‹ዛሬ በናትሽ ዳጎስ ያለ ሰነድ ወይም መጽሐፍ ወይም ዶሴ መብላት አማረኝ›› አለች አንዲት ነጭ አይጥ ለጓደኛዋ፡፡
‹‹ለምን አንዱ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት አልወስድሽም›› አለቻት ጥቁሯ አይጥ፡፡
‹‹እኔን ለማስደብደብ ነው እንዴ ፍላጎትሽ›› አለቻት ነጯ
‹‹ማነው ደግሞ የሚደበድብሽ››
‹‹ሠራተኞቹ ናቸዋ››
‹‹ስለ ሕዝብ ቤተ መጻሕፍት አታውቂም ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥኮ አንድ ነገር የሕዝብ ነው ከተባለ ሁለት ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ወይ የማንም አይደለም፤ ወይም የጥቂቶች ብቻ ነው፡፡ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ማለት የማንም ያልሆነ ቤተ መጻሕፍት ማለት ነው፡፡ በጀት የለው፤ ተቆጣጣሪ የለው፤ ባለቤት የለው፡፡ ማዘጋጃ ቤት የባህል ቢሮ ነው ይለዋል፤ የባህል ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ነው ይለዋል፤ ኮሙኒኬሽን ጽ/ ቤት የወጣቶች ሊግ ነው ይለዋል፤ የወጣቶች ሊግ የሕዝብ ነው ይለዋል፡፡ ስንትና ስንት የጥንት መጽሐፍ ባለቤት ስላጣ ማንም ዘወር ብሎ አያየውም፡፡ ይልቅ ተነሽ እንሂድ››
ተያይዘው ሄዱ፡፡ ገቡ፡፡ አንድ አስነባቢ ገቢያቸውን ለብሰው ጠረጲዛ ላይ ክንዳቸውን ተንተርሰው ሸለብ አድርገዋል፡፡ አይጦቹ በበሩ ሲገቡ እንኳን አላዩዋቸውም፡፡
‹‹ያንን መጽሐፍ አውርጂው›› አለቻት ጥቁሯ፡፡ ነጯ አይጥ ሄደችና አወረደችው፡፡ ዳስ ካፒታል የሚለው የማርክስ መጽሐፍ ነው፡፡ ‹‹ለእኔ ደግሞ እዚያ ማዶ ያለውን አምጭልኝ›› አለቻት፡፡ ኦክስፎርድ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ነው፡፡ ሁለቱም ተቀምጠው መቆርጠም ጀመሩ፡፡
አስነባቢው የሆነ ድምጽ ስለሰሙ ቀና አሉና መልሰው ተኙ፡፡
‹‹እንዴ በሙሉ የድሮ መጽሐፍ ብቻ ነው እንዴ›› አለች ነጯ አይጥ፡፡
‹‹እዚህ ከተማ ለስብሰባ፣ ለድግስ፣ ለቲሸርት፣ ለኮፍያ፣ ለቢል ቦርድ፣ ለሲምፖዝየም፣ ለምናምን መታሰቢያ ቀን፣ ለምናም መመሥረቻ ቀን የሚሆን በጀት እንጂ ለዕውቀት የሚሆን በጀት የለም፡፡ አታይም ሠላሳ ሺ ሕዝብ የሚይዝ ኮንዶሚንየም ሲገነባ በግ ማረጃ እንጂ ቤተ መጻሕፍት ተገንብቷል? ለመጠጥ ቤት፣ ለጫት ቤት፣ የሚሆን ቦታ ግን ሕንጻዎቹ ሥር ተሠርቷል፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ በየቢሮው ያሉት ከዕውቀት የጸዱ፣ ከሆድ የተዛመዱ ናቸዋ፡፡ ያለ አእምሮ ልማት ቁሳዊ ልማት ከየት ይመጣል፡፡ መገንባት ብቻውን አያለማምኮ፡፡ የገነባሽውን በሚገባ የሚጠቀም፣ የሚከባከብ፣ እድሜውን የሚያረዝም፣ እሴት የሚጨምርም ዜጋ ያስፈልጋል፡፡ በጎጆ አስተሳሰብ ዘጠኝ ፎቅ ላይ መኖር ትርፉ በረንዳ ላይ በግ ማረድ ነው፡፡ ከወረቀት ግብር የቢራ ግብር በሚቀንስባት ሀገር፤ ኪነ ጥበብ ከማይበረታቱ ኢንዱስትሪዎች መደብ በተመደበባት ሀገር ምን ትጠብቂያለሽ›› አለች ጥቁሯ፡፡
‹‹ባለፈው አንዲት ጓደኛዬን ለአዲስ ዓመት ወጣ ብለን እንዝናና ስላት የት እንደወሰደችኝ ታውቂያለሽ››
‹‹ዱከም ወስዳ ሥጋ ጋበዘችሽ››
‹‹ኧረ አይደለም፤ አቃቂ››
‹‹አቃቂ ደግሞ ምን አለ?››
‹‹ድሮ በደርግ ጊዜ ኩራዝ አሳታሚ እያለ ሊታተሙ የተሰበሰቡ ረቂቆች አሉ ብላ ይዛኝ ሄደች፡፡ አንድ ትልቅ የቆርቆሮ መጋዘን ውስጥ ተከምረውልሻል፡፡ እዚያ ይዛኝ ገባች፡፡ እዚህ ሀገር የታወቁ ደራስያንን ሥራ ስንከሰክስ ስንከሰክስ ዋልንልሽ፡፡ አንዳንዱ ታርሟል፤ አንዳንዱ አልፏል የሚል ተጽፎበታል፡፡ አንዳንዱ ማኅተም አለው፡፡
‹‹ዝም አሏችሁ››
‹‹ማንም ዝር አይልም ከአይጥ በቀር አሉ የለመዱትማ ሲነግሩን››
‹‹ወይ ይህቺ ሀገር፣ ከገዛ ታሪኳና ቅርሷ፣ ከገዛ መዛግብቷና ሰነዶቿ ጋር የምትጣላ ሀገር፡፡ ባለፈው የባድሜ ጉዳይ በዓለም ፍርድ ቤት ሲዳኝ አንዱ የተጠየቅነው ሰነድ ነበር አሉ፡፡ የተቆረጠ ደረሰኝ፣ የተሰጠ ሹመት፣ ከዚያ አካባቢ የተጻፈ ነገር፣ የሐኪም ቤት ካርድ፣ ያ ቦታ የኢትዮጵያን እንደነበረ የሚያሳይ ዶሴ አምጡ ተብሎ ነበር አሉ፡፡ እዚህ ሀገርኮ ስንቱ ፋይል፣ ስንቱ ዶክመንት፣ ስንቱ ደብዳቤ፣ ስንቱ መረጃ አሮጌ ነው እየተባለ ተጥሎ በየቆርቆሮው ቤት ታሽጎበታል መሰለሽ፡፡ ለኛማ ሠርግና ምላሽ ነው፡፡ እርሱን እየበላን እንኖራለን፡፡ ሀገሪቱ ግን ታሳዝናለች፡፡››
‹‹ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት የሚባል ድርጅት አለ አይደል እንዴ››
‹‹አንድ ለእናቱ የሆነውን ነው የምትይኝ? ይኼው ሰማንያ ዓመት ሆኖታል አንድ ለእናቱ ነው፡፡ እስኪ ክልል ውረጅ አንድ የመዛግብት ማዕከል ታገኛለሽ? በተለይማ ባለፉት ሥርዓቶች የነበሩ መዛግብት የጠላት ገንዘብ ተደርገው የማንም መጫወቻ ሆነዋል፡፡ ወይ ቆርቆሮ ቤት ገብተዋል፤ ወይ ተቃጥለዋል፤ ያለበለዚያም በኪሎ ተሸጠዋል፡፡››
‹‹ይበላቸው እባክሽ፤ እነርሱ በዘመናቸው እኛ ድርሽ እንዳንል ድመት ለሚያረባ ሰው የድመት መሬት እየሰጡ አሳድደውናል፡፡ይኼው ዛሬ የሀብታም መሬት እንጂ የድመት መሬት የለ፡፡እንደልባችን ታሪክ ስንበላ እንውላለን፡፡››
