የሕወሃትን ከፓርቲነት መሰረዝ መነሻ በማድረግ የተጻፈ።
(ከአሁንገና ዓለማየሁ)
ምናልባት የትግራይ ሕዝብ በሕወሃትና በአጋሮቹ (የኦነግ ዲቃላውን ኦህዴድን ጨምሮ) የደረሰበት ቃጠሎና ውድመት አንድ በጎ ነገር ከተገኘበት የትኋኑ (የሕወሃት) መጥፋት ቢሆን ከዚህ መከራም ውስጥ አንድ መልካም ነገር ተፈጠረ ለማለት ይቻላል። ይሄንን አባባል እንደቀላል የሚያዩት ሰዎች ይኖራሉ። የቤቴ (ትግራይ) መቃጠል ለትኋኑ (ሕወሃት) በጀኝ። ቤቴ መቃጠሉ መዐትና ቁጣ ቢሆንም፣ በቃጠሎው ባይሆን እንኳን ደሜን ሲጠጣ፣ እንቅልፍ ሲነሳኝ የነበረውን ተባይ ተገላገልኩት እንደማለት ነው።
እኔ በትግራይ ሕዝብ ላይ ጄኖሳይድ (የዘር ማጥፋት) አልተካሄደም ከሚሉት ሰዎች መካከል አይደለሁም። የጄኖሳይድን ታዋቂ መስፈርቶች በማየት ጄኖሳይድ ተፈጽሞበታል ባይ ነኝ። ጄኖሳይዱን በዋነኝነት ያካሄደውም ሕወሃት ነው። የዚህም ዋናው ክፍል የተፈጸመው ከኦህዴድ ጋር ካደረጉት ጦርነት በፊት ነው። የትግራይን ሕዝብ ባሕላዊ፣ ሀገራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እሴቶች፣ የሕዝቡን ሃብቶች እና ማንነቶች አጥቅቶ በብዙዎቹ ላይ የማይቀለበስ ወይም እጅግ የከፋ አደጋ አድርሷል። ሕወሃት።የ “ዘር ማጥፋት” የሕግ ፍቺ በዋነኝነት የሚያተኩረው በአካላዊ ጥፋት/ ፍጅት ላይ ነው። ቢሆንም የባህል፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ የዘር ማጥፋት ድርጊቶችም የግድ አካላዊ ጉዳትን ባያጠቃልሉም፣ የቡድንን ህልውና በተደራጀ መልኩ ለማዳከም እስከተከናወኑ ድረስ የሰፊው የዘር ማጥፋት ሂደት አካል ተደርገው ይወሰዳሉ። እነዚህን በዝርዝርና በተተነተነ መልኩ ለመዳሰስ መጻሕፍት ስለማይበቁ ዛሬ በዋነኝነት አንዱን የጂኖሳይድ አካል ብቻ ወስደን በጥቂት አረፍተ ነገሮች እንመለከታለን። እዚህ ላይ ስለትግራይ ሕዝብ ስለተነሳ እንጂ አማራን በተመለከተ ሕወሃት በአማራ ላይ ጄኖሳይድ ስለመፈጸሙና ስለማስፈጸሙ ኅሊና ያለው ሁሉ የሚቀበለው ጉዳይ ነው።
ወደዚህ ሕወሃት ከብልጽግና ጋር ከገባው ጦርነት አስቀድሞ በትግራይ ሕዝብ ላይ ስላከናወነው ጄኖሳይድ ማብራሪያ ከመግባታችን በፊት ከኦህዴድ ጋር ባካሄደው ጦርነት የፍጅቱ አስፈጻሚ አሁንም ሕወሃት መሆኑን ጠቁመን እንለፍ። ይሄን ፍጅት ጄኖሳይድ እንበለው ከተባለ አሁንም ሕወሃት ነው በጥሩምባ ነፊነት፣ በተንኳሽነት፣ ሁኔታውን ያመቻቸው (አጥፊዎቹን አሰልጥኖ፣ አጎልብቶ አፋፍቶ፣ የቂም በቀል መንገድ አበጅቶ የጥላቻ ተረኮችን ዘርቶ፣ ሕገ መንግሥት ቀርጾ፣ የዘር መታወቂያ አድሎ) የሚሉት አሉ። ሕወሃት ከሥልጣን ከመባረሩ በፊት ባደረገው ግምገማ አመጽ የተነሳብኝ ጠያቂ ትውልድ ስለተፈጠረ ነው ብሎ ነበር። ትግራይ ገብቶ ይሄንን ጠያቂ ትውልድ ሆን ብሎ በጦርነት ማግዶ ፈጅቶታል፣ አስፈጅቶታል። ያለበቂ ዝግጅት ገባበትም ይበሉ ምን ሕወሃት በጦርነቱ በቂ ወታደራዊ ስልጠና ያልወሰደ በመቶ ሺህ የሚገመት ወጣት አስፈጅቷል። ይህ በደርግ 17 አመት በኤርትራም በትግራይም በቀረውም ከሞተው ወጣት ይበልጣል። የራሱን ሥልጣን ለማስጠበቅ፣ ከወንጀል ተጠያቂነት ለመሸሽና ጠያቂ ትውልድን ለማጥፋት ያደረሰው ይህ በደል መጠኑ ጂኖሳይድ ቢባል መጋነን ሊሆን አይችልም። እንዲህ የሚሉ ትንተናዎችን እየሰማን ነው።
በእኔ አመለካከት ግን ከዚያም ይልቅ ጦርነቱን ወደ ትግራይ ስቦ፣ ጎረቤቶቹንም ተነኳኩሶ የሕዝብ ለሕዝብ እልቂት መልክ ያስያዘበት አመክንዮ ሕወሃት ሲጠነሰስ የታቀደለትን የፖለቲካ ግብ ለማሳካት አቅዶና ይሁነኝ ብሎ ያደረገው ነው ባይ ነኝ። ይህ ስሌት ሕወሃት እንደኤርትራ በቅኝ ግዛት ሰበብ ትግራይን ከኢትዮጵያ መገንጠል እንደማይችል በመገንዝቡ ገና መለስ ዜናዊ በሥልጣን ላይ እያለ ከተደረሰበት ሕወሃታዊ መረዳት የመጣ ስሌት ነው። በትጥቅ ትግሉ ወቅት ተግዳሮት ይሆናል ብለው ያላሰቡበት፣ ሥልጣን ሲይዙ በአንቀጽ 39ኝ እናሳካዋለን ብለው የተለሙት፣ በኋላ ግን ትግራይን ለመገንጠል ከባድ መሆኑን የተረዱበትና ጄኖሳይድን ብቻ እንደ መገንጠያ ስልት የሙጥኝ ካሉበት መረዳት የመነጨ ስሌት ማለት ነው። ስለዚህም ሕወሃት ገና ለገና ቅንጅት አሸንፎ ሥልጣን ይይዛል ብሎ (ከማእከል የሚባረር በመሰለው ጊዜ) በመበርገግና በችኮላ ራሱ በሥልጣን ላይ ሆኖ፣ ራሱም ዘር ተኮር ጭፍጨፋ የሚያካሂድ አግአዚ የሚባል ሠራዊት አሰማርቶ ሳለ በተገላቢጦሽ“ኢንተርሃምዌ! ጄኖሳይድ!” እያለ መክሰስና መጮህ ጀምሮ ነበር። ገና በ1997፣ ከሃያ አመት በፊት! ሕወሃት የጄኖሳይድን ክስ በፖለቲካዊ ስልትነት እንጂ በሕዝብ ተቆርቋሪነት የማያነሳ መሆኑን በቅርቡ በብልጽግና ጦርነት ወቅት ያጯጯኸውን ወቀሳና ክስ፣ አሁን ሳንዱቅ ውስጥ ቆልፎ ጄኖሳይዱን ፈጸሙ ካላቸው አካላት ጋር ለሁለት ተከፍሎ እየተዳራ መሆኑን ማየቱ በቂ አስረጅ ነው። ያኔም በ97 ምርጫውን አጭበርብሮ የሚረሸነውን ረሽኖ ሥልጣኑን ሲያስቀጥል የጄኖሳይድን ካርድ መሳቢያው ውስጥ ቆለፋት። ቄሮን ሸሽቶ መቀሌ ሲገባ መልሶ አቧራዋን አራግፎ ያራግባት ገባ። የሞኙ ልጅና የእንሽላሊቷ ታሪክ ከዚህ የሕወሃት ታሪክ ጋር ይመሳሰላል።*
