ድርጅታችን መኢአድ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ድምጽ ሆኖ መቆየቱና ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ መቀጠሉን በአሁናዊይውም ዘመኑን የዋጀ ሰላማዊ ትግሉን እያካሄደ ይገኛል፡፡ ስለሆነም መኢአድ ሀገርን ከጥፋት ህዝብንም ከአስከፊ ረሃብ፣ ስደትና ሞት በማላቀቅ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀድም በህዝብ አመኔታ የተመረጠ ድሞክራሲያዊ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ፤ የሃገርን ታሪክና ህዝባዊነቱን ተሸክሞ በፅናት መታገሉን ቀጥሏል። አሁንም በማይናማር እየተሰቃዩ ስለሚገኙት ኢትዮጵያዊያን መንግስት በህዝብ ላይ በሚያደርሰው ሁለንተናዊ ግፍ ምክኒያት በሃገራቸው ተስፋ ቆርጠው ወደ የመን ሲሰደዱ ማዕበል ተነስቶ ስለጠፉት ኢትዮጲያዊያን ሰብዓዊነት ለሚሰማው ሁሉ ድምፃችንን እናሰማለን።
በሀገር ውስጥም በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በአማራ ፣ በትግራይ እና በኦሮሚያ ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሱን እያሰፋ በመጣው ጦረኝነትና የንፁሃን እልቂት በጦርነት የሚመጣ ሰላምም ሆነ የሀገር አንድነት አለመኖሩን ደግመን ደጋግመን ያለመሰልቸት ትናንትም ዛሬም ድምፃችን በማሰማት ላይ እንገኛለን ይባስ ተብሎ በሀይማኖት መካከል ሌላ ግጭትና ጦርነት ለመክፈት ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲደረግ ሰሞኑን በስፋት አይተናል፡፡
ከዚህ አሳፋሪ ድርጊትም የሚገኝ አንዳች ትርፍ አለመኖሩ በግልፅ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም አማኙ ህዝብም ሆነ አጠቃላይ ማህበረሰቡ እንዲህ አይነቱ ድርጊት ሆን ተብሎ እየተቀነባበረ የሚፈፀም የሴራ ተግባር መሆኑን በመረዳትና አስቀድሞ በመንቃት በማወቅም ሆነ ባለ ማወቅ የዚህ ተራ ተግባር ተባባሪ ባለመሆን ሀይማኖቱን መጠበቅና ማስጠበቅ እንዳለበት እያስገነዘብን ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ጥሪዎች እናስተላልፋለን።
1ኛ ዜጋ ጠል በሆነ አመለካከቱ ወጣቱ በአግባቡ እንዳይማር ተምሮ ስራ እንደያገኝ በማድአግ በሀገሩ ላይ የተለያዩ የስራ አማራጮችን ፈጥሮ እንዲሰሩ ከማድረግ ይልቅ እራሱ መንግስት ደላላ ሆኖ ወደ ውጭ ሀገር በመላክ በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የቀረውን የባርነት ኑሮ ለማሰቀጠል እያደረገ ያለውን የወደቀና ለዘመኑ የማይመጥን የዲፕሎማሲ ሂደቱን እንዲያጤንና እንዲያስተካክል ስንል አጥብቀን እናሳስባለን።
2ኛ በማይናማር እና በተለያዩ ሀገራት እየተሰቃዩ ለሚገኙ ዜጎቻችን አስቸኳይ መንግስታዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እናሳስባለን ።
3ኛ ሀገራዊ እራይ እና ህዝባዊ ተቆርቋሪነት ስሜት በሌለው መንግሥታዊ ስርአት ምክኒያት በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም ለሚሰደዱ ዜጎቻችን ሰው የሆነ ሁሉ ድምፅ እንዲሆናቸው አጥብቀን እንጠይቃለን።
4ኛ አሁንም ይኸው ስርዓት በወለደውና ህገ ወጥ ባለስልጣናት በሚያደርሱት አይለኬ ግፍ፤ ወደ የመንና የሰላም ችግር ወደ አለባቸው ሀገራት ጭምር መሰደድ አማራጭ የሌለው አድርገው መቁጠራቸው የሚያሳየው በሀገራቸው ምን ያህል ግዞተኛ መሆናቸውን ነው። ስለሆነም ይህንን ግፍ ለማስወገድ በጋራ እንቁም።
5ኛ እንደ እስስት መልካችሁንና ሀሳባችሁን እየቀያየራችሁ እንደምሁር ያልሰራችሁትን ፖለቲካ እየተነተናችሁ ባለተጠራችሁበት ድግስ እየተገኛችሁ ጊዜ ጣለው ብላችሁ ስታስቡ የምትሰድቡትን ህዝብ ጊዜው የሱ ሲመስላችሁ ደግሞ እያሞገሳችሁ የራሳችሁን የስልጣን ጥምና ጥቅም የምታሳድዱ የወንጭፍ ፖለቲከኞች ከሀገር አፍራሽ እኩይ ተግባራችሁ እንድትታቀቡ አሁንም ደጋግመን እንጠይቃለን።
6ኛ የሰላም እጦቱ፣ ሥራ አጥነቱ፣ የኑሮው ውድነት በአጠቃላይ ብዙ ችግር ተደማምሮባችሁ ስደትን እንደ አማራጭ የመረጣችሁ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ሀገራችን ኢትዮጵያን ለአልጠግብ ባዮችና ለሀገር ጠል ፖለቲከኞች ሀገርን ለቆ መሄድ እና መሰደድ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይሆን ተገንዝባችሁ ስለሀገር የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል ለራሳችንም ሆነ ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ሀገር እንድትኖረን በጋራ በአንድነትና በፅናት አብረን በመቆም ይህንን አስከፊ ሥርዓት እንድንታገለው ስንል አጥብቀን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
“አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!”
መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም
አ.አበባ
