የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከ81 (ሰማንያ አንድ) በላይ የሆኑ የብሔር፣ የብሔረሰብና የማህረሰብ ቅንብር ያላት መሆኑ ግልጽ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላት ብቻ ከአላቸው ባህላቸውና የዝርያቸው ሐረግ ሊዋጥና – ጨርሶም ሊጠፋ ጥቂት ከቀራቸው ማህበረሰቦች አንስቶ፣ ብዙ ሚሊዮን አባላት እስከ አሏቸው አያልና ሠፋፊ መሬት እስከ ያዙት የኦሮሞና የአማራ ብሔሮች ባህሏን የሚያበለጽጉና ሕብረሰባዊነቷን የሚያጠናክሩ፣ ሕብሯን የሚያሞሽሩ ህዝቦች የሚኖሩባት አገር ነች።
ምልዓተ ፀጋዋና ባህላዊ ብልጽግናዋ በመላ አፍሪካ ተወዳዳሪ የሌላት ኢትዮጵያ፣ እንደ ዛሬው አይበለውና በቀድሞው ዓለም የታሪክ ማኅደሮች ተደጋግማ ስትወሳ የኖረች ነች። መወሳትም ሳይሆን፣ በማይለቅ ቀለም ተከትባ ትገኛለች። ፍፁምና ዘለዓለማዊ ታሪክ ከአላቸው ጥቂቶች የቀድሞው የጥንታዊው ዓለም አገሮች መካከል ተጋና የተተረከች አገር ነች።
የሰው ልጆች ታሪክ መተረክ፣ ሥዕል መጫጫርና፣ ጽሑፍ መጻፍ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የእነዚህ ጥንታዊ ጥበቦች አፍ መፍቻና ጣት ማንቀሳቀሻ የሆነችው ኢትዮጵያ ነች። ከግሪክ የአምልኮ ትረካ (ሚቶሎጂ) እስከ ሮማይስጣዊ ሥልጣኔ፣ ከዚያም መካከል በዘመን ወርድ በተረባረቡት ክፍላተ ዘመን በጽርዕ (ጥንታዊ ግሪክ)፣ በእብራይስጥና በላቲን፣ ከዚያም በዓረብኛና በሌሎች የዕድገት ለጣቂ ቋንቋዎች የተጻፉ የሃይማኖት፣ የታሪክ፣ የባሕል፣ የጦርነትና የሌሎች ጽሑፎች አዛይ መጻሕፍት ውስጥ ኢትዮጵያ ያልተጠቀሰችባቸው የጥንት መጻሕፍት የሉም። ይህች ምኑም የማይሻር ታሪካዊ ዝናና ምሩጽ ስም፣ ማንም ሆነ ምን ዝቅ ሊያደርገው የማይችል ትልቅነት ያላት አገር በእነዚሁ ዘመናት ውስጥ የሕዝቧን ባህል ስታበለጽግ ኖራለች። ከማሕረሰቡ እስከ ብሔር ስፋት ያለው ሕዝብ በፍቅር ግዛቱን አስከብሮ፣ ባህሉን አበልጽጎ፣ ሁሉም አካሏ በዘመናት ርዝመት በፈፀማቸው የተከበሩ ተግባሮች ተኩራርቶ ኖሯል።
ኢትዮጵያ ከዕውቅና ሥራዓታዊ ሃይማኖት እስከ- ባህላዊ ዕምነት ያለው ሕዝብ ሲኖራት፣ ከዓላማውያን እስከ ክርስቲያን- በአንፃሩም፣ እስከ ቤተ እሥራኤላዊ ሃይማኖት የሚከተሉ ሕዝቦቿ በየበኩላቸው ለባህሏ ይህ ነው የማይባል አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በረከታቸውም አላቋረጠም።