(ይቺን ተማስሎ መጨረሻ ላይ በጽሑፉ ግርጌ ይመልከቱ)
ይህንን ካልን ወደዚህ ጽሑፍ ዓላማ ትኩረታችንን እንመልስ። ሕወሃት በትግራይ ሕዝብ እምነት ላይ ስላደረሰው በደል።
ቅድመ ጦርነት (TPLF-PP WAR) ሕወሃት በትግራይ ከፈጸመው ጄኖሳይድ አንዱ ገጽታ
ጄኖሳይድ ተፈጸመ ለማለት ሕዝቡ ሁሉ በአካል ተፈጅቶ ማለቅ አለበት ማለት አይደለም። አንድን ሕዝብ ከእምነቱ፣ ከባህሉ፣ ወይም ከርስቱ መንቀል የጄኖሳይድ መስፈርትን ያሟላል። የትግራይ ሕዝብ ከዘጠና አምስት በመቶ በላይ የተዋሕዶ እምነት ተከታይ ነው ይባላል። በተጨማሪ ክርስትና ወደ ሀገር ከገባበት ጀምሮ የኖረበት ሕይወቱ እንደመሆኑ እጅግ ብዙ እሴቶቹ ከዚህ የክርስትና እምነቱ ይቀዳሉ። ሕወሃት ከምሥረታው ጀምሮ በተዋሕዶ እምነት ላይ በከፍተኛ ደረጃ ዘምቷል። የዚህ የተዋሕዶ ጥላቻው መንስኤ የመነጨው ከተልእኮ ይሁን ፣ ከኮሚኒዝም እሳቤ ይሁን ወይም የመሥራችና የነጋሽ አንጋሹ የስብሃት ነጋ እና ቤተሰብ ከኒሻ (ፕሮቴስታንት) ሆኖ ከማደግ ይሁን አይታወቅም። ብቻ የሕወሃት አመራር ያለመታከት፣ ያለመዘናጋት፣ ያለማሰለስ ካጠቃቸው ተቋማት ውስጥ የተዋሕዶ ቤተክርስትያን ግንባር ቀደም ናት። ገና ከጥንስሱ ሕወሃት ቄሶችና ዲያቆናትን እያስገደደ ነፍሰ ገዳይ አድርጓቸዋል። ገና ከማለዳው የዛሬ ሃምሳ አመት ገዳማትን ሠርገው እንዲገቡ ታጣቂዎቹን እና ሰላዮቹን አሰልጥኖ አሰማርቷል። በዚህም የጥፋት ታታሪነቱ ከዘመናት በኋላ ቤተክህነቱን፣ እምነቱን፣ ሃብቱን፣ ሕዝቡን የሚቆጣጠሩ፣ የሚያወድሙ፣ የሚመዘብሩ ታጋይ መነኮሳት፣ ታጋይ ጳጳሳትን ለማፍራት ችሏል። ሕወሃት ደርግን ከጣለ በኋላ የተደራጀ ስውርና ይፋዊ የእስልምና እና የፕሮቴስታንት ዘመቻ በተዋሕዶ ላይ እንዲከፈት ከማድረግ አልፎ በተዋሕዶ ውስጥ የተሀድሶ ሠርጎ ገቦች አስገብቶ ምእመኑ ላይ ውዥንብርና ቤተክርስትያን ላይ ክፍፍል እንዲፈጠር ሰርቷል። በትግራይ ጎሰኝነትን በእምነት ቦታ የተካው ሕወሃት ራሱን ደግሞ በአምላክ ቦታ ተክቶ ሁሉን አድራጊ፣ ሁሉን ፈጣሪ፣ ሁሉን አስቻይ፣ አምልኮ የሚገባው አድርጎ አስቀምጧል። እንዲያውም ከዚያ በላይ። በትግራይ አምላክን ማማት፣ ማማረርም የተፈቀደ ሲሆን ሕወሃትን ማማት ግን ያስቀስፍ ነበር። ሕወሃትን አምላኬ ነው የማይለው የትግራይ ሕዝብ ክፍል ቢያንስ ግን የዲያብሎስን ያህል ይፈራው ነበር። (አይፈረድብትም። ከሕወሃት ቁጣ የሚያስጥለው ነገር አልነበረምና። ኢህአፓን፣ ኢድዮን፣ ደርግን የተማመኑ ሁሉ አላስጣሏቸውም። ሕወሃት ነው ያሸነፈው። ጀብሃንም ሻዕቢያንም ጭምር። አቢይ አህመድ እንኳን ሕወሃትን አሸነፈው ተብሎ ሕወሃት መልሶ በኢትዮጵያ ጦርነት ታሪክ ያልታየ የምርኮ ሰልፍ እስኪታይ ከመቀሌ እስከ ሞላሌ አሩሩጦታል። ሃምሳ አመት ሞተ ሲሉት እየገደለ የማይሰበር ቀንበር ሆኖ በትግራይ አለ።)
