ይድረስ ለኢትዮጵያውያንና ለትውልደ ኢትዮጵያዊያን
ሎንዶን-ታላቅዋ ብሪታንያ
በኢትዮጵያ መጭው የ2015 ዓ.ም. አዲስ ዓመት በአስታራቂ ሃሳቦች ፣ በይቅርታ፣ በመግባባት እና ስሉጥ በሆኑ የለውጥ አካሄዶችና ጠቋሚ ሃሳቦች ተዋጅተን በብሩህ ተስፋ ታጅበን ዓመቱን እድንቀበልና እድንጓዝ ከአደራ ጭምር እንመኛለን።
በቅድሚያ ለመላው በሃገር ውስጥ ሆነ በውጭ ሃገር ነዋሪ ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ እንላለን።
አዲስ ዓመት የብሩህ ተስፋና ወደፊት የመሻገር ነፀብራቅ እንደመሆኑ አሮጌውን ፣ ለህዝብ ሆነ ለወገን ስንክ የሆኑ ጉዳዮችን፣ አካሄዶችንና እፀፆችን በማረቅ አቀራራቢ፣ የጋራና ስሉጥ የሆኑ ዘዴዎችንና አሰራሮችን ሰንቀን መጓዝና በደቦ ወጥነን መንቀሳቀስ ይገባናል፣
በዚህ እምርታዊ፣ አሻጋሪ ህሳቤና ግንዛቤ ከተጓዝንና ከተገበርን የአዲስ ዓመት መነሻ አሳብን ፣ ጭብጥንና ፋይዳን ተገነዘብን ለማለት ያስችላል ።
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሚወዷት ሃገራቸው፣ ከወላጆቻቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው ፣ ከቅርብ ጓደኞቻቸው ወዘተ ወደውም ሆነ ሳይወዱ በመራቃቸው እንዲሁም ተሰደው በሚኖሩበት ሃገር በሚፈጠረው የባህል መጋጨት ፣ ልዮነቶችና የአሰራር ጫናዎች ፣ የስነ-ልቦና መዘበራረቅ፣ መዋዥቅና መወሳሰብ ሊፈጠር ስለሚችል በዚህም ምክንያት በመካከላቸው የአለመስማማትና የስብህና ግጭቶች ሊከሰቱባቸው ይችላል ።
ይህንን ፈታኝ ኩነት በመተሳሰብና በመወያየት ለመፍታት መመካከር የግድ ይላል እንላለን። ይህም ሆኖ አንዳንድ ግለሰቦች በያዙት የተፈጥሮ ቁመናና ለየት ባለ አመለካከታቸው ሆነ “ከእኔ ወዲያ ላሳር” በሚል ስሜት በኢትዮጵያዊውና ትውልደ ኢትዮጵያዊው መካከል ስምምነት እንዳይኖር ምክንያት ሊሆኑ ስለሚችሉ እንደዚህ ዓይነቶቹን ኢ-ማህበረሰባዊ ኩነቶች በአዲሱ ዓመት አሻሽለው ሊቀርቡ የሚገባ ይሆናል።
የፖለቲካ ድርጅቶችና አባላት መመሪያቸውንና መርሆዎቻቸውን ተቀባይነት በሌለው አካሄድና ተቃርኖ በተላበሰ መልኩ ለማስረፅ ፣ ለመጫን ሆነ የአቅም ልዮነቶችንና ክፍተቶችን ህሳቤ ውስጥ በማስገባ ከማጋጨት ከማናቆርና ልዮነቶች እዲሰፉ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ከአደራ ጭምር እንጠይቃለን።
እንደዚህ ዓይነት የበላይነት ስሜትና የእኔ ብቻ አውቅልሃለሁ አባዜ የተጠናወታቸው አንዳንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያን አየቆጠቆጡ ስለሆነ ፣ ስላሉም ከዚህ መሰሉ አጉል አስተሳሰብና ባህሪያት እንዲታረሙ የግድ ይላል። ሁሉም በአስተዋፅኦውና በተግባር ስለሚፈተን።
ለአንዳንድ ጥፋቶችና ግጭቶች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አጋዥ የሚሆኗቸው በሃገር ቤት መንግስት የተቋቋሙ ተቋማት ለምሳሌ እንደ ኢምባሲ ያሉና ስደተኞችን ተቀባይ በሆኑት ሃገሮች የተመሰረቱ እንደ ግብረ-ስናይ ያሉ ድርጅቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ከዚህ አይነቱ ከሕግ ያፈነገጠ አካሄዳቸውና አቀራረባቸው ሊታረሙና ሊታቀቡ ይግድ ይላል እንላለን ።
ለሃገርም ሆነ ለሰብአዊ ፍጡር የማይበጁና የማይፈይዱ አካሄዶችንና አስተሳሰቦች በተቻለ መጠን በአዲሱ ዓመት ገሸሽ ልናደርጋቸውና ሊወገዱ የሚገባ ይሆናል።
