አማራ እስኪነሣ የሚያየው አበሣ! – ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

February 26, 2025

አልማዝን የሚቆርጠው አልማዝ ብቻ ነው ይባላል፡፡ ከወርቅ የሚሠራ መጋዝ አልማዝን አይቆርጥም፡፡ ከብርና ከነሐስ የሚበጅ ጎራዴ አልማዝን አይሞነጭረውም፡፡ ለአልማዝ መዳኒቱ አልማዝ ብቻ ነው፡፡ “እግዜር ሲቆጣ ሽመል አይቆርጥም፤ ያደርጋል እንጂ ነገር እንዳይጥም” የሚለውንም ብሂል አንርሣ፡፡

አማራ እስካሁን ነፃ መውጣት ያልቻለው ጠላቶቹ በሸረቡበት ሤራና ለሆዳቸው ባደሩ የአማራ ልሂቃን አማካይነት የገጠመውን መሰናክል ለመበጣጠስ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ነው፡፡ ሌላ ሌላው ወደአማራ ምድር የሚጎርፍ ዕብቅ ግትልትል ሒሣቡን እያገኘ ሙትና ቁስለኛ ወይም ምርኮኛ ሲሆን አማራን እንዲገጥም በጥቅምና በከንቱ ፕሮፓጋንዳ የተያዘው አማራ የሚያደርሰው ጉዳት ግን ቀላል አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ማሰብ የሚችሉ ፋኖዎች በገዛ ወገን ላይ ጥቃት መክፈቱን ከኅሊናና ከሞራል አኳያ የሚቀበሉት አልሆነምና እንደምንሰማው በዚያ ረገድም ትልቅ መሰናክል መፈጠሩ አልቀረም፡፡ በዚያ ላይ በፋኖዎች መካከል የሚታየው አደባባይ የወጣ መከፋፈልና በአንዳንዶች የድብቅ አጀንዳ አራማጅነት የተነሣ ድሉ ሊዘገይ ችሏል፡፡ ውስብስብ ችግሮች እዚህም እዚያም ይታያሉ፡፡ ቢሆንም …

ሆኖም ቢሆን ታዲያ ነፃነታችን የማይቀር ነው ተብሎ በፉከራና በሽለላ ብቻ የሚቀር ሣይሆን በአደጋና በድንገተኛ ሞት ካልተነጠቅን በስተቀር ማናችንም የምናየው የዛሬ ከሰዓት ወይም የነገ ጧት ያህል ቅርብ ነው፡፡ አማራና አማራውያን፣ በወያኔና ልጁ ኦነግ/ኦህዲድ እንዳትሆን ሆና የተበለሻሸችውን  ኢትዮጵያ ከእግዚአብሔር በረከት ረድኤት ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስተካክሏታል – ሥራው ትልቅ ትግስትንና ጥበብን የተላበሰ አስተዋይነትን እንደሚጠይቅ ግን ግልጽ ነው፡፡ ያደርሰናል!!

ወጣት እያለሁ እንዲህ ሲባል እሰማ ነበር – የዛሬ 40 ዓመት ገደማ፡፡ “የኋላ ኋላ አንድ (ከፈሱ የተጣላ) ጨካኝ ንጉሥ ይነግሣል፡፡ ሕዝቡ ካለቀሰና ወደፈጣሪው ከተመለሰ ያ ዐረመኔ ንጉሥ በሦስት ዓመታት ይነሣል፡፡ ሕዝቡ ወደፈጣሪ ካልተመለሰና ንስሃ ካልገባ ግን እስከሰባት ዓመት ድረስ ሀገሪቱንና ዜጎችን ደም እያስነባ ይቆያል፡፡ ያኔ ሰው ይረክሳል፤ እህልና የሚበላ ነገር ሁሉ ይጠፋል፤ይወደዳል፡፡ በመጨረሻው ግን ያንን ክፉ ንጉሥ የሚተካ ደግ ንጉሥ ይመጣል፡፡” ይህ እንግዲህ ከሰማኋቸው ቀደምት ትንቢቶች አንዱ ነው፡፡ ሌሎች በርካታዎችም አሉ – የተፈጸሙም ያልተፈጸሙም፡፡ ከሁሉም ተነስቼ የምለው ነገር ቢኖር ነፃነታችን በእጅጉ ቀርቧል – ለዚህም ነው ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ብዕራቸውን ባሳረፉበት በአሁኑ ወቅት እንደመጥምቁ ዮሐንስ ከሞላ ጎደል ብቻየን እየጮሁ ያለሁት፤ ለሌላ አይደለም እየጮሁ መሆኔን ለማሳወቅ ብቻ ነው፡፡ ይህን ስል ግና የወፈፌውን የዳኛቸው አሰፋን አነጋገር ገልብጬ ከአህመድ ልጅ ይልቅ የካሤና የነጋ ወይም የወዳጆ ልጆች ይመጡልኛል ከሚል የዋህነት አይደለም፡፡ ማንም ይራኮት እግዚአብሔር ግን በመምጫ መንገዱና በፈለገው አቅጣጫ  ይመጣና ይህን ኢትዮጵያን እንደዘመነ ኖኅ በንፍር ውኃና እንደዘመነ ሎጥ በዲኝ እሳተ ገሞራ እያጠፋ ያለውን የኦሮሙማ ዘረኛ መንጋ እንደዱቄት ይበትነዋል፡፡ እንኳንስ ከመቶ ሚሊዮን የሚበልጥን ሕዝብ የደም ዕንባ እያስለቀሰ የሚገኘውን አቢይ አህመድን የመሰለ ጭራቅ ይቅርና ደጋግ የመንግሥታት መሪዎችም ከዚህች ዓለም ባልታሰበ ጊዜ ይለያሉ፡፡ ነባራዊውን እውነት ነው እየተናገርኩ ያለሁት፡፡ ደርግና ወያኔ ያላሸቁት ሞራላችንም ያገግማል፡፡ የመኖር ተስፋችንም እንዳዲስ ይለመልማል፡፡