ሕወሃት በስደት ዓለም የትግራይ ተወላጆች ከሌላው ተዋሕዶ ምእመን ተለይተው የራሳቸውን ተነጣይ አብያተ ክርስቲያናት እንዲያቋቁሙ አድርጓል። ይህ ነውር ከሠላሳ አመታት በላይ ዘልቋል። የኢትዮጵያ ቤተክርስያን ራስ የሆኑት ፓትርያርኮች የትግራይ ተወላጆች በሆኑበትም ጊዜ ሁሉ ከፍርሻና የቤተከርስትያን ግንጠላ ዓላማው አልተናጠበም። ያሳደጋቸውን ታጋይ ካህናትና ጳጳሳት ተጠቅሞ የትግራይ ሕዝብ ከእናት ቤተክርስትያን እንዲነጠል ይፋዊም ስውርም ደባዎች ሠርቶ ምእመኑን ላሞራ በትኖታል። ዛሬ ክህነታቸውም እምነታቸውም ጥያቄ ውስጥ ብቻ የገባ ሳይሆን በማስረጃም የታወቁ አላውያን የሚመሩት ተገንጣይ ሲኖዶስ አቋቁሞ በሕዝቡ ላይ የማይጠገን ስብራት እያደርሰ ይገኛል።
ሕዝቡን በእርዳታ እህል እየደለሉ ከሃይማኖቱ ለሚነጥቁት ተኩላዎች አቀብሎታል። የድርጅቱ አንጋፋ መሪዎች በኩራትና በአደባባይ ኦርቶዶክስን ሰባበርናት ብለዋል። ቤተክርስትያኗ ሁሉ ነገሩ በሆነችበት ኅብረተሰብ ቤተክርስትያኒቱን ሰባበርን ማለት የሆነ ግዑዝ ነገር ወይም ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ ተቋም ሰባበርን እንደማለት አይደለም። እምነቱ የማንነቱ ግዙፍ አምድ ለነበረው የትግራይ ሕዝብ በዚህ መስፈርት ብቻ ለተፈጸመበት ጄኖሳይድ ሕወሃት ግንባር ቀደም ፈጻሚ መሆኗን ለመረዳት እንችላለን።
ይህንን በዝርዝር ካብራራን ተጓዳኝ ጄኖሳይዳዊ በደሎችን ጠቀስ አድርገን እንለፍ። የትግራይ ሕዝብ በዚሁ በሕወሃት ጽኑ ትግል ከአክሱም ዘመን ጀምሮ ከነበረው ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊ፣ ቋንቋዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ተፈጥሯዊ ማንነቱም ተፈናቅሏል፣ ተናጥቧል ። የትግሬን ሕዝብ ለሁለት ክፍሎ ሐማሴን፣ ሰራዬና አካለጉዛይ የተባሉት ታሪካዊ አካሉ ተከፍለውና ተለይተው እንዲቀሩ ሕወሃት ሁሉንም መስዋእትነት ከፍሏል። ከታሪካዊ ወደቦቹና የባሕር ጠረፉ ገንጥሎታል። ወገን፣ መሬትና የባሕር በር ነስቶታል። በትግሉ፣ በብርቱ ጥረቱ፣ በገዛ ልጆቹ መስዋእትነት ነው የተፈጸመው። ይሄ ሁሉ ሲደረግ ምንም ዓይነት የዲሞክራሲ ወይም የነጻነት እንጥፍጣፊ በሌለበት በአስገዳጅነት ያለ አማራጭ በትግራይ ሕዝብ ላይ የተጫነበት ነበር።