ከዚህ በታች ይበጃሉ ፣ በጋራ ፣ በሰላምና እጅ በእጅ ተያይዘን አዲስ ዓመትን በብሩህ ተስፋ፣ በፍቅርና በአንድነት ሊያሻግሩን ይችላሉ ብለን ያሰብናቸውን አሳላጭና መታረቅ ይገባቸዋል ያልናቸውን አስተሳሰቦችና አካሄዶች ለመላው ኢትዮጵያዊ ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ፣ በመንግስት ለተቋቋሙ ተቋማትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደሚከተለው እናቀርባለን :
- መላው ኢትዮጵያዊውና ትውልደ ኢትዮጵያዊው የዕርቅ ፣ የሳላም፣ እራስን የመግዛትና የይቅርታ መንፈስ ማጎልበት ይገባዋል እንላለን ፣
- መንግስት በጦርነት አባዜና አዙሪት ተዘፍቆ ሃገር መምራት የመቀጠሉን አባዜና ህሳቤ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባ ሲሆን ፣ ጦርነት አጥፊ እደመሆኑ ፣ ሁሉን የሰላም አማራጮች አሟጦ ስለተጠቀመ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማያዳግም መልኩ ጦርነቱን አገባዶ ወደ ልማት ፊቱን ያዞር ዘንድ እናሳስባለን፣
- ዛሬ ሃገራችን ያለችበት ሁኔታና እየተጋፈጠችው ያለችውን ችግሮች ከግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ስልጡን ፣ አንፃራዊ ሰላምና ጠንካራ የኢኮኖሚ ቁመና ባለቤት በሆኑ ሃገራት የምንኖር እንደመሆናችን መጠን አዋጭና ጠቃሚ ህሳቤዎችን፣ ሞራልና ሰናይ ልምዶችን፣ ዕውቀቶችንና ጭብጦችን መቅሰምና መላበስ ሊጠቅመን የሚችል ይሆናል፣
- መንግስት በጦርነት አባዜ ተወጥሮ የሚኖር ሳይሆን ጦርነቱ
- ጠቃሚ ይሆናሉ የምንላቸውን ተሞክሮዎችና ዕውቀቶች ለሃገርና ለወገን ማስተላለፍ አስፈላጊ እንደሆነ እንጠቁማለን፣
- ሃገረ ኢትዮጵያን ወክለው በውጭ ሃገራት የተሰየሙ እንደ ኢምባሲ ፣ ግብረ -ሰናይ ድርጅቶች እና መሰል ተቋማት የያዙትን ፖለቲካዊ ፣ ብሄርና የዕምነት አቋም እንደያዙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በሃቅ ፣ ያለ ፓለቲካ፣ ሃይማኖትና የብሄር ልዮነት፣ ያለአድሎና ያለ ጣልቃ ገብነት ማገልግል የግድ ይላቸዋል እንላለን፣
- በማወቅ ሆነ ፣ ባለማወቅ፣ ከግላዊ ስሜት ፣ ለግለሰባዊ ጥቅም መሻት ፣ ልዕልናና ለፖለቲካ ወገንተኝነት ሲባል ሕዝብ ሳይወክላቸው በኢምባሲ ሆነ በሌላ ተቋማት ድጋፍ ራሳቸውን ሹመው ሆነ አሹመው የተሰየሙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንመራለን የሚሉ ገቢ ሲያሰባስቡ የተጠቀሙባቸው የባንክ አካውንቶች የኢንባሲዎች ከሆነ የገቢና የወጭ ሂሳቦችን ለማወራረድ የሚያስቸግርና የማይቻል ስለሆነ ይህ አይነቱን አካሄድ ለሚመለከተው የኢትዮጵያ መንግስት ሕገ ወጥ መሆኑን ማሳወቅና ለወደፊቱ እንዲህ አይነቱ አሰራር እዳይደገም ማረጋገጫ ማግኘት፣
- ነገር ግን በግለሰቦች አካውንት ወይም በግል ፊርማ ርክክብ ተከናውኖ ከሆነ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሚወከሏቸው የሃገር ሽማግሌዎች ፣ የዕምነት ተቋማት ተወካዮችና ምሁራን አማካኝነት ያሉትን ሰነዶችና መረጃዎች ሰብስቦ ኢንዲመረመሩ ሁኔታዎችን በቀናነት ማመቻቸትና ከተቻለ የውጭ ኦዲተሮች ተቀጥረው ሙያዊ እገዛ በማድረግ ለኢትዮጵያዊያን ፣ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ፣ ለሚመለከታቸው የኢትዮጵያ የመንግስት አካላት ውጤቱን እንዲያሳውቁ ቢደረግ፣
