ሰይጣን አንዳንዴ እውነትን ይናገራል – ከዘመነ ወያኔ ድቅድቅ ጨለማ ወጥተን ወደ ለዬለት ሲዖል ከገባን ድፍን ስድስት ዓመት

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ጊዜው ይከንፋል፡፡ ይሄውና ከዘመነ ወያኔ ድቅድቅ ጨለማ ወጥተን ወደ ለዬለት ሲዖል ከገባን ድፍን ስድስት ዓመት ከስምንት ወር ከ11 ቀናት ሆነን – ዛሬ ታኅሣስ 15 ቀን 2017 ዓ.ም፡፡ የሲዖላዊው መርዶ ከተነገረበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓመተ ፍዳ ተነስተን ስንቆጥረው እሳቱ ከማይበርድበት፣ ትሉም ከማያንቀላፋበት ገሃነም ውስጥ መኖር ከጀመርን የጠቀስኩትን ጊዜ ሆነን፡፡ ይገርማል፡፡ መጻፍ አልፈለግሁም ነበር፡፡ ግን ከገባንበት ሶዶም ወገሞራዊ የእቶን እሳት የምተርፍና ለትንሣኤው መባቻም የምደርስ ከሆነ “በዚያን ዘመን ይህን ብዬ ነበር” ለማለት ያህል ብቻ ትንሽ መተንፈስን ወደድኩ፡፡ እንጂ ዘመኑ የአርምሞና የጸሎት ነው፡፡ ዘመኑ የንግግር ሳይሆን የድርጊት ነው፡፡ ሰሚ አላገኘንም እንጂ ጩኸትንስ ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት ጮኽናት፡፡ አሁን የጩኸታችን ሁሉ ፍጻሜ ላይ ደረስን፡፡ ደግሞም ይህም ያልፋል፡፡

አቢይ አህመድ አንዳንዴ መንፈስ እያመላከተው ይመስላል እውነትን ይናገራል፡፡ ያ ከመቶ አንድ ወይ ሁለት እጅ የሚከሰት እውነተኛ ንግግሩ “ማንም ሽህ ዓመት ቢንደፋደፍ እኛን ማሸነፍ አይችልም፡፡ ምክንያቱም እርስ በርሱ የሚለያይና ለግል ዓላማና የሥልጣን ፍላጎት የሚራኮት ተቃዋሚ እዚያው እርስ በርሱ ይፋጃታል እንጂ አራት ኪሎ ህልሙ እንደሆነች ትቀራለች፡፡” በማለት የተናገረው ሰዎች ሳይረዱት ያጥላሉታል እንጂ እውነቱን ነው፡፡ ማብጠልጠል ከተፈለገስ “አንዲት የጤና ባለሙያ ዐርባና ሃምሣ ዶሮ በዚያች ሣጥን በምታክለዋ ቤቷ ብታረባና በቀን 30 እና 40 ዕንቁላል ብታገኝ በዚያ ላይ ማሩ ሲጨመር፣ ዓሣው ሲጨመር፣ ወተቱ ሲጨመር … ደመወዟ ማጣፈጫ ይሆናል” ሲል የቀባዠረው መሣቂያ ቧልት ላይ ነው፡፡ ይህን ንግግሩን እየደጋገምኩ ብሰማው ልጠግበው አልቻልኩም – በጣም ያዝናናኛል፡፡ ይህን የመሰለ ጉደኛ መሪ ፈጣሪ ስለሰጠን ማመስገን ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ (የአቢይ ንግግር ቃል በቃል አይደለም!)

“የደላው ሙቅ ያኝካል” ነው ነገሩ፡፡ በየትኛው ጊዜዋ፣ በየትኛው ሰፊ ቤቷ፣ በየትኛው የመኖ ባጀት፣ በየትኛው ዕውቀትና መነሻ ወረት …. ብቻ ይህን ሰው ካዳመጡት የዕብደት መለኪያ እስኪጠፋን ድረስ በአእምሮው መሣት እንገረማለን፡፡ 120 ሚሊዮን ሕዝብ በዚህን መሰሉ የሚናገረውን የማያውቅ ወፈፌ መመራቱ ደግሞ የሚገርም ነው፡፡ የኃጢኣታችን ብዛትና የምናወራርደው የአያት የቅድመ አያት የትውልድ ዕዳ መኖሩም ቁልጭ ብሎ እየታየኝ ነው፡፡

ወደጀመርኩት ዋና ሃሣብ ልመለስ፡፡ በፋኖ አካባቢ የሚስተዋለውና ከጅማሬው ብዙ የጮኽንበት መሬት ላይ በማይታይ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል ከአሁኑ መራኮት ትግሉን ለአደጋ እየዳረገው ነው፡፡ “የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ሉካንዳ ደጅ ላይ ተገኘ” ይባላል፡፡ ዕድገቱ ማንንም የሚያስቀናው ሸምበቆም እንደሙቀጫ እንደሚንከባለል በተረት ይጠቀሳል – “ወጣ ወጣና እንደሸምበቆ ተንከባለለ እንደሙቀጫ” – ተብሎ፡፡ ከነዚህና ከሌሎች ብሂሎች መማር የተሣነው ፋኖ ሕዝቡን በተስፋ ከቀበተተ በኋላ አሁን አሁን ኆልቁ መሣፍርት በሌላቸው ሰበር ዜናዎች ሶሻል ሚዲያዎች ቢጥለቀለቁም የሚጨበጥ ድል ግን እንደራቀንና እንደናፈቀንም አለን፡፡ እርስ በርሳቸው የሚወራረፉ የተቃውሞው ጎራ ሚዲያዎችም ለዕለት ጉርሳቸው የምትሆን እስካገኙ ድረስ ማለቂያ በሌለው ሰበር ዜና የተጠመዱ መሆናቸውን የሚጠሉት አይመስልም፡፡ ዕድገታችን ሁሉ እንደካሮት ቁልቁል መሆኑ እኔንማ ሊያሳብደኝ ነው፡፡ ለማንኛውም ከዚህ በፋኖ ውስጥና ዙሪያ ከሚታየው ነባራዊ እውነታ አንጻር አቢይ እውነቱን አፍርጦታል ማለት ይቻላል፡፡ ተቃዋሚው ጎራ የዚህን ዕብድ ንግግር በአወንታዊነቱ ቢወስደው ይጠቀምበታል፡፡ ምሬ፣ ባዬ፣ ደሳለኝ፣ ዘመነ፣ አስረስ … እየተባባሉ እርስ በርስ በመጎሻመጥና በሸጥና በጎጥ በመከፋፈል የትም አይደርሱም፡፡ “አማራ ምቀኛ ነው፣ አማራ ሥልጣን ወዳድ ነው፣ አማራ በወንድሙ ሳይቀር ስለሚቀና ተያይዞ መውደቅን እንጂ ተያይዞ ማደግን አይወድም፣ አማራ በአካባቢው ስለሚቆረቁዝ ወደሌላ ቦታ ሲሄድ ነው የሚያልፍለት ….” የሚባሉትን የኋላቀርነት መግለጫዎችን ለማጥፋት ሁሉም በቅን ልቦና ይተባበር፡፡ ከዚያ በኋላ ችግራችን ከሣምንትና ከወር አያልፍም፡፡ ያስቸገረን በማይረቡ ነገሮች መለያየታችን ነው፡፡ በክፍለ ሀገርና በነገድ ከተከፋፈልን ለጠላት ምቹ ሆነን እንቀራለን፡፡

