ዶ/ር አብይ አህመድ የጋምቤላን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው መስራታቸው የሚያስመሰግን ቢሆንም ሕወሓት ካሴረው የግንጠላ ሴራ ክልሉን እንዲጠብቁ ማሳሰቢያ ተሰጣቸው

October 26, 2018

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተገኙበት ጋምቤላን እየመራ የሚገኘው የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዲሞክራሲዊ ንቅናቄ የማዕከላዊ ኮሚቴ በአዲስ አበባ የጀመረውን ግምገማ እንደቀጠለ ነው፡፡ እስካሁን ባደረገው ግምገማም የፓርቲው ሊቀመንበር እና የክልሉ መንግስት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ጋትሉዋክ ቱት እና ምክትላቸው አቶ ሰናይ አኩዎር ኃላፊነታቸው በፈዳቸው እንዲለቁ ተደርጓል:: ይህን ተከትሎም ፓርቲው አቶ ኦሙድ ኡጁሉን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አኙአያ ጃከን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡ ታውቋል፡፡

አቶ ፍፁም አረጋ እንደገለፁት በግምገማው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የክልሉ ህዝብ ልማት የተጠማ በመሆኑ አዲሱ አመራር ጊዜውን በግል አጀንዳዎችና ሽኩቻ ከማጥፋት ይልቅ ራሱን ከጎሰኝነትና ከጥላቻ በማጽዳት የክልሉን አመራር በማጠናከር የህዝቡን ችግር ሊፈታ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ከኃላፊነት የተነሱት አመራሮችም በድርጊታቸው ተጸጽተው ይቅርታ መጠየቃቸው እና ህዝቡን ለመካስ በተመደቡበት የስራ መስክ ለመሰማራት መወሰናቸውም ተጠቁሟል፡፡

በጋምቤላ ‘ዳልዲም’ በመባል የሚታወቁት ወጣቶች ዶ/ር አብይ አህመድ የጀመሩት ለውጥ በጋምቤላ አልደረሰም በሚል ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ሲያቀርቡ ነበር:: በዚህም የተነሳ የሰው ሕይወት ጠፍቷል:: ንብረት ወድሟል:: ጋምቤላም ላለፈው አንድ ወር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኮማንድ ፖስት ስር እየተዳደረች መሆኑን ዘ-ሐበሻ በተደጋጋሚ ዘግቧል::

በሰሜን አሜሪካ የጋምቤላ ማህበረሰብ በብዛት በሚኖርባት ሚኒሶታም ተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ የዶ/ር ዓብይ አህመድ መንግስት ለጋምቤላ ህዝብ ትኩረት እንዲሰጥ; የወጣቶች ግድያ እንዲቆም; የታሰሩት እንዲፈቱ; የክልሉ ፕሬዚዳንት እንዲነሱ መጠየቃቸውን ዘግበናል:: ዶ/ር አብይ በአስቸኳይ ለጋምቤላ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው የክልሉን አመራሮች በጽህፈት ቤታቸው ሰብስበው እያነጋገሩ መገኘቱ በርካታ የጋምቤላ ተወላጆችን እያስደስተ ቢሆንም አሁንም በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ያቀረቡ ዜጎች እንዲፈቱ እየጠየቁ ነው::

ነዋሪነታቸው በሚኒሶታ የሆኑ የተለያዩ የጋምቤላ ተወላጆችን ዘ-ሐበሻ በስልክ ለማነጋገር ሞክro አብዛኞቹ የክልሉ ፕሬዚዳንት በመነሳታቸው ደስታቸውን እየገለጹ ቢሆንም ቀጣዩ ጊዜ ለጋምቤላ ምን ይዞ እንደሚመጣ አሁንም ስጋት አጭሮባቸዋል:: በተለይም ሕወሃት ታላቋን ትግራይ ለመመስረት በጋምቤላ የደቡብ ሱዳን አራት መቶ ሺህ ስደተኞች ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዲያገኙ ያሴረው ሴራና የክልሉ መሪዎችም ይህንን ለማስፈጸም ከጌታቸው አሰፋና ስዩም መስፍን ጋር ይሰሩ ስለነበር ለደቡብ ሱዳናውያኑ ኢትዮጵያዊ ዜግነት መስጠት ጋምቤላን ለመገንጠል የሚደረግ ተንኮል በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ ያሳሰቡ ወገኖች አሉ:: ያነጋገርናቸው ወግኖች እንደሚሉት ዶ/ር አብይ ይህን የሕወሓት ሴራ ተገንዝበው ክልሉን ከመገንጠል ሴራ ሊታደጉት ይገባል::
https://www.youtube.com/watch?v=nwAe0H54xdQ

Previous Story

ለመሆኑ መስዋእትነት ከፈሎ ለውጡን ማን አመጣው ? ግቡስ ምን ነበር ?

Next Story

በአዲስ አበባ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ 15 ተማሪዎች ራሳቸውን ስተው ወደቁ

Go toTop