ይድረስልኝ ላንተ በቁምህ ለሞትከው በደም ተጨማልቀህ ገምተህ ለሸተትከው

February 9, 2023
ይድረስልኝ ላንተ በቁምህ ለሞትከው
በደም ተጨማልቀህ ገምተህ ለሸተትከው
ክቡር አልልህም ክብር የት ታውቅና
ዶክተር አልልህም ምኑን ተማርክና
ሃገር ሞተች እንጂ ባንተ ድድብና
እስኪ ልጠይቅህ ማነው ያለህ በርታ
እንደዚህ አርክሶ ያጣላህ ከጌታ
እንዳሻህ ገደልከን እንደጉድ ሞትንልህ
ቤተ እምነት አቃጠልክ አልቅሰን ዝም አልንህ
በርሃም ቀጣኸን ላንተም ጸለይንልህ
ማን አይዞህ ብሎህ ነው አሁን የለየልህ
ባንተ ዘመን እኮ
አባቱን ያልሰዋ ወንድም ያልቀበረ
እህቱ ተደፍራ ቅስሙ ያልተሰበረ
እናቱ ታርዳበት በደም ያልሰከረ
በጦቢያዬ ምድር ሰው የለም ነበረ
ግን…
ሁሉንም አልፈናል አዝነን ብናለቅስም
ያሁኑ ድፍረት ግን አያለሳልስም
ቤተ እምነቷ ሲነድ ይሁን ያልፋል ባለች
ሃገር ሲተራመስ ምህላ በያዘች
ካንተ ክፉ እንዲርቅ ጾማ በጸለየች
ልጆቿን ሰብስባ ይቅር በሉ ባለች
ፍቅር ባስተማረች
ምኗ ቀሎህ ይሆን ባንተ የተደፈረች
አላወክም እንጂ
ኦርቶዶክስ መሆን የሃይማኖት ጥጉ
ለእምነቱ መሞት ነው ወግ እና ማረጉ
የአቡነ ጴጥሮስ የእየሱስ ልጆች ነን
በሞት ውስጥ ነው ትንሳኤን ያገኘን
ስለዚህ አንፈራም እመነን አንተ ሰው
ረጋ በል ሰከን ሞትክን አታርክሰው።
“የመጨረሻው ደብዳቤ”

ፀጋየ ወልኪቴ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ላይ የሚደርሰውን አፈናና በደል በ አስቸኳይ የማይቆም ከሆነ ከስልጣኔ በፍቃዴ እለቃለሁ

Next Story

የት ሄደች ኢትዮጵያ (አንዱ ዓለም ተፈራ)

Go toTop