በሰለሞን ኃይለማርያም (ዶ/ር)
ባለፈው ሳምንት ጽሑፍ ስለ የፖለቲካ ባህል ፅንሰ ሃሳብ ፣ ከኢትዮጵያ የልሒቃን የፖለቲካ ባህል ውስጥ ስም ማጥፋትን ፤ ተቀናቃኝን ማጥቃትንና የመደራደርና የሰጥቶ መቀበል ባህል አለመኖርን ባጭሩ ዳሰናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሌሎች የዓለም ሀገራት የተሳሳተ ያሉትን የፖለቲካ ባህል እንዴት ቀየሩ? በመቀየራቸውስ ምን አገኙ? በማለት የጃፓንና የቺሊን የፖለቲካ ባህል እናያለን ፡፡
መግቢያ
የጥንት አባቶቻችን ትክክል ነው ፤ ያዋጣል፤ ተገቢ ነው ባሉበት መንገድ ሀገራችንን ሲያስተዳድሩ ቆይተው ኢትዮጵያን እዚህ አድርሰዋል፡ በየጊዜው ያጋጠማቸውን በሚያውቁትና በሚገባቸው መንገድ ችግራቸውን እየፈቱ እዚህ ደርሰናል፡፡ የዛሬ ሺህ ዓመታት ፤ የዛሬ 400 ዓመት ወይንም የዛሬ 100 ዓመት ቀደምት ትውልድ በጊዜው ለነበረው ተግዳሮት የተጠቀሙበትን ዘዴና መፍትሔዎች ዛሬ መጠቀም አይቻልም፡፡ ዛሬ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅት ፤ የሰው ልጆች ወደ ጨረቃ ፤ ወደ ማርስ፤ ወደ እየመጠቁ ስለጠፈር በሚመራመሩበት ወቅት “ጥራኝ ጫካው፤ ጥራኝ ዱሩ” ማለት መሳቂያ ከመሆን ያለፈ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ የዓለም ሕዝብ ስለሳይንስ ስለቴክኖሎጂ ሲጨነቅ እኛ ስለዳቦ ፤ ስለረሀብና ስለችጋር ማውራት ማቆም ያለብን ጊዜ አሁን ነው፡፡
ከእልቂት አዙሪት እንዴት እንውጣ የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ብዙ እሴት የተሸከመ ንግግር ነው፡፡ “ጥራኝ ጫካው፤ ጥራኝ ዱሩ’ የሚለው የኢትዮጵያ የልሒቃን የፖለቲካ ባህል ከሞት፤ ከድህነት፤ ከኋላቀርነት ማህበረሰብን ወደ ተሻለ ደረጃ ከማሸጋገር የሚያሰናክል ጋሬጣ ነው፡፡ ኩራት፤ በራስ መተማመን፤ ነፃነት፤ ዕድገትና ሥልጣኔ የሚመጣው በመተባበር፤ በብልሀት ፤ ጠንክሮ በመሥራት፤ ትውልዱን በትምህርት በማነፅና የተሻለ ኑሮ በማኖር ነው፡፡ የዓለም ታሪክ የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ “ውርደት” “መንበርከክ ” “ከዚህስ መሞት ይሻላል” የሚያስብለው እጅ፤ እግር፤ አዕምሮ እያለን፤ መሬት፤ ውሃ፤ ፀሐይ እያለን በረሀብ ስንሞት፤ በበሽታ ስናልቅ ፤ በኋላ ቀርነት ስንማቅቅ ነው፡፡ በርግጥ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ ተራቆ ስለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፤ ስለኳንተም ቲዎሪ፤ በሚያወራበት ወቅት በረሃብ መሞት “ውርደት” ነው። ውርደት ማለት ወደታች፤ ቁልቁል መውረድ ማለት ነው፡፡ የዓለም ሕዝብ ወደ ላይ ሲወጣ፤ ሽቅብ ሲንጠራራ እኛ ባረጀና ባፈጀ የ“ጥራኝ ጫካው፤ ጥራኝ ዱሩ ‘’የፖለቲካ ባህላችን የተነሳ ቁልቁል እየወረድን ነው፡፡ እኛ “ውርደት” “መንበርከክ” “ከዚህስ መሞት ይሻላል’ የምንለው ፤ እያልን ያለነው ወደ ዝንተ ዓለም ይዞን የሚዘቅጥ ፤ የበለጠ የሚያዋርደን ነው፡፡ “ውርደት” ልንለው የሚገባው ልጆቻችን በረሃብ፤ በጠኔ፤ በበሽታ፤ በመሀይምነት፤ በጦርነት፤ በባርነት (በባርነት” ሲባል በየባዕድ ሀገሩ እንጀራ ፍለጋ በባህር የሚበሉ በበረሃ ቀልጠው የሚቀሩ በዓረብና በሌሎች ሀገሮች ተንቀው ፤ ተገፍተው ተዋርደውና ተሰቃይተው የሚያልቁ ዜጐቻችንን ያጠቃልላል) ዓይናችን እያየ ሲያልቁ ዝም ብለን ማየታችን ውርደት ሊሆን ይገባል፡፡ ለብዙ ሺህ ዓመታት በበሬ እያረሰ ከረሃብና ጠኔ ያልተላቀቀውን የሀገራችንን ገበሬ ጠመንጃ እየነቀነቁ ማስፈራራት፤ መቀማት፤ የበለጠ ደሀ ፤ የደሀ ደሀ የሚያደርገውን የጦረኛ ባህላችንን ማስፋፋት፤ ጥራኝ ዱሩ ጥራኝ ጫካ እያሉ ወጣቱ እንዳይማር እንዳይመራመር፤ እንዳይሠራና እንዳይሻሻል እየተጋደለ እንዲኖር ማድረግ ካልቆመ የዓለም መተረቻ፤ መሳቂያና የድህነት ምሳሌ ሆነን መቅረታችን ነው፡፡
እስኪ ከዓለም ታሪክ በጥቂቱ ጨልፈን ሌሎች ሀገሮች ይህንንያረጀና ያፈጀ የ ጥራኝ ጫካው፤ ‘’ጥራኝ ዱሩ።”የምንለውንየመሰለ የፖለቲካ ባህል እንዴት እንደተሻገሩት ባጭር ጭሩ እንመልከት፡፡
የጃፓን የፖለቲካ ባህል መቀየር
