የፕሬሥ ነፃነትን፣ ከመናገርና ከመፃፍ ነፃነት ነጥሎ ማየት አይቻልም – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ 

“ Freedom of speech is the liberty to speak and write without fear of government restraint. It is closely linked to freedom of the press. “

ይድረስ  ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት ።

ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥት ያሥፈልጋታል። ይኽንን አምናለሁ። ይሁን እንጂ በየፈርጁ የተጠናከሩ ተቋማት እሥከሌሉ ድረሥ መንግሥት ጠንካራ ለመሆን እንደማይችልም ይታወቃል። የኢትዮጵያን መንግሥት ጨምሮ  ፤ በዚህ በ21 ኛው ክፍለ ዘመን የነቃውን ህዝብ በወጉ ለመምራት የሚችሉት ዘመኑንን የሚዋጁ ተቋማት ሲኖራቸው  ነው። ከዘመኑ ጋር የሚመጣጠን ፣ የፍትህ ተቋም ፣ የወታደራዊ ተቋም ፣ የደህንነት ተቋም ፣ የጤና ፤ የትምህርት የአስተዳደር ና የአገልግሎት   ተቋም ። ወዘተ። ከሌላቸው በእያንዳንዱ አገር ዜጋ ህይወት ና ኑሮ ላይ ትልልቅ ና ትንንሽ ጠባሣ ማሥከተላቸው አይቀሬ ይሆናል።  መንግሥታት ሁሉ።

ይኽንን ኃቅ በአሜሪካ በጥቂት  በቀወሱ ግለሰቦች የእብድ ድርጊት በየጊዜው ፤ ህዝብ በተሰበሰበበት ሥፍራ ፤ በእምነት ቦታ እና በትምህርት ተቋማት ሣይቀር ፣  የሚፈፀመውን ፣ የጦር መሣሪያ ድንገተኛ ጥቃት አንፃር ተመልክቶ  ማረጋገጥ ይቻላል  ። በየትምህርት ቤቱ ፣ የንፁሀን ዜጎች ና የህፃናቶች ፣  የአዱኑን ፣ ጩኸት በየጊዜው የሚሰማው ፣ የጦር መሣሪያ ሽያጪን በወጉ የሚቆጣጠር ተቋም በአሜሪካ ባለመኖሩ ነው ።

አሜሪካ በፍትህ ፣ በወታደራዊ ፣ እና በሲቪል አሥተዳደራዊ ተቋማት ከፍታ ላይ ብትገኝም ፣ እንደ ከረሜላ የሚሸጠውን የመግደያ መሣሪያ በወጉ የሚቆጣጠር ተቋም ግን የላትም ። እናም የአእምሮ መቃወስ ያለባቸው ዜጎች ሣይቀሩ የጦር መሣሪያ ከሚቸረቸርባቸው ሱቆች እየገዙ  እምቦቃቅላዎችን በትምህርት ገበታቸው ላይ እያሉ እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ ሲደፏቸው በእንባ ታጥበን መረጃውን እያየን ነው  ።  በነገራችን ላይ በቻይና የጦር መሣሪያ መሸጫ ሱቅ የለም ። ሁሉም መሣሪያ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነው ያለው ። በመሆኑም  በግለሰብ  የተከሰተ  እንደ አሜሪካ አይነቱ ፣ የአቶማቲክ መሣሪያ  ግድያ እሥከዛሬ  የለም ። ቆየት ባለ ዘመን በአንድ ትምህርት ቤት በጩቤ አንድ ወጣት ቻይናዊ የተወሰኑ ተማሪዎችን ካቆሰለ በኋላ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ግን እርግጥ ነው ። የሞተ ግን አልነበረም ። ይኽንን እውነት ሰሞኑንን ሲኤን ኤን በሐሚዲ ዘካርያን በኩል በአሜሪካን የህፃናቱን ግድያ አሥመልክቶ ያቀረበውን ዘገባ ማየት ይቻላል ።

በአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን በኩል ፣  የጦር መሣሪያን ሽያጭና የሚሸጡትንም ቀላል መሣሪያዎች ገደብና አይነት ፣ማን እና በምን ሁኔታ መግዛት እንዳለበት ፤  በሽያጭ ህጉ ውሥጥ ፣ የመቆጣጠሪያ አንቀፆችን  በመካተት ቁጥጥሩን ማጥበቅ  እና የጦር መሣሪያ ሽያጭ ልቅ መሆኑ እንዲቀር  በዜጎች ግፊት እየተደረገ ነው ።የአሜሪካ  መንግሥትም በአራተኛው መንግሥት አማካኝነት ፣ በቅርቡ በአንድ  ወፈፊ  አሜሪካዊ ወጣት በትምህርት ላይ ያሉ ህፃናትና መምህራኖቻቸውን ልክ በጦር ሜዳ እንደተገኙ ጠላቶች እየተኮሰ በመግደሉ የተነሣ ፣ የጠመንጃን ቁጥጥር አልባነት ጦሥ ጥንቡሣሥን  በቅጡ የተገነዘበ ይመሥላል ።

የኢትዮጵያ መንግሥትም በሁለት እግሩ ሁለት ዛፍ መውጣትን አቁሞ አንዱን ዛፍ በወጉ በመውጣት ጫፉ ላይ ከደረሰ ፣ የጠመንጃን ፣ የጦር መሣሪያን በየቦታው መነዛት አደጋ  በቅጡ እንደሚገነዘብ አምናለሁ ።

ይሁን እንጂ ዛሬና አሁን ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ያለበትን ሥራ የዘነጋ ይመሥላል ። የጦር መሣሪያ በአማራ ክልል  የበዛበትና እያንዳንዱ አርሶ አደር በለጠመንጃ የሆነው ፣  የኢህአዴግ የከፋፍለህ ፤ የጎሣ ና የቋንቋ  ሥርዓት ፤ ትልቁን ኢትዮጵያዊነት ሥለ አንኳሰው ነው ።

ኢትዮጵያ ከወያኔ   በኋላ በአዲሱ የለውጥ መንግሥት ከወደቀችበት ብትነሣም ፣ ዛሬ ደግሞ ተመልሣ ወደ ነውጥ የምትገባበት እና የምትወድቅበት መንገድ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እየተፈፀመ ነው ።

አገር ሠላም አጥታ ፤ ክልሎች እርስ በእርስ ጦርነት ውሥጥ ተዘፍቀው ፣ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ፣ እልል በቅምጤ እንዳይሉ እና ወደ ቀደመው ኢትዮጵያ የሚለውን ሥያሜ የማጥፋት ተልዕኳቸው ሥኬት በተጠናከረ  ኃይልና በተቀናጀ ኃይል መራመድ እንዳይጀምሩ ፤   ባለማወቅ   ለእነዚህ ፀረ ኢትዮጵያ  ኃይሎች ፣ ተባባሪ የሆኑ የመንግሥት እጆች ፣ ዛሬ ላይ መንቃት ይኖርባቸዋል ። ነቅተውም ከአፍራሽ ድርጊት ተባባሪነት ራሳቸውን ማግለል ይጠበቅባቸዋል ። አለበለዚያ ባለማወቅ መከላከያውን ጭምር ለሁለተኛ ጊዜ ሊያፈርሱት ይችላሉ ። በወያኔ ፈርሶ ነበር ። በብልፅግና መንግሥት ግን መደገም የለበትም ።

መንግሥት በሚያሥመሠግነው  መልኩ  የገነባው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ፣ እንዳይፈርሥ ከተፈለገ ፣ መንግሥት በሁለት እግሩ ከወጣበት አንድ ዛፍ ላይ ሆኖ መፃኢውን አደጋ በመገንዘብ የሁሉንም ክልሎች ሠራዊት ወደ አንድ ዕዝ በማምጣት የክልል ልዩ ኃይሎችን በሙሉ “ የፈጥኖ ደራሽ  ሠራዊት “ በማለት እንደገና በማቋቋም እንጂ የመከላከያ ሠራዊት ተገዳዳሪ ጦርን እዛና እዚህ በየክልሉ ጡንቻቸው ሲፈረጥም በማድረግ መሆን የለበትም   ።

