የኢትዮጵያ አየር መንገድ 39 አዳዲስ አውሮፕላኖችን በቅርቡ ወደ ሥራ ሊያስገባ ነው

October 21, 2022
 የኢትዮጵያ አየር መንገድ 39 አዳዲስ አውሮፕላኖችን በቅርቡ ወደ ሥራ ሊያስገባ መሆኑን የአየር መንገዱ የቦርድ ሊቀመንበር ግርማ ዋቄ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሊቀመንበር ግርማ ዋቄ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካን አየር መንገዶች በባለ ድርሻነት የማስተዳደር ሂደቱን በማስፋት ላይ ይገኛል።
በስኬታማነቱ የሚታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ የኮንጎና የናይጄሪያን አየር መንገዶች ባለድርሻ ሆኖ ለማስተዳደር በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰባት አሥርት ዓመታት በላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አንግቦ በዓለም ስመ- ገናና ሆኖ መዝለቁንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ ዘርፎች በስኬታማነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ በመሆን በምርጥ አየር መንገድነቱ ቀጥሏል ብለዋል።
አየር መንገዱ የስኬት መንገዱን በአስተማማኝ መልኩ ለማስቀጠልና በየአምስት ዓመቱ በእጥፍ የማደግ ትልም ይዞ እየሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
በቅርቡም 39 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ወደ ሥራ ለማስገባት ትዕዛዝ ሰጥቶ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአውስትራሊያ በቀር በዓለም አህጉራት የሚበር መሆኑን በመግለጽ፤ በሂደት አውስትራሊያንም ተደራሽ መሆኑ አይቀርም ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ የቶጎ አየር መንገድ አስካይ፣ የዛምቢያ አየር መንገድና የማላዊ አየር መንገድን በከፊልና በተለያዩ መጠን በባለድርሻነት በማስተዳደር ላይ መሆኑ ይታወቃል።
በአሁኑ ወቅትም የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን አየር መንገድ ኤር-ኮንጎና የናይጄሪያን አየር መንገድ በባለድርሻነት ለማስተዳደር ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
የኮንጎን አየር መንገድ ከኮንጎ መንግሥት ጋር፣ የናይጄሪያን አየር መንገድ ደግሞ ከናይጄሪያ መንግሥትና ባለሀብቶች ጋር በመሆን አዳዲስ ሁለት አየር መንገዶችን ለማቋቋም ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ገበያውን እያሰፋ አፍሪካንም እንደራሱ ቤት ይዞ ለመጓዝ የሚያስችል እድል የሚፈጥር መሆኑን አቶ ግርማ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ወደ ዙሪክ የሚጀምረውን በረራ ጨምሮ
130 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች የሚኖረው ሲሆን 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች አሉት።
ኢዜአ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ችግርን ከነ ምንጩ ማለባበስ እና ማሳነስ ከኢትዮጵያ ምድር ይደምሰስ !

Next Story

አገር በህግ የበላይነት፤ በጠንካራ ዲሲፕሊን እና በተጠያቂነት መመራት አለባት – ትወራ ለህዝብ ዳቦ አይሆነውም!!

Go toTop