ጃፓን አውሮፓንና አሜሪካን ጨምሮ “Barbaric’ ወይንም ደግሞ አረመኔ ፣ ኋላ ቀር ያልሠለጠኑ እያሉ መጥራት ብቻ ሳይሆን በርግጥም ከጃፓን በስተቀር የተቀረው ዓለም ኋላ ቀር፣ የበታችና ደንቆሮ አድርገው ያምኑ ነበር፡፡ ወይንም እንዲያምኑ ተደርጐ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ከ1839 1842 በቻይናና በእንግሊዝ በተካሄደው የኦፒየም ዋር እየተባለ በሚታወቀው የንግድ ጦርነት እንግሊዝ የሠለጠነና በደንብ የተደራጀ የባህር ኃይል ስለነበራት ቻይናን በቀላሉ ማሸነፍ ቻለች፡፡ ይህ ድል በጃፓን እንደተሰማ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር እንግሊዞች እኛንም መፈተሻቸው አይቀርም በማለት ተደናገጡ፡፡ “የጠሉትን ይወርሳል፤ የፈሩትም ይደርሳል” እንደሚባለው አሜሪካኖች የጃፓንን ወደቦች ማንኳኳት ጀመሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1843 አሜሪካ በወርቅ የተሞላችውን ካሊፎርኒያን ከሜክሲኮ በመውሰድ በኃይል ወደ ግዛቷ ከቀላቀለች በኋላ መርከቦቿ በብዛት ወደ ፓስፊክ የባህር ዳርቻ መጓዝ ጀመሩ፡፡ በዚህ ወቅት ብዙ መርከቦች በባህሩ ሞገድ አየተሰባበሩ ጃፓን የባህር ጠረፍ ይታዩ ጀመር፡፡
ከመርከቦቹ አደጋ የተረፉ “የአረመኔ” ዜጎች ባህርተኞች በጃፓን ሲያዙ ወይ ይገደላሉ ወይ በአሰቃቂ ሁኔታ ተይዘው ይገኛሉ፡ አሜሪካኖች ይህንን ካስተዋሉ በኋላ ከመርኩበ አደጋ የተረፉ አሜሪካውያን ከመገደልና ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ አያያዝ የሚድኑበትን ሁኔታ ከዚያም አልፎ አሜሪካ በጃፓን የተንሠራፋውን የድንጋይ ከሰል በርካሽ የምታገኝበትን መንገድ ሲያጤኑ ቆይተው በወቅቱ የነበረው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሚላርድ ፊልሞር በኮሞዶር ማቲው ፔራን መልዕክት ላከ፡፡ ኮሞዶር በወቅቱ ዘመናዊ የሚባል ሞተሩ በእንፋሎት የሚሠራ መድፍ በሚተፋ በአራት የጦር መርከቦች ታጅቦ ወደ ጃፓን ገሰገሰ፡፡
የፕሬዚዳንት ፊልሞርን ደብዳቤ ይዞ ሳይጋበዝ ፤ መጣሁ ደረስኩ ሳይል እኤአ በሐምሌ 8 ቀን 1853 ኮሞዶር ፔሪ ኤዶ ባህረሰላጤ ያሁኑ ቶኪዮ ባህረሰላጤ ደረሰ፡፡ የጃፓን ጦር ኃይል ወደኋላ እንዲመለስ ቢጠይቁ፤ ቢያስፈራሩ፤ ቢተኩሱ፤ ቢያቅራሩ ቢደነፉ ከሞዶር ፔሪ በጦር መርከቦቹ ተማምኖ በትዕቢት “ይህንን ደብዳቤ አንብባችሁ የዛሬ ዓመት ስመለስ መልስ አዘጋጁ” በማለት ትዕዛዝ አስተላልፎ ተመለሰ፡፡ በዚህ ጉዳይ ጃፓኖች አጥንታቸውን የነካ ውርደት ተሰማቸው፡፡ ሾገን እየተባለ የሚጠራው ወታደራዊ አገዛዝ ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ እ.ኤ.አ በ1853 በመላው ጃፓን ካሉ አስተዳዳሪዎች ጋር ምከር እንዲካሄድ አደረገ፡፡ በመላው ጃፓን ያሉ ልሂቃን ከተወያዩበት በኋላ ሁለት አንኳር ሃሳቦች ተንሸራሸሩ፡፡ አንደኛው ኮሞዶር ፔሪ ሲመለስ መዋጋትና የጃፓንን ክብር ማስመለስ ሲሆን ሁለተኛው ጃፓን አሜሪካ ያላትን ዘመናዊ የጦር መርከቦች አይነት እስከትሰራ ድረስ ጊዜ መግዛትና መለሳለስ የሚሉ ነበሩ፡፡ አብዛኛው ሁለተኛውን መፍትሔ በመደገፉ በዚሁ ፀና፡፡
ኮሞዶር ፔሪ እንዳለውም እ.ኤ.አ በየካቲት 13 ቀን 1854 ዘጠኝ ተዋጊ የጦር መርከቦችን አስከትሎ ጃፓን ደረሰ፡፡ ለ215 ዓመታት የቆየውን የጃፓን ከማንም ጋር ያለመዋዋል ፖሊሲ በማፍረስ ባኩፋ እየተባለ የሚጠራውና የሚታወቀው ወታደራዊ አገዛዝ ከኮሞዶር ፔሪ ጋር ውል ተፈራረመ፡፡ በዚህም መሠረት በባህር አደጋ ከሚሰባበረው የንግድ መርከብ የሚተርፉ አሜሪካዊያን በሰብአዊነት እንዲያዙ ሁለት የጃፓን ወደቦች በቋሚነት የአሜሪካንን የንግድ መርከቦች እንዲያስተናግዱ ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ እንግሊዝ ፤ ራሺያ፣ ደች እና ሌሎች ምዕራባውያን ተመሳሳይ ውል ከጃፓን ጋር ተፈራረሙ፡፡ጃፓን ካለፍቃዷ በኃይል ከተቀረው ዓለም በተለይም ለምዕራባውያን በሯን በርግዳ ከፈተች፡፡ ይህ ለጃፓን ልሂቃን ሕመም ነበር፡፡
