አምባቸው ዓለሙ (ወልዲያ)
“በውስጣቸው ነጣቂ ተኵላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው መካከላችሁ በመግባት ከሚያሸምቁ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ። በፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾኽ ቍጥቋጦ ወይን፣ ከኵርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁም ጥሩ ዛፍ ሁሉ ጥሩ ፍሬ፣ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል።”ማቴዎስ 7፡15

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንዳሁኗ ቅጽበት ተደስቼ አላውቅም፡፡ ለተወሰኑ ሰዓታት ቲክቶክና ዩቲዩብ እያየሁ ነበር፡፡ በዛሬዋ ግንቦት 2017 በዕለተ ቅ. ገብርኤል ወደምሽቱ እየተጠጋሁ ባለሁበት ለ12 ሩብ ጉዳይ አካባቢ የሆነ መንፈስ ከአልጋየ እመር ብዬ ይህችን ማስታወሻ እንድጽፍ ገፋፋኝ፡፡ በዚህ መልክ ጽሑፌን ጀምሬ አላውቅም፡፡ እርግጥ ነው – የተከታተልኳቸው የቲኪቶክም ሆኑ የዩቲዩብ ዝግጅቶች ከእስከዛሬው የተለዩ አልነበሩም፡፡ የምወደው የመምህር ፋንታሁን ዋቄ ሰሞነኛ ቁጭትና ብስጭት ግን እኔንም የሚጨምር በመሆኑ ለውስጣዊ ደስታየ ሳይሆን ለመጻፌ እንደአንዱ መነሻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ያነሳሳኝ መንፈስ ምን ሊለን እንደፈለገ አብረን እንከታተል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከነእንከኖቿ ለኢትዮጵያ በአሃዳዊ መንግሥትነት ፀንታ መቆየት የበኩሏን አስተዋፅዖ ለዘመናት ስታበረክት መቆየቷ ደረታቸውን ለጣሊያን ቅኝ ገዢ ጥይት የሰጡት የቀድሞው አቡነ ጴጥሮስ ዋነኛና ኅያው ምሥክር ናቸው፡፡ የጣሊያን ሶላቶዎች “ሕዝቡ ለኢጣሊያ እንዲገብር ያግባቡልን፤ አሊያ እንገድልዎታለን” የሚል ተማፅኖና ማስፈራያ ለአቡኑ አቀረቡ፡፡ እሳቸው ግን በተቃራኒው ለጣሊያን የገበረ እንዲወገዝ በመስቀላቸው ዐውጀው የሰማዕትነትን ተልእኮ በማከናወን ከዚህች ቆሻሻ ምድር በክብር ተሰናበቱ፡፡ በእርሳቸው ቦታ የተተኩ የአሁኖቹ ጉዶች ግን ጥቁር ታሪክ እያስቀመጡ ናቸው፡፡
ሃይማኖት ከሥጋዊ ምግባር ከተቀላቀለ በህክምናው የቃላት አጠቃቀም ፊስቱላዊ ሊባል የሚችል ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ የሮማው ጳጳስ ጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ ለቅኝ ግዛት ሲመጣ ባርከውና ቀድሰው ነው የላኩት፡፡ ማውገዝ ሲገባቸው የጣሊያን ሠራዊት ሌላ ሀገርን በባርነት እንዲገዛ መርቀው ላኩ፡፡ ይህም ከክርስቶስ አስተምህሮ ውጪ ነው፤ ኃጢኣት ነው፤ ወንጀልም ነው፡፡ ስለዚህ ጳጳሱ በምድርም በሰማይም የሚያስጠይቃቸውን መጥፎ ተግባር ፈጸሙና ስማቸው እስካሁንና ወደፊትም እስከዓለም ፍጻሜ በክፉ እንዲነሳ በራሳቸው ላይ መጥፎ ታሪክ ሠርተው አለፉ፡፡ ሆድንና ሥጋዊ ፍላጎትን አለመግራት ለዚህ ይዳርጋል፡፡ ከመለኮታዊ ትዕዛዛትና አስተምህሮ መውጣትና አእምሮን ከዕውቀትና ጥበብ ማዕድ ማራቅ ጦሱ ለሀገርም ይተርፋል፡፡ የ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሮደሪጎ ቦርጊያ (በጵጵስና ስማቸው ሳዊሮስ ማለቴ Alexander VI የተሰኙ ፖፕም በግልጽ የሦስት ልጆች አባት እንደነበሩና ሴዛር ቦርጂያ የተባለውን ልጃቸውን ለፖፕነት እንዳሳጩት ተጽፏል፡፡ ወራሪን ባርኮ መላክም ህገ ቀኖናን ማፍረስም ያው ነው – እኩል ኃጢኣት፡፡ “ምን ይዘባርቃል” ለሚለኝ ምላሽ መስጠቴ ነው፡፡ ብቻ … ምን አለፋህ … በሃይማኖት መሪዎችና በሃይማኖት አባቶች ዙሪያ የማይሰማ ነገር የለም፡፡ የፖለቲካ መሪዎችን ክፋትንና ተንኮልን ማን ያስተምራቸው ታዲያ?
