ወዳጆቼ እንዴት ናችሁ? ትራምፕ ከተመረጠ ጊዜ ጀምሮ አልተገናኘንም፤ በነገራችን ላይ፥ ትራምፕ ማለት ለኔ የሜሲ ቦዲጋርድ ማለት ነው፤ የሜሲ ቦዲጋርድ ድንገት ከመሬት ተንስቶ ወደ ጨዋታው ሜዳ ሲሮጥ ታዩታላችሁ፤አሯሯጡ ደግሞ ፥ቀነኒሳ የይርጋ ጨፌን ቡና ጠጥቶ ቢሮጥ ብላችሁ አስቡት ፤ ሜሲ ከማርስ በመጡ ፍጡራን ታግቶ እሱን ለማስጣል የሚሮጥ ነው የሚመስለው፤ ምንጉድ ተፈጥሮ ነው ብየ አያለሁ፥የሆነ ብላቴና ልጅ ወደ ሜዳው ሰርጎ ገብቶ፥ ከሜሲ ጋር ሰልፊ ሊጠባጠብ እየሞከረ ነው፤ ቦዲጋርዱ ሮጦ ከደረሰ በሁዋላ ሰልፊ ጠያቂውን ልጅ እንደ በቆሎ በቁንጮው አንጠልጥሎ ያስወጣዋል ብየ ሳስብ፤ የሰልፊው ተሳታፊ ሆኖ ወደ ቦታው ተመለሰ፤ እምደንቅ ነው! እስከዚህ ድረስ ያለውን ለትራምፕ ቆርጣችሁ ላኩለት
ስሙኝማ! አዚህ ከተማ ፥ጨዋ ጨዋ፥ የሚጫወቱ ሀብታሞች እየተበራከቱ ነው፤ ሚድያ ላይ ይወጡና ” በዚህ ድሀ ህዝብ ላይ የሀያ ሚሊዮን ብር መኪና አልነዳበትም ብየ ዱባይ ውስጥ ቀለል ያለ ሪልስቴት እየገነባሁ ነው፤ “ የሚል ይዘት ያለው ቃለመጠይቅ ይሰጣሉ፤ ግዴለህም በላብህ ካመጣኸው ሀብታምነት ምንም የሚያሸማቅቅ ነገር የለውም፤ ፈይሳ ሌሊሳ የተመኘልን ጋሪ በጎርፍ ከሚረጨን፥ የሃያ ሚሊዮን ብር መኪና ቢገጨን ለኛም ክብር ነው፤
እኔ ሀብታም መሆን እንደምፈልግ በተደጋጋሚ ተናግርያለሁ፤ ሱፐርማርኬቴ በር ላይ “ የግብር ከፋዩ ስም በእውቀቱ ስዩም የሚል ፥ በደብዛዛ ጉርድ ፎቶግራፌ የታጀበ ሰርተፍኬት ደቅ ብሎ ማየት እፈልጋለሁ፤
በተቻለኝ መጠን እቆጥባለሁ ፤ ያ ማለት ግን ትራምፕ እንደ ሰረራት አሜሪካ፥ ችሮታየን አቋርጫለሁ ማለት አይደለም፤ ሀበሻ ምስጋና አያውቀም እንጂ፥ እኔማ የተራበ ከማብላት የተጠማ ከማጠጣት ቦዝኜ አላውቅም:
:
በቀደም ደቻሳ ክትፎ ቤት በረንዳ ላይ ቁጭ ብየ ያዘዝኩትን ስጠብቅ ሁለት ጎረምሶች ከፊቴ ቁጭ ብለዋል፤
አንደኛው “ በውቄ ! የሎስ አንጀለሱ ሳያልቅ ጋብዘና “ አለኝ፤
“ በደስታ “ አልሁና በክትፎ ቤቱ በር የሚያልፈውን ቆሎ አዙዋሪ በፉጨት ጠርቼ፥
“ ከለውዙ አንዳንድ ማንኪያ፥ ከሽንብራው አንዳንድ ጭልፋ ስጥልኝ ” ብየ አዘዝኩት፤
በጋበዝኳቸው ለጠብ ተጋበዙ፤ ግማሹን የኮንደሚኒየም ነዋሪ ያሳተፈ ግልግል ተደርጎ ከሞትና ከቁስለት ተረፍኩ::
ከጥቂት ቀናት በፊት ደሞ፥ የረከቦትን ጎዳና ይዤ፥ በእግሬ ስዠልጠው፥ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የቀፈለኝ ልጅ ከጎን ከጎኔ ያጅበኝ ጀመር፤ “በውቄ ደብሮኛል “አለኝ፤
“ ዠለስ ፤ ቢኖረኝ ኖሮ፥ በዚህ ማጅራትና ግንባር አስተባብሮ በሚመታ ጠራራ ጸሀይ፤ በእግሬ እሄድ ነበር” ብለውም ሊፋታኝ አልቻለም:
:
ትንሽ እንደተራመድን፥ መንገዱ ዳር ካለው ካፌ አንድ የማውቀው ሰውየ ሲወጣ ተመለከትኩ፤
“በውቄ እንዴት ነህ፡ “ ብሎኝ ሊያልፍ ሲል፥ ቀረብ ብየ እጁን ያዝኩና አስቆምኩት፤
“በናትህ ይሄ ልጅ እየነዘነዘኝ ስለሆነ እንዲሄድልኝ ትንሽ አውራኝ “ አልሁት፤ ፈንጠር ብሎ ቆሞ ወደሚጠብቀኝ ጎረምሳ እየጠቆምኩት፤
“ ብራዘሬ እኮ ነው፤ ከስራ ተቀንሶ እንጂ የሰው ፊት ማየት የሚወድ ሰው አልነበረም ” አለና ከቴስታ የማይተናነስ ግልምጫ አበረከተልኝ::
አቤት ! እንደ እንደ ድሮ ሻንጣ ሽምቅቅ ስል ይሰማኛል፤
“ በል ስራ እስኪያገኝ ድረስ ይሄ አንተ ጋ ይቀመጥለትና እየቀነስህ ስጠው”
አልሁና ድፍን መቶ ብር ሰጥቼው ጉዞየን ቀጠልኩ:;