠት፣ ዘረኝነት፣ ኢሰብአዊነት፣ ማስመሰል፣ ቅጥፈትና ውሸት፣ ብሔራዊ ስሜት ማጣት፣ በሰው ስቃይና መከራ መዝናናትና መደሰት ወዘተ. የሀገራችን መለያ ከሆኑ ጥቂት የማይባሉ አሠርት ዓመታትን አስቆጠርን፡፡
ፕሮ. የኛ ጉድ ተወርቶ አያልቅም፡፡ እናት ወንድ ልጇን ብቻ ሣይሆን ሴት ልጇን፣ አባት ሴት ልጁን ብቻ ሣይሆን ወንድ ልጁን የሚያገቡበት የመጨረሻው ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ለይቶላቸው ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር እንደተለያዩ የሚነገርላቸው አንዳንድ አደጉ የሚባሉ ሀገሮች ውስጥ ይደረጋሉ ሲባል እንሰማው የነበረው ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ሰይጣናዊ ተግባር አሁን በሀገራችን በግላጭ እየታዬ ነው – “ዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ” እንበለው፡፡ ምክንያቱም እነሱ ቢያንስ ፊደል ቆጥረዋል ፤ ሞሰባቸውም እንደኛው ባዶ ሣይሆን ሙሉ ነው፡፡ የመንግሥታችን አወቃቀርም ይህን ዕኩይ ተግባር እውን ለማድረግ ከጥልቁ የኔዘርወርልድ የተላከ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ እግዚአብሔር ፈጥኖ ካልደረሰልን – እንደሚደርስልንም ተስፋየ ትልቅ ነው – ጨርሰን መጥፋታችን ነው፡፡ ቤተ እምነቶች ከውስጣቸው በተጀመረ የመጥፋት ሂደት አሁን አሁን በተሟላ የክስረት መንገድ ላይ የሚገኙ ይመስላል፡፡ እዚያ አካባቢ እየሆነ ያለውን ብትሰማ ሃይማኖተኝነትን ብቻ አይደለም ሃይማኖትን ራሱን ትጠላለህ፡፡ ለዚህም ነው እረኞች ሲጠፉ በጎች በተኩላና በቀበሮ ፍዳቸውን እያዩ ያሉት፡፡ ሁለሉ ነገር ቢዝነስ(የንግድ ሸቀጥ) ሆነ፡፡ የነፍስ ሥራ በሥጋ ድሎት ተለወጠ፡፡ ፈጣሪ ተረሣና ፍቅረ ንዋይ ነገሠ፡፡ በዚህ መሃል እንግዲህ የእግዚአብሔር በዚህ የክፋትና የኃጢኣት ማዕበል ውስጥ መገኘት አይጠበቅም፤ ጸሎት ምህላውም እንኳንስ ጽርሃ አርያም ሊደርስ ችፍርግንና ቁጥቋጦን አልፎ ከቤታችን ጣሪያም አይጠጋም፡፡
ሰይጣን እንኳን ሰውን አምላክን በብርቱ የተፈታተነና የሚፈታተንም አደገኛ ፍጡር ነው፡፡ ጳጳስና መነኩሴን እስከማሦዶም የሚደርስ ሣጥናኤል ለተራው ጎጋ ዜጋማ እንዴት አይበረታ!
ለማንኛውም ባለህበት በርታልኝ፡፡ ከዕንቁ የኦሮሞ ትውልድ ያላቸው ዜጎች አንዱ በመሆንህ እኔን ጨምሮ ብዙዎች እንኮራብሃለን፡፡ ባለህበት ያጽናህ፡፡ ዘመኑ የፈተና ነው፡፡ የበረቱ ፈተናውንና ወጀቡን ያልፋሉ፡፡ የደከማቸው ልክ እንደአቤ ቶላ፣ እንደሲሳይ አጌና፣ እንደኤርምያስ ለገሠ … ዳገት ላይ ይቀራሉ፡፡ እኔ ነኝ ያልኩት ይሄን፡፡ በቅርብ ዐይን ለዐይን እንደምንተያይ ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡
“ንቁም በበኅላዌነ እስከንረክባ ነፃነታ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ!” (ከቅ. ገብርኤል ‘የጦርነት ወቅት’ ንግግር ለኔ መልእክት እንዲስማማ በመጠኑ ተሻሽሎ የተኮረጀ)
ግልባጭ – ለዘሃበሻ ድረገፅ