መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
“If you cannot find a good companion to walk with, walk alone, like an elephant roaming the jungle. It is better to be alone than to be with those who will hinder your progress . “
Gautama Buddha
“ የዓለማህ ተባባሪ ወይም አቻ የሆነ ጥሩ ተጣማሪ ተጓዥ ካላገኘህ ፣ ብቻህን መጓዝ ምረጥ ። ልክ ጫካውን እያተረማመሰ ወደ ግቡ እንደሚጓዝ ዝሆን ። ከጉዞህ ከሚያደናቅፍህ ጓደኛ ይልቅ ዝሆናዊ ጉዞን ብትመርጥ ይበጅሃል ። “ የጥቅሱ መጨረሻ ።
ከዚህ ጥቅስ የምንማረው ፣ በህይወት መንገድ ላይ አስተዋይ ፣ ብልህና ጥበበኛ ሰው የሚያጋጥመውን መሰናክል በስኬት ማጠናቀቅ ወይም መሰናክሉን ማለፍ የሚችለው ከብልህ ባልንጀራ ጋር በመሆን ፣ የሚያጋጥመውን ችግር በእኩል ስሜት ና በአንድ ልብ ሆኖ በማሸነፍ በመጓዝ እንጂ ከራዕይ አልባ ጓደኛ ጋር ያለ ዓላማ በደመነፍስ በመጎዝ እንዳልሆነ ነው ።
ሁሉንም የህይወት ፈተናዎቾ በየፈርጁ በመፈተሽ በዘዴ ና በመላ በድል ለመወጣት የሚቻለው በህይወት መንገድ ዓላማ ካለው ሰው ጋር ሲጣመሩ እንጂ በደመነፍስ በመጓዝ አይደለም ። በደመነፍስ ፣ በዘፈቀደ እና በምንግዴ በጣምራ መጓዝ ለውድቀት ይዳርጋል ።
ሰው ሁሉ በህይወት ዘመኑ መጀመሪያ የሚመርጠው ጓደኛ ደመነፍሳዊ የህይወት ጉዟን አራማጅ ከሆነ አጥፊው ይሆናል ። እናም ነፍስ አውቆ ብቻውን በህይወት ጎዳና መጓዝ ሲጀምር መልካም ቅን ፣ አርቆ አሳቢ ፣ ሃይማኖተኛ እና ከማንኛውም ሱስ የፀዳ ጎደኛ ካለ መረጠ ወይም ብቻውን በንፁህ ህሊና ፈጣሪ በመረጠለት ጎዳና መጓዝ ካልጀመረ በስተቀር ከድሉ ይልቅ ሽንፈቱ ፤ ከስኬቱ ይልቅ ውድቀቱ የጎላ ይሆናል ።
ሰው በህይወት መንገድ ሲጎዝ በተለያየ ምክንያት ውድቀት ቢያጋጥመውም ትልቁ የውድቀት ሰበብ ወይም ምክንያት የሚከሰተው ፣ በፍፁም ቁርጠኝነት ኑሮውን ለመለወጥ በትክክለኛው መንገድ ሲጎዝ ሣለ ፣ በመንገዱ ሞኝ ፣ ጅልና ጅላፎ ሰው ፣ አብሮት እንዲጎዝ ሲፈቅድ ነው ።
ለህይወት ግድ የሌላቸው እና ለገዛ ነፍስያቸው የማይጠነቀቁ ሰዎች በደመነፈስ የሚኖሩ ህልም አልባ በመሆናቸው “ ከአህያ ጋር የዋለች በቅሎ …ተምራ እንደምትመጣ “ ሁሉ መጥፎ ምግባርን አለማምደው ለውድቀት ሊዳርጉን ይችላሉ ። እናም በእነዚህ ራዕይ አልባ ሰዎች ሰበብ ፣ ቀና ልብን ይዞ በህይወት ጓዳና የሚያጋጥመውን ሁሉ በትግል ለመወጣት ቆርጦ የተነሳ ሰው ፣ ጠማማ ባህሪን ይወርስና በህይወት እና በኑሮው ተስፋ የመቁረጥ ባህሪን ቀስ በቀስ በማዳበር ሙሉ ለሙሉ ከሥኬት ጎዳና ወጥቶ በውድቀት ጎዳና ላይ ሊታይ ይችላል ።
