የአቶ በረከት ስምዖን ባለቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማነጋገር እፈልጋለሁ አለች | Video

February 9, 2019

ከሁለት ሳምንት በፊት ጥረት ውስጥ በተፈጸመ ሌብነት የተነሳ ተጠርጥረው በባህርዳር የታሰሩት የአቶ በረከት ስምኦን ባለቤት ወይዘሮ አሰፋሽ ፈንቴ ስለበረከት ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይን ማነጋገር እፈልጋለሁ አለች::

https://www.youtube.com/watch?v=VptwBeTfg_U&t=1165s

ወ/ሮ አሰፋሽ ዛሬ በአዲስ አበባ ከወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ አቶ በረከት እንዴት እንደተያዘ ተጠቃ ስትመለስ  “አቶ በረከት የተያዘው ከቤቱ ነው፡፡ እኔ ልጄን ት/ቤት ለመውሰድ ከእንቅልፌ ተነስቼአለሁ። እሱ ተኝቶ ነበር፡፡ ጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ገደማ ይሆናል። “አሴ፤ ፖሊሶች ሊወስዱኝ መጡ” አለኝ። ሁሌም ስለሚቀልድ እውነት አልመሠለኝም ነበር። “የእውነትህን ነው?” ብዬ ስጠይቀው፣ ዘና ብሎ ነበር የሚያወራው። በመስኮት ብቅ ብዬ ለማየት ስሞክር፣ ገና አልነጋም ነበር፡፡ ግቢ ውስጥ ዛፍ አለ፤ ከዛፉ ስር ሬንጀር የፌደራል ልብስ የለበሱ ፖሊሶች ነበሩ፡፡ እውነት መሆኑን ሳይ በጣም ደነገጥኩ። ነገር ግን ብደነግጥም የተሰማኝ ስሜት ለቅሶ ወይም አንገት መድፋት አልነበረም፡፡ ይህንን ንፁህ ሰው እንዲህ አሳዶ መያዝ ምን ማለት ነው? የሚለው ነገር፣ በውስጤ ከፍተኛ የሆነ እልህና ቆራጥነት፣ ከጎኑ የመቆም ነገር ነው የተሰማኝ፡፡”  ብላለች:: “የአማራ ክልል ከዚህ አሳጅቦ ይወስደኛል ብሎ አልጠበቀም፤ ምናልባት በፌደራል መንግስት ልጠራ እችል ይሆናል ብሎ ገምቶ ነበር፡፡ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሊገባ ሲል ግቢ በር ላይ ነበር ወረቀቱን የሰጡት። ፖሊሶቹ የዚህን ጊዜ እጁን ለመያዝ ሞከሩ፤ አትይዙኝም አለ፡፡ በካቴና ሊያስሩትም ሞከሩ፤ አትወስዱኝም አለ፡፡ ምክንያቱም “የክልሉ መንግስት ፍርዱን በሚዲያ ጨርሶታል፤ ሙሰኞች ብሎ አውጆታል፤ ስለዚህ ይህንን አልቀበልም፤ ወደ አማራ ክልል አልሄድም፤ የፌደራል መንግስት ስሜን አላጠፋም፤ ስለዚህ የፌደራል መንግስት ይክሰሰኝ እንጂ አማራ ክልል ባህርዳር ተይዤ አልሄድም” በማለት ከሁለት ሰአት በላይ ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ፣ ፖሊሶቹም እየተጨመሩ ሄዱ፡፡ ከእሱም ጋር እንመካከር ነበር፡፡ “ወደ ክልል ይዞ መሄድ ምን ያህል ህጋዊ ነው? እሱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ነው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ሚና የነበረው፣ ከፍተኛ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍ ነበር፤ እንዴት ከፌደራል አልፎ ወደ ክልል ይሄዳል?” በማለት ሰዎች ለማማከር ለመደወል ሞክሬ ነበር፤ ምላሽ የሚሰጥ አልነበረም፡፡” ብላለች::

“አቶ በረከት ከተያዙ በኋላ  ጠ/ ሚኒስትር ዐቢይን ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ አለ?’ በሚል ለረቀረበላት ጥያቄም “በረከት ሲያዝ ጠ/ሚኒስትሩ አገር ውስጥ አልነበሩም፡፡ ብዙ የሚባሉ ነገሮች በአሉ፡፡ እውነቱን ሳላውቅ መናገር አልፈልግም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ሳይሰጡ ፌደራል ፖሊስ ሊተባበር አይችልም የሚሉም አሉ፡፡  እኔ ግን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይን ማናገር እፈልጋለሁ። ጉዳዩን አያውቁትም  ወይ? ምንድነው የታሰበው ነገር? የሚለውን ለመጠየቅ፣ እኛ ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሌለን፣ በሚቀርቧቸው ሰዎች በኩል ጥያቄውን አቅርበናል፡፡ እስካሁን የተሰጠን መልስ የለም፡፡ በትዕግስት እየጠበቅን ነው። ቀላል ነገር አይደለም፤ በረከት ለአገር የከፈለው ዋጋ መታየት አለበት፡፡” ብላለች::

የወ/ሮ አሰፋሽ ፈንቴን ቃለምልልስ ለዘ-ሐበሻ ቤተሰቦች በሚመች መልኩ አቀናብረን ከደቂቃዎች በኋላ በዘ-ሐበሻ ኦፊሻል ዩቱብ እናቀብላችኋለን:: በተለይ ከበረከት ወገን ያሉ ሰዎች ምን ይላሉ? በረከት ስም ዖንስ በቤተሰቡ ዓየን ምን ዓይነት ሰው ነው የሚለውን ለማወቅ ለምትፈልጉ ይጠቅማችኋል::

Previous Story

Video: “በህግ የሚፈለግ ተጠርጣሪን ደብቆ አልሠጥም ያለው የእኛ ክልል አይደለም” – የሱማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት ሙስጠፌ መሀመድ

Next Story

የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች ላይ በተሰነዘረ ጥቃት 7 ቤተክርስቲያኖች ተቃጠሉ | በሰዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት ደረሰ

Go toTop