በዘመኑ የሚገኙት በየክፍላተ ዘመን የተሠሩ በዕድሜ የገፉ ቤተ ክርስቲያናትን ግድግዳዎችና አጎበሮች የበለጸጉ ጥንታዊ ሥዕሎች፣ የዋሻ ምስሎች፣ ከአለት ተወቅረው፣ ከቋጥኝ ተፈልፍለው የቆሙ ሓውልቶች፣ በልዩ መልክ ታንጸው የተሰሩ መንበረ ዕምነቶች፣ በብራና ላይ የተከተቡ ጽሑፎች፣ ልዩ ቅርጾች ከዚያ ታላቅና ጥንታዊ ሕብረተሰብ ልጆች ተሠርተውና ተጠብቀው የተገኙ እና የኖሩ ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማንኛውም የዓለም ሕብረተሰብ ይልቅ – ለብዙ ሺህ ዘመናት የራሱ የሆነ፣ በዓይነቱ የበዛና የተለያየ የቤት ውስጥ፣ የማዕድ ቤት ፣ የአዳራሽ፣ የእልፍኝና የመስክ መጠቀሚያ ቁሳቁስ የነበረውና ያለው፣ ለብዙ ሺህ ዘመናት የእርሻ፣ በአደን፣ የደንበኛ ጦር፣ የወግና የማዕረግ፣ የአዘቦት መሣሪያና ትጥቅ የነበረውና ያለው ነው።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ የራሱ የሆነ የአለባበስ፣ የአጋጌጥ፣ ከወንድ፣ ከሴት፣ ከሕጻናት እስከ ጎልማሳ የፀጉር አሠራር ደንብና ፈሊጥ (ፋሽን) የአደባባይና የመስክ አለባበስ ወግና ሥርዓት ያለው፣ ከሌላው ዓለም ሕዝብ ተለይቶ ሲታወቅ የኖረ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ልማድና የአኗኗር ሥርዓት ለራቀው ለሚያስቀና ለቀረበውም ባለቤት ለሆነው ወገን የሚያኮራ፣ መታፈሪያ፣ መታደጊያ የሚሆን ነው። የሕዝቡ ልዩ ልዩ ባህላዊ ቅርስ ብሩህ ታሪካዊ መነሻና ፈለግ ያለው፣ ሲወርድ ሲዋረድ ከኖረው ታሪካዊ ሐረጉ በተዋረድ ሲበለጽግና ሲጐነጐን የመጣ፣ አንዱ ከአንዱ ሲወራረስና እትብተ ዕድገቱን ሲቋጥር እና ሲሸርብ ፣ ሲደርብ የመጣ ነው።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ በአብዛኛው ጥንታዊ መልኩን ያልተወ ቢሆንም ጥንታዊ ሥርዓት ደረጃ ላይ ይገኛሉ ከሚባሉ የሶስተኛው ዓለም ሕዝብ የተለየ ነው። በስብዕና፣ በሥነ ምግባር፣ በአኗኗር ሥርዓት፣ በታሪክ አቀራረጽና አሠራር፣ በባሕል ማበልጸግ፣ በሥልጣኔ ፈለግ ጉዞ ላይ የተለየ ይዘት ያለው ነው። ሥልጣኔ ስል፣ ሥልጣኔ ማለት፣ በአሁኑ ዘመን በሠለጠነው ዓለም የምግባር ብልሹነት፣ ነፍስ ግድያ፣ አሳፋሪ ባህሎች ወግ ማጥበቅ እንደ ሥልጣኔ ባለመቁጠርና- በዘመናዊ አኗኗር አለባበስ ኋላ ቀር ደረጃ ላይ የሚታየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከብሉይ እስከ ክርስትናና እስልምና ሃይማኖቶች የያዟቸውን ሕግጋት እያከበረ በመኖሩ የሥልጣኔ የበላይነቱን ለመግለጽ ነው።
ከማናቸውም የዓለም ሕብረተሰብ የበዛና የተለያየ የምግብና የምግብ ቅመም፣ የባሕላዊ መድኅኒት፣ የባህላዊ መጠጥ ዓይነትና ብዛት ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአለባበስም ከተለያዩ የቆዳ (የለምድ) አልባሳት እስከ ጥበብና ካባ፣ እስከ ካባና ሸልም መንጠልያ ለዓይነት የሚያስቆጥር ነው።
