ይድረስ በቅርብና ርቀት የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚከነክናችሁ፣ በአገራችን የውስጥ ትርምስ ስሜታችሁ እንደኔው ለተጎዳው ወገኖቼ – ይቺ አጭር ማሳሰቢያ ድንገት ካሸለባችሁበት እንድታነቃ ታስባ ነውና በፅሞና ተከታተሉኝ።
ባሁኑ ሰአት፣ ለምን አሜሪካ ይህን መሰሪ HR6600 የሚሉትን ህግ ልትጥልብንና ልታፀድቅ ላይ ታች ትላለች? እንደው ስታስቡት አለ ፕላን የተደረገና በግርግር መሃል እንደተበየነብን ሆኖ እንደማታዩት እገምታለሁ። ከሆነ እሰየው፣ ካልሆነ እስቲ የኔን ግምት ላስቀድም።
፩) ባለፉት ወራት በተለይም ጁንታው የአማራውንና አፋሩን ግዛቶች ከወረረ በሁዋላ ኢትዮጵያዊነት በ ፬ቱም ማእዘናት እየፈነጠቀ መውጣቱን ፅልመቶቹና ጌቶቻቸው ምቾት አልሰጣቸውም። ስለሆነም ይህን የመስበርያ እቅድ በማስፈለጉ
፪) በትዊተርና በተለይም በዛች ብርቅዬ ሄርሜላ የተጀመረው የ #NoMore ዘመቻ ከወገን አልፎ በጥቁሩና ሌላው አለም እንደ ሰደድ እሳት በመሳለጡ ጠላቶቻችን እንቅልፍ በማጣታቸው ምክንያትና ኢትዮጵያ በዶር አቢይ አመራር ወደሁዋላ ፊቷን ላትመልስ መቁረጧን በመገንዘባቸው፣
ለ 30 አመታት ያህል ልክ እንደጁንታው ባህሪያችንን ያጠኑት እነ ሱዛን ራይስ የሆነ ስትራቴጂ መንደፍ አስፈለጋቸው። ይህም እንደምገምተው እያቆጠቆጠ ያለውን የኢትዮጵያዊነት ስሜት መግደያ ዋናው መሳርያ እኛን መአት ቦታ ከፋፍሎ ከአቢይ አመራር መነጠል ነው። ለዚህም ከባድ በጀት ለመመደባቸው በግልፅ የሚታይ ነው።
ወገኖቼ ንቁ! እንንቃ!!
ከመቼ ወዲህ ነው አሜሪካ ሆነች አውሮፓ የአማራው ህይወት የገደዳቸው? እነሱዛን በደንብ አጥንተውናል። በ”ደጉ” ጊዜ ጎዝጉዘው ከፅልመት ውላጆች ጋር እየተሳለቁ ፣ ምግባችንንም እየተቃመሱ፣ ሶልዲውንም እየተቀራመቱ አሳምረው የወገንን ባህሪ አጥንተዋል። ለምሳሌ፣ የጁንታው አፈቀላጤ ልቡ የተሰበረ አማራ ይሆንና በ ዖሮሚያ እራሳቸው የሚያስገድሉትን ምስኪን የአማራውና ባለማተብ የዖሮሞ ልጆቻችንን አንገት ያስቀሉና ፣ እሪ ” አቢይ ከሃዲው፣ እነሆ ህዝባችንን አስበላ” ይሉሃል። ያኔ የኔ ቢጤው ይነሳና ” አሁንስ በዛ፣ እውነትም ይህ ሰውዬ ምኑ ይታመናል? አንድ ቀን እንኳ ሃዘን አይደርስ፣ ደንታም የለው ለአማራው ነፍስ ፣ አፋር ባለውለታው ተከዳ” እንላለን ። በርግጥም ድሃው አማራው ሆነ በቅጡ የማይመሰከርለት ዖሮሞው መታረዱ ሃቅ ነው። ታድያ የሚደንቀው ገዳይና አስገዳይ የታወቀው ጁንታና ሎሌዎቹ ሸኔዎች ሆነው ጎዝጉዘው አስለቃሾችም እነሱው መሆናቸው ነው። የኔ ቢጤው ወይ ሴራውን ለመገንዘብ ልቡ ተደፍኗል