አንደኛ፦ እኔ ክርስቲያን ታደለ ፀጋዬ ዛሬ በዚህ ችሎት በተከሳሽነት የቆምኩት፤ ለ550 ቀናትም በግፍና ችካኔ እገታ ውስጥ የምገኘው ለአንዲት ደቂቃ እንኳን በጥፋተኝነት የሚያስቀጣ አንዳችም የወንጀል ድርጊትን የሚያቋቁም የህግ መተላለፍ ስለፈፀምኩ አይደለም። ይልቁንም የአማራ ህዝብ የሚያነሳቸውን የህልውና ጥያቄዎች በይፋ በማቅረቤ፤ በህዝቤ ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል በማስረጃ በመመሞገቴ፣ የገዠውን ፓርቲ አፈናና የመንግስት አሰራሮችንና አመራሮችን ብልሹነትና ዘረፋ በመታገሌና በማጋለጤ ነው። ያደረግኋቸው ትግሎችና ማጋለጦች በሙሉ በህጋዊ መድረኮችና አማራጮች ያደረግኋቸው ናቸው። ራሴው ጭምር በኮሚቴ አባልነት ተሳትፌባቸው የተረጋገጡ አማራውን በጅምላ የመግደል፣ማፈናቀልና ማሳደድ ዘር ተኮር ጥቃት ሪፖርቶች፣ የኢትዮጵያ ሰባዊ መብት ኮሚሽን በተለያዩ ጊዚያት ያወጣቸውን ሪፖርቶች እንዲሁም ልዩ ልዩ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የሰባዊ መብት ተቋማት ያወጧቸውን ሪፖርቶች በመያዝ መንግስትና ገዘው ፓርቲ ብልሹ አሰራሮችንና አመራሮችን እንዲያስተካክል ታግያለሁ። ይህንንም በቀጥታ የሬድዮና የቴሌቪዠን ስርጭት ባገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ያደረግሁት ነው።
በምክር ቤቱ በመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነቴ በነበረኝ ኃላፊነትም በፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የተከናወኑ የኦዲት ሪፓርቶችን መሰረት በማድረግም የከፋ ችግር ያለባቸውን ተቋማት አሰራራቸውን፣ አደረጃጀታቸውን እና አመራራቸውን እንዲያሻሽሉ የመገምገም ስራ ሰርቻለሁ። ተደጋጋሚ የአመራር ብልሹነት ያሳዩ አካላትም የወንጀልና ፍትኃብሔር ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ክስ እንዲመሰረት ፍትህ ሚኒስቴርን አዝዣላሁ። በምክር ቤት አባልነቴም ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በአሰራራቸው የፋይናንስ ግልፀኝነትና ህጋዊነትን እንዲከተሉና እንዲያረጋግጡ እንዲሁም ኦዲት ለመደረግ ፈቃደኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ ጠይቂያለሁ።
እነዚህን ጥያቄዎች እንዳልጠይቅ አንዳንድ አመራሮች በግል በኢመደበኛ ሁኔታ ለማግባባት ሞክረዋል። አንዳንዶቹም ሊያስገድሉኝ፣ ሊያሳስሩኝና አንዳች አይነት ጉዳት ሊያደርስቡኝ እንደሚችሉ ጭምር ነገረውኛል፤ መልዕክትም አድርሰውኛል። ይህ ሁሉ የሆነው ያጎደልኩት ስነ- ምግባር አልያም የተላለፍኩት ወንጀል ስለነበር አልነበረም። ይልቁንም ያደረግሁት ሁሉ በህዝብ እንደራሴነቴ ህዝብና ህግ የጣለብኝን ግዴታ እና ኃላፊነት ነው የተወጣሁት። ያደረግሁት ሁሉ የሚያሸልም እንጅ የሚያስነቅፍ አልነበረም። እጅግ ሲከፋም አሁን ባለሁበት ሁኔታ የግፍ ሰለባ የሚያደርገኝ መሆን አልነበረበትም።
የተከበረው ችሎት፤ ክቡራን ዳኞች፤
ቀደም ብዬ እንዳወሳሁት ለ550 ቀናት በአስከፊ ሁኔታ የተሰቃየሁት፤ ለቀጣይ ለማይታወቁ የሰቆቃ ሌሊቶችም በአገታ የምቆየው አንዳችም ወንጀል ስለፈፀምኩ አይደለም። ማን እንዳሰረኝ፣ ለምን እንደሰረኝ አውቃለሁ። እውነታውን ፈጣሪ፣ ህዝቡም ያውቃል።
