የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትና የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ፊትለፊት ተገናኝተዉ ተወያዩ። ደቡብ ኢትዮጵያ ሐላላ ኬላ በተባለዉ የመዝናኛ ስፍራ በተደረገዉ ዉይይት ከፌደራሉ መንግስት በኩል ዓብይ አሕመድ፣ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
ከህወሓት በኩል የፓርቲዉ ዋና ተደራዳሪ ጌታቸዉ ረዳ የመሩት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ተካፍለዋል።ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ ዓሕመድ ከህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በይፋ ፊትለፊት ተገናኝተዉ ሲወያዩ ከጥቅምት 2013 ወዲሕ የዛሬዉ የመጀመሪያዉ ነዉ።የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የፀጥታ አማካሪ ሪድዋን ሁሴን በትዊተር ገፃቸዉ እንደፃፉት ዉይይቱ ሁለቱ ወገኖች የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት እስካሁን በነበረዉ ገቢራዊነት ላይ ያተኮረ ነዉ።
ዐብይ ከና ወደ ትግራይ የሚደረጉ የአዉሮፕላን በረራዎች፣የሚሰጡ የባንክና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲጨምሩ ወስነዋል።ዉሳኔዉ አምባሳደር ሪድዋን እንዳሉት በሁለቱ ወገኖች መካከል ይበልጥ መተማመን ለማስፈን ያለመ ነዉ። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትና የሕወሓት ተደራዳሪዎች ካለፈዉ ጥቅምት ጀምሮ ፕሪቶሪያና ናይሮቢ ዉስጥ የተፈራረሙት ስምምነት በአብዛኛዉ ገቢር እየሆነ ነዉ።የሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ ባለስልጣናት ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተገናኝተዉ እንደሚወያዩ አስቀድሞ በይፋ አልተነገረም።
DW Amharic