በዛሬው እለት በተደረገው የፓርላማው ውሎ እስከዛሬ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፍተኛ ክርክርና ሙግት ተደርጎበታል፡፡ ሙሉ በሙሉ ኢህአዴግ በተቆጣጠረው ፓርላማ የተፈጠረው ጉዳይ በርካቶችን ያስገረመ ሆኗል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤቱ በዛሬ ጥቅምት 27 ቀን 2011 አ.ም ስብሰባው በምክር ቤቱ የነበሩት 20 ቋሚ ኮሚቴዎች ወደ 10 ዝቅ እንዲሉ በቀረበለት ሃሳብ ላይ ወደሁለት ሰአት ያህል ከፍተኛ ሙግት አድርጎ ሃሳቡን ተቀብሏል፡፡ ቢሆንም የቋሚ ኮሚቴዎቹ ሰብሳቢዎች በሚኒስትር ማእረግ የሚል ስልጣን እንዲሰጣቸው የቀረበለትን ሀሳብ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ምክር ቤቱ በተጨማሪም አቶ አማኑኤል አብርሃም የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሆኑ እንዲሁም፣ አቶ ሞቱማ መቃሳ የውጭና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት እንዲሆኑ በእጩነት ቀርበውለት የነበረ ቢሆንም ሁለቱንም አልቀበልም ብሏል፡፡ የአቶ አማኑኤልና የአቶ ሞቱማ ሹመትን ፓርላማው ባለመቀበሉም በተጠቀሱት ቋሚ ኮሚቴዎች ማንም ሰው ሳይመረጥ ስብሰባው ተበትኗል፡፡
አቶ ሞቱማ መቃሳ፡ የሃገር መከላከያ ሚንስትር ሆነው በዶ/ር አብይ አህመድ ተሹመው ስድስት ወር ሳይሰሩ መነሳታቸው ይታወሳል::
ዛሬ በፀደቀው መሰረትም 10 ቋሚ ኮሚቴዎች፦
1. የህግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
2. የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
3. የሰው ሃብት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
4. የሴቶች፣ወጣቶችና ማህበራ ዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
5. የተፈጥሮ ሃብት፣መስኖ እና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
6. የከተማ ልማት፣ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
7. የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
8. የገቢዎች፣በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
9. የግብርና፣ አርብቶ አደር እና አከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
10. የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሚኖሩት ሲሆን አጠቃላይ የአባላት ብዛትም ከ20 እስከ 45 የሚደርስ ነው።
https://www.youtube.com/watch?v=0OBDIk-J-Do&t=71s