“ከልጓም ዘር ይስባል” እንዲሉ ዳኛቸው አሰፋ የሚባል የገነት ዘውዴ ወንድም ልክ እንደእህቱ ሁሉ በአቢይ አህመድ ፍቅር ተለክፎ በዕንባ እየተነፋረቀ እንደሆነ በሚዲያዎች እየታዘብን ነው፡፡ ሰው ያበደ ቢያብድ አማራ ነኝ ብሎ፣ በዚያም ላይ የተማርኩ የተመራመርኩ ፈላስፋ ነኝ ብሎ ሲያበቃ ጭራቅን መደገፍ ማለት የጤና አይደለም፡፡ የምወደውን የአማራ ነፃነት ታጋይ ኦመር ኤጀርሣን ጨምሮ ስንትና ስንት ሃቀኛ ኦሮሞ ኢትዮጵያውን የዚህን ዘረኛ የብል.ግና መንግሥት አምርረው ሲቃወሙና በሚዲያም በጦር ግንባርም ሲፋለሙ ይህ ወፈፌ አማራ ነኝ ባይና ልጁ የሚሆን ጌትነት አልማው የተባለ በቁሙ የሞተ ሰውዬ ምን እንደተጣባቸው አይታወቅም ፋኖንና አማራን ተግተው ሲታገሉ ይታያሉ፡፡ እንደኔ እንደኔ ከኦሮሙማ በፊት እነዚህን ዕብድ ውሾች መላ ማለት የሚገባ ይመስለኛል፡፡

በነገራችን ላይ ስለዕብደት ካነሣን የውሻ ዕብደት ብቻ 100% እንደሆነ ሲነገር ሰምቻለሁ ወይንም አንብቤያለሁ፡፡ ውሻ ካበደ መመለሻ የለውም፡፡ አይበላም፤ አይጠጣም፡፡ መንገድ አይመርጥም፡፡ ያገኘውን እየነከሰና እየለከፈ እስኪሞት ድረስ ብዙ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ለዚህም ነው ያበደ ውሻ ካልተገደለ ጠንቁ ለአካባቢም ተርፎ ያልተጠበቀ ኪሣራ የሚያስከትለው፡፡ አንድ ወቅት አንድ አካባቢ ሰባት ቤተሰቦችን አንድ ዕብድ ውሻ ለክፎ ሳይታወቃቸው መከተቢያ ሰዓቱ በማለፉ ሁሉም ቤት ተዘግቶባቸው እየጮሁ በዚያው እንዲሞቱ ተደርጓል፡፡ አያድርስ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የገጠማትም እንደዚሁ ነው – ከሥልጣኑ ውጪ ምንም ነገር በማይታዬው አቢይ በሚባል ዕብድ ውሻ ተይዛለች፡፡ ከ130 ሚሊዮን የሚበልጠው ሕዝቧ በዚህ ዕብድ ውሻና መሰል ሠራዊቱ መከበቡንና በርካታዎችም በመርዙ መነደፋቸውን እያወቁ የባሰውን በመፍራት ሁሉም ፀጥ ረጭ ብሏል፡፡ ሕዝቡ የሚጠብቀው ከእግዚአብሔር ወይም ከፈጣሪ እንጂ ከሌላ አቅጣጫ መሆኑ በተለይ አሁን አሁን እየቀረ ያለ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ነገሮች ሁሉ “የአህያ ባል ከጅብ አያስጥል” ዓይነት እየሆኑ መጡና ያመኑት ፈረስ በደንደስ መጣል በመጀመሩ ነው፡፡

