ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
(የካቲት 10፣ 2017) February 17, 2025
የዶናልድ ትረምፕ እንደሽጉጥ ያነጣጠረ ፖለቲካ የሚለውን አባባል የወሰድኩት ደር ሽፒግል(Der Spiegel) ከሚባለው በጀርመን ሀገር ከታወቀው የሳምንታዊ መጽሄትና የኦንላይን ጋዜጣ ላይ ነው። ዶናልድ ትረምፕ በፈረንጆች አቆጣጠር በጥር ወር 20፣ 2025 ዓ.ም ስልጣናቸውን ከፕሬዚደንት ጆን ባይደን በይፋ ከተረከቡና መሃላም ከፈጸሙ በኋላ የውጭውንም ሆነ የአገር ውስጥን ፖለቲካ አስመልክቶ በጣም አስፈሪና፣ የህግን የበላይነት የሚጥስ ፖለቲካ በተግባርም ባይሆን በአፍ ብቻ በመናገር በአጠቃላይ ሲታይ የአሜሪካንንም ሆነ የዓለምን ህዝብ ግራ በማጋባት ላይ ይገኛሉ።
የአገር ውስጥ ፖለቲካቸውን በተመለከተ በተለይም በስደተኞች ላይ ያተኮረ አስፈሪ አካሄዳቸው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚኖሩትን አብዛኛዎችን ከተለያዩ አገሮች የመጡ ስደተኞችንና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ እየሰሩ የሚኖሩትን ከባድ ድንጋጤ ውስጥ ከቷቸዋል። በተለይም ከአንዳንድ አፍሪካ አገሮች መጥተው አሜሪካን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሚኖሩት ውስጥ ዝርዝር በማውጣት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ክትትል እየተደረገባቸው ለመሆኑ የሚወጡ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። ከእነዚህ ውስጥም ኢትዮጵያውያንም እንዳሉበት ይታወቃል። ሌሎችም የጥገኘነት ማመልከቻ አስገብተው ገና ያልታወቀላቸው እንደዚሁ በፍርሃት ውስጥ ይገኛሉ። ሌሎች ደግሞ በተለይም አንዳንድ ሴቶች ከአረገዙ በኋላ አሜሪካን በመምጣትና በመውለድ ልጆቻቸው እዚያ ስለተወለዱ ብቻ የአሜሪካንን ዜግነት ማግኘት እንደሚችሉ የሚያረጋግጠው ህግ በፕሬዚደንቱ ኤክስኪዩቲቨ ትዕዛዝ ተሽሯል። ሌሎችም አሜሪካን እየኖሩ በፕሮፈሽናቸው የሚሰሩና የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው፣ ይሁንና ግን የአሜሪካን ዜግነት የሌላቸው ልጅ ቢወልዱም ልጆቹ አውቶማቲካሊ የአሜሪካን ዜግነት ማግኘት ይችላሉ የሚለው በፕሬዚደንቱ ተዕዛዝ እንደሚሻር ተረጋግጧል። ይሁንና ይህንን ሁኔታ የሚከታተሉ የህግ አዋቂዎች ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ፕሬዚደንቱ በኤክስኪዩቲቭ ትዕዛዝ ማስፈፀም እንዳማይችል፣ ይህ እንዲሆን ከተፈለገ ደግሞ ከፓርሊያሜንትም ሆነ ከሴናት ተጠሪዎች ውስጥ 2/3 ኛው የሚሆኑት ህገ-መንግስቱን ማሻሻል እንዳለበቻውና፣ ከተሻሻለም በኋላ በ3/4ኛው በሚሆኑት የፌዴራል ስቴቶች መጽደቅ እንዳለበት አስምረውበታል። ይህም ማለት ዶናልድ ትረምፕ በራሳቸው ተነሳሽነት ብቻ የሚፈልጉትን ተግባራዊ ለማድረግ እንደማይችሉ ነው የህግ አዋቂዎች የሚያስተምሩን። ይሁንና ይህ ዐይነቱ የአሜሪካንን ህገ-መንግስት ሳይንተራስ በዘፈቀደ በሬዚደንቱ የተስፋፋ ዜና አብዛኛውን በአሜሪካን ምድር እየሰራም ሆነ ህገ-ወጥ በሆነ መልክ የሚኖረውን የውጭ አገር ሰው ከፍተኛ የሆነ የጭንቅላት ጭንቀት ውስጥ እንደከተተው የማይታበል ጉዳይ ነው። ከዚህም በላይ በሜክሲኮ ድንበር ላይ የሚደረገው ክትትል ከፍተኛ ትኩረት ተስጥጦት፣ በተለይም ከተለያዩ የደቡብና የማዕከለኛው አሜሪካን አገሮች አሜሪካን ለመግባት የሚፈልጉ ለመግባት እንደማይችሉ ዕድሉ ተዘግቶባቸዋል። ይሁንና ይህንንም በቀላሉ ተግባራዊ ለማድረግ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ዳር ድንበሩን የሚጠብቁ ወታደሮች ማስማራትና፣ ይህንንም በሚመለከት የሰው ኃይል ዕጥረት እንዳለ ነገሩን የሚከታተሉ ይናገራሉ።