ከፍ ሲል እንደተገለጸው “የቄሣርን ለቄሣር፤ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” በሚለው ክርስቶሣዊ መርኅ ካልተጓዝን ሕይወታችን ይመሰቃቀላል – ጨርቃችንን መጣል ሳይጠበቅብን ልክ እንደአቢይ አህመድ ለይቶልን ልናብድም እንችላለን፡፡ አሁን የተቸገርነው ምድራዊ መሪዎችና የሰማዩን አባታችንን በምድር የሚወክሉት “መንፈሣዊ አባቶቻችን” ፍጹም አንድ ሆነው በሥጋም በነፍስም የሕይወት መጨለም ስለገጠመን ነው፡፡ ፂሙን አንዠርግጎና ጥቁር ካባውን በጥቁር ቀሚሱ ላይ ደርቦ ሲታይ የነፍስ ድኅነት አባት ይመስልና በውስጡ ግን በርግጥም ውስጡን ለቄስ የሆነ የሣጥናኤል ደቀ መዝሙር ይሆናል፡፡ ይህን መሰሉ ሰው በሲኖዶሱ ውስጥ አንድና ሁለት ቢሆን በኅሩያኑ በተሸፈነና ጉዳቱ በቀነሰ፡፡ አሁን ግን የተኩላና ቀበሮው ብዛት ከበጉ አየለና መንጋውን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ጭምር እየበተነው መጣ፡፡ የሦዶም ኃጢኣት ሳይቀር እንደሚፈጸምበት የሚወራበት መቼም ስም አይገዛምና “ቅዱስ ሲኖዶስ” የሚባለው የብልሹ እረኞች ካምፕ በሦዶምና ገሞራ የወረደውን የዲኝ እሳት ዶፍ እየጠራብን ነው፡፡ አንድዬ ይሁነን፡፡
በመሠረቱ ሃይማኖት ሰማያዊ ሲሆን ፖለቲካ ምድራዊ ነው፡፡ ምድራዊ ጊዜያዊ ነው፡፡ ሰማያዊ ደግሞ ዘላለማዊ ነው፡፡ ሁለቱ dimensional difference አላቸው፡፡ ምድራዊውን የሚመራ ከሰማያዊው አመራር ጋር ኅብረትም ሆነ አንድነት የለውም፡፡ ለዚህም ነው ክርስቶስ “ነፍስን የሚገድልን ፍሩ እንጂ ሥጋን የሚገድሉትን አትፍሩ” ሲል ያስተማረን፡፡ ይሁንና ሊቀላቀሉ የማይገባቸው ተቀላቅለው አሣራችን በዛ፡፡
ሃይማኖተኞችን ባለችኝ ንባብ ላይ የተመሠረተች ጭላንጭል ዕውቀትና የሕይወት ተሞክሮ በሚገባ አውቃቸዋለሁ ብል ድፍረቴ ለከፋ ስህተት ያጋልጠኛል ብዬ አልገምትም፡፡ ካቶሊኮች ጋር ነበርኩ፡፡ በሚገባ አውቃቸዋለሁ፡፡ ከዋናው ፖፕ እስከተራው ፍሬር (ከቄስ በታች ያለ በአማርኛ “ወንድም” የሚባለው)፣ ከጥንታውያኑ እስካሁኖቹ – በአብዛኛው መቶኛ አውነት ሊሆን የሚችል