የአማራ ፋኖ ትግል በይፋ ከተጀመረ ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ብቻ ይቀራሉ፡፡ እንዳነሳሱ ቢሆን ኖሮ ይሄኔ ኢትዮጵያ ከዚህ ልዕለ-አጋንንት ጭራቅ ሰውዬ ተገላግላ ነበር፡፡ ይሁንና ትግሉ በግል ጥቅምና ዝና ፍለጋ በተሞሉ ሰዎች በመበረዙ የነፃነት ጊዜው እየራቀ ሄደ፡፡ በመሠረቱ ሀገር ሳይኖር ሥልጣን የለም፡፡ ሀገር ሳይኖር ዝናና ዕውቅና የለም፡፡ ሀገር ሳይኖር ሀብትና ገንዘብ አይኖርም፡፡ ዝንጀሮዋ “ቀድሞ የመቀመጫየን” ያለችው ወዳ አይደለም፡፡ በመላዋ ኢትዮጵያ ተበትኖ የሚኖረው አማራ በተገኘበት እንደዶሮ አንገቱን እየተቆረጠ ባለበት ዘመን ለሥልጣን ሲል የአማራን ትግል የሚከፋፍል የሥልጣን ጥመኛ ካለ ዘር አይወጣለትም፡፡ “ሁለተኛ አማራ አልሆንም” ያለችው የህጻን አንሻ ደም እስከሰባት ትውልዱ እየተከተለ ዋጋውን ያስከፍለዋል፡፡ እውነቴን ነው፡፡

አካፋን አካፋ ማለት ነውር የለበትም፡፡ ፋኖ አርባና ሠላሣ ቦታ ተከፋፍሎ አንድ ሽህ አይደለም አንድ ሚሊዮን ዓመታትን ቢዋጋ አያሸንፍም፡፡ ፋኖ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ የዘመነ መሣፍንት ሥርዓት ካልወጣ አንድ ስንዝር አይራመድም፡፡ ከአስቂኝ አካሄዱ በፍጥነት ይላቀቅ፡፡ አውቶቡስ ሙሉ አማራ ጎሃ ፅዮን ላይ ታግቶ ኦነግሸኔ አንገቱን በሠይፍ በመቅላት እየተዝናናበትና ሬሣ ማስለቀቂያ በሚሊዮን እየጠየቀበት ሳለ ጫካ ውስጥ ሆኖ ስለንግሥናና የዘር ማንዘር ጀግንነት ዲኤንኤ መራቀቅ አነስ ሲል ቅዠት ከፍ ሲል ደግሞ አቢያዊ ዕብደት ነው፡፡ ከብቶቹ ሳይገዙ ሌቦቹ በረቱን ካስጨነቁ የለየለት ጅልነት ነው፡፡ ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከምቢያው ቂጢጥ ካለ እጁን ታጥቦ ሊበላ ያሰፈሰፈው ሁላ ወስፋቱን አስጩሆ ይቀራል፡፡ በምታዘበው የጅልነት አካሄድ አንጀቴ እያረረ ኢትዮጵያዊነቴን የምረግምበት አጋጣሚ እየበዛ ነው፡፡ ደጀንን ሳይቆጣጠር፣ አባይን ሳይሻገር፣ ደብረ ሲናን ሳይዝ፣ ደባርቅና የለማን አገር ቅምብቢትን የሚናፍቅ እርስ በርስ የተከፋፈለና የተጠማመደ ታጋይ እንዴት ስለአራት ኪሎ ሊያስቡና በርሱም ሊገዳደል ይችላል? ይሄንን ቡልሃነት (ጅልነት)ወንድሞቻችንና ልጆቻችን ከየት አገኙት? ይህ ዓይነቱ አማራ ከብአዴናውያን በምን ተሻለ? በጎጥና በሸጥ የተከፋፈለ ትግልስ የት ያደርሳል? በዚያ ላይ በዝርፊያና በሙስና ገና ከአሁኑ የሚታማ ታጋይ አታጋይ ነገ አራት ኪሎ ቢገባ ምን ያደርገን ይሆን? “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያስደረኝም” ይባላልና የምንሰማው ሁሉ አስደንጋጭ ነው፡፡ ለሀብትና ለሥልጣን የሚንሰፈሰፍ ነፃ አውጪ ከዚህ መሰሉ ንቀዘት ራሱን ነፃ ካላወጣ ለራሱም ለሀገርም አደጋ ነው፡፡ የገዛ ሥጋው ባሪያ የሆነ ደግሞ የነፃነት ቀንዲል ሊሆን አይችልም – በጭራሽ፡፡