ዶናልድ ትረምፕ የምርጫ ካምፒዬን ሲያደርጉ አጥብቀው ያነሱ የነበረው ከተለያዩ አገሮች የመጡ የውጭ አገር ሰዎች የአሜሪካንን ባህል እንዳበላሹና፣ እንዳዶችም አይጥና ድመት እንደሚበሉ ነግረውናል። በዚህ ዐይነቱ ቅስቀሳቸውም በተለይም ተገፋሁ ከሚለው የነጩ አሜሪካ ዜጋ ብዙ ድምጽ ለማግኘት እንደሚችሉ በማሰብ ነበር በውጭ አገር ስደተኖች ላይ እንደዚህ ዐይነት የጥላቻ ቅስቀሳ ለማካሄድ የበቁት። አንድ ለፕሬዚደንትነት እወዳደራለሁ የሚልም ሰው በእንደዚህ ዐይነቱ ርካሽ ቅስቀሳ ውስጥ መሳተፍ አልነበረበትም። በተጨማሪም ፕሬዚደንቱ በዚህ ዐይነቱ አላስፈላጊ ቅስቀሳቸው ያልተገነዘቡት ነገር ከተለያዩ አገሮች እየመጡና እየሰሩ በሚኖሩት የውጭ አገር ሰዎችና፣ ነጭ ነኝ በሚለው አሜሪካዊ፣ ወይም ደግሞ የአሜሪካን ዜግነት ባለው መሀከል የጥላቻ መንፈስን እንደሚያሳድሩ ነው።
ለማንኛውም መታወቅ ያለበት ነገር ለዚህ ዐይነቱ ወደ አሜሪካ የውጭ አገር ሰዎች ፍሰለት ዋናው ምክንያት የራሱ የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ እንደሆነ ፕሬዚደንት ትረምፕም ሆነ የቀደሙት ፕሬዚደንቶች መረዳት ነበረባቸው። እንደሚታወቀው አንድ ሰው ከሀገሩ የሚሰደደው አገሩን ስለሚጠላ ሳይሆን፣ አገሩ ውስጥ ማግኘት የማይችለውን ዕድል አሜሪካን ማግኘት እችላለሁ በሚል ነው። በየአገሮቹ ውስጥ፣ በተለይም በማዕከለኛውና በደቡብ አሜሪካ በተለያዩ ጊዜያት ስልጣን ላይ በመውጣት አገሮቻቸውን የሚያስተዳድሩ የነበሩት በሙሉ የተትረፈረፈ የጥሬ-ሀብትና ለእርሻም የሚሆን ለም መሬት ቢኖራቸውም የህዝቦቻቸው አልለኝታ በመሆን ወደ ውስጥ ያተኮረና ርስ በርሱ የተያያዘ ጠንካራና ሰፋ ያለ የስራ-መስክ ሊከፍት የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት በፍጹም አልቻሉም።
ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊያዝም የበላይነትን ከተቀዳጀ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማለቂያ በኋላ በአካባቢው ተፎካካሪ ወይም ተወዳዳሪ የሚሆነው አገዛዝና አገር እንዳይኖር አጥብቆ የሰራው ሴራ አብዛኛዎችን የማዕከለኛውና የደቡብ አሜሪካ አገሮችን ወደ ውስጥ ያተኮረና ለህዝቦቻቸው አስተማማኝ የሚሆን የኢኮኖሚ መሰረት እንዳይጥሉና ተከታታይነት ያለው፣ በቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ግንባታ እንዳያካሂዱ ሊያግዳቸው በቅቷል። አብዛኛዎቹ አገሮችም ደግሞ ተሽመድምደው እንዲቀሩ የየአገሩ የመንግስት መኪናዎች በሙሉ ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በሚስማማና የአገር ወዳድነት ስሜት በሌላቸው ሰዎች መዋቀርና መያዝ ነበረባቸው፤ አለባቸውም። ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የብዝበዛ ድርጊት የማያመቹ አገዛዞች ደግሞ በህዝብ ድምጽ ብቻ ከተመረጡ በኋላ በኩዴታ እንዲገለበጡ፣ ወይም ደግሞ እንደ አሌንዴ የመሳሰሉት እንዲገደሉ ተደርገዋል። አብዛኛዎችም ከፍተኛና ዝቅተኛ የሚሊተሪና የፀጥታ ሰዎች ፓናማ ውስጥ በአሜሪካን ጄኖራሎችና አሰልጣኞች የሰለጠኑ በመሆናቸው በራሳቸው ህሊና የሚመሩና ለአገራቸው የሚቆረቆሩ ሳይሆኑ በውሸት ቅስቀሳ መንፈሳቸው በመጠመድ የኮሙኒዝምን አስተሳሰብ ያራምዳሉ የሚሏቸውን በሙሉ በመግደል፣ በማሰርና፣ የተቀረውን ደግሞ እንዲሰደድ በማድረግ ማዕከለኛውንና ደቡብ አሜሪካን አገሮችን የምሁራን አልባ ለማድረግ በቅተዋል። ከዚህም በላይ አብዛኛዎቹ የደቡብ አሜሪካ አገሮች ከ1950ኛው መጀመሪያ ዓመታት አንስቶ የተከተሉት የምትክ ተከላ ኢንዱስትሪ(Import-Substitution Industrialization) ወደ ውስጥ ያተኮረና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመረኮዘ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ እንዳይገነቡ አስገድዷቸዋል። ወደ ማዕከለኛው አሜሪካ(Central America) አገሮች ስንመጣ ደግሞ አብዛኛዎቹ አገሮች ለአሜሪካን ገበያ የሚሆን ሙዝ፣ ቡናና ካካኦ፣ እንዲሁም ሌሎች ፍራፍሬዎችን ብቻ የሚያመርቱ በመሆናቸው ስራ ፈላጊ ለሆነው ሰፊው ህዝባቸው በቂ የስራ መስክ መክፈት የሚችሉ አይደሉም። በተለይም እንደሙዝና ሌሎች ፍራፍሬዎችን የሚቆጣጠረው ዩናይትድ ፍሩት ካምፓኒ(United Fruit Company) የሚባለው የአሜሪካ የፍራ-ፍሬ አስመጭ ኩባንያና በብዙ የመንግስት ግልበጣዎችም ውስጥ የተካፈለው ይህ የምዝበራና አገሮችን የማቀጨጭ ሂደት በዚያው እንዲቀጥል አጥብቆ የሚሰራ ትልቅ ኩባንያ ነው።ይህ ኩባንያ በሚቆጣጠራቸው ማሳዎች ውስጥ የሚሰሩት ገበሬዎችና ወዛደሮች ደግሞ በዝቅተኛ ደሞዝ የሚሰሩና ልጆቻቸውን ማስተማር የሚችሉ አይደሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ሙያው ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ በመሆን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን ህይወት ያቀጨጨ ነው። እነዚህ ነገሮች በመደማመር በተለያዩ የማዕከለኛውና የደቡብ አሜሪካን አገሮች ውስጥ ያሉት አገዛዞች ለህዝቦቻቸው አስተማማኝና አለኝታ የሚሆኑና ኢኮኖሚውን ሰፋ ባለ መስክ ለማዋቀርና ህዝቦቻቸውን ለመያዝ የሚችሉ የኢኮኖሚ መሰረቶች ለመጣልና ለመገንባት በፍጹም አልቻሉም። በተለይም አብዛዎቹ የደቡብ አሜሪካ አገሮች ከ1970ኛው ዓመት መጨራሻና ከ1980ዎች መጀመሪያ ዓመታት ጀምሮ በወጭ ዕዳ በመተብተባቸውና በተከታታይ አንጀት አጥብቂኝ የሆነ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተላቸው የተነሳ የዕዳ ከፋይ ከመሆን በስተቀር ከስህተታቸው በመማርና ሌላ አማራጭ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል ኢኮኖሚያቸውን በተሻለና ለህዝቦቻቸው አስተማማኝ በሆነ መልክ ለማዋቀር ባለመቻላቸው የተነሳ በየራገሩ ውስጥ የመኖር ዕድል ለማግኘት ያልቻለውና የማይችለው ሰፊው ህዝብ በዚህም በዚያም ብሎ ወደ ታላቁ አሜሪካ እንዲሰደድ ተገደደ። ይህም ሁኔታ በአሜሪካን ምድር ልዩ ዐይነት የሆነ የጎሳ ምስቅልቅል ሁኔታን በመፍጠር፣ በዚያው መጠንም የዲሞግራፊውንም ሁኔታ ሊቀይረው ችሏል። በተለያዩ ጊዜያት በአሜሪካን ምድር ለፕሬዚደንትነት ተወዳደረው በአሸናፊነት የሚወጡና አዲስ መንግስትም የሚመሰርቱት ከተደጋጋሚ ስህተታቸው ለመማር ባለመቻላቸው የሚያሳብቡት በስደተኞች ወይም ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ አሜሪካን ገብተው በሚኖሩት ከተለያዩ የማዕከለኛውና የደቡብ አሜሪካን አገሮች በመጡ ሰዎች ላይ ነው። ይሁንና ግን እነዚህ ህጋዊም ሆነ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚመጡት ሰዎች በጽዳት ስራና፣ በተለይም ሽማግሌ ሰዎችን ለመንከባከብ ተቀጥረው በመስራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ናቸው። ወደ አመጽና ወደ ድረግ ስራ ውስጥ የሚሰማሩት ደግሞ ከመጀመሪያውኑ በአሜሪካን ህብረተሰብ ውስጥ እንዲቀላቀሉ አስፈላጊው የሙያና የቋንቋ ስልጠና ቢሰጣቸው ኖሮና፣ ከውጭም ጭንቅላትን የሚያደነዝዙ ድረጎች እንዳይገቡ ከፍተኛ ቁጥጥር ቢደረግባቸው ኖሮ እነዚህ እንደወንጀለኛ የሚቆጠሩት ሰዎች ጤናማ ህይወት መኖር በቻሉ ነበር። ባጭሩ ለማለት የምፈልገው ይህ ሁሉ ነገር ሊፈጠር የቻለውና በስደተኞች ላይም ዘመቻ የሚደረገው ዋናው ምክንያትና ተጠያቂው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚያካሂደው የማንአለኝበትና የፀረ-ዕድገት ፖሊሲ ነው። ይህ እስካልቆመና በየአገሮች ውስጥ ያሉ አገዛዞችም በሰለጠኑና የአገር ወዳድነት ስሜት ባላቸው ሰዎች እስካልተያዙ ድረስ ጉዳዩ መቋረጫ የሚያገኝ አይደለም።