የማንኛውም ሰው ቀና ልቦና አንዴ ከተጣመመ ፣ ድርጊቱ ሁሉ ከሞራል ውጪ ይሆናል ። ሰው ሁሉ በሂደት ነው ሞራል አልባ እና ህሊና ቢስ የሚሆነው ። እየተጣመመ የሚመጣው ። በመንገዱ ላይ ከሚያገኛቸው ፣ ከቤተሰቡ ፣ ከጎረቤቱ ፣ ከማህበረሰቡ ፣ ከትምህርት ቤት እና ከማህበራዊ መድረኮች ፣ ወዘተ ። መጥፎ ምግባርን በመቅሰም ። …
ዛሬ ደግሞ መጥፎ ምግባርን መዳፋችንን በምታክለው የሞባይል ሥልክ ለመማር በምንችልበት ዘመን ላይ ደርሰናል ። በዚህ ዘመናዊ “ በየነ መረብ “ በመጠቀም ቅን ፣ በጎ፣ ታታሪ ፣ ጥበበኛ ፣ ወዘተ ። የሆኑ መኖራቸው እርግጥ ቢሆንም ፤ በተገላቢጦሹ ህሊናቸውን እና ጤናቸውን ያጡ ብዙ ሰዎች አሉ ። ሌላ ፣ ሌላውን ትተን በየነ መረብ የሚስተናገደው ፣ የቴሌግራሙ እና የቲክቶክ ቻናል ትውልዱ ካልባነነ እና መርጦ ካልተከታተለው በፍጥነት ወደ ሞት እና ወደ ውድቀት እንደሚያደርሰው እየታየ ነው ።
ዘመን እና ጊዜ ሁሉንም ነገር በበየነ መረብ በኩል እካችሁ ብሎናል ። ዕውቀትን በሙሉ በቲዎሪና በተግባር ከበየነ መረብ ማግኘት ተችሏል ። ተራ ወሬን ጨምሮ አገር ነቅናቂ ዜና በደቂቃዎች ውስጥ በሁሉም ዓለም ይዳርሳል ። የሚያነቃቁ ፣ የሚያዝናኑ ፣ የሚያስተምሩ እንዲሁም ሥድ የሚያደርጉ ቪዲዮዎችን እያማረጡ ከተለያዩ ዩቲበሮች በፈለጉት ሰዓት ማግኘት ተችሏል ።
ይኽ እውነት የሚያመለክተን ፣ የዛሬው ትውልድ ዕውቀትን የማግኘት ችግሩ በኢንተርኔት አማካይነት እንደተቃለለለት ነው ። በዚህ በጎ ተፅዕኖ የተነሳም ፣ ብልህ እና ቅን ልብ ያለው ወጣት ከሚያስተምረው አስተማሪ የበለጠ እውቀት ይዞ ክፍል ውስጥ በመገኘት መምህሩን ሊሞግተው ወይም እውቀቱን ሊያዳብርለት ይችላል ። በዚህ ረገድ ለወጣቱ ኢንተርኔት ወንዝ አሻጋሪ የዕውቀት ጓደኛው ለመሆን ችሏል ።
በተቃራኒው ደግሞ ጎታች ና ወደ አዘቅት ጣይ ዌብ ሳይቶች በሽ ፣ በሽ ናቸው ። በዚህ የሞት መንገድም በመጎዝ በገዛ እራሱ የራሱን የመቀበሪያ ጉድጎድ ቆፍሮ በቁም የተቀበረ ጥቂት አይደለም ። ስለዚህም ነው ” ከጅምሩ ቀና እና አሻጋሪ የህይወት ጎደኛ በኮበሌነትህ ምረጥ አልያም በራስህ ቅን ልቦና በእምነትህ ፀንተህ ብቻህን በመንገድህ ተጉዘህ ስኬትህን እውን አድርግ ። ” ብለን ለመመከር በዚህ ጽሑፍ የተነሳነው ።