ወንበሩ አንድ ነው፡፡ ስልሳና ሰባ ሚሊዮን አማራ ይቅርና ሁለት ሰው እንኳን አያስቀምጥም፡፡ ታዲያ ይሄን የሥልጣን ሽሚያ ገልቱነት ምን አመጣው? በግል ቂምና በጥላቻ ተሞልቶ የጋራ ዓላማን ማደናቀፍስ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? …. በዚህ መልክ የሚደረግ ጉዞ ሕዝብን ማስፈጀት ነው፡፡ እነዚህ በቀለኞች ደግሞ ጎጃምና ጎንደር አንድ ጥይት ጢው ባለ ቁጥር አዲስ አበባና አካባቢው በሚኖር አማራ ላይ ገመዳቸውን በማጠባበቅ ጉሮሮውን ሲጥ ያደርጉታል፡፡ እውነቱን ለመናገር በአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች በሚኖር አማራ ላይ ለሚደርሰው ቤት ፈረሳና መፈናቀል ዋና ተጠያቂው ፋኖ ነው፡፡ ፋኖ ከጅብ እንደማያስጥላት የአህያ ባል ከመሆን በአፋጣኝ ካልወጣ ኦነግሸኔ አማራን በቅርብ ይጨርሰዋል – እንደሰውኛ አተያይ፡፡ መጨረሻው ግን ሌላ ነው፡፡

እንደፈጣሪ የቀደመ ብያኔ አሁን ሁለንተናዊ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ብንገኝም መዳረሻችን ያማረና ትንሣኤያችን የቀረበ ነው፡፡ የትንሣኤያችን ምክንያት የደረሰብንና እየደረሰብን ያለው ግፍና በደል ሲሆን ለብርሃናማው ዘመን መምጣት ደግሞ ፈጣሪ የሚልካቸው ደጋግ ሰዎች ናቸው፡፡ አሁን ባሉበት አሉ – በርግጠኝነት በቅርቡ ይመጣሉ፡፡ እኛም ነፃ እንወጣለን፡፡ ይህን እናውቃለን፡፡ የዚያን የወርቃማ ዘመን መባቻ ጊዜ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ፋኖ የዚህ ቅዱስ ተልእኮ አስፈጻሚ የመሆን ዕድል ያለው ይመስለኝ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ጨርሼ ተስፋ አልቆረጥኩበትም፡፡ የዚያ ቅዱስ ተልእኮ አስፈጻሚ አካል እንዲሆን ከፈለገ ግና በውሰጡ የሚገኙ ቅዠታሞችንና የአንድነት ትግል ደንቃራዎችን ይምከር ያስመክር፤ ራሱን በቶሎ ያጥራ፡፡ በላም አለኝ በሰማይ የሥልጣን ሽኩቻ ሕዝብ አያስጨርስ፤ አያስመርር፡፡ “እርስ በርሷ የተከፋፈለች መንግሥት አትጸናም” ይላል መጽሐፉ፡፡ በደረት ላይ ትላልቅ መስቀሎችን ማንጠልጠል ብቻውን ፋይዳ የለውም – ከሥራ ጋር ይሁን ማለቴ ነው፡፡ አእምሮን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ኅሊናን ከግል ጥቅምና ፍላጎት ግርዶሽ መከላከል ይገባል፡፡ ንግሥና ዘራችን ነው ማለት በራሱ እኔን ያሳፍረኛል፡፡ ከማይምም አይጠበቅም እንኳን ፊደል ከቆጠረ፡፡ ዘመንን የዋጀ ንግግርም አንድ ተስፋ ነው፡፡ አንደበትን ማረቅ ከአሁኑ ነው፡፡ አቢይን የጠላነው በጭካኔው ብቻ ሳይሆን እዚህ ግባ በማይባል ውሽከታውም ጭምር ነውና ለትዝብት ከሚዳርጉን ንግግሮች እንቆጠብ፡፡ በአእምሮ እንደግ፡፡ ሰው እንሁን፡፡ ይህም ይቻላል፡፡