በዚህ ወቅት የጃፓን መሪዎች ዋና ዓላማ ጃፓን ከምዕራባዊያን ጋር ሳይጋጩ ጃፓን ከምዕራባዊያን ያነሰችባቸውን ጉዳይ ዘርዝሮ ያንን ለማስተካከል ቀን ከሌት መሥራት ነበር፡ ለምሳሌ የመከላከያ ኃይላቸውን ለማጠናከር የምዕራባዊያን የጦር መርከቦችን መግዛት፤ ወጣቶችን ወደ አውሮፓና አሜሪካ በመላክ የምዕራባውያንን ዕወቀት እንዲቀስሙ አደረጉ፡፡ የመርከብ አሠራርን፤ የኢንዱስትሪ ግንባታ፤ ምህንድስና፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ሕግ፤ ቋንቋ፤ ሕገ መንግስት፣ ኢኮኖሚክስ የፖለቲካ ሳይንስ እና ሌሎች ዝርዝር ዕውቀቶችን ወጣቶቹ ልቅም አድርገው እንዲያጠኑ ተደረገ፡፡ የወቅቱ የጃፓን መንግስት “የአረመኔዎቹን ያልሰለጠኑትን” እነሱ ባርባሪያን የሚሏቸውን ዕውቀትና ሥልጣኔ የሚያጠና ተቋም መሠረቱ፡፡ በዚህ ተቋም የማንኛውም የምዕራባውያን መጽሐፍ ወደ ጃፓን ቋንቋ ይተረጉማል፤ ይተነተናል፡፡ ዕውቀቱ ወደ ጃፓን ይሸጋገራል፡፡ ይህ ተቋም የሚሠራው ሥራ ግዙፍ በመሆኑ የተነሳ በመጨረሻ ጃፓን ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ተዘፈቀች፡፡ በተለይ የጃፓን ወጣቶችን ወደ ምዕራባውያን ሀገር መላክና የምዕራባውያን የጦር መሣሪያ መግዛት ሀብታቸውን ሙጥጥ አድርጐ ጨርሶ ለከባድ ብድር ዳረጋቸው:: በጃፓን የኢኮኖሚ ቀውስ ተፈጠረ፡፡ የኢኮኖሚ ቀውሱ በተራው የፖለቲካ ቀውስ ፈጠረ፡፡ ሌላው ቀርቶ በጃፓን ንጉሰ ነገስት ስምና ፈቃድ በሚንቀሳቀሰው በባኩፋ እና በንጉሡ መካከል ቅራኔ ተፈጠረ፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ1858 ባኩፋ ከምዕራባውያን ጋር የፈረመውን ውል ንጉሡ አላጸድቅም ቢሉም የባኩፋ መንግስት ውሉን ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ፡፡ ባኩፋ በፈረመው ” አዋራጅና ያላቻ ውል ” የተነሳ የጃፓን ከብር ተነከቷል በሚል ሕዝቡ በባኩፋ በሾገንና በሌሎች ባላባቶች ከፍተኛ ቅራኔ ተፈጠረ፡፡
ባኩፋ ጃፓን በታሪኳ አይታው የማታውቀው የውርደት ውል ለማስተካከል መፍትሔ ለማፈላለግ ቢጥርም አልተሳካም፡ በዚህ የተነሳ የጃፓን ህብረተሰብ በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ ለማለፍ ተገደደ፡፡ በመጨረሻም የሾገን ወታደራዊ አገዛዝ በዚሁ ሳቢያ በተገዳዳሪው ሊገለበጥ ቻለ ፡፡ በባኩፋ የተፈረመው ውል በጃፓኖች “አዋራጅ ያላአቻ’’ ውል እየተባለ ይታወቃል፡፡ “አዋራጅ ያላአቻ ውል” የተባለበት ምክንያት ምዕራባውያን እርስ በርሳቸው እንዲህ ያለ ውል ስለማይዋዋሉ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የምዕራባዊ ዜጋ በጃፓን ሲኖር በጃፓን ሕግና ደንብ ተገዥ የመሆን ግዴታ የለብትም፡፡ ጃፓን ይህ “አዋራጅ ያላአቻ’’ ውል የእግር እሳት ሆኖባት ለግማሽ ምዕተ ዓመት ቆየች፡፡
እ.ኤ.አ በ1859 ጦረኞቹ ሳምራዮች በተለይ “ሺሺ” ወይንም ” ታላቅ ዓላማ ያነገቡ ሰዎች” የሚባሉት የውጭ ሀገር ዜጋ ባገኙበት ይገደሉ ጀመር፡፡ እ.ኤ.አ በመስከረም 14 ቀን 1862 ቻርልስ ሪቻርድሰን የተባለ የ28 ዓመት የእንግሊዝ ነጋዴ ሲገደል የእንግሊዝ መንግስት ጃፓን ይቅርታ እንድትጠይቅና ካሣ እንድትከፍል ገዳዩም እንዲሰቀል ጠየቀች፡፡ በጊዜው የነበረው የጃፓን መንግስት እንቢተኛ በመሆኑ ከአንድ ዓመት በኋላ ነጋዴው የተገደለበትን የሳትሶማ ዋና ከተማ ካጐሺማን የእንግሊዝ የጦር መርከቦች በቦምብ ደብ በው 1,500 ሰዎችን ገደሉ፡፡ እ.ኤ.አ በሰኔ 1863 ሌላ ፀብ ተፈጥሮ የእንግሊዝ፤ ፈረንሣይ፤ አሜሪካና የደች 17 የጦር መርከቦች ጃፓንን ቀጠቀጡ፡፡ እነዚህ ሁለት አጋጣሚዎች ጃፓን ምዕራባውያንን ለመገዳደር ገና መሆኗንና አንገታቸውንደፍተው ራሳቸው ማደራጀት እንዳለባቸው ለሁሉም ጃፓናውያን ግልጽ ያደረገ ከስተት ነበር፡፡ እ.ኤአ በ1866 ቀድሞ የነበረው ሾገን ሲሞት አሲ ሾገን ጃፓንን የማዘመን ተግባሩን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ከፈረንሳይ ወታደራዊ አማካሪና የጦር መሣሪያዎች በብዛት አስገባ፡፡ ያም ሆኖ እ.ኤ.አ በጥር 3 ቀን 1868 የሾገን አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ተገለበጠ፡፡ ሾገንን የገለበጡት ሕዝቡን ለማረጋጋት ብዙ ጥረት አደረጉ፡፡
እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነበር “የሜጂ መመለስ ወይንም የሜጂ ዘመን” እየተባለ የሚታወቀው አዲስ ሥርዓት የጀመረው፡፡ የሜጂ መሪዎች መላዋን ጃፓን ከተቆጣጠሩ በኋላ ሾገን ራሱ መሸነፉን አምኖ ቢቀበልም ብዙዎቹ ደጋፊዎች ሳይቀበሉ በመቅረታቸው የእርስ በርስ ጦርነት መነሳቱ አልቀረም፡፡ በመጨረሻም የሜጂ ኃይሎች በማሸነፋቸው የማጂ አዲስ ዕቅድ ይፋ ሆነ፡፡ የሜጂ መሪዎች ዋና ተግባር “አዋራጅና ያላቻ የተባለው ውል” እንዲስተካከል ከምዕራባውያን ጋር የአቻ ውል እንዲፈረም ሌት ተቀን መሥራት ነበር፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም ጃፓን “አረመኔ ፣ ኋላቀር ፣ “የበታች” እያለች ከምታንቋሸሻቸው ምዕራባውያን ማንኛውንም ዕውቀት ወደ ጃፓን ማስገባት፣ ከጃፓን ባህል ጋር ማስተሳሰር በመጨረሻም ከምዕራባውያን ሥልጣኔ፤ ዕውቀት ቴከኖሎጂ ልቆ መገኘት ነበር፡፡ በዚም መሠረት ከእንግሊዝ ፤ ጀርመን ፤ ፈረንሳይ እና ከአሜሪካ ኩረጃ ተጀመረ፡፡ ለምሳሌ ከእንግሊዝ የጦር መርከብና የኒቪ ሥርዓትን ፤ የጀርመን የጦር አደረጃጀትንና ሥልጠናን ልቅም አድርገው ቀዱ፡፡
ሌላው ቀርቶ እ.ኤ.አ በ1870 በፈረንሳይና በፕሩሲያ መካከል ጦርነት ሲቀሰቀስ ጃፓኖች አውሮፓውያን እንዴት እንደሚዋጉ ለማየት “ታዛቢ” ልከው ነበር፡ በመጨረሻም ምዕራባውያንን ልቅም አድርገው የሚያውቁ፣ እዛ የተማሩ የሜጂ ዘመን መሪዎች ለመሆን ችለዋል፡፡
ብዙ ቀውስ ብዙ ነውጥ፤ ግራመጋባትና መንገራገጭ ቢፈጠርም የሜጂ መሪዎች በብልሃት፤ ጦርነትን በማስቀረትና ሕዝቡን ለማሳመን በመጣር ጃፓንን እንደገና ፈጠሯት፡ ለውጡ መላውን ጃፓን ከእግር እስከራሷ ነካክቷታል ማለት ይቻላል፡፡
በፖለቲካ ሥርዓት ( ነባሩ የጃፓን የፖለቲካ ባህል ተሻሸሏል)፣ በኢኮኖሚ ፣ በትምህርት የንጉሰ ነገስቱ ሥልጣንና ተግባር የመሬት ሥርዓቱ ፤ የውጭ ፖሊሲ አሠራር ፤ ርዕዮተ ዓለም ፤ ሕግ ፤ የጦር ሠራዊቱ ሥርዓት አያያዝ፣ የማህበረሰቡ መስተጋብር ፣ ቴክኖሎጂው የፀጉር አሠራርና ተዘርዝሮ የማያልቅ የማህበረሰብ ለውጥ በሜጂ ዘመን ተከስቷል፡፡ ፡፡ በጃፓን እያንዳንዱ ባለርስት የራሱ ታጣቂ ነበረው፡፡ እነዚህ ታጣቂዎች ሳምራዮች ይባላሉ፡፡ ሳምራዮች ከምዕራባውያን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ፊት ቆመው መዋጋት እንደማይችሉ በመታወቁ ከዚህም ባሻገር ለሜጂ መሪዎች አደጋ ስለሆኑ ባለጐራዴዎቹ ሳምራዮች ጐራዴ እንዳይታጠቁ፤ በየሰፈራቸው እንደፖሊስ ቀጪና ሕግ አስከባሪ መሆናቸውን እንዲያቆሙ ታዘዙ፡፡ ሳምራዮች በሕግ ፈረሱ፡፡ ለዘመናት የተንሰራፋው የፊውዳል ሥርዓት ፈርሶ የመሬት ከበርቴዎች አስተዳዳሪዎች ሆኑ፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ እንደምዕራባውያን ሆነ፡፡በምዕራባውያን ዘንድ እንደእኩል ለመቆጠርና ክብርና ሞገስን ለማግኘት የሜጂ መሪዎች የሚቻላቸውን ሁሉ አደረጉ፡፡ አሰቃቂው የጃፓን ንቶርቸር ከማስቀረት ጀምሮ የሞት ቅጣትን አስከ መሰረዝ ደረሱ፡፡ የወንጀል፤ የንግድና የፍታብሔር ሕጋቸውን ከምዕራባውያን ሕግ ጋር እንዲስማማ አደረጉ፡፡ እ.አ.አ በ1872 በጃፓኖች የመጀመሪያውን ብሔራዊ የፖስታ አገልግሎት አስጀመሩ፡፡ የስልክ መሥመር ዝርጋታ፤ ብሔራዊ ባንክ፤ የመንገድ መብራቶች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በሚቀጥሉት ዓመታት በስፋት ተዘረጉ፡፡
ጃፓን የፖለቲካ ባህሏን ለመቀየር የወሰነችው ኋላቀር” “አረመኔ” እያለች የምትንቃቸው ምዕራባውያን ከሷ የተሻሉ እንደውም እጅጉን የበለጡ መሆናቸውን ስታረጋግጥ ከዛም አልፎ ጃፓኖች ” የሚያዋርድና ያላቻ የሆነ ውል ተገደው እንዲፈርሙ ከተደረጉ በኋላ ነበር፡፡
ጃፓኖች የፖለቲካ ባህላቸውን፣ አስተሳሰባቸውን ፣ የሲቪል ሕግ፤ ሕገ መንግስታቸውን ፣ የትምህርት ሥርዓታቸውን፣ ወታደራዊ አደረጃጀታቸውን ሌላው ቀርቶ አለባበባቸውን ቀይረዋል፡፡ ይሁንና የጀርመን፣ የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝ የደች የትምህርት ሥርዓትን ወሰዱ እንጂ ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው በፈረንሳይኛ፣ ወይንም በእንግሊዝኛ አለበለዚያ በጀርመንኛ አልነበረም፡፡ የራሳቸውን የጃፓን ቋንቋ እንደያዙ ዘልቀዋል፡፡ ለምሳሌ ከእንግሊዝ የጦር መርከብ በውድ ገዝተው መርከቡን እንዴት እንደተሠራ አጥንተው የራሳቸውን የጦር መርከብ ሰሩ እንጂ ዕድሜ ልካቸውን የሌላ ሀገር