ማንኛውም ቅን እና የዋህ ሰው ባለመው የስኬት ጎዳና ሲጎዝ በጎና ቅን ህሊና ያለው ሰው በመንገዱ ካልተቀላቀለው እና ከህልም አልባ ፣ ምንግዴ ሰው ጋር ጉዞ ከጀመረ ያሰበው ስኬት ላይ ለመድረስ ከቶም አይችልም ። ምናልባትም ያሰበው የስኬት ጉዞ ሊሰናከል ወይም ሩቅ አስቦ ቅርብ ሊያድር ይችላል ።
እንኳን የህይወት ጉዞን ይቅርና ተራ የመንገድ ጉዞን እንኳን ከጅል ሰው ጋር መጓዝ ፣ ጉዞውን እጅግ አሰልቺ ያደርገዋል ። ወይም አጭሩ መንገድ እጅግ ይረዝምበታል ። መንገዱ ጨርቅ አይሆንለትም ። ለዚህም ነው ጉተማ ” ከጅል ጋር ከመጓዝ ለብቻ መጎዝ ይመረጣል ። ” በማለት አጥብቆ የመከረው ።
የጉተማ ቡዳኸ መልዕክት ፣ በህይወትህ አጭር ጉዞ ወቅት ፣ በአንተ መንገድ ላይ የሚጓዘውን የበዛ ሰው በጥያቄዎች በመርምር እና እውቀቱ የመጠቀ ወይም የኮሰመነ መሆኑንን በመረዳት ጉዞህን አንድ ላይ ለማድረግ መወሰን ብልህነት ነው ። ዋናው ጥያቄ ” አብሮህ ለመጎዝ የተነሳው ሰው ማነው ነው ? ” በቅድሚያ ማንነቱን ማወቅ አለብህ ። እንከፍና ጅላንፎ ከሆነ ፣ የእርሱን የጉዞ አቅጣጫ ጠይቀህ በመረዳት ፣ የአንተን የጉዞ አቅጣጫ ከእርሱ በተቃራኒ እንደሆነ በማሳወቅ ከጉዞህ አቅጣጫህ ጅሉን ሰው ማራቅ ይገባሃል ። አልያም መንገድህ ሳያልቅ ” ጉዞዬን አጠናቀቅሁ ። ይኸው በቃ ደረስኩ ። ጉዞዬ ተጠናቀቀ ። ” ብለህ በዘዴ በጊዜ መለየት ከመሰናከል ያድንሃል ። ይሁን እንጂ አብሮ ለመያዝ የተቀላቀለህ ሰው ፣ ከአንተ በላይ ብልህ ሊሆን ስለሚችል ፣ ማንነቱን ለመረዳት በጥበብ የተሞሉ የህይወት ጥያቄዎችን ጠይቀው ።
ስለ ህይወት እና ሞት ፤ ሰለ ሥራ እና ሥንፍና ፤ ስለተድላና ምንዱባንነት አንስተህ ሃሳቡን ተረዳ ። ለአፍታ ብልህ ነው ወይስ ብልጣብልጥ ብለህ ፣ በህሊናህ ገምግመው ። ጥያቄህን በወጉ ከመለስ አብረኸው ተጎዝ ። እርሱ ተጨማሪ የህይወት ትምህርትን ያጎናፅፍሃልና ። ካልመለሰ ደግሞ በዘዴ ተለየውና ብቻህን ተጎዝ ።
ብቻህን በመጓዝህ እምብዛም አትጨነቅ ። በመጀመሪያ ነገር ማወቅ ያለብህ እያንዳንዳችን ወደ ምድር የመጣነው ብቻኛ ሆነን ነው ። ከእኛ ጋር የተጣመረ ሌላ ሰው የለም ። የመጣነው ብቻችንን ነው ። ምድሪቶን የምሰሰናበታትም ለየብቻ ነው ። በተራ ፣ በተራ እንቀባበራለን ። ተራ ሟቾች ለሞች እየለቀስን ።