ነገር ከተለያዩ ምንጮች ተገንዝቤያለሁ፡፡ ከኃጢኣት መራቅ እጅግ ከባድ መሆኑ አይካድም፡፡ የምድር ሕይወት አስቸጋሪ ነውና፡፡ ከሰማይ ወደምድር የተጣለው ሣጥናኤል እያለ ማንም ንጹሕ ሊሆን እንደማይችል ደግሞ በብዙ አብነቶች እያስረገጡ መናገር ይቻላል – ጊዜ ይፈጃል እንጂ፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ኃጢኣት መሥራቱ የነበረና ያለም ነው – እንደእኛዎቹ ጉዶች ያላንዳች ሀፍረትና ይሉኝታ ለዝንታለሙ በኃጢኣት ቆርቦ በውሸት ሲኖዶስ ስምና በሃይማኖት ሽፋን ሥጋዊ ፍላጎትን አንድም ሳትቀር እያሟሉ የማይተገበር ቃለ ዐዋዲ አስቀምጦ አምላክን ለማታለል መሞከር ግን ስህተትም ኃጢኣትም ነው፡፡ በዚያን ሰሞን በ600 ሺህ ብር ገደማ የተሸጠውን የቤቱ በር ፈርሶ የወጣ የበሬ ኮርማ የመሰለ ጳጳስ የሚታየው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ነገሬን በጣም ላሳጥር፡፡ አለበለዚያ “ቴዎፍሎስ እንትና የሚባል ልጅ አለው፣ እንትና የሚባለው ሊቀ ጳጳስ እገሊት የምትባል የነጭ ሴት ቅምጥ ነበረችው” እያልኩ እቀጥልና ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያኑ ሥር ተሸጉጦ የሚያጭበረብረውን ባህታዊ ነኝ ባይ የሰው ሚስት ደፋሪ ወንበዴ ሳይቀር ለመጥቀስ ልገደድ ነው፡፡ ሃይማኖትንና ፖለቲካን ተታኮ የገጠመን አጠቃላይ ኪሣራ እኮ ተወርቶ አያልቅም፡፡
ሲጀመር ሃይማኖት ይበልጥ የሚያምረው በሥራ (በግብር) እንጂ በዐውደ ምሕረት ላይ ስብከት አይደለም፡፡ እርሱንማ ሰይጣንም በሚያማልል ድምፁና በሚያስቀና ዕውቀቱ ሚሊዮኖችን ከእስልምና ወደክርስትና ወይም ከክርስትና ወደ እስልምና በደቂቃዎች ውስጥ ሊለውጥ ይችላል፡፡ ስብከቱንም፣ ሰባኪውንም፣ መዝሙሩንም ዘማሪውንም፣ ቅዳሤውንም፣ ቀዳሹንም፣ ምን አለፋችሁ ሁሉንም አየነው፡፡ ግን ሁሉም ዜሮ ዜሮ ሆነና አሁን ላለንበት ምስቅልቅል ሕይወት ተዳረግን፡፡ የሚታየው ሁሉ ዐይንን ከማጥበርበር ባለፈ የእግዜርን ትኩረትና ምሕረት ሊስብ አልቻለም፡፡ ይቺ አንዲት እንጀራ የሚሏት ነገር እግዜር ይይላት!