የጦር መርከብ ሲገዙ አልኖሩም፡፡ ለሺህ ዓመታት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን የጐራዴ ታጣቂ የሳሞራይ ባህል ጃፓንን ከባዕድ ወረራ እንደማይጠብቅ፤ ከምዕራባውያን እጅግ ዘመናዊ የጦር ስልትና የጦር መሳሪያ ጋር የሰማይና የመሬት መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ባለጎራዴው ሳሞራይ ባህል፣ አስተሳሰብና ልማድ በአንድ ምሽት አዋጅ እንዲቆም አድርገዋል፡፡ እንደዚህ ያሉ ስር የሰደዱ የሺህ ዓመታት የቆዩ፤ የማይጠቅሙ ልማዶች፤ ወጐች ባህሎችና አስተሳሰቦች ማህበረሰቡን ወደ ተሻለ ሕይወት፤ ወደ ልማት፤ ወደ ዕድገት፤ ወደ ሥልጣኔና በጊዜው የሳይንስና ቴከኖሎጂ ማማ ላይ ማውጣት የማይችሉ ማህበረሰብን ከድህነት ከመሐይምነትና ከድንቁርና የማያላቅቁ ከሆነ መቀየራቸው መሻራቸውና መደምሰሳቸው ችግሩ ምኑ ላይ ነው? ጃፓን የጐራዴ ታጣቂውን የሳሞራይ ባህል ሙጥኝ ብትል ኖሮ ይሄኔ የምናውቃት ዓይነትን ጃፓን ባላገኘን ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ኋላቀር የፖለቲካ ባህሎች ባንቀልባ ተሸከሞ እሹሩሩ ማለት በሽታን፤ ኋላቀርነትን፤ ድንቁርናን፤ ድህነትንና ረሃብን በአንቀልባ ተሸክሞ እሹሩሩ እንደማለት ይቆጠራል፡፡
እ.ኤ.አ በመጋቢት በ1868 የሜጃ ዘመን ወይንም የጃፓን ማንሰራራት እንደገና ወደገናናነቷ መመለስን የጠነሰሱት ባላባቶች ሳትሰማ ይባሉ ነበር፡፡ እነዚህ ባላባቶች መሬታቸውን ለጃፓን ሕዝብና ንጉሠነገስት በማስረከብ ለጃፓን ልሒቃን አርአያ ሆነው ነበር፡፡ በመቀጠልም ሌሎች በማግባባትና በጃፓን ለሺህ ዓመታት የተንሰራፋውን ፊውዳሊዝም በሦስት ዓመታት ለመገርሰስ ችለው ነበር፡፡ የፖለቲካ ባህል ምን ያህል ስር የሰደደ ቢሆን ማህበረሰቡ እስከነቃ ድረስ ባጭር ጊዜ መቀየር እንደሚቻል በጃፓን በሜጂ ዘመን የተፈጸመው የሳሞራይ እና የፊውዳን ሥርዓት መቀየር ማሳያ ነው፡፡
ኩራትን ዋጥ አድርጎ ለበለጠ፤ ለተሻለ፣ ማህበረሰብን ከመከራ፣ እልቂት ከውድመት፣ ከዝንተ ዓለም ድህነትና ድንቁርና ለማውጣት መደራደር፣ ዝቅ ማለት፤ ሥልጣኔና ዕድገትን ፣ ቴከኖሎጂን ሳይንስን፤ የተሻለ አኗኗርን ሰላምና ብልፅግናን ለማስቀደም መደራደር፤ የማንፈልገውን ፤ አዋርዶናል ብለን የምንገምተው ውል እንኳን በመቀበል ማህበረሰብን ማሻገር እንደሚቻል ይህ የተመጠነ የጃፓን ታሪክ የሚያስገነዝበን ይመስለኛል፡፡ የማጂ ዘመን ብዙ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን ለአሁኑ ሁሉንም ነገር ለድርድር ክፍት ማድረግ፤ አንድ ነገር ላይ ድርቅ ከማለት ፣ከእልህና ከጉራ ተላቀን በመነጋገር፤ በመወያየት በመ ራደር፣ በብልሀትና በሥልጣኔ ወደ ተሻለ ፤ ወደ በለጠ ማደግ መመንደግ እንደምንችል የገለጸ ይመስለኛል፡፡
የቺሊ የፖለቲካ ባህል መቀየር
እ.ኤ.አ ከ1973 ጀምሮ ከ17 ዓመታት በላይ በሥልጣን የቆየው የወታደራዊው መሪ አውግስቶ ፒኖሼን ቺሊን አንቀጥቅጦ ነበር የገዛው፡፡ ገና ስልጣን እንደተቆጣጠረ ‘’የአንድነት ፓርቲ’’ እየተባለ የሚታወቀውን ገዥ ፓርቲ አባላት፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፤ ምሁራንና ባጠቃላይ ኮሙዩኒስት ሳይሆኑ አይቀሩም የተባሉ በሙሉ መሳደድ ጀመሩ፡፡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የቀድሞ መንግስት አባላት ናችሁ ወይንም የቀድሞው የገዥ ፓርቲ ትደግፋላችሁ በማለት በግፍ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ፔኖሼ በቺሊም ሆነ በዓለም ላይ የሚታወቀው በፈጸመው ጭፍጨፋና ግፍ ነው፡፡ ይህም ሆኖ “በቃ’’ ወይንም” ‘’ኖ’’ በተባለ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የታጀበው እ.ኤ.