ከአንድ መሐፀን በደቂቃዎች ልዩነት ብንወጣ እንኳን በደቂቃዎች ልዩነት በአንድ ቀን አንሞትም ። በአንድ ቀን እና በእኩል ሰዓት የመሞት አጋጣሚ ከሚሊዮን አንድ ሊሆን ይችላል ። …እናም ሰዎች ሁሉ ህልውናችን ለየብቻ ነው ። በጣምራ አይደለም ። በግለሰብ ደረጃ ነው ህይወትን የምንኖራት ። ሰዎች በባዮሎጂካል አቋማችን አንድ ግለሰብ መሆናችንን መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው ። ራሱን ፣ ግለሰብነቱን ያልተረዳ ወይም በሚገባ ያልተረዳ ከሌላ ጋር ቢደባለቅ ዜሮ አበርክቶ ነው ያለው ።
ሰው ግለሰብነቱን በመረዳት የሌሎችን ግለሰቦች ማንነት ለማወቅ በፅሞና ሊመረምራቸው እና ሊያዳምጣቸው ይገባል ። እርግጥ ነው አንድ ግለሰብ ምን ያህል አስተዋይ እንደሆነ ማወቅ የሚቻለው ግለሰቡ እንዲናገር ዕድል በመሥጠት ነው ። መቼም “ ሲቪህን አሳየኝ “ አትሉትም ። እርሱ የግለሰቡን ስብዕና እና እውቀት በትክክል አይገልፀውም ። …ያውም በእኛ አገር የተዝረከረከ የመማር ማስተማር ሂደት የተለያዩ ዲግሪዎች የባለዲግሪውን እውቀት አይመሰክሩም ። የሰው እውቀቱን ለመመስከር የሚቻለው በተግባሩ ነው ። አብረኸው ስትሰራ ወይም አገልግሎቱን ስትፈልግ ብቃቱን ትረዳለህ ። ያን ጊዜ ታደንቀዋለህ ። ያን ጊዜ ዲግሪውን እንደገዛ ትገነዘባለህ ። ወዳጄ ህይወት ስታስተሳስርህ ነው ሰውን በቅጡ የምታውቀው ።
እኛ ሰዎች ከሌሎች ፍጡራን የምንለየው በማህበራዊ ግንኙነት በመተሳሰራችን ነው ። ህይወታችን ና ኑሮአችን በማህበራዊ ኑሮ እና በተስማማንበት እና ባልተስማማንበት ህግ የተጋመደ ነው ። ሰው ከሰው ጋር ያለማህበራዊ ግንኙነትና ያለህግ በወጉ መኖር አይችልም ።
ይኽ ማለት ግን አንድ ላይ ተጣምሮ በአንድ ሥፍራ እንዲኖር ይገደዳል ማለት አይደለም ። ወይም አብሮት የሚኖረውን ለመምረጥ አይችልም ማለት አይደለም ።
አብረህ ለመኖር ኃይማኖትህ ፣ ባህልህ ፣ የአእምሮህ ግዝፈትህ ፣ የምትኖርበት አገር ሥልጣኔ እና መልካምድሩ የጎላ ሚና ይጫወታሉ ።
ምንም እንእንኳኳ በአፈጣጠሩ ሰው ከሌሎች ፍጡራን ቢለይም ፤ በፍጥረቱ እፁብና ድንቅ ቢሆንም ፣ ከሚኖርበት ህብረተሰብ በኑሮ ሂደት የቀሰመው ገንቢና አፍራሽ ትምህርት ፣ ጠቃሚና ጎጂ ባህል ና ኃይማኖት በአስተሳሰቡና በአመለካከቱ ላይ ተፅኖ ያሳድርበታል ። …
ሰው ማለት በራሱ ሙሉ የሆነ የተሟላ ማለት ቢሆንም ። ነፍሱ እስካልወጣች ጊዜ ድረስ በራስ ተነሳሽነት ያለአንዳች አሥገዳጅ አጋጣሚ ድንገት በአዲስ ድርጊት ተከስቶ ሊያስገርመን ይችላል ። ነገ ራሳችን ተመሳሳይ ድርጊት ስንፈፅም ደግሞ በተራው እርሱ ይገረማል ።
