HR_6600 ን እንደግፋለን የምትሉ ሰዎች አስቡበት! – ከጌታቸው ሽፈራው

March 23, 2022

1) ይህ ማዕቀብ የመጣው በትህነግና በፀረ ኢትዮጵያውያን ግፊት ነው። ትህነግ ገዥዎቹ ጋር ብቻ አልገጠመም። ከአገር ጋር ነው የገጠመው። ለትህነግ ከኢትዮጵያ እነ አብይ ይቀርቡታል። እንታረቅ ቢሉ በቀላሉ ከገዥዎቹ ጋር ይታረቃሉ። እየሞከሩም ነው። ፀባቸው የሚቆየው ከኢትዮጵያ ጋር ነው። በኢትዮጵያ ላይ ነው ያሳወጀው። እናም ስትደግፉ ከትህነግ ወገን ሆናችሁ ወደኢትዮጵያ እየተኮሳችሁ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። ያን ሁሉ ውድመት የፈፀመ ትህነግ በውጭ በኩል ሌላ ጥቃት ሲፈፅም መደገፍ ምኑ ትግል ይሆናል?

2) ማዕቀብ የተጣለባቸው አገራት ሕዝቦች እንጅ ገዥዎቹን ጎድቶ አያውቅም። ሙጋቤ አልተራበም። ኢሳያስ አልተራበም። ሙጋቤ በማዕቀብ ከስልጣን አልወረደም። ኢሳያስ በማዕቀብ ከስልጣን አልወረደም። ኤርትራውያን ለስደትና ለመከራ ነው የተዳረጉት። ዚምባቡያዊያን ለችጋር ነው የተዳረጉት። እንዲያውም ማዕቀብ የተጣለባቸው አገር ገዥዎች ይበልጥ አፋኝ ሆነዋል።

3) ይህ ሪዞሉሽን እንዲፀድቅ ያባበሉት የትህነግ ሰዎች ናቸው። እነ ቴድሮስ አድሃኖም እንደ አክቲቪስት የሚጮሁት ለዚህ ድጋፍ ነው። ይህን የወራሪ ድምፅ ደግፋችሁ እንደቆማችሁ እወቁት። ትህነግ ወረራ ሲጀምርም አራት ኪሎ ድረስ ይምጣ፣ አሳልፉት ተብሎ ነበር። ያጠቃው ግን ሕዝብን ነው። አሁንም ይህን ሪዞሉሽን መደገፍ ትህነግን መደገፍ ነው። ያን ዘረፋ፣ በሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር፣ በንብረት ላይ ውድመት፣ በንፁሃን ላይ ጭፍጨፋ የፈፀመውን በሌላ ግንባር ሲመጣ መንገድ መሪ ብቻ ሳይሆን ተዋጊው ሆኖ የመሰለፍ ያህል ነው።

4) ገዥዎችን መቃወም አንድ ነገር ነው። በአገር ላይ የመጣን መደገፍ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው። በአድዋም በሁለተኛው የጣሊያን ወረራም የነገስታቱ ተቃዋሚዎች ነበሩ። “ይበላቸው” ያሉት ባንዳ ተብለው የእድሜ ዘመን ስም ነው የተሰጣቸው። ተቃውሟቸውን ይዘው ጠላትን የተፋለሙት ደግሞ ጀግኖች ሆነዋል። በገዥዎች ተካዱም አልተካዱም። አገር አልወቀሳቸውም። ገዥዎቹ መልካም ይሁኑም መጥፎ ከውጭ ጠላት ጋር አብሮ መቆም ባንዳነት ነው። የወቅት ልዩነት የለውም።

5) አሜሪካና ምዕራባውያኑ በዪክሬን ላይ የምታደርገውን እያየን ነው። በኢትዮጵያም ላይ ከመርህ አንፃር የምታደርገው አይደለም። ይህን የዘመናችን ጫና ከጠላት ጋር ሆኖ መደገፍ የሆነ ጊዜ አንገት የሚያስደፋ ይሆናል።

6) ማዕቀቡ ለአማራ ሕዝብ ያግዛል፣ ለእንትን ሕዝብ ይሆናል የምትሉ ደግሞ ምዕራባውያኑን አስታውሱ። በትህነግ የተፈፀመብንን በደል፣ በኦነግ የሚፈፀመውን ጭፍጨፋ ለመናገር ፍላጎት የላቸውም። የትህነግን ውሸት ግን ሲያስተጋቡ ይውላሉ። እየሞትክ እያዩ ዝምታን የመረጡ ለነገህ ሊያስቡልህ አይችሉም። እንዲያውም ምዕራባውያኑ ጦረኛ አድርገው በሀሰት የሳሉት አማራን ነው። ማዕቀቡ እንደ ሕዝብ አማራን ቢጎዳ ደስታቸው ነው።

7) ከትህነግ ጋር የጋራ አጀንዳ የያዙ፣ አገር ከገዥዎቹ ጋር ተመሳስላ እንድትወቀጥ የሚፈልጉ ዩቱዩበሮችንና ፌስቡከኞችን ሰምታችሁ እደግፋለሁ የምትሉት ትናንት እነ አብይን ከደገፋችሁበት በላይ አሳፋሪ ታሪክ ትሸከማላችሁ። አስቡበት። በአገር ላይ ይቅርባችሁ። ባንድነትን እየተፀየፋችሁ ተገንጣዮች ወትውተው፣ የውጭ ጠላቶች ያቀዲትን አላማ ለማስፈፀም ድጋፍ ከማድረግ መቆጠብ ቢያንስ ለራሳችሁ ታሪክ ይጠቅማል። ይቆጫችኋል።

8/ በአገር ላይ የመጣውን ብቻውን ለዩት። ገዥዎቹን በሌላ መልክ ታገሉ። የሚያዋጣው ይሄ ነው። ነገ አንተ ስልጣን ብትይዝና ማዕቀብ ቢመጣ “አገራዊ ነው” ትላለህ፣ ዛሬ አፋኞቹ ስር ያለ አገር ላይ ሲመጣ “ለእነሱ ነው” ልትል አትችልም።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

እስከ መቼ አልቃሽና ዘፋኝ ሆነን በገዢዎች ሽንገላ በጎራ እንቧቀሳለን? | Hiber Radio Special Program Mar 23, 2022

Next Story

የ2013 ዓ.ም የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናን አስመልከቶ በቀረበ ቅሬታና በተካሄደ ምርመራ መሰረት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

Go toTop