በመላው አፍሪካ ከአለው የሴቶችና የወንድ የፀጉር አሠራር ፈሊጥ አጠቃልሎ የሚበልጥ አይነት ይመዘግባል። በአኳኳል፣ አነቃቀልና በንቅሳት፣ በአተላተል፣ የሰውነት አጋጌጥ ዓይነትና ባህላዊ ትርጉም ወግ የተራቀቀና የተደነቀ ለመሆኑ አስተባባይ የለውም። የሰብል መሰብሰቢያ መኸር እስከ አደን፣ ከሠርግ እስከ ኃዘን ወቅቱ ያሉ፣ ከሙሾ እስከ ድለቃ፣ ከሽለላ እስከ በገና ድርደራ ያሉ የግጥም አደራደር፣ የአዛዜምና የጭፈራ ባህሉ በዓለም ሕብረተሰብ የሚያህለውም የሚመስለውም ፣ አቻዬ ነው የሚለውም የሌለው ነው። የቤተክርስቲያን ሥርዓቱ የተለየ፣ የራሱ የሆነ ጽሑፍ ያለው ራሱን ልዩና ተደናቂ አድርጎ የኖረና ያስመዘገበ ሕዝብ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ የበለፀገ ጥሩ ባህል ያለው መሆኑን ሳንረሳ፣ ጎጂና ሊታረሙ ወይም ሊቀሩ የሚገባቸው ባህሎችም አብረው እንዳሉ ሳልጠቅስ ማለፍ የለብኝም። ይሁን እንጂ፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ምልዕተ ባህል ድንቅና ብልፁግ፣ ልዩ እንደሆነ የኖረ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በየብሔራዊ፣ ብሔረሰባዊ፣ ጎሳዊ፣ ነገዳዊ፣ ማህበረሰባዊ፣ እንዲሁም ማህበራዊ ኑሮ የተለያዩ እያንዳንዱ ክፍል የእኔ አንጡራ ባህል ነው የሚለው ባህላዊ ፀጋ ቢኖረውም አንዱ ባህል የሌላው ቅራፊ፣ አንዱ የሌላው አበልፃጊና ተደጋጋፊ ሆኖ ይገኛል። የባህል ተመሳሳይነቱም አንድነትን አጽንቶ የኖረ ኃይሉ መሆኑን በዚህ እንረዳለን። የባህላዊ ቅርሶቹ ገጽታዎች መለያዎችና አቀራራቢ መረጃዎች የሚታዩት በዕምነቶቹ፣ በዕደ ጥበብና በሌላው ውጤቶች፣ በእርሻ፣ በወግ፣ በልዩ ልዩ ሞያ መሣሪያዎቹ፣ በጋብቻ፣ በኃዘን፣ በውጊያ በአደባባይ፣ በሃይማኖታዊ በዓላትና በሌላው ሥርዓቱ የተለያዩትን ባህላዊ መልኮቹን ያሳያል።
ዋሻዎችን ምሰውና ፈልፍለው ሥዕሎችን እየሳሉ፣ ልዩ ልዩ ነገሮችን ሲቀርጹ፣ አለቶችን፣ ግንዶችን ወቅረው ሀውልቶችን ሲያቆሙ ጣዖቶችን ሲሠሩ፣ መሠውያዎችን ሲተክሉ፣ በሸክላ፣ በዕምነ በረድ፣ በዕብን (ደንጊያ) በጭቃ ሃውልቶችን ሠርተው አቁመው የመስዋዕት መፈፀሚያቸውና መሰባሰቢያቸውን ሲያዘጋጁ ባህላቸውን እያሰፉ፣ የወግ፣ የስፖርት፣ የእርሻ መሳሪያዎች በየዘመኑ እያሻሻሉ የመጡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሥራ ሳይፈቱ ኖረዋል። ከዘመናዊ ሥልጣኔ ኋላ መቅረት ሌላ ያጡት ነገር የለም።