አዎ ሕወሃት በትግራይ ሕዝብ ላይ ጄኖሳይድ ፈጽሟል። የከፋው ነገር ደግሞ ከሱ የሚያስንቅ ፍራንከንስታይን ኦህዴድንም ፈጥሮ ይህ ፍጡሩ በትግራይም ሆነ በአማራ ሕዝብ፣ በተዋሕዶ ምእመናን ላይ የጀመረውን ጄኖሳይድ እያስቀጠለለት ይገኛል።
ሕወሃትና መንግሥቱ ኃይለማርያም
በሁለቱ መካከል ያለው ተማስሎ የደም ማኅተም ነው። ምንድነው ይህ የደም ማኅተም? መንግሥቱ ኃይለማርያም ያሰራቸውን የንጉሡ ዘመን (የቀድሞ) ባለሥልጣናት ለመረሸን ይወስናል። እነዚህን ሰዎች ሲረሽን ግን የሁሉም የደርግ አባላት እጅ እንዲኖርበት ይፈልጋል። በዚህም የሴራ ተግባሩ ለውጡ በሆነ ምክንያት ቢቀለበስ ጥቂት መኮንኖች ብቻ ተጋፍጠው በወንጀል ተጠያቂ እንዳይደረጉ የሁሉንም እጅ በደም ለመንከር በዚያም ዘዴ ሁሉም ተባባሪና ወደ ኋላ ማፈግፈጊያ የሌላቸው እንዲሆኑ አድርጓል። መንግሥቱ ኃይለማሪያም ሃምሳ ምናምን ባላስልጣናት እንዲገደሉ የስም ዝርዝር ጽፎ ካጸደቀ ከሁለት ቀን በኋላ ደርግን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ ስም እያስነበበ እጅ እያስወጣ በስብሰባው ላይ የተወሰነ አስመስሎ ቀድሞ ብቻውን የፈረደውን የሞት ፍርድ አስፈርዶባቸዋል። ሕወሃት ደግሞ ሕዝቡን የወንጀሏ ተባባሪ ለማድረግ ከየአንዳንዱ የትግራይ ቤተሰብ በውድም በግድ ቢያንስ አንድ ልጅ ወስዳለች። ስለተሰዋው ልጁ ሲል ሕወሃትን ቢያንስ በስነልቡና ይደግፋታል። ይሄ ስነልቡና ምን እንደሚመስል ከኤርትራ ትግል አንድ ምሳሌ እንመልከት።
አቢይና ኢሳያስ የተጋቡ ሰሞን ከጓደኛዬ ጋር አሥመራ ሄደን ነበር። መንገድ ላይ አማረኛ እያወራን ስንሄድ አንድ ሰው ከብስክሌት ወርዶ አቀፈን። ያገሬ ልጆች ምን ያህል ደስ እንዳለን አታውቁም። እንኳን ለመገኛኘት አበቃን። አለ እንባው እየወረደ። እኔ ደግሞ ጓደኛዬ አሥመራ ተወልዶ ያደገ ስለነበር የሚተዋወቁ መስሎኝ አመነታሁ። ሰውዬው ግን ማናችንንም የማያውቅና ኢትዮጵያውያን አሥመራ በመምጣታችን የተደሰተ ነበር። ከዚያ ሸሚዙን አወለቀና ሦስት ጥይቶች(ክንዱ፣ ትከሻውና ደረቱ ላይ) የገቡባቸውን ጠባሳዎች አሳየን። እኔ አለን ወዳጅነት ከመፍጠርም አልፎ ሁለቱ አገሮቻችን ተመልሰው አንድ ቢሆኑ እንኳን ደስ ነው የሚለኝ። ከመለያየት ቁርቁዝና እንጂ ምን ተገኘ? እነዚህን ሦስት ለኤርትራ ነጻነት ስል የቆሰልኳቸውን የጥይት ቁስሎች እንኳን እተዋቸዋለሁ። አለና እንደ መቆዘም አደረገው። ትንሽ ቅር የሚለኝ በጦርነቱ ያጣኋቸውን ሦስት ወንድሞቼን ሳስብ ነው። የነሱ መስዋእትነት ከንቱ ሊሆን? ብዬ እተክዛለሁ። አለን። ሳቅና ለቅሶ። በትግራይም በኩል ሕወሃት ከንቱ መሆኑን ቢያውቁም ይህ የልጆቻቸው መስዋእትነት መቶ ሺ ወላጆችን ከሕወሃት ጋር በስነ ልቡና የተቆራኙ የማድረግ ኅይል አለው። በዚህም ምክንያት ሕወሃት ሕዝቡ ላይ ከመዥገርም በላይ የተጣበቀችበት ድርጅት ናት።
በነገራችን ላይ የሕወሃት መሰረዝ የትግራይን ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ያስከብራል ብሎ ካሰበ፣ ወይም ለኢትዮጵያ (አማራ፣ አፋር ወዘተ) እረፍት ይሰጣል ብሎ ከደመደመ፣ አቢይ አህመድ መሰረዟን ሰርዞ ሕልው እንደሚያደርጋት ሙሉ እምነቴ ነው። ሻዕቢያም ሕወሃትን በውለታ ሊታደጋት ቢመጣ ልንገረም አይገባም። ሕወሃት የኢትዮጵያን ወጣቶች ገብራ ሻዕቢያን ከመደምሰስ አራት ጊዜ ታድጋዋለችና። በሣህል (ከጀብሃ ጋር)፣ በናቅፋ፣ በምጽዋ፣ እና በባድመ ጦርነቶች። በሌላ በኩል ወገቧ እስኪቀንቀጠቀጥ ያገለገለቻቸው ምእራባውያንም ሕወሃት የተፈጠረችበትን የትግራይ ትግሪኝ ዓላማ ሳታሳካ ይተዉአታል ተብሎ አይገመትም። ስለዚህ እዚህ ጽሑፍ ላይ ያነሳነው ቤቴ ከተቃጠለ አይቀር ባይሆን እንኳን ትኋኑም አብሮ በተቃጠለልኝ የሚል ምኞትን እንጂ ተባዩ ወይም ተውሳኩ በቃ ተቃጥሏል የሚል እርግጠኝነትን አይደለም። አንድ ሰው ምንኛ ይከፋው …. በተቃጠለው ቤቱ አመድ ላይ ተኝቶ ትኋኑ ከቃጠሎው ተርፎ ተመልሶ ላዩ ላይ ሰፍሮ ባልበላ አንጀቱ ደሙን ቢመጠው? ይሰውረን! በዘራችሁ አይድረስ ነው ያለው አሥር አለቃ?
*የመለስ የጄኖሳይድ ጩኸትና የሞኙ ልጅ እንሽላሊት
አንድ ብልጥና አንድ ሞኝ ገንዘብ አልቆባቸው ተራቡ። እስኪ ሥራ ከተገኘ ብለው ለመሸቀል በየፊናቸው ይሰማሩና ተመልሰው ይገናኛሉ። ብልጡ ልጅ አፉን እየላሰ ሲመጣ ሞኙ ምን አገኘህ? ቀማመስክ እንዴ? ይለዋል። አዎ ረሃቡ ሲጠናብኝ እንሽላሊት ገደልኩና ልበላት ስል አንድ ሃሳብ መጣልኝ። በኪሴ አድርጊያት አንድ ምግብ ቤት ገባሁ። ቅቅል አዝዤ በዳቦ እና በእንጀራ አጣጥሜ በላሁና ድገሙኝ አልኳቸው። ድጋሚ አንድ ሳህን ቅቅል አመጡልኝ። ሳያዩኝ እንሽላሊቷን ሳህን ውስጥ ጨመርኩና ኡ! ኡ! ብዬ ጮህኩ። አስተናጋጁና አለቃው እየሮጡ መጡ። ምንድነው? የሞተ እንስሳ አብሮ ተቀቅሎ ነው እንዴ የምትሸጡት? ብዬ እሪ ስል። በቃ ሌላ ይምጣልህ አሉኝ። በፍጹም ወስፋቴን ነው የዘጋው እንዴት ብዬ እበላለሁ? ስላቸው