ወደ ሌላ ነጥቦች ስንመጣ ደግሞ በፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ የሚመራው አዲሱ አገዛዝ የመንግስቱን መኪና ለእሱ በሚስማማው መንገድ እያደራጀና፣ ታማኝ ያልሆኑና፣ የፕሬዚደቱንም ትዕዛዝ ሊያስፈጽሙ አይችሉም የሚሏቸውን ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ የመንግስት ሰራተኞችን ከስራቸው ለማባረር ቆርጠው ተነስተዋል። ይህንን ተግባራዊ የሚያደርገው ደግሞ የቴስላ ዋና ኃላፊ የሆነው ኤለን መስክ ነው። ይህ ሰው ደግሞ በመንግስት መኪና ወይም ቢሮክራሲ ውስጥ ያላለፈና ልምድም የሌለው ነው። የመንግስትንም መኪናና ቢሮክራቶችን የተመለከተው የተለያዩ ምርቶችን እንደሚያመርት ፋብሪካ ወይም የንግድ ድርጅት ነው። ይሁንና ኤለን መስክ በአካሄዱ ከአሁኑ ለብዙ ዓመታት በየመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥረው ሲሰሩ ለቆዩት የብዙ ሰዎችን መንፈስ በከፍተኛ ደረጃ ሊረብሽ ችሏል። ይህ ዐይነቱ የመንግስቱን መኪና ለዶናልድ ትረምፕ በሚስማማ መልክ ማዘጋጀትና ማመሰቃቀል አንዳንድ የጀርመንና የሌሎች የውጭ አገር ጋዜጣዎች ስርዓት ያለው የመንግስት ግልበጣ ዐይነት ብለው ይተረጉሙታል። ከዚህ ዐይነቱ ሂደትም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለው የአሜሪካ ዕርዳታ ስጭ(USAID) የሚባለው ድርጅትም አልተረፈም። ይሁንና ይህም ድርጅት በፓርሊያሜትና በሴናት የፀደቀና ለተለያዩ አገሮችም “ዕርዳታ” የሚሰጥ በመሆኑ በቀላሉ በፕሬዚደንት ትዕዛዝ ሊዘጋ እንደማይችል በዚህ ጉዳይ ላይ ዕውቀት ያላቸው የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በሌላ ወገን ግን ይህ የዕርዳታ ሰጭ የሚባለው ድርጅት ተዘጋ አልተዘጋ የሚያመጣው ፋይዳ የለም። ዕርዳታ እሰጣለሁ ወይም ፕሮጀክቶችን አካሂዳለው በሚላቸው አገሮች ውስጥ አንዳችም ተከታታይነት ያለውና በየአካባቢዎች አስተማማኝ የሚሆን የኢኮኖሚ ግንባታ ሲያካሂድ በፍጹም አይታይም። በየአገሮች ውስጥም በአንድ አካባቢ ብቻ ርስ በርሳቸው ሊያያዙና በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ ልዩ ልዩ ምርቶችን ሊያመርቱ የሚችሉ ትናንሽ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ለማድረግ አልቻለም። በዕርዳታ ስም አገሮች ዘለዓለማዊ ለማኝ ሆነው እንዲቀሩ የሚሰራ አሻጥረኛ ድርጅት ነው። ስለሆነም በዕርዳታ ስም እንደሚነግዱት ሌሎች ድርጅቶችም በየአገሮች ውስጥ ሁለ-ገብ የሆነና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ክንዋኔ እንዳይገነባ መሰናክል የሚፈጥር ነው። ለምሳሌ የጀርመኑ ማህበራዊ ዓለም አቀፋዊ የትብብር ስራ ድርጅት(GIZ) የሚባለውና የውጭ አገርን በሚመለከት በተቋቋመው የሚኒስተር መስሪያ ቤት(BMZ) ቁጥጥር ስር ያለው በሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ የበላይነት ስሜት በማሳደርና ጥቃቅን ነገሮች ከመስራት ያለፈ ነገር ሲሰራ በፍጹም አይታይም። እነዚህን በመሳሰሉት የውጭ ዕርዳታ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩት በሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ፣ አገራችንም ጭምር ነጮች እንደ ንጉሶች የሚቆጠሩና፣ ከሃያና ከሰላሳ ዓመት በኋላ የየድርጅቶቹ ኃላፊዎችና ተቀጣሪዎቻቸው በዘረፉት ገንዘብ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ትላልቅ ቪላ ቤቶች ገዝተው ወይም ሰርተው የሚኖሩ ናቸው። አንዳንዶችም እንደ አጋጣሚ ያገኘኋቸው የጀርመን ዕርዳታ ሰጭ ሰራተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ለስራ በቆዩበት ዘመናት ብዙ ነገሮችን እንዳመሰቃቀሉ ነው በመፀፀት የነገሩኝ። ዕርዳታ በመስጠት አሳበውም መረጃዎችን የሚሰበስቡና በየአገሮችም ውስጥ አለመረጋጋትን የሚፈጥሩ ሴራዎችን እንደሚሰሩ ይታወቃል። የዕርዳታ ስጭ ድርጅቶችም የሚባሉት ከየአገሩ የስለላ ድርጅቶች ጋር እንደሚሰሩ የታወቀ ጉዳይ ነው። በተለይም የአሜሪካን የዕርዳታ ሰጭ ድርጅት በተዘዋዋሪ የሚደጎመው ጆርጅ ሶሮን በሚባለውና በተለያዩ የምስራቅ አውሮፓ አገሮች ውስጥ የመንግስት ለውጥ(Regime Change) እንዲካሄድ የሚሸርበው ጋር አብረው በመስራት የመንግስት ለውጥ እንዲካሄድ የውስጥ ለውስጥ ቅስቀሳ ከሚያካሂዱት ከአሜሪካን ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ነው።
ይህንን ትተን የዶናልድ ትረምፕን የውጭ ፖለቲካ ስንመለከት ፖለቲካ ብለን ልንጠራው የምንችለው ነገር አይደለም። ይህ ዐይነቱ አካሄድ የአብዛኛዎቹ የአሜሪካን ፕሬዚደንቶችና አገዛዞቻቸው ፖለቲካ ቢሆንም፣ እንደ ዶናልድ ትረምፕ ዐይን ባወጣና በንቀት መልክ የሚካሂድ ፖለቲካ አልነበረም። የዶናልድ ትረምፕን የውጭ ፖለቲካ ለየት የሚያደርገው በቀጥታ የየአገሩን ብሄራዊ ነፃነት የሚጋፋና አደጋም የሚያስከትል ነው። ለምሳሌ የፓናማ ካናልን መልሰን በአሜሪካን ቁጥጥር ስር ማስገባት አለብን የሚለውና፣ በአውቶኖመስ ደረጃ የምትደዳረውን ግሪን ላንድን በአሜሪካን ስር ማምጣት አለብን የሚለው አካሄድ ሁሉንም አገዛዞችና አስተዳደሮች አስቆጥቷል። የዴንማርክ መንግስት ደግሞ የኔቶ አባል አገር የሆነና አገዛዙም የአሜሪካን ወዳጅ ነው። በዚህ የተናደደው በሴት ጠቅላይ ሚኒስተር የሚመራው የዴንማርክ መንግስት አሜሪካ ግሪን ላንድን ትወራለች በሚል ምክንያት የተነሳ ሁለት ቢሊዮን ኦይሮ የሚጠጋ ለመሳሪያ መግዣ መድቧል። ይሁንና ግን አሜሪካ በቀጥታ ወረራ ካካሄደና ግሪን ላንድን በቁጥጥሩ ስር ካመጣ የዴንማርክ መንግስት ይህንን መክቶ የመመለስ አቅም በፍጹም የለውም። ከዚህም በላይ ካናዳን የአሜሪካን አካል እናደርጋለን የሚለው አነጋገር የካናዳን መንግስትና የህዝብ ተጠሪዎች የሆኑትን በጣም አስቆጥቷል። ሌላው ደግሞ በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቆ በመሄድ ጋዛ የሚባለውንና በተደጋጋሚ በእስራኤል ወታደሮች የቦንብ ድብደባ የሚካሄድበትን የፍልስጤማውያንን ግዛት ገዝቼ በአሜሪካን ቁጥጥር ስር በማምጣት ልዩ ዕድገት እንዲመጣ አደርጋለሁ የሚለው የዶናልድ ትረምፕ አባባል አብዛኛዎቹን አገሮችና፣ የአረብ አገሮችንም ጭምር በጣም አስቆጥቷል። ይህንና ሌሎችንም ርስ በርሳቸው የሚጋጩ ወይም የሚቃረኑ የዶናልድ ትረምፕንና የአገዛዛቸውን ፖለቲካ ስንመለከት በጣም አደገኛ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ንቀትም የተሞላበት ነው። እኛን የሚቋቋም ኃይል ስሌለና ኃያል መንግስትም ስለሆን ማንኛውም አገር እኛ የምንለውን መቀበል አለበት፤ ካለበሊዚያ እናሳየዋለን የሚለው የሰለጠነ ፖለቲካ አይደለም። በእርግጥ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በተፈጥሮው በኃይልና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብን በመጨፍጨፍና ጥቁሩን ህዝብ ባርያ በማድረግ የተመሰረተ አገር ስለሆነ በታሪኩ ውስጥ የሰለጠነና የሌሎችን አገሮች ብሄራዊ ነፃነት የሚያከብር የውጭ ፖለቲካ በፍጹም ተከትሎ አያውቅም።
ከዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ጋር የተያያዘው ደግሞ ሰሞኑን በጀርመን ምድር ሙኒክ በሚባለው ከተማ ውስጥ በየዓመቱ በክረምት ወራት፣ በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ የሴኪዩሪቲ ስብሰባ ብለው የሚጠሩትና በብዙ መቶ ሰዎች የሚቆጠሩ የአውሮፓና የሌሎች አገሮች ተጠሪዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ የዶናልድ ትረምፕ ምክትል ፕሬዚደንት የሆነው ጂዲ ቫንስ የሚባለው ያደረገው ንግግር ብዙዎችን አስቆጥቷል። እንደሚታወቀው በአብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ በተለይም እንደጀርመን በመሳሰሉት ውስጥ በጣም የቀኝ አዝማሚያ፣ እንዳንዶቹ እንደሚሉት የፋሽሽት አዝማሚያ ያላቸው ፓርቲዎች ከ2015 ዓ.ም በኋላ በጣም እየተጠናከሩ መጥተዋል። እነዚህም ፓርቲዎች በተለይም የውጭ አገር ዜጋ በመሳሰሉት ላይ ያተኮረና የጥላቻ ቅስቀሳ በማካሄድ በቀላሉ የማይናቅ ድምጽ ያገኙ ናቸው።፡ በተለይም በሪጂናል ፓርሊያሜንት ውስጥ ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት አዲስ አገዛዝ ለመመስረት እንቅፋት ፈጥረዋል። ይሁንና በአለፉት 20ና ሰላሳ ዐመታት በጀርመንም ሆነ በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ውስጥ በፍጹም የድምፅ ብልጫ በማግኘት ብቻውን አገር ለማስተዳደር የሚችል ፓርቲ እስካሁን ድረስ ብቅ ሊል አልቻለም። ትናንሽ ፓርቲዎችም ፓርሊያሜንት ውስጥ ለመግባት የሚያስችላቸውን የድምፅ ቁጥር በማግኘትና ፓርሊያሜንት ውስጥ በመግባትና መቀመጫ በመያዝ ለማስተዳደር ወይም በቀላሉ ጣምራ መንግስት ለመመስረት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በተለይም ቀኝ አክራሪዎች የሆኑ ፓርቲዎች ከፍተኛ ድምጽ እያገኙ በመምጣታቸው የተነሳ የሶሻል ዲሞክራቲክንና የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲዎችን ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከቶአቸዋል። እነዚህም ራሳቸውን ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ነን ብለው የሚጠሩት የቀኝ አዝማሚያ ወይም አክራሪና የውጭ አገር ሰዎችን ከሚጠሉ ፓርቲዎች ጋር ጣምራ መንግስት ለመመስረት እንደማይችሉና፣ ፓርሊያሜንት ውስጥም አጠገብ ለአጠገብ ለመቀመጥ አይፈልጉም። በፓርሊያሜንታሪ አጣሪ ኮሚቴ ውስጥም የተለያዩ ኮሚሽኖችን ለመምራት የመመረጥ ዕድል በፍጹም የላቸውም። ሌሎች ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ነን የሚባሉት አንድ ላይ በመሆን የመመረጥ ዕድል እንዳይኖራቸው ያደርጋሉ።
በሙኒኩ የሲኩሪቱ ስብሰባ ላይ የተገኘው የአሜሪካኑ ምክትል ፕሬዚደንት ጂዲ ቫን ዕድል ተሰጥቶት ንግግር ሲያደርግ የጀርመንንም ሆነ የሌሎች አገሮችን መንግስታት ዲሞክራቶች አይደላችሁም በማለት በግልጽ ወንጅሏቸዋል። እሱ እንደሚለው እነዚህ የቀኝ አዝማሚያ ያላቸው ወይም አክራሪ ፓርቲዎች በብዙ የህዝብ ድምጽ የተመረጡ ስለሆነ የግዴታ መከበርና የአገዛዝንም ኃላፊነት መቀበል አለባቸው። ይህ አባባሉ በአገሮች የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ እንደመግባትና፣ በተለይም ደግሞ አክራሪ ፓርቲዎች የበለጠ ተደማጭነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው። በነገራችን ላይ በጀርመን ምድር አማራጭ ፓርቲ ለጀርመን(AFD) የሚባለው ድርጅት ራሱ ፀረ-አሜሪካንና አንዳንድ መሪዎችም