ብሔረሰቦች፣ ነገዶች፣ ጎሳዎች፣ ጐጦች፣ ማህበረሰቦች ሁሉ አንዱ ከሌላው ለየት ያለ፣ የሴትና የወንድ ሞያና ተግባር፣ የመስክና የቤት ውስጥ ሥራ ክፍፍል፣ የአበላል፣ የአጠጣጥ፣ ያለባበስና ያጋጌጥ የማጀትና ያደባባይ፣ ሌላም ባህል አላቸው። በአብዛኛው የተለያየ፣ ከመጠኑም የመወራረስ ባህል በአንዳንድ አካባቢ መተዳደሪያ ሕግ ነው። ዕምነትንም በውስጡ ያቅፋል። በግርዘት፣ በገላ መብጣት፣ በንቅሳት፣ በትልተላ እና በመሰል ጠቃሚም ሆነ ጐጂ አድራጎቶች ላይ ባህልን ግልጽ እና ልዩ አድርጎ እናያለን። ጉግሥ፣ የገና ጫወታ፣ የልጆች የእርግጫ፣ የጭቃ፣ የውኃ አረጫጨት፣ የኩበት ጦርነት፣ የሴቶች የበዓላት የባህላዊ ዘፈኖችና ድለቃዎች ዝግጅት የባህልን ሌላው መልክ ያሳያሉ።
ሙሾ፣ ቅዳሴ፣ የእስላሞች መንዙማ፣ ለቦረንቲቻ፣ ለገዳ፣ ለግርዘት፣ ለሰብል አጨዳና አሰባሰብ በአውድማ ላይ፣ በመኸር፣ በእርሻና በበጉልጓሎጓ፣ በዓረምና በቃርሚያ ወቅት የሚደረጉ ልዩ ልዩ ነገሮች ባህሎችን እየቀረጹና እያበለፀጉ ሄደዋል። በአንዳንድ አካባቢ ምልዓተ ገበያ መሃል ጋያ በማህበር ማጨስ፣ ቦርዴና ኰረፌ በበርበሬ፣ ጠላና ጠጅ መጠጣት፣ ደጀን ለይቶ ትግል መታገልና በበትር መዋቃት፣ መዝፈን፣ መደለቅ፣ ሙሽራን አጅቦ ገበያ መግባት፣ ቅርጫ አርዶ መከፋፈል የተዘወተሩ ነገሮች ሲሆኑ፣ በአንዳንድ አካባቢ ሴት ዘወትር ወደ ማጀት ገበያና መስክ – ወንድ ወደ አደባባይ፣ ወደ ቤተክርስቲያንና መስጊድ ሄዶ መዋል የተከበረ ባህል ነው። በአንዳንድ አካባቢ – አብዛኛውም በገጠር ነዋሪው መተዳደሪያ ሥራ ሴት ስትከታተል ወንዱ ጠላትን መጠበቅ፣ ጥርስ መፋጫውን አፉ ውስጥ ዶሎ፣ ጦሩን ሰብቆ፣ ጋሻውን አንግቦ መንገላወድ፣ የወንድነት ማሳያ ወጉ ነው።
የግንቦት ልደታ ማርያምን – በየመንደሩ ማክበር፣ በሌላ በኩል ለተለያዩ ጠንቋዮች ስጦታ ማቅረብ፣ በዛር በአል አክብሮ በዛር ዘፈን መዝፈን የየአካባቢው ሕዝብ ባህላዊ እንቅስቃሴዎች ናቸው። ሲዳሩ ማልቀስ፣ ሲዳሩ መዝፈን በየልዩ ልዩ ባህላዊ ክፍል አሉ። በእስላሞች መጅሊስ፣ በክርስቲያኖች ሰንበቴ፣ ማህበር፣ የተለያዩ ጠበሎችን መጠጣት- ተመሳሳይ ዕምነትና ባህል ያላቸው ማህበራዊ ኅይሎች አብረው እንዲኖሩ የሚያደርግ ባህል ነው። በዓለማውያን በኩል ለተለያዩ ርኩሳን መናፍስት መስዋዕት ማቅረብ በጣዖት አምልኮ ሥፍራዎች ላይ መፀለይ፣ መጨፈር፣ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ማዘጋጀት የአካባቢው ሕዝብ ባህላዊ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ በክርስቲያንና በእስላም፣ በቤተ እሥራኤላዊ አካባቢ – የሃይማኖት – በዓላትን አስታክኮ ደግሶ መደሰትን፣ ምህላ ማድረግንና ሌሎችም ዕምነታዊ ጉዳዮች ተመሳሳይ ባህል ያላቸውን ሰዎች የሚያሰባስብ ነገር ነው።