አ 1988 በተካሄደው ምርጫ ፔኖሺ ባልጠበቀው ሁኔታ 42 ከመቶ በማግኘት ለመሸነፍ በቃ፡፡ ይሁንና የፔኖሺ ተቃዋሚዎች ቢያሸንፉም መንግስት ለመመሥረት ችግር ተፈጠረ፡፡ “በቃ’’ የተባለውን የሕዝባዊ እምቢተኝነት ያስተባበሩ 17 የተለያዩ ቡድኖች ለቺሊ ይበጃል ፤ ይጠቅማል ያሉት 17 የተለያየ ራዕይና ፕሮግራም ስለነበር አሁንም ፒኖሺ የበላይነት ነበረው፡፡ እነዚህ አስራ ሰባት ቡድኖች ከፒኖሺ ጋር መደራደር ነበረባቸው፡፡ በዚህ ድርድር በቀድሞ ሥርዓት ብዙ ሰው የጨፈጨፉ፤ በሕግ ያልተዳኙ ተመልሰው ወደ መንግስት መጡ፡፡ ምንም እንኳ የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን ቢነፈግም ፔኖሺ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የዕድሜ ልክ የፓርላማ አባል፤ የተወሰኑ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ዳኞች ሿሚ ፤ እና ሌሎች ሥልጣኖችን ለምሳሌ 10 በመቶ የሚሆነው የቺሊ የመዳብ ማዕድን ሽያጭ ለወታደሩ እንዲበጀት ፔኖሽ ጠይቆ ተፈቅዷል፡፡
እዚህ ላይ ትልቁ ነገር በ”በቃ የምርጫ ቅስቀሳ ወደ ሥልጣን የመጡት ዲሞክራቶች 42 በመቶ የሕዝብ ድጋፍ ያገኘውን የቀድሞውን የወታደራዊ ጁንታ ልክ ፔኖሺ እንዳደረገው ጠራርጐ በማሠርና በመግደል ቢበቀሉ ኖሮ ቺሊ ወደ ሌላ የእርስ በርስ ጦርነት ትገባ ነበር፡፡ ይሁንና እነዚህ አዲስ የፖለቲካ መሪዎች አርቀው በማሰብ ጦርነትን ለማስቀረት፣ ቺሊን ወደፊት ለማራመድ ችለዋል፡፡ እነዚያ የቺሊ ልሒቃን ከጨፍጫፊ፣ ከቀድሞ ወታደራዊ አምባገነን ጋር አብረው ለመሥራት የወሰኑት ትልቁን ሥዕል በማየትና ሀገራቸውን ከግጭት አዙሪት ለማላቀቅ አርቆ ማስተዋልና ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ በመወሰናቸው ነው፡፡ ፔኖሺ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ ጨፍጫፊ ነው፡፡ ይህ ሐቅ ነው፡፡ ይህንን ዕውነት ይዞ ጨፍጫፊውን መጨፍጨፍና መበቀል ወደሌላ የጭፍጨፋ አዙሪት እንደሚወስድ ከስሜታዊነት፤ ከግልፍተኛነትና ከደቦ ፍርድ ተቆጥበው ሀገራቸውን በማሻገር ቺሊ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ አበቁ፡፡ ይህ ተግባራቸው የቺሊን እጣ ፈንታ ወሰነ፡፡ ቺሊ ወደ እርስ በርስ ጦርነት፤ ወደ ግጭት፤ ወደ እልቂት እንዳታመራ በማድረግ የቺሊን የልሒቃን የፖለቲካ ባህል አስተካከሉ፡፡ የፖለቲካ ባህላቸው ቀየሩ፡፡
ወደ ሀገራችን ስንመለስ የደርግ አገዛዝ የኃይለሥላሴን ሥርዓት እንዳለ ከመገርሰስ ልክ እንደቺሊ ሁሉ አብሮ ቢሠራ ኖሮ የት በደረስን ነበር፡፡ የፖለቲካ ባህላችንም በታረቀ ነበር፡፡ ልክ እንደቺሊ ሁሉ የሕወሀት/ኢሕአዴግ/ መንግስት ደርግን “ሰው በላ” መንግስት እያለ ስንት ዘመን የተሻገረን የኢትዮጵያ ሠራዊት ባያፈርስ፣ አሰብን ለኤርትራ አሳልፎ ባይሰጥ ፣ ከደርግ ጋር አንድ ዓይነት መግባባት ቢፈጥር ኖሮ የግጭት አዙሪት የፖለቲካ ባህላችን በታከመ ነበር፡፡ አሁን ስላለፈው እያነሳሁ ለመቆጨት ሳይሆን ይህንን ጽሑፍ እያሰናዳሁ ባለሁበት ጊዜም ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ በመሆናችን ዞር ብለን እንድናይና የተሻለ አቅጣጫ እንድንከተል ለማመላከት ነው፡፡ የተበላሸ የፖለቲካ ባህላችንን ማንም መጥቶ አያቃናልንም፡፡ ያበላሸነውም እኛ ነን፡፡ ማስተካከል የምንችለውም እኛው ነን፡፡ የቺሊና የጃፓን የፖለቲካ ባህል የማቃናት ታሪካዊ ልምድ በእጃችን አለ፡፡ የመንግስት ሥልጣን የያዘውም፤ የመንግስት ሥልጣን የሚፈልጉትም በመቻቻልና በሰጥቶ መቀበል ሀገርን የማስቀጠል ኃላፊነት አለባቸው፡፡
በሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ፣ ተግባራዊ ተደርጐ የማህበረሰብ ለውጥ፣ ዕድገት፤ ሰላምና መሻሻል ያመጣን ሃሳብ፣ በተግባር ተሞክሮ ከሀገር ጋር አግባብቶ ፣ አሰላስሎ፣ አስማምቶ ተግባራዊ ማድረግ የተለመደ የዓለም ሕዝቦች ታሪክ ነው፡፡ በሌላ ሀገር ተሞክሮ ውጤታማ የሆነ አሠራር እያለ እኛ እንደ አዲስ ሌላ ዘዴ ለመፍጠር መቶ ዓመት መጠበቅ የለብንም፡፡ ሌሎች ጠፈር ለመምጠቅ የቻሉበት አሠራር አቅጣጫና ምርምር እያለ እኛ በዛ ላይ ተመሥርተን የተሻለ ፤ የበለጠ ከማድረግ ይልቅ እንደ አዲስ በራሳችን መንገድ ወደ ጠፈር መምጠቅ አለብን ማለት ጊዜያችንንና ሁበታችንን መጨረስ ካልሆነ በስተቀር ብዙ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ሀገር ወይንም መንግስት ከሌላ ሳይዋስ ፣ ከሌላ ሳይቀዳ ከሌላ ሳይማር በራሱ ብቻ የትም የደረሰ ሀገርም ሆነ መንግስት አላስታውስም፡፡ ሁላችንም የምንኖረው በአንድ ፕላኔት ነው፡፡ በተለያየ ምክንያት አንዱ ሀገር ሌላውን ቢያከብርም ቢንቅም ሁላችንም ሁለት እግር ፤ ሁለት እጅ፣ የሚያስብ ጭንቅላት ያለን ፍጡራን ነን፡፡ መልካችንና የቆዳ ቀለማችን ቢለያዩም ሁለመናችን ተመሳሳይ ነው፡፡ ሌላ ሀገር ጠግቦ በልቶ በሰላም ማደር ከቻለ የኛም ሀገር ይህንን ከማድረግ የሚያግደው ነገር የለም፡፡ ሌላ ሀገር በሥልጣኔና በዕድገት ጐዳና ከተራመደ ሀገራችንም ይህንን ማድረግ ትችላለች፡፡ ሌላው ሀገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ከተራቀቀ እኛም ይህንን ለማድረግ ሰው ሆነን ተፈጥረናል፡፡ በሀገራችንና በሌሎቹ ሀገራት መካከል ሊኖሩ የቻሉ ልዩነቶችን በመተንተን እነሱ ያላቸው እኛ የሌለን፤ እኛ ያለን እነሱ የሌላቸው፣ እኛ የማናደርገው እነሱ የሚያደርጉት እያልን ልዩነቶቻችንና አንድነታችንን አጥንተን መጓዝ የግድ ነው፡፡ ሠልጥነዋል፤ አድገዋል፤ መጥቀዋል፤ ተሻሽለዋል የሚባሉ ሀገሮችን መልካም ተሞከሮ ወደ ሀገራችን በማምጣት ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ተግባራዊ በማድረግ እኛም እንደነሱ ለማደግ፣ ለመሠልጠን ፤ ለመምጠቅ መሥራታችን ተገቢና ትክክለኛ አቅጣጫ ይመስለኛል፡፡ የዓለም የዕድገት ታሪክም ይህንኑ ያሳያል።
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ስለመቀየር
ስም ማጥፋት በሥልጣን ላይ ያለን እንደዳቢሎስ ማጠልሸት በኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ልጅ እያሱን እናስወግድ እንጂ ኢትዮጵያን የማር የወተት ሀገር እናደርጋለን በማለት ሕጋዊ ወራሽ የነበሩትን ልጅ እያሱን ከሥልጣን ለማስወገድ ያልቀቧቸው ጥላሸት፣ ያልተነገረ ውሸት አልነበረም፡፡ ቀጠሎም ደርግ እንዲሁ በኃይለ ሥላሴ ላይ ያልለጠፈው ቆሻሻ : ያላለው ከፉ ነገር አልነበረም፡፡ “ይህ የጃጃ ሥርዓት ይወረድ እንጂ ኢትዮጵያ ህብረተሰባዊ ሥርዓት ዘርግታ በሰላም፤ በሀሴት በዕድገት ጐዳና እናተማታለን በማለት የሕዝቡ ችግር የሀገሪቱ የዘመናት ጉስቁልና ዋና ችግር ንጉሰ ነገስቱ ናቸው በማለት የንጉሱን ሥርዓት ለመንቀል ስም ማጥፋትና የማጠልሸት ዘመቻ ተጠናክሮ ንጉሰ ነገስቱ ተነቀሉ፡፡ ኢትዮጵያ በሌላት ገንዘብ ያስተማረቻቸው ውድ ልጆች በግፍ ተገደሉ፡፡ የተነገረው የማር፤ የወተት፣ የሰላም የወንድማማችነትና የዕድገት ዘመን አልመጣም፡፡ በምትኩ ሞት፤ ሥቃይ ፤ ረሃብ፣ ስደት፤ መከራ፣ ጉስቁልና ኋላቀርነት መጣ፡፡ ይህ አዙሪት አሁንም ቀጥሏል፡፡ ተምረናል፤ አውቀናል፤ ፀሐፊ ነን፤ ተመራምረናል የሚሉ የሚሰብኩት፤ የሚተነፍሱት፤ የሚጽፉት የሚያልሙት ጥላቻ፣ ተንኮል፣ ብጥብጥ፤ ብቻ ሆኗል፡፡ መለስ ብለን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ብናይ ተደጋግሞ፤ ተደጋግሞ የሚታይ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ልሒቃን ባህል ይህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በዚሁ አዙሪት መዝቀጧ ነው፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና ፕሮፌሰር መስፍን ” መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ ” በሚለው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ልሒቃን መንቀል እንደሚችሉና ማሳደግ፤ ማለምለም፤ መንከባከብ፣ ማረምና ማስተካከል እንደማይችሉ ፍንትው አድርገው አሳይተዋል፡፡ አሁን ልብ ልንለው የሚገባው ለመንቀል ሌት ተቀን የሚሠሩ ሰዎች ዋናው ዓላማቸው በተነቀለው ቦታ ራሳቸውን ለመተካት እንጂ በኢትዮጵያ ያለው ድህነት፣ ችግር፣ ርሀብ፣ ጠኔ፤ ኋላቀርነት በሽታና ፡ ድንቁርና ለማጥፋት፣ ለመቅረፍ አይደለም፡፡ መንግስት ሲነቀል ምን ይፈጠራል? የሚለው በፍጹም አያሳስባቸውም፡፡ “አሁን ያለው መንግስት ይጥፋልን እኛ በቦታው እንተካ ነው” ስንት መንግስት በኢትዮጵያ ተነቀለ፡፡ የተተካው መንግስት ድህነትን፣ ድንቁርናን አልቀነሰም፡፡ ይልቁንስ በኢትዮጵያ ያለውን ስቃይ ተባብሶ ነው የታየው፡፡ አሁንም ይህ የፖለቲካ ደዌ ፤ይህ የፖለቲካ ባህል በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ከዚህ አዙሪት የምንላቀቀው መቼ ነው?