የደርጉ ዘመን የሃምሣ ሣንቲም አንድ ኪሎ ምሥር ክክ 300 ብር ሲገባ፣ የ3 ብር በርበሬ 500 ሲገባ፣ የ10 ብር ሥጋ ቁርጥ 3000ን ሲዘል፣ የ20 ብር ኮረሪማ 1700ን ሲታከክ፣ የ5 ብር ባለ12 ቁጥር ፌሮ 2000 ሲያልፍ፣ የ3 ብር ቤት ኪራይ 5000 ሲባል፣ የ10 ሣንቲም ያበሻ ዶሮ ዕንቁላል 23 ብር ሲሸጥ … የመንግሥት የወር ደሞዝ ከአንድ ቀን መኖሪያነት የማይዘል ሲሆን እየታዘብን ሁላችንም ቃል ላለመተንፈስ ፀጥ ረጭ ብለናል፡፡ ምክንያቱም ዕብዱ ውሻ ያስፈራላ፡፡ ለምን ተናገራችሁ ተብለው አይደል እነክርስቲያን ታደለ ፍዳቸውን እያዩ ያሉት? አዎ፣ እባብ ያዬ … ነው ነገሩ ሁሉ፡፡

&nbspበኮሪደር ልማት ስም አማራን ከአዲስ አበባና ጅማን ከመሰሉ ከተሞች ለማባረር በተደረገውና እየተደረገ ባለው ኦነጋዊ ዘመቻ ስንቶች ራሳቸውን ሲያጠፉ ራሣቸውን ማጥፋታቸው ካልቀረ አንድ እንኳን ይዘው አለመሞታቸው ዕብድ ውሻ ሟችን ሳይቀር እንዴት በፍርሀት እንደሚያርድ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ሰው የተላከው እርግጠኛ ነኝ ከሰው ማኅጸን ሣይሆን ከለየለት ጥልቁ የጨለማው ዓለም እንደሆነ መገንዘብ አያቅትም፡፡ በዚህ ዕድሜ ማንም የዓለም ዜጋ ይህን ያህል በክፋትና በተንኮል፣ በሤራና በሸር፣ በሰው ደም ጥማትና የሰው ሥጋ በልነት ሊሰለጥን አይችልም፡፡ ተንኮሉና ዕድሜው በፍጹም አይመጣጠኑም፡፡ ይህ ሰው በዚህች አጭር ዕድሜ፣ ይህ ነው የሚባል ዘመናዊ ትምህርት ሣይኖረው፣ ይህ ነው የሚባል የወታደራዊ ሣይንስ ዕውቀት ሳያገኝ እንዲሁ በጨረባ ተዝካር ዓይነት የሙልጭልጭ ጉዞ 130 ሚሊዮን ሕዝብ ማፍዘዝና ማደንገዙ አለነገር እንዳልሆነ እየገባኝ ነው፡፡ ግን ግን ከፍ ሲል እንዳልኩት በቅርቡ ተዝካሩን ቄስም ሆነ ቃልቻ ሳይበላው እንደቢን ላደን የውኃ ሽታ ሆኖ ይቀራል፡፡ ከርሱ ኅልፈትም በኋላ የሰውዬው ንግግሮች በታሪክ ተቀምጠው ወንጀለኛ የእሥር ቅጣት ሲፈረድበት “የአቢይን ንግግር ለአንድ ሰዓት ብታዳምጥ ይሻልሃል ወይንስ ስድስት ወር ብትታሰር” እየተባለ የቅጣት አማራጭ እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ እሱ ሲናገር መስማት እኮ ትልቅ ቅጣት ነው፡፡