የክልል ልዩ ኃይል በሙሉ ፣ “  የፈጥኖ ደራሽ ጦር “ ተብሎ በመከላከያ ሥር እንደገና መዋቀር አለበት ። የትግራይ ልዪ ኃይልን ጨምሮ ።  በአዋጅ ጥሪ ሊደረግለት ይችላል ። ይኽም ለውጥ ፣ በልዩ ኃይሉ ጉያ የተጠለሉትን ቱጃር የወያኔ አባላት እርቃናቸውን እንደሚያሥቀራቸው  አሥባለሁ ።

ይኽንን አደረጃጀት ለመፍጠር የሚያሥችሉ የህግ መአቀፎችን በአሥቸኳይ ማውጣት አገራችንን ከእርሥ በእርሥ ግጭት የሚታደጋት እንደሆነ አምናለሁ ። በፍፁም የየክልል ጦር ወይም ልዩ ኃይል ፤ ብሎ ነገር መኖር የለበትም ። ከህግ አሥከባሪ ፣ ከፍትህ አካላት ጋር የሚሰራ ፖሊሥ እንኳን ቢሆን ሥልጠናውን በፊደራል ደረጃ መውሰድ አለበት ። ብሎ ያምናል ይኽ ፀሐፊ ።

የሁሉንም ክልል ፖሊሶች በማሠልጠን በከተማ እና በገጠር እንደ አግባብነቱ ሊመድባቸውም ይገባል ። ይኽንን ሲያደርግም በሥልጠና ወቅት ፣ ሰዎች በሆኑ ዜጎች መካከል መቀራረብን በመፍጠር ጠባብ አሥተሣሠብን ያስወግዳል ።

ይኽንን ሳያደርግ ፣ እንደወረደ ፣ የኢህአዴግን የጦር አደረጃጀት ተከትሎ ፣ በየክልሉ ፣ የክልል ልዩ ኃይል ና ፖሊሥ የሚል ሥያሜ ሠጥቶ አገርን በሠላም ማሥተዳደር ከቶም የሚቻል አይመሥለኝም ።

የአማራ ፋኖንም ሆነ በፋኖ ሥም የሚንቀሣቀሥ ሥውር ኃይልን ትጥቁን በሠላም ለማሥፈታት እና የጦር መሣሪያን ጦሥ ለማሥቀረት የሚቻለው በአዋጅ የነበረውን የየክልሉን ጦር አደረጃጀት አፍርሶ በፊደራል መንግሥት ሥር በማድረግ ና አገሩን በውትድርና እና በፖሊሥ ለማገልገል የሚፈልገውን እና ብቁ የሆነውን በወጉ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የፖሊሥ ኃይል ጋራ እንዲቀላቀል በማድረግ ነው ። ይኽንን ጠቃሚ እና አገርን የሚታደግ ሃሳብ መከላከያው እንደሚቀበለው አምናለሁ ። የሚኒሥትሮች ምክር ቤትም አገርን ለማዳን ሌላ አማራጭ እንደሌለ የሚገነዘብ ይመሥለኛል ። እናም በአፈ ቅቤዎች በልበ ጩቤዎች ሰበብ  ከእውነታው ውጪ በመሆን ተገቢ አይሆንም ። የቀደመው ሥርዓት በፈጠሰው ድንብርብር ውሥጥ እያለን ፤ ሥለመከላከያ ና ፋኖ እንዲሁም ሥለ አገር ሠላምና ፀጥታ ጉዳይ አንሥተው ፣ መንግሥትን ለምን ተቹ ፤ ለምን ለአገር ጎጂ የሆነ የክልል እና የፊደራሉን መንግሥት ሀፀፅ እና ሥህተት አጋለጡ በማለት ፣ ከብዕር ና ከአንደበት ውጪ ጉልበት የሌላቸውን ጋዜጠኞች ና ማህበራዊ አንቂዎችን ማሠርና ማጎሣቆል ፤  ገዢው ፓርቲ ብልፅግና ኃቁን እያወቀ  ከገባበት አጣብቂኝ የሚያላቅቀው ከቶም አይሆንም    ።