ሁለተኛ፦ እኔ አማራ የሆንኩት አማራ ሆኘ ስለተወለድኩ ነው። የአማራ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ የሆንኩትም ፈቅጀ፣ መርጨና ወድጄ ነው።በየትኛውም ቦታና ሁኔታ ለአማራነቴ ጥብቅና መቆምም ተፈጥሯዊ ግዴታዬ ነው። በዚህም በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሱ ያሉ ስርዓታዊ፣ ተቋማዊ ህገመንግስታዊ ሁለንተናዊ በደሎችና መገፋቶችን ለማስቆምና የህዝባችንን ዘላቂ መብቶች፣ ፍላጎቶችና ጥቅሞችን ለማስከበር የአማራ ህዝብ የህልውና ጥያቄዎች ናቸው ብሎ በለያቸው የፓለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ ፕሮግራምና ፖሊሲ በመቅረፅ እንዲሁም የመመስረቻ ማንፌስቶ በማዘጋጀት ከትግል ጓዶቼ ጋር በመሆን በምርጫ ቦርድ በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰኜ ፓርቲ አቋቁሚያለሁ። በ6ኛው ዙር አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫም 5 የፓርላማና 13 የክልል ምክር ቤት ወንበሮችን አሸንፈናል። ባነኘነው ወንበርና በመራጮች ድምፅ ብዛትም የኢትዮጵያ ትልቁ ተቃዋሚ ፓርቲ ነው።
እኔም የህዝብ እንደራሴ የሆንሁት ገዠውን ፓርቲ ጨምሮ ከተፎካካሩ ሌሎች 8 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወዳድሬ አሸንፌ ነው። በምርጫ ማንፌስቷችን፣ በመመስረቻ ጽሑፋችን በልዩ ልዩ መድረኮች ባካሄድናቸው የምርጫ ክርክሮች ጭምር የህዝባችንን እሴቶች እንደምንጠብቅ፣ የአማራ ብሔርተኝነት የማደራጃና የርዕዮተ-ዓለም ማዕቀፋችን እንደሆነ እንዲሁም ህዝቡ መርጦን መንግስት ከሆን የህዝባችንን የህልውና ጥያቄዎች እንደምንመልስ ተከራክረናል፣ ቃል ገብተናል። አማራዊ እሴታችን ለእኛ ቅዱስ ነው። እኛነታችን ከደምና ስጋ ብቻ ሳይሆን ከአማራዊ እሴት ጭምር የተሰራ ነው። በዚህም ደስተኞች ነን።
ይሁንና አቃቤ ህግ ባቀረበው የፖለቲካ ውንጀላ ሰነድ ላይ ”አማራ ርስቱን ተቀምቷል፤ አገሪቱ በአማራ እሴት መመራት አለባት” የሚል የርዕዮተዓላማዊ አቋም መያዛችን ክስ ሆኖ ቀርቧል።
የተከበረው ችሎት፤ ክቡራን ዳኞች፤
”የአማራ ህዝብ የህዝብና ግዛት አንድነትና ኢ-ተነጣጣይነት ተገርስሷል” የሚለው እውነት እኔ ብቻ ሳልሆን መላው አማራና በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚጋሩት ኃቅ፣ ፓርቲዬ አብንም በመመስረቻ ሰነዱና በምርጫ ማንፌስቶው በግልፅ ያሰፈረው፣ ያሁኑ የአማራ ብልፅግና የቀድሞው አዴፓ በ12 መደበኛ ጉባኤው ተገቢነቱን አምኖ የሚታገልለት የአማራ ጥያቄ መሆኑን በይፋዊ መግለጫ ጭምር የተቀበለው ነው። የፌደራል መንግስቱም የአማራ ህዝብን ጨምሮ በሌሎችም ብሔረሰቦች የሚቀርቡ የማንነትና ወሰን ጉዳዮችን እልባት ለመስጠት ኮሚሽን እስከ ማቋቋም መድረሱ፣ አሁን በስራ ላይ ባለው አገራዊ ምክክር ኮሚሽንም እንዲፈቱ ከተያዙ ቁልፍ አገራዊ አጀንዳዎች አንደኛው መሆኑን ወስዶታል። ታዲያ እንዴት ክስ ሆኖ እኛ ላይ በልዪነት ሊቀርብ ቻለ?
