በሲሳይ ሳህሉ|ሪፖርተር
የአማራ ክልል ዳኞች ማኅበር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ፣ ሕገ መንግሥቱንና የፓርላማውን ሥልጣን በመጣስ ዳኞችን ሰይሟል የሚል ቅሬታ አቀረበ፡፡ ለዳኞቹ የተሰጠ ሹመት እንደሌለ፣ ነገር ግን ውዝፍ መዛግብትን ከሰኔ 2014 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 2015 ዓ.ም. ድረስ ለማጠናቀቅ የሚያግዙ አራት ዳኞች ከከፍተኛ ፍርድ ቤት መመደባቸውን ሪፖርተር ከምንጮች ሰምቷል፡፡
ጉባዔው ሥራዎችን ለማከናወን በፌዴራል ከፍተኛና በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የሚገኙ ዳኞችን ጨምሮ በክልል ደረጃ በዳኝነት ከሚያገለግሉ ዳኞች በፈተና አወዳድሮ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየሾመ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ላይ አሠራሩን ከሕግ ውጪ እንደቀየረ ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚሾምበትን ሥርዓት ሳይከተልና በክልል የሚገኙ ዳኞችን መብት ሳይጠብቅ፣ ለፌዴራል ፍርድ ቤት የሚሠሩ ዳኞች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይሾሙ፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ውሳኔ ብቻ ዳኛ በማድረግ ተሰይመው እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም አሠራሩ በክልል ደረጃ የሚሠሩ ዳኞች በፌዴራል መንግሥቱ ዳኝነት ሒደት ላይ የመሳተፍን መብት የነፈገ እንደሆነ በመግለጽ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በዚህ ረገድ የሰጠውን ውሳኔ እንዲከልስና የተለመደውን ሕጋዊ አሠራር በመከተል የክልል ዳኞችን መብት፣ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮችን ሥልጣን እንዲያከብር ‹‹አጥብቀን እንጠይቃለን‹‹ ሲል ሰኔ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአሁን ቀደም በፈተና አወዳድሮ ያለፉትን የክልሉን ዳኞች በማግለል፣ ያለ ውድድር የሚፈልጋቸውን ሰዎች ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት እንዲመደቡ በማድረግ፣ በሕገወጥ መንገድ መሥራቱንም በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ውሳኔው የሕገ መንግሥቱን ዓላማ ያላገናዘበ በአገሪቱ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት ሥርዓት የመሳተፍ መብትን የነፈገ መሆኑን ማኅበሩ ገልጿል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ብቻ የታጠረ አድርጎ በመገንዘብ የክልሎችን ተሳትፎ መንፈጉ፣ በክልል ደረጃ ሲያገለግሉ የቆዩትን ከፍተኛ የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን ዳኞች የሚያገል፣ ለሚፈለገውም ‹‹አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት›› የሚለው የሕገ መንግሥቱን መርህ የጣሰ እንደሆነ አስረድቷል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78(2) መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የዳኝነት አካል እንደሆነ መደንገጉን፣ እንዲሁም በአንቀጽ 80(3)(ሀ) እንደተመላከተው፣ በክልል ፍርድ ቤቶች የሚታዩትን የፌዴራል ጉዳዮችና የክልል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን የተሰጡትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔዎች በሰበር የማየት ሥልጣኑን በመጠቀም፣ ጉዳዮችን እየተቀበሉና እያስተናገዱ እንደሚገኙ ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአሁን ቀደም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሲሾም በአገሪቱ ከሚገኙ ዳኞች መካከል በማስታወቂያ ጥሪ ተደርጎ በፈተናና በትምህርት ዝግጅት መሠረት በማወዳደርና አሸናፊዎችን በመለየት፣ በመጨረሻም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሾም እንደነበር ማኅበሩ አውስቷል፡፡
ማኅበሩ ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች አስተዳድር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት በላከው ደብዳቤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ውሳኔ እንዲነሳና እንዲታረም ሲል ጠይቋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሕገ መንግሥታዊ አሠራርን በመጣስ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራርና በጉባዔው ውሳኔ ብቻ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚሠሩ ዳኞችን ያለ ምንም ውድድርና ምልመላ ሥርዓት መርጦ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት ተሰይመው እንዲሠሩ መሾሙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የሕዝብ ሉዓላዊነት ሥልጣን የሚጥስ፣ በመንግሥት አካላት መካከል ያለውን የእርስ በርስ ቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት የሚፃረርና በፌዴራል ሥርዓቱ መርህ የሆነውን የዜጎች በፌዴራል መንግሥቱ የመሳተፍና የመወከል መብታቸውን የሚጥስ ኢሕገ መንግሥታዊ አሠራር ስለሆነ ሊታረም እንደሚገባው አስረድቷል፡፡
በሌላ በኩል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሠራር፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ዳኞች በሕግ ያላቸውን የመወዳደርና የመሳተፍ መብት ላይ መዋቅራዊ በሆነ መንገድ አድልኦ እንዲፈጠር ማድረጉን በመግለጫው አመላክቷል፡፡
ዳኞች በሕገ መንግሥቱ ያላቸውን የእኩልነት መብት የሚጥስና የሚያገል፣ ዜጎች በሕግ አግባብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባልተሾመ ዳኛ የሕይወት፣ የነፃነትና የንብረት ክርክሮችን እንዲያዩ ማድረግ ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ያለ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲያጡ የሚያደርግ መሆኑን፣ እንዲሁም ዳኞች በአስተዳደሩ ይሁንታ እንዲመረጡ ማድረጉ አስተዳደሩ የፈለገውን ሰው/ዳኛ የሚያደርግበትና በደረጃ የሚያሳድግበት ሥርዓት የመፍጠርና ይህም ሥልጣንን ባልተገባ መንገድ ለመገልገል በር እንዲከፈት የሚያደርግ መሆኑን፣ ማንኛውም መሥፈርቱን የሚያሟላ ዳኛ በውድድር እንዲሳተፍ በማድረግ የተሻለ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ዳኞች እንዲሾሙ የፈጠረውን ዕድል የሚጥስ ሰለሆነ እንዲታረም ሲል አሳስቧል፡፡
ጉባዔው ዳኞችን ለመሾም ሥልጣን የሌለው ስለመሆኑ ጠቁሞ፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55(13) እና 81(2) መሠረት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ለመሾም ሥልጣን የተሰጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን፣ ጉባዔው በምልመላ መሥፈርቱ መሠረት መልምሎ ዕጩዎችን ለምክር ቤቱ ከማቅረብ ያለፈ የመሾም ሥልጣን እንዳልተሰጠውም አብራርቷል፡፡
በዚህም ሒደት ዳኞች ያለ ውድድርና ያለ መሥፈርት በጉባዔው መመረጣቸው አንድ አስተዳደራዊ ውሳኔ ሲወሰን ሊከተል የሚገባውን ሒደት፣ የምክንያታዊነት መርህንና የግልጽነትን አሠራር የሚጥስ ከመሆኑም በላይ በአመራሩ (አስተዳደሩ) የማይታወቁ በክልሎች ያሉ ጠንካራ ዳኞችን ያለ ምክንያት ያገለለ አሠራር መሆኑንም ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ዳኞች ማኅበር ያቀረበውን ቅሬታ በሚመለከት ሪፖርተር ማብራሪያ ለማግኘት የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊን በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የጉባዔ ሰብሳቢንና ምክትል ሰብሳቢን ለማግኘት የተደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ፣ አጭር የጽሑፍ መልዕክት የተሳካ ቢሆንም ምላሽ ለማግኘት አልተቻለም፡፡