ደግሞም መናገር በተፈጥሮ የተሠጠ የፈጣሪ ሥጦታ መሆኑንን አንዳንድ የፓርቲው  ከፍተኛ አመራሮች በቅጡ ቢገነዘቡ ፣ ያልተገባ ማዋከቡን ረገብ አድርገው ፣ ፓርቲውን ከውድቀት ያድኑታል ብዬ አምናለሁ  ። ሠው በንግግሩ ፣ ብቻ ሊታሠር አይገባም ። እገሌን በለው  እረደው ፣ አቃጥለው ፣ ጣለው  እያለ የሚፎክርና የሚያሥፎክር እሥካልሆነ ድረስ ፣   ጣለው በራሱ ትልቅ ችግር ያሥከትላል ።    ሥነ ቃላችንም ችግሩን አበክሮ ይነግረናል ።

የምን ጣለው ጣለው

የምን በለው ፣  በለው ፣ የምን ጣለው ፣ ጣለው ፣  ይቸግር የለም ወይ ደም መላሽስ ካለው ፣ በማለት ። እናም ለእውነተኛ እና ላልተጭበረበረ ፍትህ መገዛት እና ከህግ በታች መሆን እንጂ ፣ በትዕቢት ፣ በማን አህሎኝነት ፣ በአጋዚ ሠራዊት መተማመን ተገቢ አይሆንም ። ከህዝብ አብራክ በወጣ በመከላከያ ሠራዊት ኃይልም መመካት የኋላ ፣ ኋላ ዋጋ ያሥከፍላል ።  ኢህአዴግም በአጋዚ ተመክቶ ፣ በአፍጢሙ ተደፋ እንጂ ፤ በጉልበት ሥልጣኑንን ማሥቀጠል ከቶም አልቻለም   ። ጉልበተኝነት ሌላ ጉልበተኛ ይወልዳል እንጂ  የተረጋጋ ሠላምን  አያዋልድም ።  ። እናም “ ተበታችሁ “ ፣ ብሎ በጭካኔ ለመውገር ፣ መቀርቀሪያ እና አጣና ማንሣት ፤  ናቃችሁኝ ብሎ አንደበትን መዝጋት በህዝብ ያሥጠላል እንጂ አያሶድድም    ። መንግሥትን የሚያሶድደው በፍትህ ፣ በነፃነት እና በእኩልነት ማመን ነው ። ልክ እንደ አሜሪካን መንግሥት የህግ የበላይነትን ከዳኝነት ነፃነት ጋር ፣ በተጠናከረ ተቋም ማረጋገጥ ነው ። መንግሥት የሚጠበቅበት ። ሥልጣኔው ቢያቅተን መልካም አሥተዳደሩን መኮረጅ እንዴት ያቅተናል ፦

የአሀገሬ መንግሥት ፣  ይህንን ሃቅ ከድሮ የአሜሪካን የህግ ታሪክ መገንዘብ ይችላል ። በአሜሪካ የህግ ታሪክ በመናገር መብት ላይ ትልቅ አሥተዋፆ የነበራቸውን ግለሰቦች እያንዳንዱን ህግ ና የወጣበትን መንሥኤ አንብቦ በመረዳት መረዳት ይቻላል ። …

