“ፋኖ ማለት በየትኛውም የሀገራችን አካባቢ የሚኖር የሀገር ባለውለታ ማለት ነው” ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ

May 30, 2022
"ሀገርን የሚረግመው ሽማግሌ ብቻ አይደለም! ለሀገሩ መስዋዕት የከፈለ ወጣትም ተገቢውን ዋጋ ካላገኘ ይረግማል።"

ሰሞኑን ፋኖ ትጥቅ ይፍታ ተብሏል ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨው ውጅንብር በሕዝቡ መረበሽን ፈጥሮ፥ ውጥረትን አንግሦ፤ የውጅንብሩ ማጀቢያም በጥርጣሬ በሚያዙ ሕዝብ ባለውለታችን ናቸው ብሎ ከሚፈርጃቸው የሚመደቡ አንዳንድ መሪዎች ጭምር የተያዙበት አግባብና የተጠረጠሩበት ምክንያት በመንግሥት ሚዲያ አለመገለጹ ሰውን የመረጠውን መንግሥት ከማመንና ለምን? ብሎ በሥርዓት ከመጠየቅ ይልቅ እንዲመራው ያልመረጠውን ፌስቡክ በማመን ወደ ስጋትና ውጥረት አዝማሚያ እንዲገባ ጫና ፈጥሮበታል። ይህ መጥፎ አዝማሚያ ከተጋረጠበት አካባቢ አንዱ ወልድያ ከተማ ሲሆን፤ መጥፎውን አዝማሚያ ለመቀልበስ “በሀገሩ የማያገባው ባላገር የለም” በማለት ከአዲስ አበባ የቅዱስ ሲኖዶሱን ጉባኤ አቋርጠው ወልድያ የዘለቁት ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ሁሉንም አካል የቃኘ እና ላልተበከለ የሠላም አየር መኖር ይበጃል ያሉትን አባታዊ ምክርና ተግሳጽ ለግሰዋል። እኛም ከሞላ ጎደል እንዲህ ከትበነዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊትን፤ ልዩ ኃይልን፤ ፋኖን ለመንቀፍ ቀርቶ ለመገምገም የሚያስችል ማንነት የለንም። ሰው ትርፍ ነገር እየሰጠ ከጀርባ ሆኖ አግዞ ይሆናል። እነሱ ግን የሚሰጡት ሕይወታቸውን ነው። ከፈጣሪ በታች አካባቢያችን፣ ሀገራችን፣ የሠላም አየር እንዲተነፍስበት የሚያደርጉ ናቸው። ምን አልባት በሰማነውና በተረዳነው ልክ በእነሱ ስም የሚነግዱ አንድ አንድ አረሞች ካሉ እንዲወያዩበት ለእነሱ በመጠቆም እራሳቸው ፈጥነው እንዲያርሙት የመጠቆም ያህል ነው የእኛ ድርሻ በማለት አመላክተዋል አቡነ ኤርምያስ።

ሳይመዘገብ የሚሮጥ አትሌት የለም። ይህን ያህል ኪሎ ሜትር እሮጠህ ብታሸነፍ ይህን ያህል ገንዘብ ትሸለማለህ። የወርቅ ሜዳልያ ታጠልቃለህ ተብሎ ነው። ፋኖ ግን የሚሮጠው ሀገሬ በነጻነት መቆየቷ፤ ወገኔ በሠላም መኖሩ ለእኔ ሽልማት ነው ብሎ ነው። ደሙን የሚያፈሰው፥ የሚራበው፥ የሚጠማው በፍፁም ተችዎቻቸው ሳንሆን አክባሪዎቻቸው ነን በማለት በተጠየቃዊ ንፅፅር ጭምር አስረድተዋል ብፁዕነታቸው።

አቡነ ኤርምያስ የግል ማኅበራዊ ሚዲያው ተፅዕኖ የመረጃ መዛባትም ይሁን እርስ በእርስ አለመተማመን መጠራጠር ጋር ተያይዞ ከጊዜ በኋላ መንግሥት አወጣ እየተባለ የሚወራው መመሪያ ፋኖን ይጎዳል የሚለው ሕዝባችንን ግራ እያጋባው፣ እያስጨነቀው ነው። ምንም ይሁን ምንም ግን ወጥ የሆነ የእዝ ሰንሰለት ከሌለን ሀገር የማቆየት አቅም አይኖረንም። ደካሞች ነው የምንሆነው። “እርስ፡ በእርሷ፡ የምትለያይ፡ መንግሥት፥ ትጠፋለች።” ነው መጽሐፍ የሚለው። ሁላችንም በየፊናችን ፈራጅ፣ ፈላጭ ቆራጭ ከሆነ አያሰነብተንም። የእዝ ሰንሰለት መጠበቅ፣ መከተል ይገባል። ተቀራርቦ በግልፅ መነጋገሩ ከውጅንብር ያድናል ሲሉም መክረዋል።