ከእነ ፕሬዚደንት ፑቲን ጋር የቀረበ ግኑኝነት አላቸው። ይህም የጀርመን የቀኝ ፓርቲ የሆነው አሜሪካና የተቀሩት የኔቶ አባል አገሮች በመተባበር በራሽያ ላይ የሚያካሂዱትን የውክልና ጦርነት አጥብቆ የሚቃወምና የጀርመን መንግስት ማንኛውንም ለዩክሬይን የሚሰጠውን ድጋፍ ማቆም አለበት ብሎ የሚከራከር ነው። ይህንን ዐይነቱን ፓርቲ ነው የአሜሪካኑ የምክትል ፕሬዚደንትና ኤለን መስክም የሚደግፉትና እንደ ጠበቃም በመሆን የሚከራከሩለት። ኤለን መስክም ከአንድ ወር በፊት ከዚህ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ከሆነችው ሴት ጋር ሁለት ሰዓት የፈጀ በቪዲዮ የተላለፈ የቃለ-መጠይቅ ምልልስና ውይይት አካሂደዋል። የኤለን መስክም አካሄድ በሶሻል ዲሞክራቶችና በግሪን ፓርቲ የሚመራውን አገዛዝ በጣም አስቆጥቷቸዋል። ይህ ዐይነቱ አላስፈላጊ የሆነ በአንድ አገር የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ መግባትና መረበሽ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል። ከዚህ ዐይነቱ የዶናልድ ትረምፕ ፖለቲካና በአካባቢው ከተሰበሰቡት ሰዎች ወይም በአገዛዝ ውስጥ እንዲካተቱ ከተደረጉት ሰዎች ስንነሳ በአሜሪካን ምድር አክራሪ የሆነ የቀኝ መንግስት የተመሰረተ ይመስላል። ይህም ዐይነቱ የቀኝ አዝማሚያ ፖለቲካ በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በተለይም ደግሞ በአውሮፓ ምድር እንዲተገበርና ስርም እንዲሰድ የሚፈልግ ይመስላል። ለዚህም ነው የአሜሪካኑ ምክትል ፕሬዚደንት በሴኪዩሪቲው ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያደርግ ራሽያም ሆነ ቻይና የአውሮፓ ጠላቶች ሳይሆኑ፣ ራሳቸው የየአገሩ የአውሮፓ መንግስታት ናቸው የራሳቸው አገሮች ጠላቶች ናቸው በማለት የፈረጀው። ራሽያና ቻይና የአውሮፓ አገሮች ጠላቶች አይደሉም የሚለው አባባል ትክክል ቢሆንም፣ በሌላ ወገን ግን የየአገሩን አገዛዞች የአገሮቻችሁና የህዝቦቻችሁ ጠላቶች ናችሁ የሚለው አባባል ተቀባይነት የለውም። እንደዚህም ብሎ በተጋበዘበት ስብሰባ ላይ በከፍተኛ የህዝብ ድምጽ የተመረጡትን መወንጀል ፖለቲካዊ አነጋገር አይደለም። ብስለት የጎደለ አባባል ነው።
ሰለሆነም ሰሞኑን ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ከፕሬዚደንት ፑቲን ጋር ዘጠና ደቂቃ ያህል የፈጀው የስልክ ንግግራቸው አብዛኛዎችን የጀርመንን፣ የእንግሊዝን፣ የፈረንሳይንና፣ ራሽያን እንደ ዋና ጠላት አድርገው የሚቆጥሩትን የድሮዎችን የሶቭየት ህብረት አጋር የሆኑትንና፣ በአሁኑ ወቅት የኔቶ አባል በመሆን የአሜሪካ ቡችላ የሆኑትን በሙሉ አናዷቸዋል። ፕሬዚደንት ትረምፕም ሆነ ምክትል ፕሬዚደንታቸው በጦርነቱ ምክንያት የተነሳ ዩክሬይን ያጣችውን 20% የሚጠጋ መሪቷን መልሳ የማግኘት ዕድል የላትም፤ ስለሆነም ዩክሬይን ያላት ምርጫ ከራሽያ ጋር አብራ በመቀመጥ ጦርነቱ መቋጭ እንዲያገኝ ንግግር መጀመር ብቻ ነው የሚያዋጣት ብለው የቅጩን ተናግረዋል። ዩክሬይንም፣ በተለይም ፕሬዚደንት ሲሌንስኪ የቋመጠውን የኔቶ አባል የመሆን ዕድል እንደማያገኝና ይህንን በመረዳት ህዝቡን የሚያስጨርሰውን ጦርነት እንዲቆም የግዴታ ከራሽያ ጋር ተቀምቶ መነጋገር አለበት ብለዋል። በዶናልድ ትረምፕ የሚመራውም አገዛዝ ጆን ባይደንና አገዛዛቸው እንዳደረጉት የሚሊተሪና ሌሎች ዕርዳታዎችን አሜሪካን ከእንግዲህ ወዲያ ለዩክሬይን እንደማትለግስ አስታውቀዋል። ይህ እንዲሆን ከተፈለገ ደግሞ ዩክሬይን ያላትን ልዩ ዐይነት ሚታሎች፤ በተለይም ለኤሌክትሮኒክስ ዲቫይስና ለባትሪ የሚያገለግሉ ሜታሎች ውስጥ የአሜሪካ ኩባንያዎች የማውጣትና የመሳተፍ ዕድል እንዲኖራቸው አጥብቀው ተናግረዋል። ስሌትም እንደሚያሳየው ዩክሬን ውስጥ ወደ 23 ትሬሊየን ዶላር የሚጠጋ ስትራቴጂክ ሜታሎች እንደሚገኙ ሲታወቅ፣ የጥርነቱም አንደኛው ምክንያት ይህ ነው።