ይቅርታ ጠየቁኝና በቃ የቅድሙም በኛ ሂሳብ ነው፤ ከፈለግክ ሻይ ቡናም ውሰድ አሉኝ። እና ሳልከፍል በልቼ ጠጥቼ መጣሁ ይለዋል። ሞኙም በራብ በደከመ አንጀቱ ካብ ለካብ እንሽላሊት ሲያባርር ቆይቶ ተሳክቶለት አንድ የሞተች እንሽላሊት በኪሱ ይዞ እዚያው ምግብ ቤት ይሄዳል። ቅቅል አዘዘና ገና አንዳመጡለት እንሽላሊቱን ከኪሱ አውጥቷት ወደ ላይ አንጠልጥሎ ኡ! ኡ! ይላል። ሰዎቹ ሲመጡ ደረቋን እንሽላሊት እያወዛወዘ እንዴት የሞተ እንስሳ ያለበት ምግብ ለሰው ታቀርባላችሁ? ይላቸዋል። ነገሩ የተገለጸላቸው የምግብ ቤቱ ሰዎች አጭበርባሪ! ብለው በመጥረጊያ አንክተው አንክተው ያባርሩታል።
መለስ ዜናዊም ሆዬ ገና በሥልጣን ላይ ሆኖ ሕወሃት በአማራ፣ በአኙዋክ ወዘተ ላይ ግልጽና ስውር ጄኖሳይድ በምታካሂድበት ዘመን ገና ለገና ቅንጅት ከሥልጣን ሊያባርረን ነው ብሎ የመገንጠያውን ደረቅ፣ መረቅ ያልነካው ፕላን ቢ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ሲያወዛውዝ ነበር። ኢንተርሃምዌይ! ጂኖሳይድ! እያለ። አግአዚን ይዞ እየቀጠቀጠ ባዶ እጁን ሰልፍ የወጣውን ሕዝብ ሲከስ ነበር። ሞኝ አጭበርባሪ! በቅኝ ከመገዛት ቅድመ ታሪክ ውጪ ከሉዓላዊ ግዛት ላይ አዲስ ሀገሮች ለመገንጠል የቻሉበት መንገድ የጄኖሳይድ ክስ ነው። ምእራባውያን ባልካን ሀገሮችን ብትንትናቸውን ያወጡበት ተንኮል በዚህ መሠረት ላይ ነበር። ይህንን በይበልጥ ለመረዳት ወደ ባልካንስም ታሪክ መሄድ ሳያስፈልገን ዛሬ እነትራምፕ የደቡብ አፍሪካ ወራሪና ዘረኛ ነጮችን ከደቡብ አፍሪካ ላይ ለመገንጠል የሐሰት የፍጅትና የጄኖሳይድ ተረት እየተረቱ በፈጣጣ መዝመታቸውን አንባቢ ልብ ይበል። የወያኔም አማካሪዎቿ ይቺኑ አስቀጽለዋት ነው ሕወሃት ፊትም በቅንጅት ዘመን ኋላም በአቢይ ጊዜ ጄኖሳይድ! ጄኖሳይድ! ያለችበት ዋናው ምክንያት። እናም የሐውዜንን ጭፍጨፋ አቀናጅታ የፖለቲካ ትርፍ ያገኘቸው ሕወሃት አሁንም የፖለቲካ ግቧን ለማሳካት የትግራይን ሕዝብ ማስጨፍጨፏ እንግዳ ነገር አይሆንም።
ግንቦት ሃያ 2017 ዓ.ም.
(ወይ አጋጣሚ። ግንቦት 20? ግንቦት ሃያ 1984 የሚገርም ስሜት ነበር የፈጠረብኝ። ሻይ በስኳርና በጨው አንድ ላይ አድርጋችሁ ጠጥታችሁ ታውቃላችሁ? በደርግ መወገድ ስኳር እና በሀገር መፍርስ ጨው ሻይ ተፈልቶ ብትጠጡ እንዴት እንደሚያቅለሸልሽ? ደርግ ወደቀ ብለን ደስታ እንዳይሰማን የሀገራችን ፍርሻ መርዶ በዚያው ቅጽበት ስለሚያስለቅሰን ግንቦት ሃያ እጅግ አጓጉል ስሜትን የፈጠረብን ነበር። )