ኢትዮጵያ ከህወሓት ጋር እየተደራደረች ነው? ኦቦሳንጆ ትላንት መቀሌ ዛሬ ባሌ ናቸው – መሳይ መኮነን

June 4, 2022

 ኢትዮጵያ ከህወሓት ጋር እየተደራደረች ነው!! ኦሊሴጉን ኦቦሳንጆ ትላንት መቀሌ ነበሩ ከደብረጺዮን ጋር። ዛሬ ባሌ ናቸው ከጠ/ሚር አብይ ጋር። አሁን ድርድር የለም ብሎ የሚናገር የትኛውም ወገን አይኖርም። ኢትዮጵያ ከህወሀት ጋር እየተደራደረች ነው። በአካል መገናኘት እንጂ የቀረው ሁለቱ ወገኖች በተለያዩ ጉዳዮች ጠብሰቅ ባለ ሁኔታ እየተደራደሩ ነው። የኦቦሳንጆ በ24ሰዓት ልዩነት ከመቀሌ ባሌ የመከሰታቸው ጉዳይ ደግሞ ድርድሩ በፍጥነት እየተካሄደ፣ ምናልባትም ከጫፍ የደረሰ ውጤት ይፋ የሚደረግበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን የሚያመላክት ነው። ከእንግዲህ ድርድር እየተካሄደ አይደለም የሚል ማስተባበያ ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት እንደማይሰጥ እርግጠኛ ነኝ። እውነት ለመናገር ድርድር መኖሩ የሚከፋ አይደለም። የየትኛውም ጦርነት መቋጪያው ድርድር ነው። በርሊን በጆሴፍ ስታሊን እጅ በወደቀችበት ጊዜ እንኳን ከናዚ መሪዎች ጋር ድርድር ተደርጓል። ይሁንና ድርድሩ ምንድን ነው? ምን ለማትረፍ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ቁልፍና መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው።

በእርግጥም ኢትዮጵያ ድርድር ውስጥ የገባችው ምን ልታተርፍ ነው? ምን ሰጥታ ምን ልትቀበል ነው? የኦቦሳንጆን የትላንትና የቢቢሲ ቃለመጠይቅ ላዳመጠ ትንሽ ፍንጭ ያገኝበታል። ሰውዬው በተስፋ ተሞልተዋል። የሆነ ስምምነት ላይ ሁለቱ ወገኖች የደረሱ ይመስላል። ግልጽ አድርገው ባይናገሩትም ከስድስት ወራት በፊት የነበረው ጭጋጋማ ሁኔታ አሁን ወከክ እያለ መሆኑን ግን አልደበቁም። እሰየው ይሁን። ጦርነት ቢያሸንፉት እንኳን መዘዙ ከባድ ነውና ያን የሚያስቀር ነገር ከተገኘ መቀበል ግድ ይሆናል። ችግሩ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የሚያስገኝላት ምንድን ነው? የሚለው ነው። አንዳንድ ስምምነቶች ለሌላ ጊዜ የማያባራ ጦርነት መነሻ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚኖር ይታወቃል። የአልጀርሱ ስምምነት የኢትዮ-ኤርትራን ፍጥጫ አባባሰው እንጂ አልቀነሰውም። ሌላም ታሪክ መጥቀስ ይቻላል። እናም ኢትዮጵያ ድርድር ውስጥ የገባችው ዳግም ጦርነት እንዳይከሰትና የህወሀትን መርዝ በማስተፋት ለቀጠናው ዘላቂ ሰላም ለማስገኘት ካልሆነ በቀር ምንም ትርጉም አይኖረውም። ምንም ስላልተነገረን ከግምት ያለፈ አስተያየት መስጠት ይከብዳል።

ስጋቶቻችን ግን ብናነሳ ችግር የለውም። ድርድሩ ለትግራይ ህዝብ በቂ እርዳታ እንዲገባ የሚያደርግ ነው የሚለውን ማንም የሚቃወም አይኖርም። ከኦቦሳንጆ የትላንት መግለጪያ የተረዳሁት ህወሀት እንዲደረጉለት የሚፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ድርድር እየተካሄደ ይመስላል። መብራት፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ ባንክና የመሳሰሉ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ የሚለው ቃል በቃል የተናገሩት የድርድሩ አንዱ ጉዳይ ነው። ለትግራይ ወገናችን ይህ መሆኑ ትክክለኛ ነገር ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ግን ህወሀት የሚባል አውሬ በሚቆጣጠረው ክልል ውስጥ እነዚህ አገልግሎቶች ለዳግም ወረራ ጉልበት የማይሰጡበት እድል አለ ወይ? በጭምጭምታ እንደሰማነው ደግሞ ለ2015 የትግራይ በጀት ቀመር ተሰርቶ አልቋል። እንግዲህ በራሳችን ትጥቅና ስንቅ ሁለት ግዙፍ ጦርነቶችን የከፈተው ህወሀት አሁንም በገዛ ሀብታችንና ገንዘባችን ለሶስተኛና ብሎም ወደማያባራ ጦርነት ውስጥ ጎትቶ እንደማያስገባን ምን ዋስትና የሚሰጥ ድርድር ነው? የህወሀት ምኞት ዳግም ወደአራት ኪሎ መመለስ ነው። በጦርነትም ይሁን ሸፍጥ በሞላው ድርድር መዳረሻውን አራት ኪሎ ስለማድረጉ በተደጋጋሚ ነግሮናል። ሰሞኑንም ሁለተኛውን ግንቦት 20 ጠብቁ ብሎናል።