እንግዲህ ይህ ድንገቴ ድርጊትን ለመቆጣጠርና አውዳሚ እንዳይሆን ለማድረግ ፣ ሰው በተፃፈና ባልተፃፈ ህግ እንዲመራ ወይም እንዲያድር ተደርጓል ።
ያም ቢሆን ሰዎች በእርስ በእርስ ግንኙነት ጊዜ ሰው በመሆናቸው ብቻ ሥለጋራ ችግራቸው በመወያየት ጓደኝነት ሊፈጥሩ ቀስ በቀስም በአስገዳጁ የኑር ሁኔታ ላይ የጋራ መፍትሄ ለማምጣት ሊመክሩ ይችላሉ ። መምከር ብቻ ሳይሆን ድንገት አንዳች አብዮት እንዲቀጣጠል ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ።
እርግጥ ነው ፣ ከአምሳያው ጋር ተቀላቅሎ አብዮተኛ ለመሆን የሚችል ሰው እንዳለ ሁሉ ፣ ያለአንዳች ተሳትፎ ራሱን አግልሎ በመቀመጥ በጥልቅ በማሰብ ዓለምን የሚለውጥ ሃሳብ ሊያመነጭ የሚችልም ኃያል አእምሮ ያለው ግለሰብም ይኖራል ።
እንግዲህ ያንን እና ይህንን አይነቱን የግለሰብ ስብስብ ነው ፤ ” እኛ ” የምንለው ። ህዝብ የግለሰቦች ስብስብ ነው ። …
ህዝብ የግለሰብ ስብስብ ነው ። ግለሰብ ማለት የማይካፈል ማለት ነው ። የእንጊሊዘኛውን ” ኢን ዲይቪይጇልን ” ውሰዱት ። ግለሰብ ማለት አንድ ና ያው ማለት ነው ። ነገር ግን ግለሰብች በውስጣቸው የሚጋጩ አያሌ የህሊና ሙግቶች የሉባቸውም ማለት አይደለም ። ። እናም ጥሩ ሥራቸው ጎልቶ በሰዎች ዘንድ ሲታይ “ የእኔ ቲሩፋት ወይም ግኝት ነው ። “ ብለው ሊኮፈሱ ይችላሉ ። መጥፎ ሲሰሩ ደግሞ “ ሤጣን አሳሳተኝ ። “ የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም ። እጅግ ስኬተማ ሲሆኑ ራሳቸውን ሲያደንቁ እናገኛቸዋለን ። በዝቅታ ደረጃ እና በችግር ውስጥ ሲወድቁ ደግሞ በአርባ ቀን ዕድላቸው ሲያማርሩና በመተት ፣ በድግምት ፣ በጠንቆይ ሥራ ሲያመካኙ እናስተውላለን ።
እውነቱ ግን ይኽ አይደለም ። እውነቱ ነፍስ አውቀው ፣ ለአቅመ አዳምና ሄዋን ደርሰው ፣ በፍላሎታቸው ሰዓት በህይወት መንገድ ላይ ሲጎዙ የመረጡት መንገድ ለዛሬ ታላቅ ሰብዕና አደርሷቸዋል ። አልያም የመረጡት የጥፋት መንገድ ለታላቅ ውድቀት ዳርጓቸዋል ። ጉተማ ቡዳኽ እንዳለውም በፍላሎት ዘመን ከጅል ጋር ተጉዘው እስከወዲያኛው ተጃጅለውም ሊሆን ይችላል ።…
"ባልሻገር ወንዝ ባህር ያልተሰደድኩ እንዳይመስልህ
ያውም ክፉ መጥፎ ስደት : ባይተዋርነት በሃገር ቤት" ስደት በሃገር ቤት! 💔 pic.twitter.com/zLGuP4Ygbm— Phጨ (@kyisfa) February 18, 2025