- ይህ የማጣራት ስራ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ፣ ኢትዮጵያውያንና ለትውልደ ኢትዮጵያንዊያን በግልፅ የማጣራቱን ውጤት እንዲረድ በማድረግና በአፅንኦት ምላሽና አስተያየታቸውን እንዲሰጡ መመካከር፣
- መንግስት ሆነ የሚመለከታቸው አካላት የማጣራቱን ውጤት ተመልክተው የእርምት እርምጃ ካለ ማስተካከያ ሃሳብ እንዲያቀርቡ መሻት፣
- ይህን ተንተርሶ በስራው ሂደት ከተሳተፉት መካከል በአንፃራዊነት ምስጋና ሊቸራቸው የሚገባቸው ካሉ ማበረታታ፣
- እንዲሁም መንግስትና ኢምባሲዎች ሆደ ሰፊ ሆኖው የአስታራቂነት ሚናውን እንዲጫወቱ እንጠይቃለን፣
- ይህ ከሆነ በኋላ በኢምባሲው ፖለቲካዊ ወገንተኝነት፣ በጎ ፈቃድ ፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አጋጣሚውንና የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅመው ያለ ሕዝብ ይሁንታ፣ ፍቃድና ድምፅ የተሰየሙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ይወክላሉ ተብለው በተለያየ ስም የተቋቋሙ ቡድን ተወካይ ነን ባዮች በሙሉ በምስጋና እዲሰናበቱ በማድረግ ከኢምባሲ ቅጥር ግቢ ውጭ ማልሃተ ጉባኤ ተጠርቶ ማህበረሰቡን ሊወክሉ የሚችሉ አቅሙ ያላቸው፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ያልወገኑ፣ ከሙስና ፣ ከዝርፊያ የፀዱ እና በኢትዮጵያዊነታቸው አቱታን ያተረፉ የኮሚኒቲ ተወካዮች በየሃገሮቹ ሕግጋት መሰረት ተቋቁመው እንዲሰየሙና ስራቸውን እንዲያከነውኑ ሁኔታውን ማመቻቸት፣
- በአዲሱ የስራ-አስፈፃሚ ምርጫ ተመጣጣኝ ባለው መልኩ የብሄር ብሄረሰቦችን መሉ ውክልና ከግንዛቤ ውስጥ ባስገባና በአካተተ መልኩ እንዲከወን እያሰሰብን ፣ ከዚህ በፊት በህውሃት ዘመን እንደነበረው ሆነ ከለውጡ በኋላ ይታይ የነበረው የአንድ ብሄር ስብስብ የኮሚኒቲ የኮሚቴ አባላት መርጦ የመሰየም አካሄድ እንዳይደገም በአፅንኦት እናሳስባለን፣
- እንዲሁም ተመራጮች በውጭ ሃገር ሲኖሩ በኢትዮጵያዊነታቸው ጥገኝነት ያገኙ መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፣
- ሃገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ማዕበል ላይ ስትሆን እዳለመታደል ሆኖ ያጋጠሟትን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ፣ የወገን መፈናቀልን ፣ ለመከላከያ ኃይላችንና ጥምር ጦሩን ለማበረታታት እየተከወኑያለው የድጋፍና የሞራል መነሳሳቶች እሰየው የሚያሰኝ በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው እንዲሁም የሁሉም ማህበረሰብ መሻትና ማበረታታት ሊሆን ይገባዋል እያልን መላው ኢትዮጵያውን ያሳተፈ እንዲሆን መትጋት የሚሻ ይሆናል፣
- ነገር ግን በቅርቡ ሆነ ከለውጡ በፊት በነበረው ስርዓት ይታዮ የነበሩ የቡድተኝነት መፍጨርጭርና መሰል እንቅፋቶቹ ሊወገዱ ይገባል እንላለን፣
- ነገር ግን ይህን ሃገርን የመደገፍና የአለሁ ባይነት መነሳሳት ተጠቅመው የግል ኑሯቸውን ለመደጎምና ኪሳቸውን ለማሳበጥ የሚሞክሩትን ጥቂት ስግብግቦችና በሃገር ስም የሚነግዱትን እንቃወማለን ፣ እጃቸውን ይሰብስቡ እንላለን፣