በቀደመው እና አርጅቶ እንደ ጨርቅ በተጠቀለለው ከኋላችን ተከምሮ በሚታየው ዘመን ፣በአሜሪካ ዴሞክራሲ ውሥጥ የዜጎችን ልብ በደስታ ያሞቀ   ! ዕፁብ ! ድንቅ !  ያሰኘ ፣ ውሳኔ በመናገር የተፈጥሮ ነፃነት ፤ የህግ ጉዳይ ላይ መሠጠቱ  በታሪክ ይታወሳል ። ይኼ ጉዳይ የአሜሪካንን ገፅታ በማበላሸት ላይ የጠነጠነ ፣ እሱን ተከትሎ የመጣ የፖሊሥ ክልከላ ነው ። ነገሩ እንዲህ ነው ፣ አንድ አሜሪካዊ የበዙ ቱሪስቶች ዘወትር በሚጎርፉበት ባቡር ጣቢያ ይለምን ነበር ። የአሜሪካንን ገፅታ ታበላሻለህ ተብሎ ፤ እንዳይለምን በፖሊሥ ተከለከለ ። ይኽንን የሰሙ የሰብዓዊ መብት ተሞጋች ጠበቆች የፖሊሥ ተቋሙን ከሰሱ ። በክርክሩም እረቱ እና ሰውየው መለመኑንን ቀጠለ ።     በክርክሩ ወቅት ጠበቆቹ የረቱበት መከራከሪያ ዋና ጭብጥ  ፤ መንግሥታችን ቆም ብሎ በዕውቀት እና በጥበብ እንዲያሥብ የሚያሥችልው ነው ። እናም የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ጠበቆቹ   የረቱበትን ጭብጥ     ። መንግሥት የሰው ሥብሥብ ፤ አንድ  ግዙፍ ተቋም ነውና ። በራሱ ።

መንግሥት  ከእውነት ጋር ከመጋጨት ከእውነት መማር ይጠቅመዋል ። እናም … ለለማኙ አሜሪካዊ ጥብቅና የቆሙለት ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ጠንካራ  ህገመንግሥታዊ  መከራከሪያን በማሥተዋል ይመልከተው ።  የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ጠበቆች መከራከሪያ ነጥባቸው ይኽ ነው ። ” ይኽ ሰውዬ በተፈጥሮ የተሰጠውን የመናገር ነፃነት ፣ የማውራት ነፃነት ፣ አንዳች ሃሳቡን አውጥቶ ለሌላው   አምሣያው የመግለፅ ፣ የማሳበቅ ፣ የማሳወቅ ፣ ዝባዝንኬ ሣይቀር ለፍልፎ የማሥጠንቀቅ ነፃነት ። ተፈጥሮውን የመጠቀም መብት ፣ የትም ሥፍራ ማንንም እርዳታ የመጠየቅ ። ወዘተ ። ያልተገደበ መብት አለው ። አይደለም ባቡር ጣብያ ፣ በነጩ ቤተመንግሥት ፊት ለፊትም ተቃውሞውን በሠላማዊ መንገድ ማሣወቅ ይችላልና በገፅታ ማበላሸት ሰበብ የግለሰቡ የተፈጥሮ መብት ማፈን አይገባም ። ” የሚል ነበር ። ፍርድ ቤቱም በዚህ መከራከሪያ ነጥብ እውነተኛነት አምኖ ፣ እንዳይለምን  ገፅታ ያበላሻል የተባለውን ዜጋ  ” መለመን መብትህ ነው ። አንደበትህን ማንም የመዝጋት መብት የለውም ። ቀጥልበት ። ” በማለት አሥደናቂ ፍርዱን ሠጥቷል ።

ከዚህ እውነት ተነሥተን የአገሬ ጋዜጠኞች ፣ በተፈጥሯዊ መብታቸው ሃሳብ ከማዋጣት  የዘለለ ምን የሰሩት ምድራዊ ሐጢያት አለ ? …

ተመስገን ደሣለኝን ጨምሮ ፣ ጋዜጠኞች ከመናገር እና ከመፃፍ ባሻገር ዲሽቃ ይቅርና ምላጭ ይዘው መንግሥትን ለማድማት የተሠለፉ ያለመሆናቸው ይታወቃል ። እና ለምን የተፈጥሮ ነፃነታቸው ተገፎ ይታሰራሉ ?

አብይ መራሹ የብልፅግና መንግሥት መለሥ መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት ለአሥራአራት ዓመታት የሠጠውን  የፕሬሥ ነፃነት ያህል እንዴት ገና ከጅምሩ መሥጠት አቃተው ? በበኩሌ ገና ሁለት ዓመት ሳይሞላው ማፈን መጀመሩ እጅግ አሥገርሞኛል ። ለማመንም ከብዶኛል ።

እሥከ 1997ድረሥ በግል መፅሔቶችና ጋዜጦች ምን ሲፃፍ እንደነበር የታወቀ ነው ። በተለይም በጦቢያ መፅሔት የሚቀርቡ ሃሣቦች ዛሬ ላይ ሆኜ ሣያቸው በዛሬው የመንግሥት ፍራቻ ግራ እጋባለሁ ። ከአሁኖቹ መፅሔትና ጋዜጦች እጅግ የበዙ እነ አርያ ተሥፋማርያም በብዕር ሥም የሚሣተፉባቸውም ጋዜጦች ነበሩ ።  በካርቶን ሥዕል ሣይቀር እነመለሥ በአሥቀያሚ መልኩ ፣ እንዴት ይገለፁ እንደነበር ዞር ብሎ መመልከት ይቻላል ።

( እኔም በዛን ወቅት ከአሁኑ ጊዜ ሃሳብ እጅግ የጠነከሩ መንግሥትን የሚሸነቁጡ ሂሶች ፣አሥተያየቶችና አሽሙረኛ ፅሑፎች ይሥተናገዱ ነበር ። እኔም የበኩሌን ሃሳብ በኔሽን  ፣ በሪፖርተር ጋዜጣ እና በአዲሥ ዘመን ጋዜጣ ጭምር በዘመነ መለሥ ሃሳብ  አዋጣ ነበር ። )

ዛሬ እና አሁን ጋዜጠኞች እና የተለያዩ ሰዎች ሃሳባቸውን በተለያየ ሚዲያ ያዋጣሉ እንጂ እንደ ቀደመው ጊዜ የመፀሔት ክምር የለም  ። ይሁን እንጂ በዘመኑ ሚዲያ ፣ የሚያዋጡት ሃሳብ የሚረባም ይሁን የማይረባ ሃሳባቸውን ለተደራሲው ማቅረባቸው ሊወገዝ እና ሊያሣሠራቸው አይገባም ። ሃሳቡ ጥፋትን የሚጭር ፤ የጦርነት ነጋሪትን የሚጎሥም ፣ ጥላቻን የሚሠብክ ፣ ከሙያዊ ሥነምግባር ይልቅ ለሆድ የተገዛ ከሆነ ፤  በለው ፣ ግደለው ፣ ጨርሰው ፣ አጥፋው ወዘተ የሚል ይዘት  ካለው ፣ እና ጥላቻን የሚያራግብ ከሆነ ያ ንግግርና ፅሐፋቸው ተጠቅሶ በግልፅ በአደባባይ ፣ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባቸዋል እንጂ ፣ ሊታፈኑ በድንገት በመሣሪያ ታጅበው እንደሽፍታ ወደ እሥር ቤት ሊወረወሩ አይገባቸውም ። ሀግን ከጣሱ በአግባቡ እንደማንኛውም ህግን እንደጣሠ ግለሰብ  ክስ ሊመሠረትባቸው ና በአንድ ፖሊሥ መጥሪያ ፤ ከአንድ ፖሊሥ ጋራ ፣ ወደ ሀግ ሥፍራ ሊሄዱ ይችላሉ ። በአጀብና በአፈና መልክመ መውሰድ እና ከወሰዱ በኋላ ሰበብ መፍጠር በእውነቱ ፀረ ፍትህ ድርጊት ነው ። ይሄ ኩንን ድርጊትም  በሰው ባያሥጠይቅ በፈጣሪ ያሥጠይቃል ።