ከጭብጨባ ደግሞ እንውጣ፡፡ ሀገር እያጠፋ ያለው ናላን በሚያዞር ጭብጨባ እየተኮፈስን ራሳችንን ሰማየ ሰማያት የመስቀል የግብዞች አባዜ ነው፡፡ በባዶ ጭብጨባ የተደገፈ ባዶ ጭንቅላት ዕቡያን መንግሥቱዎችን፣ መለሶችንና አቢዮችን ይቀፈቅፋል፡፡ ያኔ አሣራችን ይበዛል፡፡ በበኩሌ ጭብጨባ እንዲቀር ዐዋጅ ቢታወጅ ደስታውን አልችለውም፡፡ ጉርጥና ዕንቁራሪትን ወደ ዝኆንነት እንዲለወጡ እየገፋፋ በራስ ቅሎች የሚጫወትብን ይሄ ጭብጨባ ነው – ስጠላው! ….

ስለአማራና ትግሬ ትንሽ ብናገርስ? በዐረመኔነትና ወደር-የለሽ ጭካኔ ሊቀ ሣጥናኤልን ዕጥፍ ድርብ የሚያስከነዳው ልዕለ-አጋንንቱ አቢይ አህመድ እነዚህን ሁለት ነገዶች እርስ በርስ እያባላ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም መልፋቱ የታወቀ ነው፡፡ ትግሬንና አማራን በጦርነትና በርሀብ የመፍጀት ሤራው ተግባር ላይ ውሏል፡፡ በመከላከያና በክልላዊ የታጠቁ ኃይላት ሕዝብን ከማጨራረስ ጎን ለጎን በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ርሀብና ድርቅ ሕዝብ እንዲያልቅ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ ለተራበው ሕዝብ ምግብና መድኃኒት እንዳይገባለትም መከላከያው መግቢያ መውጫ በሮችን ጠርቅሞ ዘግቶ አሁን ሕዝብ በርሀብ እያለቀ ነው፡፡ አማራና ትግሬ በአገዛዙ እንደጠላት ስለተፈረጀ ትምህርት እንዳይማር፣ የመሠረታዊ ዕቃዎች አቅርቦት እንዳይኖረው፣ ህክምና እንዳያገኝ፣ ታህታይና ላዕላይ መዋቅሮቹ እንዲፈራርሱ፣ መደበኛ የመንግሥት ሥራዎችና የልማት እንቅስቃሴዎች እንዳይኖሩ፣ …. በጥቅሉ ከመኖር ወዳለመኖር እንዲወርድ በልዕለ-አጋንንታዊው አቢይ ተፈርዶበት አማራና ትግሬ ከምድረ ገጽ ሊጠፋ ተቃርቧል፡፡ መወሻሸት አያስፈልግም፡፡ እነዚህ ሕዝቦች አንድነት ቢፈጥሩ የአገዛዙ ዕድሜ ከሣምንታት እንደማያልፍ አቢይም ሆነ የላኩት ሉሲፈራውን በደምብ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህም ነው አማራና ትግሬ ወልቃይትንና ራያን ጨምሮ በጥቃቅን ሰበቦች እርስ በርስ እንዲፋጅ አቢይ ሁኔታዎችን እያመቻቸ የሚገኘው፡፡ አሁን የተቸገርነው እውነተኛና ሃቀኛ የአማራና የትግሬ ልጆች ተሰባስበው በመሃላቸው የተዋለባቸውን አቢያዊ ድግምትና ነባር የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ደለል በማራገፍ የሚዋደዱ ግን በጠላት ግርዶሽ የተራራቁ የሚመስሉ ትግሬዎችንና አማሮችን በአንድነት ጎራ የሚያሰልፍ ሰው ማጣታችን ነው፡፡ ዕድሉ ያላችሁ እባካችሁን ጠብን ከመዝራት ይልቅ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ፍቅርን በማስፈን የጋራ ጠላታቸውን አስወግደው የታፈረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ፍጠሩ፡፡ እግር የሌለው ሰው ስለካልሲ ጥራትና ዋጋ ቢጨቃጨቅ ትርፉ ትዝብት ነው፡፡ Better late than never.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ሙት ይዞ ሲሞት – ጥሩነህ ግርማ

Next Story

“መካር የሌለው ንጉስ እንዳይሆኑ” ፤ ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተፃፈ አቶ ያሬድ ሀ/ማሪያም

Go toTop