አልያም በቁጭትና ሃዘን ልቡ ስለተኮማተረ እነ ሱዛን ቀድመው ወደ አቀዱለት ወጥመድ ዘው ብሎ ይገባላቸዋል። ወደድንም ጠላንም የተፈለገው አለምአቀፉን የወገን ሬዚስታንስ ለማኮላሸት ነው – በትንሹም ትንሽ የተሳካ ይመስላል ። ልብ ብላችሁዋል የ ኖ-ሞሩ ሞቅሞቅ ቀዝቀዝ እንዳለ? ያልተጠበቁ አንቱ የተባሉ አገር ወዳዶች ሸርተት እንዳሉ? ይህ ነው የተፈለገው ወገኖቼ. እንንቃ!!!ለኢትዮጵያችን ስንል ።
አንዱ ወንድም በትዊተር ዛሬ አንድ ወቅታዊ ጥያቄ ስለ ብልፅግና ጠየቀ። በርግጥም ግራ ቀኝ ባየው ዛሬን ላይ ቆሜ፣ ስለእውነት አገሬን የምወድ ከሆነ ከብልፅግና የተሻለ ማን ሊመጣ እንደታሰበ ግራ ይገባል። እንደው የህዝቡ በምርጫ ብልፅግናን መምረጡ ገደል ይግባ ቢባል እንኳ አቢይ ላይ ሌባ ጣቱን የሚቀስር ሁላ ማንን ለኢትዮጵያ አጭቶላት እንደሆነ ግራ ይገባል። የወያኔን ተለጣፊ ፌዴራሌውን ነው? ልቡ የተሰወረውን ልደቱን ነው? የሚሰራውን ያሳጣውን እስክንድርን ነው ወይስ ማንን ይሆን? ወይስ ስለ ፈጣሪ ሰዎቹ ይመለሱልን ነው?ብቻ የሚገርምና የሚያሳዝን ወቅት ነው።
ምን ይደረግ? መፍትሄዎች!
፩) የወታደሩን ለነ ፊ/ማ ብርሃኑና ጄ/ አበባው ልተውና ወደ ሌላ ጥቆማ እዘልቃለሁ። እነ አጅሬ ለምን እስካሁን እንዳደፈጡ እነሱ ያውቃሉና የቄሳርን ለቄሳር።
፪) ወገን የተባልክ በተለይም አሜሪካ የምንኖር እያንዳንዱን ሴንተር ወጥረን መያዝ የግድ ነው። አደገኛው ረቂቅ ፉርሽ ሆኖ እንዲጨናገፍ ጡንቻችንን የምናሳይበት ወሳኝ ወቅት ነው። አሜሪካኖቹ የውስጥ ችግሮቻችንን እኛን መለያያ ስትራቴጂ አድርገው የሸረቡትን በተባበረ ክንዳችን ፉርሽ ማድረጊያው አሁን ነው
፫) መጪው ሚደተርም ዴሞዎችን አይቀጡ ቅጣት የምናሳርፍባቸው ለመሆኑ ካሁኑ በየቢሮዎቻቸው ማስታወቅ። ስንተባበር የማንደረመስ ጉልበት ነን ወገኖች።
፬) የወያኔዎቹን የመሰናበቻ የመጨረሻውን ጦርነት በቸልታ አለ ማየት ። ህዝቡን ነው የምለው እንጅ መንግስት ምን እንደማሰላቸው መገመት አይከብድም። ካልሰማችሁ የጄ/አበባውን ቃለመጠይቅ አንዴ ሳይሆን ሶስቴ ስሙት። ያን የሰማ ኢትዮጵያዊ በስሜት እየጋለበ አፋርና አማራ ተከዳ አይልም ነበር። ደግሞ ካልተጠበቁ ወገኖች። የፅልመት ውላጆቹን አይደለም የምለው። እነሱማ እንደፈለጋቸው እያማረጡ፣ አንዴ የወለጋ ዖሮሞ፣ ያ አልሆን ሲል ደግሞ ቅልጥ ያሉ ወለዬዎች ይሆናሉና ምን ችግር አለው። አልቅሰው ያላቅሱናል፣ አስገድለው በቁም ይቀብሩናል። ግን እንዴት አንነቃም? በአገርቤት ያሉትን ህፃናት ሆን ብለው ለ ሰላሳ አመት ስርአት ትምህርቱን ገድለው የልጆቻችንን ማሰቢያ ሰውረውብን ፣ እንዳይጠይቁና እንዳይመራመሩ ተብትበው ከ 14 ክፍላተሃገራት ወደ 86 ንኡሳን ቡድኖች እንደ አሜባ አራብተውን አጨልመውብናል። እኔን የሚያሳዝነኝ በውጭ ያለው የትግራይ ልጅ ይሁን የሌላው እንዴት በእንዲህ አይነት ጥልቀት እነዚህ ሰዎች ጭንቅላታችንን ሊቆጣጠሩ ቻሉ ያስብላል። ለነገሩ በገዛ ገንዘባችን የሸመቷቸው አናሊስቶች፣ የአይምሮ ጠበብቶች ብዙ ስለሆኑ ምንስ ይገርማል ። ትግራዋይ ሆነ ሌላው ለቀን ጉርሱ ሲከንፍ ምንስ ጊዜ አግኝቶ ሊመራመርባቸው ኖሯል። ፈጣሪ ብቻ ይፍረደው።
ዛሬ ስታሊን ስለተባለው አንጋች ዲ/ዳንኤል ክብረት ያጋለጡትን ሰምቼ አጃኢብ አስብሎኛል። በጤና አይደለም በአብያተ ክርስቲያናት ዙርያ የሱቅ በደረቴ ሱቆች እንደ አሸን የፈሉት። በኛ ዘመን እንኳንስ በተእምነት ቤት ስር ሱቅ ሊከፈትና ሊገበያዩበት በአካባቢውም ለእይታ አይኖርም ነበር። ይህን ስሰማ የከንቲባዋ አበሳና ፍጥጫ ታየኝና ከልብ አዘንኩ። ለነገሩ ሰዎቹ ደስ የሚለው ከ አርባ አመታት በፊት ገና ጫካ እያሉ ኦርቶዶክስ ላይ ክንዳቸውን እንደሚያሳርፉ ነግረውን ነበርና ምንስ ይገርማል ።
፫) የእንገነጠላለን ቀረርቶ
አንድ የማልንቀው የነዚህን ሰዎች ጉዳይ፣ እያንዳንዱን የኢትዮጵያዊ ሃሳብ ያውቃሉ። ለዚህም ነው ከየኪሳቸው እያወለቁ አጀንዳ የሚያቀብሉን። እንደማይሆንላቸው ያውቁታል፣ ሆኖም በስሜት ክፉኛ የተወጣጠርን መሆኑን ስለሚያውቁት ለምሳሌ እንዲህ ይላሉ፣
ወልቃይትን እናስመልሳለን
አድዋ የኛ ነው
ሲሉ በዖሮሚያ የሚያስቀነጥሱትን የአማራውና ዖሮሞው ደም ደመከልብ ሆኖ እንዲቀር አጀንዳ ማስቀየሻና ህዝብና መንግስትን ለመለያየት የታለመች ታክቲክ መሆኗ ነው። እስቲ በምን ተአምር ወልቃይትን ያስመልሳሉ መቀሌ ተሸሽገው? ይቺ በየጉድጓዱ የደበቋት አስቤዛ እየተጣራች መሆኗን ስላወቁና መጪውን ክረምት እንደማታዛልቅ ስለተረዱ እንደ እብደትም እያረጋቸው ቢሆን እንጅ አድዋን ምናልባት በታሪክ አጋጣሚ በአካባቢው ከመወለድ ሌላ ለአድዋና ኢትዮጵያ የሞተው እንኳ የመሃል አገር ህዝቡ ነው። እኛም የኛ ነው አላልን የጀግኖቹና የሰመአታት ትውልድ። የአድዋን ስም ከሃዲ ሲጠራው ይወረኛልና ነው እንጅ ለሌላ አልነበረም።
ማጠቃለያ!
አገራችን ከምንጊዜውም የበለጠ የሁላችን ርብርብን ስለምትፈልግ በትጋት እንስራ። ከአቢይ ቁርሾ ያላችሁ፣ ወይም አካሄዱን ያልተረዳችሁ፣ ስለ እናት አገር ብላችሁ የሚሰራብንን ደባ ለመረዳት አይናችሁንና ልባችሁን ክፈቱ። ኢትዮጵያን ካስቀደማችሁ የግለሰቦች ሚና ኢምንት ይሆናልና። የችኮላ ሃሳብ ስለሆነ እያረማችሁ አንብቡት። ለራሴውም ይሆናል የፃፍኩት። አገራችንን ሰላም ያርግልን።