ቺሊንና ጃፓንን እንደምሳሌ አነሳሁ እንጂ በዓለም ላይ ብዙ ምሳሌዎች አሉ፡፡ ችግራችን የምሳሌ ማጣት አይመስለኝም፡፡ ችግራችን በቃን ድህነት፣ በቃን ኋላቀርነት ፣ በቃን ጉስቁልና፣ በቃን ስደት ፤ በቃን ረሃብ፤ በቃን መጨፋጨፍ፣ በቃን መተላለቅ፣ በቃን ውድመት ብለን በአርቆ አስተዋይነት፤ በብልሀት፤ በቁርጠኝነት ለሰላም፣ ለንግግር፣ ለውይይት፤ ለሰጥቶ መቀበል፤ትዕቢታችንና ፤ ጉራችንን፤ ስሜታዊ መሆናችንን፤ እኔ ያልኩት ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ ማለታችንን፤ ይህ ከሚሆን ብሞት ይሻላል ማለታችንን፤ ይህማ ውርደት ነው የሚል ጠመንጃ ነቅናቂ የፖለቲካ ባህላችንን በመተው ወደትከክለኛ አቅጣጫ ለመሄድ ታሪክ እንደገና አጃችን ላይ ወድቋል፡፡
ማጠቃለያ
ጃርድ ዳይመንድ የተባሉ ፕሮፌሰር የስድስት ሀገራት ቀውስና ከቀውስ የወጡበትን ዘዴ ካጠኑ በኋላ እ.ኤ.አ በ2019″ መንግስታት ግርግርን ቀውስንና ለውጥን እንዴት መቋቋም ይችላሉ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ ቀውስን ለመቋቋም አሥራ ሁለት ነጥቦችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ጠቃሚ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ፕሮፌሰር ዳይመንድ እነዚህ ነጥቦች ለግለሰብ ቀውስ ጭምር ሊረዱ እንደሚችሉ ከራሳቸው የግል ተሞክሮ በመነሳት ያብራራሉ፡፡ ቀውስ ግርግርና ነውጥ ያለማቋረጥ ሲፈጠር፡ አንድ ማህበረሰብ ቁልቁል ሲወርድ፣ ዕድገትና ሰላም ሲጠፋ ረሃብና ቸነፈር የአንድ ሀገር መገለጫ ሲሆን የዛን ሀገር የፖለቲካ ባህል መፈተሽና ኋላቀርና ጊዜውን ያልዋጀ የሆነውን መቀየር የግድ ይላል። በለውጥ ጊዜ ደግሞ የሚከተሉትን ነጥቦች ማስተዋል ያሻል፡፡
1ኛ. በቀውስ ውስጥ መሆናችንን አምኖ መቀበል
2ኛ. አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብንና ይህም የኛ ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ
3ኛ. መቀየር ያለበትን በትከከል በዝርዝር ማወቅ፡፡ ለምሳሌ ጃፓኖች የሳሞራይ ባህልንና ፊውዳሊዝም ነቅሰው እንዳወጡት ማለት ነው፡፡
4ኛ. ከሌሎች የቁስም ሆነ የሞራል ድጋፍ ለመቀበል ዝግጁ መሆን፡፡ ቀውሱን የሚፈታ፣ ግርግሩን የሚያረግብ ጠቃሚ እርዳታ መሻት
5ኛ. ሌሎች ተመሳሳይ ችግር፤ ቀውስ ሲያጋጥማቸው እንዴት እንደተወጡት በማጥናት፣ በማየትና በመማር፤ እንደምሳሌ፤ እንደአርአያ መከተል
6ኛ. በራስ መተማመንን ለራስ ያለ ግምትን ከፍ ማድረግ
7ኛ. በሐቅና በትክክል የራስን ድክመትና ጥንካሬ መገምገም
8ኛ. ከዚህ በፊት ቀውስ፤ ግርግር ሲያጋጥም የነበረንን ልምድ መለስ ብሎ ማየት መቃኘት፣
9ኛ. ትዕግስት፣ አለመቸኮል ፤አለመጣደፍ
10ኛ. ይሄ ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ አለማለት፡፡ መተጣጠፍ ፤ ድርቅ አለማለት፡፡ የተለያዩ አማራጮችን ለመቀበል ሆደሰፊና ክፍት መሆን
11ኛ. ይህም ሆኖ የእኔ ማንነት ይህ ነው፡፡ ይህ እኔነቴን የሚገልጽ ነው፡፡ እኔ ማለት ይህ ነኝ ብሎ ዋናውን የማንነት መሠረት መጣል
12ኛ. ችግሮችና መሰናክሎች ሲያጋጥም ፀንቶ መቆም፡፡ የተነሳንበትን ቀውስን፣ ነውጥን፤ ችግርን የመፍታት ትልቁን ሥዕል አለመዘንጋት፡ ሁሌም ዋናው ትኩረታችን የተነሳንበት ዓላማ ላይ ፤ ቀውሱን መፍታት ላይ እንዲያተኩር ማድረግ፡፡
መወያየት፤በስከነት መነጋገርን ፤ መተማመንን፤ መደራደርንና ሰጥቶ መቀበልን የፖለቲካ ባህላችን በማድረግ መምህራን በተለይ የአንደኛ ደረጃ መምህራን፤ ባጠቃላይ በሁሉም ደረጃ ያሉ መምህራን፤ ወላጆች፤ የሃይማኖት መሪዎች ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡
የትምህርት ሚኒስትርም እንዲህ ያሉ ታላላቅ እሴቶችን በየትምህርቱ ውስጥ፤ በሥርዓተ ትምህርቱ አስገብቶ በጥብቅ ክትትል ሊፈጽሙ የሚገባቸው ዋና ቁም ነገሮች ናቸው፡፡ የትምህርት ተቋማት ባጠቃላይ የመወያየት፤ የመደራደርና ሰጥቶ የመቀበል፤ የመከባበርና የሌላውን ሰው ሃሳብ የማዳመጥ፤ የማክበር ፅንሰ ሃሳብ ማስረጽ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጋዜጠኞችና ማህበራዊ አንቂዎች በዚህ ጉዳይ በስፋትና በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ ሊሰሩ ይገባል፡ ምንም እንኳ ያደግንበት ባይሆን ም ፖለቲከኞቻችንና ኃላፊዎች የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ በየፊናቸው በመነጋገር በመወያየት ችግሮችን የመፍታት ባህል ማዳበርና ማስረፅ ያስፈልጋል፡፡ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ልክ እንደ አንድ ታላቅ ስኬት በየትምህርቱ እየገባ ልንነጋገርበት ልንወያይበት ይገባል፡፡ ሕፃናትንና ታዳጊዎችን የመወያየት፤ የመነጋገር የሰጥቶ መቀበልና የሌላውን ሃሳብ ማክበር ባህል እየተማሩ፤ እንዲያጉ በማድረግ ፤ አሁን በፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉ፤ እየተሳተፉ ያሉ ደግሞ በታላቅ ትዕግስትና በጥልቅ አመከንዮ እየተመሩ በመደራደር በሰጥቶ መቀበል በመነጋገር ችግሮቻቸውን እየፈቱ ወደፊት መራመድ ይኖርብናል፡፡ ሌላው ዓለም በመነጋገርና በመወያየት ከኛ የባሰ ከኛ የማይተናነስ የፖለቲካ ችግሮቹን ከፈታ እኛ ምን ያቅተናል? እነሱም የሰው ልጆች እኛም የሰው ልጆች ለምን ለመሳደብ፤ ለጥፋትና ለጥላቻ ፤ ለመግደል እንቸኩላለን?
ዶ/ር ሰለሞን ኃይለማርያም በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ የልሒቃን የፖለቲካ ባህል ላይ ጥናት ያደረገ ሲሆን በዚህ ጽሑፍ
ላይ አስተያየት ካላችሁ [email protected] ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
የኢትዮጵያ ልሒቃን የፖለቲካ ባህል ከእልቂትና ከውድመት አዙሪት እንዴት እንውጣ ?