ለማንኛውም በፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ የሚመራው አዲሱ አገዛዝ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ፖለቲካው ትርምስ እየፈጠረና የብዙ አገር መሪዎችንም እያስቆጣ ነው። አሜሪካ ትቅደም የሚለው ፖለቲካ አብዛኛዎችንም አስደንግጧል። ከዚህም በላይ ከአውሮፓ፣ ከቻይና፣ ከካናዳና ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶች ከፍተኛ የግምሩክ ቀረጥ እንደሚከፍልባቸው አስታውቀዋል። ለማንኛውም ይህ ዐይነቱ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕና የአገዛዛቸው የውጭ ፖለቲካ እስካሁን ድረስ በህግ ላይ የተመሰረተውን(Rule-based System) የሚባለውን የዓለምን ህዝብ ዕድል በቀላሉ የሚያሽከረክሩበትን ስርዓታቸውን እንደሚናጋባቸው በተለይም የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችን መንግስታትና የፀጥታ ኃይሎቻቸውን አስደንግጧቸዋል። የምዕራብ አውሮፓ መንግስታትም፣ በተለይም ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ሌሎችም የባልቲክ አገሮች እዚህ አውሮፓ ምድር ውስጥ የሚካሄደው ጦርነትና እስካሁንም ድረስ የተገነባውን ስልጣኔ ሊያወድም የሚችለው በራሽያና በእነሱ መሀከል ሊካሄድ የሚችለው ጦርነት ለምን መግፋት እንዳለበት እንደሚታገሉ ግልጽ አይደለም። አይ ዞሮባቸዋል፣ ወይም የፖለቲካን ትርጉም ወደ ፍጹም የበላይነትና የማንአለኝበት መሳሪያ ለውጠውታል ማለት ነው። ይህ ድርጊታቸውና አመለካከታቸው ደግሞ የኢንላይተንሜንት፣ ወይም የሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ በተፀነሰበትና ዓለም አቀፋዊም እንዲሆን ትግል በሚደረግበት አህጉር ውስጥ ነው። የኢንላይተንሜንትም ዋናው መልዕክት አርቆ አሳቢነትና መቻቻል ሲሆን፣ ማንኛውንም አለመግባባት ዲፕሎማሲያዊ ወይም በሰለጠነ መልክ መፈታት እንዳለበት የሚያስተምር ነው። በአጭሩ ኢንላይተንሜንት ማለት መገለጽ ማለት ሲሆን፣ ከከረረ አስተሳሰብ በመላቀቅ ማንኛውንም የሃሳብ ልዩነት በሚያሳምንና በሚያግባባ መልክ ለመፍታት መቻል ነው። በሌላ ወገን ግን ይህ ዐይነቱ በኔቶ አባል አገሮች መሀከል ያለው ቅራኔ ለአብዛኛዎቹ አገሮች፣ በተለይም ለሶስተኛው ዓለም አገሮች የመተንፈሻና ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያገኙ ዕድል ሊሰጣቸው ይችላል የሚል ግምት አለኝ። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገዛዞች፣ ከድንቁርና ፖለቲካቸው በመላቀቅና፣ በተለይም ሰፋ ላለ ምሁራዊና ሳይንሳዊ እንቅስቃሴ የሚያመች ሁኔታን በመፍጠር ህዝባቸውን ሰብሰብ በማድረግ ሁለ-ገብ ወደ ሆነ የአገር ግንባታ ላይ ማተኮር አለባቸው። በእርግጥ እንደዚህ ዐይነቱ እሳቤ በእኛ አገር ውስጥ የሚታሰብ አይደለም። በብሄረ ጠባብ አስተሳበ ናላው የዞረው የትግራይና የኦሮሞ ኤሊት ይህንን የተወሳሰበና በቅራኔ የተሞላ የዓለም ፖለቲካ የመረዳት ዕድልና ኃይልም ስለሌለው አጥፍቶ በመጥፋት ፖለቲካው ይገፋበታል። በዚያ የድንቁርናው ፖለቲካ በመግፋት የኢትዮጵያን ውድቀት ያፋጥናል እንጂ የሚመለስ አይሆንም። ጭንቅላቱም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የተዳፈነ ሰለሆነ ነገሮችን የማየት ኃይል በፍጹም የለውም። መልካም ግንዛቤ!!
[email protected]
www.fekadubekele.com
https://www.youtube.com/watch?v=w8afHkRaOnU