መጋቢት 4፣ 2009 (ማርች 13፣ 2017)
በትላንትናው እለት በሀገራችን ኢትዮጵያ ዋና ከተማ በአዲስ አባባ እጅግ ዘግናኝ እልቂት ተፈጽሟል።
የሚላስ የሚቀመስ የሌላቸው ፣ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይኖሩበት የነበረው የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ ከስልሳ በላይ ወገኖቻችን በህይወት ተቀብረዋል። የስርአቱ ባለስልጣኖች ያመኑት 60 ግለሰቦች እንደሞቱ ይሁን እንጂ እውነተኛው ቁጥር ግን ከተባለው በላይ እጅግ ብዙ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ በትላንትናው እለት ህይወታቸው በጠፋው ወገኞቻችን መክንያት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ ለሟቾች ወዳጅና ዘመዶችም ጽናቱን ይመኛል።
ከአንድ መንግሰት መሰረታዊ ተግባሮች ውስጥ የመጀመሪያው የሚሆነው የሚያሰተዳድረውን ህዝብ በህይወት ለመኖር አሰፈላጊና መሰረታዊ የሆኑትን ማለትም ምግብ መጠለያ የመሳሰሉትን እንደሟሉ ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ችሮታና የበጎ አድራጎት ስራ ሳይሆን የመንግስት ግዴታ ነው። የሰው ልጆችም፣ ሰው በመሆናቸው ብቻ ሊከበሩላቸው የሚገባው መሰረታዊ ሰብአዊ መብት ነው።
አንድ መንግስተ ለህዝቡ እነዚህን መሰረታዊ ጉዳዮች ሳያሟላ መንግስታዊ ሀላፊነቴን ተወጥቻለሁ ማለቱ አሳፋሪና ባዶ ጩኸት ነው።
ህወሀት/ ኢህአዴግ የሀገሪቱን መንግስታዊ ስልጣን ከተቆጣጠረ እነሆ 26 አመት ሆኖታል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ሁሉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በ10 እና በ12 ፐርሰንት አሳደግኩ ይበል እንጂ የሀገራችን ህዝብ ድሀው ይበልጥ ድሀ እየሆነ ነው የመጣው። በትላንትናው እለት በቆሻሳሻ ታፍነውና በእሳት ተቃጥለው ለሞቱት ወገኖቻችን ግን ያተረፈው አንዳችም ጥቅም የለም። ይህ የሚያሳየው ኢኮኖሚው አድጓል ቢባል እንኳ፣ ተጠቃሚ የሆኑት የህወሀት/ ኢእአዴግ ባለስልጣኖችና ሽሪኮቻቸው እንጂ ብዙሀኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ድሀው እንዳልሆነ ነው። ማንም የማይክደው ሀቅ ዛሬ የህወሀት/ ኢህአዴግ ባለስልጣኖች ድንገት ባለ ሚሊዮን ዶላር ባለሀብት የብዙ ህንጻና ፋብሪካወች ባለንብረት ሆነዋል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ከሌላው ኢትዮጵያዊ በሚዘረፍ ሀብትና ንብረት ከድሀው ህዝብ አፍ በሚነጠቅ ንብረት ነው። ብዙዎቹም ለዚህ ዓይነት ኑሮ የዳረጋቸው መንግስት ራሱ መሬታቸውን ነጥቆ ያለ ተገቢ ካሳ ስላባረራቸው ነው።
በትላንትናው እለት ህይወታቸው የጠፋው ወገኖቻችን እጅግ አደገናኛና ጤናማ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ ወይም በዚህ ቦታ ምግብና መጠለያ ይፈልጉ እንደነበር ይህ መንግሰት ለ26 አመታት ያውቃል። በዚህ ጊዜ ሁሉ የነዚህን ወገኖቻንንን ኑሮ ለማሻሻል፤ በዚህ አደገኛ ቦታም ሊደርስባቸው የሚችለውን አደጋ ገምቶ ካደጋ ለመከላከል መንግስት የወሰደው አንዳችም እርምጃ አልነበረም። ይሀ ደግሞ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሰት ለህዝበ ስቃይ፣ ለህዝብ ደህንነት ግድ የሌሽነቱን ቁልጭ አድርጎ ያመለካታል።
በዚህ የመንግሰት ግድየለሽነት ለደረሰው ጥፋት በሀላፊነት ተጠያቂ አድርገን የምንይዘው በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት እንደሆነ ማሳወቅ እንወዳለን። ለእኛ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ህይወት እኩል ዋጋ አለው። የሁሉንም ህይወትና ደህንነት መጠበቅ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው።
ይህ ስርአት ከ26 አመት መንግስታዊ ስልጣን በኋላ ዛሬም ለህይወት መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ለህዝብ ማቅረብ አልቻለም። ባላፈው አመት 10 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን በርሀብ ሲገረፉ ነበር ። አሁን ደግሞ ስድስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ረሀብ እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ኢትዮጵያውያን ከምን ግዜውም በላይ በተደጋጋሚ በረሀብ የተሰቃዩት በዚህ ስርአት ውስጥ ነው። ባጠቃላይ ስርአቱ መሰረታዊ ሀላፊነቱን መወጣት አቅቶታል።
የዜጎቹን ህይወት መታደግ የማይችል መንግስት በስልጣን ለመቆየትም የሞራል ብቃት የለውም።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ(ሸንጎ)