- ይህን አፀያፊ የሞራል ድቀት እና ኢ-ማህበረሰባዊ ዝቅጠት በተለያየ መንገድ የተጋፈጡትን ምስጋናችንን እየቸርን የእርቅ፣ የሰላም ጥሪውን ተንተርሰው ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ትግላቸውን እንዲቀጥሉና የመፍቴውም አካል እንዲሆኑ እናበረታታቸዋልን፣
- ኢትዮጵያዊውንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ፣ በአመራር ኮሚቴነት ተሰይመው እንዲመሩ በሕዝብ ተሳትፎ፣ድምፅና መሻት የሚወከሉ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መላው ኢትዮጵያዊያንን የሚመለከቱበት መነፀር በአንድነት፣ ከልዮነትና ከጥላቻ በፀዳ መንፈስ ሊሆን የሚገባ ሲሆን ይህ እንቅስቃሴያቸው ከግል ሙካሻ መሻት የፀዳ እንዲሆን እንመክራለን፣
- ነገር ግን ባለፈው ስርዓቶች የተወረሱ የመከፋፈል አካኤዶች ማለትም ህዝቦች በተለያየ ሥርዐተ መንግስታት ይፈጠራሉ ፣ ያድጋሉ፣ ይማራሉ፣ መንግስትን፣ ሃገርንና ሕዝብን በቅንነት ያገለግላሉ። በየሥርዓቱምችች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ነገር ግን ባልተጨበጠ ማረጋገጫ ኢትዮጵያዊያንን “አንተ የደርግ ፣ የኢሰፖ፣ የኢሕአፓ ፣የወያኔ፣ የብአዲን የኦነግ ፣ የኦዲድ ፣ የኦነግ ሸኔና የብልፅግና ወዘተ አባል ነህ” እያሉ መፈረጅ ፣ ማሳቀቅና ማግለል ጥዮፍ አስተሳሰብ ስለሆነ ሊወገድ ይገባል፣
- በእነዚህ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ መንግስት በወንጀለኝነት ከፈረጃቸው በቀር ግለሰቦች አባል መሆናቸው መብታቸው ሲሆን ወንጀለኛ እስካልሆኑ ድረስ ልዩነትና መቃቃር ካለ አቅረርቦ ለማህረሰቡ አስጊ አስካልሆኑ ድረስ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ብቻ በልዩነታቸው ላይ በሰከነ መልኩ ተነጋግሮ ለመፍታት መሞክር አዋጭ ነው እንላለን፣
- አንድ አነጋገርና ትብህል አለ “ ሃገር የምታደርግላትን አስብ እንጂ የምታደርግልህን አታልም” John F.Kennedy እንደተባለው ሃገሬን ጩሄላታለሁና በምላሹ ፣”ልትከፍለኝ ይገባል” በሚል ህሳቤ መወራጨትና መኮፈስ ጥዮፍ ህሳቤ ነው፣ ለምን ቢሉ በዱር በገደሉ ለሃገሩ ሉዓላዊነት እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ ነፍሱን የሚገብር ሕዝባዊ ሰራዊት አለና ፣
- መላው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ እርስ በርስ ከመካሰስ፣ ከመወነጃጀል ፣ ከመሰረተ ቢስ አሉባልታ፣ ስም ማጥፋትና መፈራረጅ በአምላክ ስም እዲፅዳ እንማፀናለን
- ድህረ ገፆች ፣ መገናኛ መረቦች /Medias/ እና በሙያው የተካኑም ሆነ ያልተካኑ ጋዜጠኞች ከስሜታዊነት ዕርቀው ማህበረሰቡን በማገልግል ሀቀኛ መረጃ እንዲያስተላልፉ ፣ ለዕርቅ ፣ ለሰላም መውረድ እዲተጉ እንዲሁም ከማህበረሰቡ ህሳቤ ፣ ፍላጎትና መቸት ውጭ አላግባብ ኢ- ሞራላዊና ስብህና የጎደላቸው ግለሰቦችና ተቋማትን ከማጋለጥ ወደ ኋላ እንዳይሉ እናሳስባለን፣
- በተረፈ ኢትዮጵያ ከተጋፈጠባት አደጋ አምላክ እንደሚዋጃት እያረጋገጥን መላ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በፀሎት እንዲተጋ እናሳስባለን።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር።
የሰላምና የዕርቅ ጉባኤ።
ተፃፈ በተዘራ አሰጉ
ለንደን-ታላቅዋ ብሪታንያ።