የመኖሪያ ቤቶች አሰራር፣ የመኝታና የሥራ አልባሳት ዝግጅት አንዱን ሕዝብ ከሌላው ለይቶ ለማየት የሚያስችል ነገር ነው። አገራችን ውስጥ ከላይ እንደጠቀስኩት የምግብ፣ የመጠጥ፣ የቤት ቁሳቁስ፣ የመስክ መሳሪያዎች አዘገጃጀት አንዱን ብሔረሰብ ከሌላው፣ አንዱን ማሕበረሰብ ከጎሳው ለየት ያደርገዋል ። የሁሉም ባህላዊ ፀጋ፣ ውበት ለማበላለጥ ማነፃፀሪያዎችን የሚያስፋፋ ጉዳይ ይሆናል። ሁሉም ልምዶች፣ ወጎች፣ የአሰራርና የአኗኗር የማህበራዊ ኑሮ ምሥረታ ዘይቤዎች በተለያዩ መልካቸው የራሳቸውን ልዩ ፀጋ ያንፀባርቃሉ። በሥራና በዕረፍት በበዓላት፣ በጨዋታ፣ በአደባባይ መሰብሰቢያ ጊዜ ሁሉም ማህበራዊ ክፍሎች ውበታቸውንና ብልጽግናቸውን ያንጸባርቃሉ።
ባህል ይበከላል፣ ይወራረሳል ፣ ያድጋል፣ ይደክማል። የአንድ ሕዝብ ባህል ሲጠበቅ የመበልፀግ አዝማሚያው የበለጠ ነው። የሠንጠረዥ፣ የገበጣ፣ ልዩ ልዩ የቤት ውስጥ ጨዋታዎች በአንዳንድ አካባቢ ሲዘወተሩ፣ በአንዳንዱ አካባቢ የጥበብ፣ የሞያ መስፋፋት የታገደ ነገር ነው። ባህሉ አግዶታል፣ አውግዞታል። ባህልም ጠብቦ ይታያል። መልካም ሥራ የሚሠሩትን ካይላ፣ ፋቂ ደበናንስ፣ ቡዳ፣ ሰላቢ፣ ባለ እጅ እያሉ በሌላው ወግ እያፌዙና እያወጉ መኖር፣ ተኮፍሶ ውሎ ትችት ማብዛት የተከበረ የወንዶች ተግባር ነው። በአገራችን፣ ደቦ – ወንፈል – ጅጌ ብንላቸውም ሁሉም በአንድነት ማህበራዊ ኑሮን ያሰፋሉ ፣ ሰዎችን ያቀራርባሉ። የየአካባቢው መጠሪያዎች ቢሆኑም ባህላዊ ተፈጥሮአቸው፣ ድርጅታቸው አንድ ነው።
ዘፈን የሚያዘወትሩ ብሔረሰቦች አሉ። ሁሉም የየአካባቢያቸው የጭፈራ፣ የዝማሬ፣ ሥልት አላቸው። ክራር፣ መሰንቆ፣ በገና፣ እምቢልታ፣ ዋሽንት፣ ከበሮ አታሞ ሁሉ በየአካባቢው ባህላዊ ደጀን የባህላዊ ጨዋታ ስሜት መግለጫዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ባህል ብዙና ብልፁግ ነው። የክራር ቅኝት፣ የበገና ድርደራ፣ ቅኔ፣ ድጓ- ፆመ ድጓ፣ ዝማሬ የፀሎት፣ የጭፈራ፣ የኅዘን፣ የሠርግ የሌላም ባህል ብዛት ብልጽግና አለን። ባልትና፣ ዕደ ጥበብ፣ የወግ ማውጋት፣ የተረት – የሌላውም ባህል በየሕዝብ ማህበራዊ ክፍል የተለየ ትኩረት ያላቸው ባህላዊ ፀጋዎች ሆነው ሲበለጽጉ ኖረዋል። ስለዚህ፣ የአንዳንዶቹን የሁለት የሶስቱን ማህበረሰብ ያጠረ፣ አነስ ተደርጎ የቀረበ ባህላዊ ነገር የሚያሳዩ ጽሑፎችን ከዚህ ጋር አባሪ አድርጌ አቅርቤአለሁ።
የሸኰ ብሔረሰብ