&nbspከፍ ሲል ለሰጠሁት አስተያየት ይቺን ለፈገግታ የምትሆን ታሪክ ልጨምር – ካነበብኩት፡፡ አንድ ወንጀለኛ በስቅላት ሊቀጣ በርሜሉ ላይ ተስተካክሎ ቆሟል አሉ፡፡ ገመዱ አንገቱ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሰቃዩ በርሚሉን ገፍትሮ ሰውዬው ሊንጠለጠል ሲል ቦታው ላይ የነበረው ያገሩ ገዢ ወደተሰበሰበው ሕዝብ ዘወር ብሎ “ይህነን ሰው አጋባዋለሁ የምትል አንዲት ሴት እጇን ካወጣች እምረዋለሁ” ይላል፡፡ ግን ሰውዬው መልኩ እንደኔ ኖሮ ብዙ ቢጠበቅም አንዲትም ሴት እጅ አላወጣችም፡፡ በመጨረሻ ግን ከወደስተኋላ አንዲት ሴት “አለሁ፣ አለሁ፣ እኔ አገባዋለሁ!” እያለች ሕዝቡን እየገፈታተረች መጣች፡፡ “እህሳ! ታገባታለህ?” በማለት ተሰቃዩን አገረ ገዢው ይጠይቀዋል፡፡ ያኔ ያ ወንጀለኛ ወደበርሜል ገፍታሪው ሰውዬ ዘወር ብሎ “ወንድሜ ጊዜየን አታባክን፤ በርሚሉን ቶሎ ገፍትረውና ገላግለኝ” በማለት ሰውን ሁሉ አስገረመው ይባላል – ሴትዮዋ ምን ያህል አስጠሊታ ልትሆን እንደምትችል የአቢይን የሀሰትና የማስመሰል አናዳጅ ንግግሮች በማስታወስ መገንዘብ አያቅትም፡፡ አብርሃም ሊንከንም ይህን የመሰለ ነገር ገጥሞታል አሉ – በእግረ መንገድ ትዝ ካለኝ ምን ላድርግ? አንዲት ሴት “አንተ ባሌ ብትሆን ኖሮ መርዝ ሰጥቼ እገድልህ ነበር” ስትለው “እኔም ያንቺ ባል ብሆን ኖሮ የምትሰጭኝን መርዝ ተቀብዬ ለመጠጣት አላመነታም ነበር” አላት አሉ፡፡ እሷን ከመሰለች ሴት ጋር ከሚኖር ሞቱን እንደሚመርጥ ባሽሙር ሊነግራት መፈለጉን ልብ ይሏል፡፡ ነገር አበዛሁ፡፡ ኹዳዴን ለምትፆሙ መልካም ፆም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ይድረስ ለውድ የክፉ ዘመን ጓዴ ፕሮ. ፍቅሬ ቶሎሣ – ከወንድምህ ይነጋል በላቸው

Latest from Same Tags

አሳሳቢው ግድያና አሉታዊ ተፅዕኖው

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ከሚዲያም ከነፃነት ትግሉም ርቀው በተደበቁበት በአሁኑ ወቅት መጻፍ ብዙም ዋጋ እንደሌለው አውቃለሁ፡፡ ይሄ አቢይ የሚባል ጭራቅ ከመጣ ወዲህ

የአማራና የኦሮሙማ ድርድር – በሣቅ አትግደሉን!

ይነጋል በላቸው “አማራ በድርድር የሚፈታ ችግር አልገጠመውም” በሚል ርዕስ በፈረንጆቹ አቆጣጠር Sept. 16, 2023 የሚከተለውን መጣጥፍ ጽፌ እንቅልፍ ሳይበግራቸው፣ ድካም ወፃማ ሳይፈታቸው ለሀገራቸው ትንሣኤ

እስክንድር ነጋ በታዛቢዎች አማካይነት ከአቢይ አህመድ ጋር የሚያደርገው ድርድር የአማራውን ህዝብ የተሟላ ነፃነት የሚያጎናፅፈው ወይስ ለዝንተ-ዓለም ኋላ ቀር ሆኖና ኑሮው ጨልሞበት እንዲቀር የሚያደርገው ?

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)  ጥር 19፣ 2017(January 27, 2025) ሰሞኑን እስክንድር ነጋ “እመራዋለሁ የሚለውን የፋኖ ክንፍ” በመወከል ከአቢይ አህመድ አገዛዝ ጋር፣ እሱ እንደሚለው ውይይት፣ በመሰረቱ ድርድር እንዳደረገ በተለይም እነ

ወሰንየለሽ ኦሮሙማዊ ዕብደት!!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ አንድ አባውራ ምንነቱ ያልታወቀ እህል ከገበያ ገዝቶ ለሚስቱ አምጥቶ ሰጣት አሉ፡፡ ከሰጣትም በኋላ ሚስቱ ያንን እህል ፈጭታ ቂጣ ላርግህ ብትለው፣ እንጀራ
Go toTop

Don't Miss