ብሥራት አለኝ፡፡ እደርስበታለሁ፡፡ አሁን ወንድሞቼና እህቶቼ – በእግዚአብሔር መቀለዳችንን ወደንና ፈቅደን ለመቀጠል እስካልፈለግን ድረስ – ይህም ዋጋ ያስከፍለናል – ያለንን ሲኖዶስ ቅዱስ ብንል ሰማይ ብቻ አይደለም ምድርም ትስቅብናለች፡፡ ሰው ፈርቶ ባይስቅ ዛፍና ቅጠሎች ከትከት ብለው ይስቁብናል፤ ይሣለቁብናልም፡፡ ዘረኝነትን የሚያበረታታ ብቻ ሳይሆን በቋሚ ማዕከላዊ ዓላማነት ዘረኝነትን የሚያራምድ ሲኖዶስ ኢትዮጵያ ሊኖራት አይገባም፡፡ አቶ ሳዊሮስ ለበርካታ ክርስቲያኖች መገደል ዋነኛ ምክንያትና ተጠያቂ እንደሆነና በዚያም ምክንያት በቤተ ክርስቲያን ተወግዞ ከክህነትም ተወግዶ እንደነበር መምህር ፋንታሁን ሲናገር ሰምቻለሁ፡፡ ሁሉን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሥልጣንና የኃላፊነት ቦታዎች ኦሮሞ ይያዘው ቢባል እንኳን አካሄዱ እንዲህ መሆን አልነበረበትም፡፡ ይህ ዐይን ያወጣ የቁጭ በሉ ሥራ የትም አያደርስም፤ ቀድሞ የሚያጠቃው ደግሞ “ብፁዓን አባቶች” እየተባለ ስያሜው ሳይገባቸው የሚቀለድባቸውን የሲኖዶስ አባላትን ነው (ቅዱስነትና ብፁዕነት ሲያምርህ ይቅር ወንድሜ – የቡና ቤት ጨፋሪና አጫፋሪ ሰብስበህ ጳጳስ ብታደርግ ሰውን እንጂ ልብና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክን አታታልልም)፡፡ በርኩሰት ሥራ የማይተናነሱ በሃይማኖታዊ ዕውቀትና በቃለ እግዚአብሔር ግን የሚበላለጡ እነዚህ ዓለማውያን ሥርዓት ባለው መንገድና መጠፋፋት ሳይኖር ቦታ ቢቀያየሩ የተለመደ ነውና ምንም አልነበረም፡፡ የአሁኑ ግን የቤተ ክርስቲያንን ልማዳዊ ሥርዓተ ቀኖና ፍጹም በተቃረነ መልኩ ኦሮሞን የሁሉም የሃይማኖትና የፖለቲካ ቦታዎች ባለቤት ለማድረግና ታሪክን ለማጥፋት የተነሣ ኃይል በመኖሩ ይህን ማጋለጥና ወደአምላክ ፍርድ ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ It is a matter of choosing the less evil based on common characters such as degree of immorality and cruelty as well as level of intelligence and academic status, regardless of their ethnic group.
በወጣትነቴ ያየሁት አንድ ፊልም አሁን ትዝ አለኝ፡፡ ርዕሱ “The Kidnaping of the President” የሚል ይመስለኛል፡፡ ዋናው ፕሬዝደንት በአሜሪካን ጠላቶች ታግቶ ምክትሉ ሊያስፈታው እታች እላይ እየተሯሯጠ ሳለ የምክትሉ ሚስት ባሏ ፕሬዝደንት እንዲሆንላት ፈለገችና የተጠመደበት በሰዓት የተሞላ ፈንጅ ሊገድለው ደቂቃዎች የቀሩትን ፕሬዝደንት ከእገታው የማስፈታት የድርድር ጥረቱን ችላ እንዲል እንደሚከተለው ልታግባባው ትሞክራለች፡፡ እሱ ያላት ነው ደስ የሚለኝና ለአኃው ሲኖዶሳውያንም ላስተላልፍ የወደድኩት ውስጠ ወይራ፡፡ እንደዚህች ያለች ሴት ከሔዋን ጅምሮ ብትኖርም እንደዚህ ያለ ባልም ከአዳም ጀምሮ አለ፡፡
Wife: “Don’t you want to be the President of the US?”
Husband: “Well, I would like to be the President of the US throughout my life, but not in this way.”