የሸኰ ብሔረሰብ የሚገኘው በጊሚራ አውራጃ ውስጥ ነው። የሚኖረው በጐራ ፈርዳ ወረዳ ነው። ብሔረሰቡ እስከ 16,000 የሚደርስ አባላት አሉት። ብሔረሰቡ በሥልጣኔ ደረጃ ኋላ ቀር ነው። አብዛኛውንም የቀኑን ጊዜ ርቃነ ሥጋውን ይውላል። የሚተኛውም መሬት ላይ ነው ይባላል ይህም ማለት ምንም አይነት ንጣፍ ሳያዘጋጅ። ሸኰዎች አራዊትም እንዳያጠቋቸው ዙሪያቸውን እሳት አንድደው ይተኛሉ። የሚመገቡት አብዛኛውን ጊዜ ሥራ ሥር ነው። የሸኰ ብሔረሰብ ከየት እንደመጣ የተረጋገጠ ታሪክ ባይኖርም፣ የራሱ ባህልና ቋንቋ አለው። በዚሁ አካባቢ ለብዙ መቶ አመታት እንደሰፈረ የተረጋገጠ ሆኗል። የሸኰ ቋንቋ ሸኰኛ ሼኩ ይባላል። ከቤንችና ከሹሮ ብሔረሰብ ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ጋብቻቸው፣ ወንድ ለአቅመ አዳም ከመድረሱ በፊት ከ13 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ማሳ በማረስ፣ ቀፎ በመስቀልና ከብት በማርባት ለሠርጉ ይዘጋጃል። በጋብቻውም ጊዜ የሚጠቅመውን ጎጆ ሠርቶ ለብቻው መኖር ይጀምራል። ከ 15-18 ዓመት ባለው ዕድሜ ለማግባት ይዘጋጃል። የወደዳት ልጅ ካለች፣ ለአባትየው ገልጾ ይናገራል። አባትም በልጁ ምርጫ ከተስማማ ሽማግሌ ሰይሞ ወደ ልጅቱ ቤተሰብ ይልካል። አግቢው ሀብታም ከሆነ፣ የልጅቱ ቤተሰብ ያለማመንታት ይሰጣል። አንዳንዴ ሴት ልጅ ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ጠይቀው ሲከላከሉ በማባበል ወይም በመጥለፍ ያገባሉ። ይህ ከሆነ በኋላ ለቤተሰቧ ከእሱ ወገን አስታራቂ ሽማግሌዎች ይላካሉ። ጉዳዩ በሰላም እንዲፈጸም ጥረት ይደረጋል። ሆኖም ካሣ መክፈል ወሳኝ ነው። ካሣው እንደ ጥሎሽ ገንዘብ ይታሰባል። አብዛኛውን ጊዜም ጥሎሽ ከፍተኛ ይሆናል።
የሸኰ ብሔረሰብ በጠለፋ ጊዜ ከእርቅ በኋላ የሚሰጠው ጥሎሽ ሰባት ላሞች፣ 14 በጐች፣ 14 ብር አንድ መቆፈሪያ መሣሪያ ነው። ለሕጋዊ ጋብቻም የሚሠጠው ይህንኑ ያህል ነው። በተጨማሪም ልጅቱ ይዛው የምትሄደውን ያዘጋጃል። ይህም ማለት ለትዳር ተፈላጊ ናቸው የሚሏቸውን ነገሮች ከሰርጉ ቀን በፊት ወስዶ ይሰጥና በሚጋቡበት ዕለት ይዛ ትመጣለች።
በሸኰዎች የጋብቻ ዝምድና የሚያቀራርብና የሚያከባብር ነው። ሸኰዎች ለሌሎች ብሔረሰቦች ጭምር ጠቃሚ ምክርና ትምህርት የሚሆኑትን መልካም የኑሮ ምግባርና ሥርዓት እንዳላቸው የታወቀ ነው። በልብስ አለመልበሳቸውና በሩቅ አመለካከት ኋላ ቀር ኑሮአቸውን አይተን በሌላው አንፃር የማህበረሰብ ሥርዓታቸውንና ደንባቸውን ስናመዛዝን የበለፀገና ጥሩ ግምት የሚሰጠው እንደሆነ እንረዳለን።
የሱርማ ብሔረሰብ
