ኡቡንቱ ዜና ግንቦት 28 2014
በሀገራዊ የምክክር መድረክ አካሄድ ላይ መሰረታዊ ቅሬታ አለን ያሉ 10 የሚደርሱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች
“እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአትን የሚያስገኝ ሀገራዊ ውይይት አማራጭን ለማቅረብ የሚያስችል የምክክር ቤት (Caucus) አቋቁመናል” ሲሉ በዛሬው ዕለት ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል።
ሀገራዊ ምክክር በምን መልኩ ይካሄድ በሚለው ላይ ክርክሮች እየተደረጉ ባለበት ወቅት ” መንግስት ሂደቱን የሚቆጣጠር ረቂቅ ህግ በማዘጋጀት በአንድ ፓርቲ የበላይነት ባለው ፓርላማ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጥያቄ እና የግብአት ሀሳብ ችላ በማለት እንዲፀድቅ ማድረጉን ያስታወሰው የፓርቲዎቹ መግለጫ የኮሚሽነሮቹን ምርጫም “የተድበሰበሰ” ነበር ሲል ኮንኗል።
በትጥቅ እየተፋለሙ የሚገኙ አካላትን ወደ ምክክሩ ለመጋበዝ የተቀመጠ ድንጋጌ አለመኖሩን የነቀፈው የምክክር ቤቱ መግለጫ “አማራጭ” በተባለው አዲስ የምክክር ቤት (Caucus) በኩልም
ለመንግስት በርከት ያሉ ምክረሀሳቦችንም አቅርቧል።
በምክረሀሳቦቹም ላይ:-
-አፋጣኝ እና አለም አቀፍ ተቋማት የሚቆጣጠሩት የተኩስ ማቆም በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ እንዲደረግ
-የምክክር ኮሚሽኑ በድጋሜ እንዲቋቋም እና ኮሚሽነሮቹም ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲመረጡ
– የውይይት አጀንዳዎቹ ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ እንዲቀረፁ እንዲሁም
-ውይይቶቹ አለም አቀፍ ታዛቢ በተገኘበት እንዲደረጉ
አሳስቧል።
የምክክር ቤቱን የመሰረቱት ፓርቲዎችም
1- መድረክ
2- ህብር ኢትዮጵያ
3- የአፋር ህዝብ ፓርቲ
4- የአፋር ፍትህ እና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
5- የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)
6- የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ
7-የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር
8- የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ
9- ዓረና ትግራይ
10- የዶንጋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
መሆናቸው ተገልፃል።
ስለ ምክክር ቤቱ ለሚዲያችን አስተያየታቸውን የሰጡት የአፋር ህዝብ ፓርቲ መሪ እና የምክክር ቤቱ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት አቶ ሙሳ አደም “ፓርቲዎቹ በተለያየ ጉዳይ ላይ የተለያየ አቋም ቢኖራቸውም ሀገራዊ ምክክሩ በሀቀኛ መንገድ መከናወን አለበት የሚለው ላይ ግን የማያወላዳ የጋራ አቋም አላቸው፤ አማራጭ የምክክር ቤት ለማቋቋም የወሰነውም ለዚህ ነው”
ብለዋል።
ኡቡንቱ ከወራት በፊት ምንጮቿን ጠቅሳ “ትይዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር መድረክ ” ሊቋቋም እንደሚችል መዘገቧ ይታወሳል።