በነገራችን ላይ ፣ በዚህ አገር ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ማለት እየተለመደ መጥቷል ። ይኽ የመበላላተ የሤራ ፖለቲካ በፍጥነትና በአሥቸኳይ ሊቆም ብቻ ሣይሆን ሊወገድ ይገባዋል ። ” የተናገሩት እና ወይም የገቡት ቃል ፣ ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ። ” ይባላል ። እናም ፤ ክቡር ዶ/ር ጠ/ሚ አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሢመጡ የገቡት የሠላም ፣ የዴሞክራሲ ፣ የብልፅግና ቃል ነበረ ። በገቡት አጅግ ተወዳጅና አጓጊ በሆኑት ቃላቸው ቢገኙ ፣ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ መጎልበት መልካም ይመሥለኛል ። ያለፉትንመንግሥታት አሥጠሊ ተግባር መንግሥታቸው እንዳይደግም ልባዊ ፍላጎት ካላቸው ያኔ ገና ወደ ሥለጣን እንደመጡ ከሦሥት ዓመት በፊት ፣ ከጅምሩ ከአርቲሥቶች ፣ ከመላው ምሁራን እና የሙያ ሰዎች ፣ ከዳያስፖራዎች ጋር ያደረጉትን ወይይት ቆም ብለው ያስታውሱ  ። እናም የመናገር ተፈጥሯዊ መብትን አክብረው ያሥከብሩ ። ህግን ማሥከበር እና  ለፍትህ የቆሙ ፣  ንፁሐን እንዳይገላንቱ መጠንቀቅ  በበኩሌ  የሚነጣጠሉ ድርጊቶች   እንዳልሆኑ እረዳለሁ   ። እናም የመናገር እና የመፃፍ ነፃነት ለመንግሥት ጭምር እጅግ ጠቃሚ ነውና  መከበር አለበት እላለሁ ።  … (መንግሥትን ያህል ትልቅ ተቋም በአንድ ግለሰብ ጫንቃ ላይ እንደተቀመጠ ቆጥሮም ፣ በአንድ ሰው ላይ ብቻ እውነትና ሐሰት የተቀላቀለበት ትችት መሰንዘርም አግባብ አይደለም ። ህግ አውጪው ፣ ህግ ተርጓማው ፣ ህግ አሥፈፃሚው   እና አራተኛው መንግሥት “ ፕሬሥ  “ ለአንድ አገር ልማትምሆነ ድህነት ፣ ዴሞክራሲም ሆነ ባርነት ተጠያቂ ናቸው ። ፕሬሱ ፣ አንቂ ፣የሠላ ሂሥ ና ትቺት አቅራቢ ፣ አሥተማሪ ፣ አሣዋቂ ና ህሊናንን የሚያሥደሥቱ ና ትውልድን የሚያንፁ ፕሮግራሞችን ዘወትር አቅራቢ ና አሥተናጋጅካልሆነ ። ህግ አውጪው ለለገር ብልፅግና የሚበጅ ህግ ካላወጣ ፣ ህግ ተርጓሚው ህጉን በሚገባ ተርጉሞ ለተግባራዊነቱ ዘብ ካልቆመ ፣ ህግ አሥፈፃሚው ህጉን ወደተግባር  በእውነት ካልተረጓመ በተዋረድ ያሉት ባለሥልጣናት ሁሉ ተጠያቂ ይሆናሉ ና ያኔ ፤ ቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ፤ በቀደም መንግሥቱ ኃይለማርያም ፤ ትላንትና መለሥ ዜናዊ ፤ ዛሬ ደግሞ አብይ አህመድ በማለት ክርስቶስ ይመሥል በአንድ ሰው ላይ ወቀሳውን ማዥጎድጎድ የለብንም ።  ለሁሉም የድርሻውን ከፋፍለን በመሥጠት በወጉ ልንተች ይገባናል ። ጠ/ሚ ተዘግቶ ሥለከረመው ቤት ልናሥታውሣቸው ይገባል ። እውንቤቱን በወጉ አፅደተውታል ወይ ? … በማለት ።  ) እናም ፣ በመጨረሻ “ የምን ጣለው ! ጣለው ! የምን በለው ፣  በለው ፣  ይቸግር የለም ወይ ደም መለሽስ ካለው ? “ በማለት ከዱላ በፊት  በጠረጴዛ ዙሪያ ለመወያየት እንትጋ። በማለት ትሁት ሃሣቤን እንሆ ፣ በማለት ፅሑፌን እቋጫለሁ።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

እንደእናቴ ሣይሆን እንደሚስቴ አውለኝ! ብሥራት ደረሰ

Next Story

ኢትዮጵያን እንዴት ከጥፋት እንታደጋት ? – ንጉሤ አሊ

Go toTop