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ በሽታ መቼ ተከሰተ፣ የት የት ቦታ ተከሰተ፣ ምን ያህል ሕዝብ ተያዘ፣ ምን ተደረገ፣ መቼ ጠፋ? ብለሽ ብትጠይቂ መልሱ ያለው የት እንደሆነ ታውቂያለሽ?››
‹‹ጤና ጥበቃ ነዋ››
‹‹ተሳስተሻል፡፡ እኛ ሆድ ውስጥ ነው፡፡ የሆስፒታል የድሮ ካርዶችኮ እንድንበላቸው ተፈቅደውልን የተከፋፈተ መጋዘን ውስጥ ተጥለዋል፡፡ እንደ ጓያ ነቃይ የዛሬን እንጂ የነገን የሚያስብ የለም፡፡ አሁንኮ ሀገሪቱ ስላደገች የወዳደቀ ትራፊ ሳይሆን አልፎልን ታሪክና መረጃ ነው የምንበላው፡፡ አንዳንድ መረጃዎችን ወደ እናንተ እናደርሳለን አሉ ጋዜጠኞች፡፡ የሚደርሰውኮ ወደኛ ነው፡፡››
‹‹አንድ ነገር አስታወስሽኝ፡፡ ከሆነ ዓመት በፊት አንድ ትልቅ ባለ ሥልጣን የተናገረው ነገር፡፡ ኢሕአዴግ ባሕርዳር ሲገባ እነርሱ የኢሠፓ ጽ/ቤት ነበር ያደሩት፡፡ ብርድ ስለነበር ሌሊቱን ፋይል እያነደዱ ሲሞቁ፡፡ በመካከል የአንድ ደራሲን ልቦለድ አግኝቶ እንዳነበበውና አዲስ አበባ ፈልጎ እንደሰጠው ሲናገር ነበር፡፡ አሁን ሰነድ ማቃጠል፣ ፋይል ማንደድ በቴሌቭዥን በኩራት የሚቀርብ ገድል ነው? ሰዎቹ ናቸው እንጂ ኢሠፓ ፋይሉኮ ኢሠፓ አይደለም፡፡ ፋይሉማ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡››
‹‹የኢትዮጵያን ዕቃ ገዥ ከሌላው ዓለም ገዥ የሚለየው አንዱ ነገር ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ?››
‹‹አላውቅም››
‹‹ሌላው በተራ ወረቀትና ፌስታል ዕቃውን ይጠቀልላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን በታሪካቸው ስለሚኮሩ በታሪካዊ መዛግብትና ሰነዶች፣ በታሪካዊ ደብዳቤዎችና ፋይሎች ዕቃቸውን ይጠቀልላሉ፡፡ በየሱቁ ከምትገዥው ስኳር በላይ ባለ ሱቁ የጠቀለለበት ፋይል ዋጋው ውድ ነው፡፡
‹‹ባክሽ አሁን ወሬውን ትተን እነርሱ ሙስናቸውን እኛ ታሪካችንን እንብላ፡፡››
ቆርጠም ቆርጠም ሲል አስነባቢው ቀና አሉ፡፡ እንዳጋጣሚ አንድ አንባቢ ገብቷል፡፡
‹‹አባት፣ አይጥ ሳይሆን አይቀርም›› አላቸው፡፡
‹‹ባክህ በጨረሱትና እኔም ወደሌላ ቦታ በተዛወርኩ ይሻለኝ ነበር›› አሉት፡፡
ቆርጠም፤ ቆርጠም፤ ቆርጠም
ታሪክ እንበላለን፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው
ጥሩ ታዝበሀል። የኢትዮጵያ ጅአኦሎጂካል ሰቬይን የጅኦሎጂ መጽሀፍትም መስሪያቤቱን ወደዳይሬክቶሬት አውርደው ቤተመጽሀፍቱን ዘግተው መጽ ሐፈቶቹን መጋዘን ጥለዋቸዋል።