ፋኖ ማለት በየትኛውም የሀገራችን አካባቢ የሚኖር የሀገር ባለውለታ ማለት ነው። ከበርካታዎቹ የኢትዮጵያ ባለውለታዎች መካከል ለማሳያ አንዱን ብንጠቅስ ፋኖ ማለት በላይ ዘለቀ ማለት ነው። በላይ ዘለቀ አባቱ በኃይለ ሥላሴ ባለስልጣናት ተገድሎበት የአባቱን ደም ለመመለስ ከመንግሥት ኮብልሎ በሽፍትነት እየኖረ ሳለ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሀገር ወጡ፤ ሀገርን፥ ወገንን፥ ታሪክን፣ እምነትን የሚያጠፋ የውጭ ጠላት ገባ ተብሎ ሲነገረው በደል ያደረሰብኝን ሹማምንት ከጠላት ጋር ሆኘ የበቀል ሥራ ልስራ አላለም። በ24 ዓመት ዕድሜው ስንቅ ሳይኖረው፤ አሰልጣኝና አደራጅ ሳይኖረው ያለውን ጥቂት ኃይል አደራጅቶ 5 ዓመት ለጣሊያን ጦር እሳት ረመጥ የሆነ ለሀገር ለወገን ጀግና ባለውለታ ነው ሲሉ ታሪክን በምልሰት በማሳያነት አውስተዋል አቡነ ኤርምያስ።

ታሪክ እንዳስቀመጠው ከ5 ዓመት በዱር በገደል የአርበኝነት የትግል ኑሮ በኋላ ጠላት ወጥቶ አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ “ጃንሆይ ሀገሩንም፣ ሰራዊቱንም ከእነ መሣሪያው ይረከቡኝ እኔ ተራ ሰው ነኝ አርሼ፣ አምርቼ እበላለሁ።” ነው ያለው በላይ። ትክክለኛ የፋኖ ባህሪም ይህ ነው። መንግሥት ሆኘ ልጋተር አላለም። ጃንሆይም ጀግንነትን ከትህትና፤ ማስተዋልን ከወጣትነትና ከደግነት አጣምሮ የያዘውን አርሶ አደር የቢቼና አስተዳዳሪ ሁን ስምህም ደጃዝማች በላይ ይባል ብለው ሹመውታል በማለት ብፁዕነታቸው አስረድተዋል።

ኋላ ግን መጥፎ ባንዳዎች፣ ምቀኞች፣ ስሙን ያለ ስም አጥፍተውት ያ ትክክለኛ የሀገር ባለ ውለታ ጀግና የማይገባውን አግኝቶ በስቅላት ታንቆ ነው የተገደለው። ከመሰቀያው እንጨት ላይ ከመውጣቱ እና ሕይወቱ ከማለፉ ቀድሞም “ኢጦቢያ አገልግየሽ ከሆነ ወንድ ልጅ አይውጣብሽ፤ ካለገለገልኩሽ ደግሞ ፈጣሪ ነፍሴን አይቀበላት።” ነው ያለው። እንደበላይ ዘለቀና አሁን ስማቸውን ለመጥቀስ ጊዜ የሚገድበን የሱን ዓይነት ተገቢው ዋጋ ያልተሰጣቸው በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ይኖሩ የነበሩ የሀገር ባለውለታዎች እርግማን በኢትዮጵያ ላይ አልደረሰም ብዬ አላምንም። ከዚህ መማር ያለብን ሀገርን የሚረግመው ሽማግሌ ብቻ አይደለም። ለሀገሩ ውለታ መስዋዕት የከፈለ ወጣትም ተገቢውን ዋጋ ካለገኘ ይረግማል እና መልካም፣ ጥሩ ባለውለታዎችን እንዳንጎዳ ልንጠነቀቅ ልናስተውል ይገባል በማለት በአጽንኦት መክረዋል አቡነ ኤርምያስ።

ሕዝብም እንጠንቀቅ መሪን አንተች ሳይሆን መሪ የተባለን ሁሉ መቱን እየሰደብን፣ እየነቀፍን መልካም የሚሰሩ ወጣት መሪዎች እንዳያዝኑብን፤ ከልቡ ባለ አቅሙ ጥሩ ለውጥ ለማምጣት እየጣረ፣ እየደከመ ያለ ወጣት መሪ አዝኖ ከሄደ ይኸ እርግማን የማይደርስ እንዳይመስለን፤ ጥሩ መሪ ያሳጣኝ ብሎ በራስ ላይ መፍረድ ይሆናል ሲሉም አሳስበዋል አቡነ ኤርምያስ።