እሴትን በተመለከተ ለችሎቱ ለማስገንዘብ ያህል፦
እሴት ማለት የጋራ የሆነ ማህበረሰባዊ የነገሮች ምልከታ ሆኖ የማህበረሰብ አባላት በግልና በጋራ የሚያከናውኗቸውን የየዕለት ተግባራትና እሳቤዎች ጥሩነት አልያም መጥፎነት እንዲሁም ተገቢነቴና ኢ-ተገቢነት መለያ መርኋቸው ነው።
የአማራ እሴት ማለት የማንነቱ መገለጫዎች የሆኑት ለአብነትም አማኝነት፣ለጋስነት፣ ሩህሩህነት፣ ይቅርባይነት፣ደግነት መልካምነት፣ ኃቀኝነት፣ጀግንነት፣ ሰውዳድነት፣ ሰው አክባሪነት፣ ግልፅነት፣ ትሁትነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ቀናዒነት፣ አርበኝነት፣ ህግ አክባሪነት፣ ፍትኃዊነት፣ርቱአዊነት፣ ታማኝነት፣አስተዋይነት፣ ጥበበኝነት፣ገርነ፣ ትዕግስተኝነት፣መንፈሰ ጠንካራነት ጥቂቶቹ ናቸው።
እነዚህ የአማራ ህዝብ እሴቶችአማራነታችንን የገነቡ የስነ ልቦና ውቅሮች ናቸው። አቃቤ ህግ አንዳችም ማስረጃ ማቅረብ አይችልም እንጅ ኢትዮጵያ በእነዚህ የአማራ እሴቶች ብቻ መመራት ይኖርባታል” የሚል አቋም ብይዝ እንኳን ጉዳዩ የፖለቲካ ሙግትና ውይይት፤ ክርክርና ድርድር አጀንዳ እንዲሁም ለመራጭ ዜጎች ይሁንታ የሚቀርብ የምርጫ ኮረጆ ጉዳይ እንጂ በወንጀለኝነት የሚያስጠይቅ አይደለም። ይህ የአቃቤ ህግ ክስ ግን መንግስት ከአማራና ከአማራነት የፀዳች ኢትዮጵያ ነው ወይ የሚፈልገው የሚል ሙግት ያስነሳል። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከአማራና አማራነት በስተቀር እንዲሆኑ የሚደነግግ ህግስ አለወይ?ሶስተኛ፦ በአቃቢ ህግ ክስ ላይ ቋሪትና ደጋ ዳሞት ላሉ የሽብር ቡድን አስተባባሪዎች በስልክ ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም በመደወል መከላከያን ማጥቃት ህገ መንግስታዊ መብት መሆኑን በማሳወቅ እንዲመቱት ትዕዛዝ ሰጥቷል የሚል ነው። አቃቤ ህግ ለዚህ ክሴ አስረጅ የሚሆን አንዳችም ማስረጃ አላቀረበም። የተደወለበትና የጥሪ ተቀባይ ስልክ ቁጥሮች እንዲሁም የትዕዛዝ ተቀባይ ግለሰቦች ማንነት አልቀረበም። በቀረበ የማስረጃ ዝርዝር ላይም በተሰጠው ትዕዛዝ መነሻነት በቋሪትና ደጋዳሞት ወረዳዎች የተጎዱ ሰዎችና ንብረት ዝርዝርም አልቀረበም። የፍሬ ነገር ክርክር ሲደረግ የማቀርበው እንደተጠበቀ ሆኖ የወቅቱ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ የፌደራል መንግስት የፀጥታ ኃይሉን ወደ ክልሉ እንዲገባ የጠየቁት ሐምሌ 27/2015 ዓ.ም ነው። የመከላከያ ሰራዊት ወደ ደጋ ዳሞትና ቋሪት መግባት የሚችለውም ርዕሰ መስተዳደሩ ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ በመሆኑ ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም አቃቤ ህግ በክሱ ርምጃ ይወሰድበት ብለሃል ያለውን መከላከያ በምን አግባብ ቋሪትና ደጋዳሞት ሊገባ ቻለ የሚል ከባድ የህገ መንግስታዊነት ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።
የተከበረው ችሎት፤ ክቡራን ዳኞች፤
አቃቤ ህግ በስልክ ትዕዛዝ ሰጥቷል በሚል የሁለት ግለሰቦች ንግግር የያዘ ድምፅ አዳምጨዋለሁ። አቃቤ ህግ በስሜ በተመዘገበ የታወቀ ስልክ ቁጥር ስለመደወሌ፣ የደወልኩበትን ስልክ ቁጥር እና አስተባባሪ ነው ያለውን ግለሰብ ስም አላቀረበም። ለመሆኑ በማስረጃነት ያቀረበው የድምፅ ቅጅ የኔ ስለመሆኑ በምን አረጋገጠ? በምን መሳሪያ መረመረው? ኢትዮጵያ የድምፅ አሻራ መመርመሪያ መሳሪያና በዚህ መስክ የሰለጠነ ባለሙያ የላትም። የት አስመርምሮት? ምን ያህል ፐርሰንት ከእኔ የትኛው ኦሪጅናል ድምፅ ተነፃፅሮ ምስስሎሽ ተገኘበት? እንደ አገርስ የድምፅ ምስስስሎሽ መቁረጫው መቶኛው(cut -off percentage) ምን ያህል ሲሆን ነው ህጋዊ ውጤት የሚኖረው?
እነዚህ ቁልፍ ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው እና የቀረበው የድምፅ ማሰረጃ የእኔ አይደለም እንጅ፤ ቢሆን እንኳን ወንጀል የሚያቋቁም አንዳችም የህግ ጥሰት ግን አላገኘሁበትም።
በመጨረሻም፦ አቃቤ ህግ ያቀረበው የፀና ፈቃድ ሳይኖር የጦር መሳሪያ መያዝ ጉዳይ ህጋዊ ፈቃድ ያለኝ፣ የፈቃድ ደብተሩንም ለ8 ወራት ይዘውት ቆይተው የመለሱልኝና ማቅረብ የምችል መሆኔን ለችሎቱ አስታውቃለሁ።
አመሰግናለሁ
አቶ ክርስቲያን ታደለ ፀጋዬ