ይህም ብቻም አይደለም። ታላቋን ትግራይ ለመመስረት የተጀመረው የቅዥት መንገድ ኤርትራንም በመውረር ጭምር ተፈጻሚ እናደርጋለን የሚል ፉከራ በአደባባይ እያየን ነው። አራት ኪሎ የሚያበቃ የመሰለው የህወሀት ህልም የአስመራ ቤተመንግስትን ለመቆጣጠርም ቋምጧል። ድርድሩ ይህን ቅዠት የምርም ቅዠት ያደርገው ይሆን? ወይስ ህወሀቶች እንዲሞክሩት መንገድ የሚጠርግላቸው ነው? እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ ከዚህኛው ድርድር የምታተርፈውን አንድ ሁለት ብሎ መግለጽ ይቻል ይሆን? የህወሀትን መርዝ የማያስተፋ፣ የታጠቀውን መሳሪያ የማያስፈታ፣ እብሪቱንና እብጠቱን የማያስተነፍስ ድርድር ለኢትዮጵያ ከቶ ይበጃታልን? አሁንም ስጋታችን ከፍ የሚያደርግ አንድ አጀንዳ የድርድሩ አካል እንደሆነ እየሰማን ነው። የወልቃይትና ራያ ጉዳይ። ህወሀቶች ሁሉም ነገር ወደነበረበት ካልተመለሰ ሰማይ ምድሩን እናገለባብጣለን የሚል አቋማቸውን ለኦቦሳንጆ መቀሌ ላይ ደጋግመው እንደነገሯቸው ተሰምቷል። በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ያለው አቋም ግልጽ አለመሆኑ ደግሞ ልባችንን በስጋት ይንጠዋል።

ይህም ተባለ ያ፣ ድርድሩ እየተካሄደ ነው። ኢትዮጵያ በድርድሩ ስለምታገኘው ነገር ፍንጭ እንኳን የሚሰጠን የለም። ህወሀት በዝርዝር የሚፈልጋቸውን አስቀምጦ ወይ ፍንክች እያለ ነው። ከባሌ ምን እንሰማ ይሆን? በነገራችን ላይ ባሌ ምን የሚጎበኝ አዲስ ነገር ተሰርቶ ነው ኦቦሳንጆን ይዞ መሄድ የተፈለገው? ጠ/ሚር አብይ እንዲህ ዓይነት ታክቲክ ሲጠቀሙ የመጀመሪያቸው አይደለም። የአሜሪካ ጉዳይ አስፈጻሚ ጄፍሪ ፊልትማን በዚያ ቀውጢ ጊዜ እንጦጦ ፓርክን እንዲጎበኙ ተደርገዋል። ልማትን እያሳዩ የራስን የድርድር ጉዳይ መጋት እንደሚሆን አይጠረጠርም። ፓርክ እያስጎበኙ የኢትዮጵያን አቋም ማሳወቅ፣ የስንዴ ማሳ እያሳዩ የኢትዮጵያን ፍላጎት መግለጽ በእርግጥ ምንም ችግር የለውም። ባሌም ተደረገ ቦሌ፣ ሞያሌም ይሁን ሰላሌ ዋናው ጉዳዩና ፍላጎቱ ምንድን ነው የሚለው ነው። ለምንስ መንግስት ድርድር ውስጥ እንዳለ ከመናገር ተቆጠበ? ድንገት ዱብእዳ ከማድረግ ከወዲሁ እያስተነፈሱ፣ ለህዝብም ትንሽ ፍንጭ እየሰጡ ድርድሩን ማድረግ ያልተፈለገው የሚያስከፍለው ኪሳራ ምን ቢሆን ነው? የጠሚ/ር አብይ አስተዳደር ምቾት ከማይሰጡኝ አካሄዶቹ ሁሉን ነገር ከህዝብ የሚደብቅበት አሰራሩ ነው። የፓርቲ የውስጥ ስብሰባዎችን ሳይቀር አንድም ሳናስቀር እንነግራችኋለን ተብሎ ቃል ለተገባለት ህዝብ ይህን ትልቅ ጉዳይ ምንም እንደሌለ አድርጎ ማካሄዱ የሚያስገኘው ጥቅም ሊታየኝ አልቻለም።

በመጨረሻም የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የመደብደቡ ጉዳይ በጠዋቱ ስሜቴን የረበሸ ሆኖ ቀኔ ተጀምሯል። ወንድሙ ታሪኩ እንደነገረን ዓይኑ እያየ ተመስገን በፖሊሶች ቡጢና እርግጫ ጉዳት ደርሶበታል። ከጋዜጠኛ ተመስገን ጋር ልዩነት ያለን መሆኑ የእሱን ድብደባ ህገወጥነት ላለመናገር የሚከለክለን አይሆንም። አረ እየተስተዋለ?! የህወሀትን ዘመን ቶርቸርና እስር ሪከርድ ለመስበር ከሆነ የሚያዋጣ አይሆንም። ወደ ጨለማው አትመልሱን። ያሳፍራል!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

እስራአኤል በኢትዮዽያ የሚፈፀመውን አፈና የሚቃወም ሰልፍ ተደረገ !!

Next Story

በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው መንግስታዊ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም የሚጠይቅ ታላቅ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ

Go toTop