ሌላው ተባብረን መክረን ልናርመው የሚገባው በየፈርጁ ያለውን ለምድ ለባሽ እና በለው በለው ባይ የመንጋ ባህሪ የያዘውን አካል ነው። በእኛ መጽሐፍ “የበግ ለምድ የለበሱ ሀሳውያን ነቢያት የሚባሉ።” አሉ። በፋኖ ስም የሚነግዱ የፋኖን ለምድ ለባሾች ካሉ መንግሥት ብቻውን አይደለም ማረም ያለበት እራሱ ትክክለኛው ፋኖም ቀዳሚ መሆን አለበት። ፋኖ በባህሪው አይኮፈስም፤ ከእኔ በላይ ጀግና የለም አይልም ልክ እንደ እነ በላይ ዘለቀ ትሁት፣ ባለ ትእግሥት ነው። አሁንም ብዙ በላይ ዘለቀዎች አሉ ከሕይወታቸው ባሻገር የሱቅ ወረታቸውንም ይዘው፣ መኪናቸውንም ሰጥተው የዘመቱ አሉ። እነሱ ለምድ ለባሹን ከሕዝብና ከመንግሥት ጋር ሁነው ሊያርሙና ሊያስተራርሙ ይገባል ሲሉም አስረድተዋል አቡነ ኤርምያስ።

አቡነ ኤርምያስ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ማስከበር፤ የዜጎችን በሠላም የመኖር ዋስትና የማረጋገጥ ኃላፊነቱን አለመወጣቱ ነው ብዙ ጣጣ እያመጣ ያለው። የሕግ የበላይነትን ያስከብር። ፍትህን ያረጋግጥ፣ መረጃ በመስጠትም በግል ማኅበራዊ ሚዲያ አይቀደም። መረጃ በመስጠትም በመቀበልም ይፍጠን ይህ ከሆነ ሕዝቡ በፌስቡክ ዘመቻ ግራ አይጋባም። በዜጎች ላይ አደጋ እንዳይደርስ የመጠበቅ ኃላፊነቱን በትክክል ይወጣ እንጅ ለቅሶ ደራሽ ከመሆን ተግባር ይውጣ። አጥፊን ይጠይቅ ልል አይሁን አጥፊ ሲቀጣ አፉ ባይናገርም አእምሮው አጥፍቼ እኮ ነው ብሎ ማመኑ አይቀርም። ንጹህ ግን ያለጥፋቱ ታስሮ እንዳይማቅቅ ጥንቃቄ ይደረግ በማለት ገልጸዋል።

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችም ኃላፊነታችንን በተገቢው መንገድ እንወጣ ያሉት ብፁዕነታቸው፤ አካባቢን፣ ሀገርን የሚያስመሰግን ትውልድ ለመቅረጽ እንትጋ። አሳፋሪ ትውልድ እንዳይበራከት የመስራት ኃላፊነት አለብን ብለዋል።

ብፁዕነታቸው አክለውም ስህተትን በሚዳፈሩ ውሱኖች ዛሬም ሌላ ስህተት እንዳይደገም መጠንቀቅን ያሻል። ፖለቲካ ነገ መቀየሩ የማይቀር ነው። በእኛ ዕድሜ የኢትዮጵያና የኤርትራ ፖለቲካ ተቀይሮ አይተናል። የኢትዮጵያ ሕዝብም የኤርትራ ወገኖቹን ቤት ጠብቆ ያስረከበ ደገኛ፣ መልካም ዜጋ መሆኑን በተግባር አይተናል። ለነገው ሕይወት ከትናንት መማር ነው ያለብን ብለዋል።

መጨረሻም ብፁዕነታቸው በአምስት ወራት የጊዜ ቆይታ ብዙ በአእምሯችን የተሳሉ ለመናገር የሚከብዱ አሰቃቂ ነገሮችን አይተናል። ራበኝ እያለች የምታለቅስ እናት፤ ምን ልቅመስና ልጄን ላጥባ የምትል እመጫት፤ አልደፈርም በማለቷ በጥይት የተመታች እህት ድጋሜ እንዳናይ አደራ ሁላችንም የድርሻችንን በመወጣት የሰላሙ አየር እንዳይበከል እንስራ እንጸልይ ብለዋል።

ወልድያ ከተማ ኮሙኒኬሽን

ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ባለሀብቶችን በማገት እና በማስፈራራት ብር በጠየቁ የሰራዊቱ አባላት ላይ ክስ ተመሠረተ

Next Story

ዘመነን መያዝ ያልቻለዉ የመንግስት ሰራዊት የእናቱን ቤት በጥይት ደብድቧል። – አስረስ ማረ ዳምጤ

Go toTop