ከዚህ ሁሉ የሲኖዶስ አባል አንድም ለነፍሱ ያደረ ሰው ማጣት በርግጥም የወረደብን እርግማን ቀላል አለመሆኑን በግልጽ ያመለክታል፡፡ የዓሣ ግማቱ ከአናቱ መባሉ ትክክል ነው፡፡ ከራስ የገማ ከግርጌ ንጹሕ እንዲኖር መጠበቅ ደግሞ የሚቻል አይደለም፡፡ አንድ ጳጳስ ሚስትና ድስት ካለው ለነፍሱ ሳይሆን ለሥጋው ነው የሚያድረው፡፡ በዚያ ላይ ለመጰጰስ 3 ሚሊዮን ብር ተከፍሎ፣ ለመቀሰስ በብዙ መቶ ሺዎች ተከፍሎ፣ ለመደቆን ብዙ ሺዎችን ተከፍሎ፣ ከዝቅተኛ ገቢ ደብር ወደከፍተኛ ገቢ ደብር በአለቅነት ለመዛወር በብዙ መቶ ሺዎች ተከፍሎ፣ ባልን/ሚስትን እየሸወዱ ከየንስሃ አባት/ልጅ ዲቃላ ተወልዶ፣ ገመናን ለመሸፈንና በማዕረገ ክህነት ለመቀጠል በመቶ ሺዎች ጉቦ ተከፍሎ፣ በግራም በቀኝም በላይም በታችም በሙስና ተጨመላልቆ፣ ወዘተ. የት እንደሚደረስ በቅርቡ የምናየው ይሆናል፡፡ ሰይጣን ሥልጣኑ ውስን ነው፡፡ በሥነ ቃላችን “ሰይጣን ቆንጆ ድስት ይሠራል መግላሊቱን(ክዳኑን) ግን አይሠራም” ይባላል፡፡ በመሆኑም አጅሬ ሣጥናኤል የሚሠራውን ዕኩይ ድርጊት ሁሉ ልብሰ ተክህኗቸውን አሣምረው ቤተ ክርስቲያንን በተቆጣጠሩ “ጳጳሣት”ና “መነኮሳት” የቻለውን ሁሉ አድርጎ አሁን ከአቅሙ በላይና ሊቆጣጠረው ወደማይችልበት ከፍተኛ ደረጃ እየደረሰ ነው፡፡ አንድም የሚቃወም ጳጳስ አለመኖሩ ደግሞ መጽሐፉ “ሁሉም በኃጢኣት ሥር ወድቋል፤ ከመካከላቸው ማንም ንጹሕ የለም” ያለውን ያስታውሰናል፡፡ ስለሆነም ክርስቶስ በምድራዊ ሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ በእግዚአብሔር ስም ንግድና ዘረፋ ያጧጡፍበት በነበረ አንድ ምኩራብ ተገኝቶ የንግድ ዕቃዎቻቸውንና ሸቀጦቻቸውን በካልቾ በማለት ድራሻቸውን እንዳጠፋው ሁሉ የኛንም “ቤተ ክርስቲያን” ሊመነቃቅራትና እውነተኛ አባቶችን ከያሉበት እውነተኛ ገዳም አሰባስቦ ሊሰይምልን ሰዓቱ እጅግ ተቃርቧል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም፣ አራት ኪሎም ይጸዳሉ፡፡ ይሄ በመተትና በደንቃራ የመጣ አቢይ የሚባል ቀውስ ጥግ ሊይዝ አበቅቴው ደርሷል፡፡ የብሥራቴ ጅማሮ ነው፡፡ ትንሽ ልቀጥልበት፡፡
አማራ ኮርቶ ያሸንፋል፡፡ አማራ የሚያሸንፈው ኢትዮጵያ መነሣት ካለባት አማራ ማሸነፍ ስለሚኖርበት ነው – የሌላውንማ እስኪያቅረንና እስኪያንገሸግሸን አየነው፡፡ አማራ ያሸንፋል ስልህ ደምህ የሚፈላ ካለህ ተወው ይንተክተክ፡፡ አማራ የሚያሸንፍበት ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ እዚህ ማንሳት ለቀባሪ የማርዳት ያህል ነው፡፡ ባጭሩ ግን አማራ ከኢትዮጵያ በቀር የሚኮራበት የነገድም ይሁን የጎሣ ማንነት ያልነበረው በመሆኑ ነው፡፡ ያልነበረው ስልህ ይግባህ፡፡ አሁን አሁን የሚታዩ ጊዜ ወለድ የማንነት ነፀብራቆች እንደጤዛ ይረግፋሉ፡፡ አይዘልቁም፡፡ ወደነበርንበት የጋራ ማንነት እንመለሳለን፡፡ የአሁኑ በጭራሽ ስለማያዋጣን፡፡ የኔ ልጅ 25 መቶኛዋ ኦሮሞ ናት፡፡ የልጄ ሚስት ከ75 መቶኛዋ በላይ ኦሮሞ ናት፡፡ የሷ ልጅ – ማለትም የልጄ ልጅ ከ40 በመቶ ባላነሰ ኦሮሞ ነው፡፡ እኔን በዚህ ስሌት ፈትሼው ስለማላውቅ ከኢትዮጵያዊነት ባነሰ የኔን ማንነት አላውቀውም፡፡ በዚህም አላዝንም፡፡ ተረት እየተረትኩ እንዳይመስልህ፤ “ወዴት ጠጋ ጠጋ!” እንዳትለኝ ደግሞ – እውነቴን ነው፡፡ በዚህን መሰሉ ድርና ማግነት የተወሳሰበን ሕዝብ በ27 እና በ7 ዓመታት ውስጥ ከመሬት ተነስተህ ልበታትነው ብትል አቢይ አህመድ እያየው ያለውን ምድራዊ አበሳ ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖርህም፡፡ ይህን መሰል ጥረቶች ችግር አያደርሱም እያልኩህ እንዳልሆነ ግን አንተም ትረዳኛለህ፡፡
እናም አማራነት ያሸንፋል – አሻሻልኩልህ፡፡ ከየት መጡ የማይባሉ አማሮች ድንገት ከአንድ አቅጣጫ ይመጡና ይህን የመርገምት ጨርቅ አቢይ አህመድ የሚባል ጂኒ ከነመንጋው የዶግ ዐመድ ያደርጉታል፡፡ ብልጽግና የሚባል ፀረ ሃይማኖት፣ ፀረ አማራ፣ ፀረ ትግሬና ፀረ ኢትዮጵያ የሆነ አጋሰስ መንጋ በያለበት እንደቅጠል ይረግፋል፡፡ በሠፈረው ቁና ይሠፈርለታል፡፡ “ወላድ በድባብ ትሂድ” የሚያስብሉ ጀግኖች ተዘጋጅተው ጊዜያቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው፤ ጦርነቱ በግልጽ እንዲጀመር በናፍቆት የሚጠብቁና የፍልሚያው ፊሽካ እስኪነፋ የሚቁነጠነጡ አማሮች ይታዩኛል፤ አማሮችም ብቻም አይደሉም ለነገሩ፡፡ ኦሮሞን ጨምሮ በሣጥናኤሉ አቢይ ልባቸው የደማ የሁሉም ነገድ ጀግኖች ከአማራ ጋር ተሠልፈው ይህን ዘረኛና ከፋፋይ የኦሮሙማ ዐረመኔ ቡድን እንደጌሾ ሲወቅጡትና መውጫ መግቢያ ሲያሳጡት ቁልጭ ብሎ ይታየኛል፡፡ አማራን ተመስለው በአማራ ትግል ውስጥ ሠርገው የገቡ ሆዳሞችና ኅሊናቢሶች በመረጡት መንገድ ተጉዘው የመጨረሻ ዕጣ ፋንታቸውን ከኦሮሙማው መንጋ ጋር አጣምረዋልና ለዘር አይተርፉም፡፡ ሽጉጥ በደረታቸው ታጥቀውና በአንጋች ወታደር ታጅበው መስቀልን ያረከሱ ጳጳሣትና ካህናትም የወንድማቸውን የዲያቢሎስን የሽንፈት ጽዋ ይጎነጫሉ፡፡ እናም ታዲያን ቀኒቷን በጉጉት እንጠብቅ፡፡ እነአይነጋ መስሏት ምን እንደሚውጣቸው ለማየት ያብቃን፤ ሆኖም ከፍተኛ ዕልቂት የተደገሰልን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፤ ያለመስዋዕትነትም ድል የለም፡፡ እንጸልይ፡፡ እውነተኞቹ አማሮች በፋኖ ስምም ይምጡ፣ በሌላ አማራጭም ይከሰቱ መምጣታቸው ግን ከነባራዊው እውነታ አኳያ ጭምር ሲታይ የፈጠጠ እውነት ነው – ቀደምት ትንቢቶችም ጭምር የደገፉት፡፡ ውይ … በስመ አብ … ዛሬ የቀረበኝ መልካም መንፈስ አሁን ለቀቅ አድርጎኝ ሲሄድ ተሰማኝ፡፡ በሉ እኔም ምን እንደጻፍኩ ተመልሼ ላንብበውና ወደምልከው ልላክ፡፡