ሱርማዎች በማጂ አውራጃ በትርማጥድ ወረዳ ይገኛሉ። ቁጥራቸው 30,000 ይደርሳል። የትርማጥድ የቀድሞ ስም ቲርማና ቻይ (ቻይ) ነበር። ቻይ ማለት ብድር መላሽ (ተበቃይ) ማለት ነው። በትርማጥድ የጥድ ተክል በብዛት ይገኛል። አዲሱ ስሙም ይህንኑ የሚያመለክት ነው።
ሱርማዎች ተረስተው የኖሩና እስካሁን በጋርዮሽ ዘመን ሥርዓተ አኗኗርና መልክ የቆዩ ናቸው። ወንዶች ልብስ አይለብሱም፣ ሴቶች ብቻ ሐፍረተ ሥጋቸውን በቁራጭ ጨርቅ ይሸፍናሉ። ንብ ማርባትና አደን ዋናው ተግባራቸው ነው። ቦርዴ መጠጥ ከዕለት ምግባቸው አንዱና ዋናው ነው። የሚበሉት የማሽላ ወይም የበቆሎ ገንፎ ነው። ብዙ ምግብ አይመገቡም።
በጋብቻና በሌላው ሥርዓት ከፍተኛ ደንብ አላቸው። ጥሎሽ እንደቀሩት አካባቢዎች ባህል የተለመደ ነው። በማጨት ዘይቤ ላይ አለመስማማት ሲፈጠር ጠለፋ አለ። የጠለፋው ቅራኔ በስምምነትና በካሳ ይፈታል። አንዲት ሴት በሁለት ወይም በበለጡ ሰዎች ከተወደደች፣ አፍቃሪዎቿ እሷን ለማግኘት ሕጋዊ በሆነና በዳኞች የሚመራ የዱላ ድብድብ ግጥሚያ ያደርጋሉ። ይህ ግጥሚያ በአንዴ ርታታ ብቻ አያበቃም። ተደጋግሞ የመጋጠም ዕድል ለተሸናፊው ይሰጠዋል።
ሱርማዎች ሌላ ባህል አላቸው። ሴት ልጅ ቆንጆ ነች የምትባለው በከንፈሮቿ ትልተላና ውጥረት ነው። በጣም ሠፋ ያለ፣ በትልቁ የተወጠረ ከንፈር ያላት ሴት በጣም ቆንጆ ነች ይባላል።
ሰው ሲሞት፣ ሟቹ በዕድሜ የገፋ እንደሆነ፣ በበሽታ ከሞተ፣ ዘመድ አዝማድ በመላላክ ይጠራል። የቅርብ ዘመድ የሆነ ሰው ከቤቱ አጥር በር ላይ ሆኖ ቃጭል ያቃጭላል። የከብቶቹን፣ የሟቹን ከብቶች ስም እየጠራ፣ እየፎከረ ሐዘንተኞችን (ለቅሶ ደራሾችን) እየተቀበለ ያስገባል፣ ያስተናግዳል። እስከ ሰባት ቀን ድረስ አስከሬኑ በእንቁጢጥ ተቀምጦ ተገንዞ ይቆያል። የሟቹ ቤተሰቦች ጭቃ ይቀባሉ፣ ትንባሆ ይጎርሳሉ። አስክሬኑ ሲቀበር ከብት ይታረዳል። ፈርሱ በገበቴ ይቀመጣል። ከዚያ እግራቸውንና ግንባራቸውን በፈርስ ይለቀለቃሉ። ይህም ማለት፣ “የዚህን ዓይነት መከራ ዳግመኛ አይግጠመን” ማለት ነው። በሬሳው ጆሮ ውስጥ ደምና ወተት ይንቆረቆራል። ከዚህ በኋላ በመቃብሩ ዙሪያ እየዞሩና በላዩም ላይ እየዘለሉ ዜማ ያሰማሉ። ባሏ የሞተባት ሴት ከንፈሯን ለቁንጅና የወጠረችበትን ገል ታወጣለች። ይህም ከፍተኛ የኅዘን ምልክት ማሳያ ነው። በሰው እጅ የሞተ ሰው ቤተዘመዶቹ አይቀብሩትም። የሚቀብረው ለወደፊቱ ልጁን በማግባት አማች መሆን የሚፈልግ ሰው ነው።
በዚህ ዓይነት የሞተውን ሰው የቀበረ ተባባሪ ለመልካም አድራጎቱ ልጃገረድ እንዲሰጡት (የሟችም ልጅ ሆነ ዘመድ የሆነች) ይጠይቃል ካልሰጡት “ቀብሬአለሁና እጄን በደም የምታጠብበት ከብት ስጡኝ” ይላል። ፍየል፣ በሬ ወይም ላም ይሰጠዋል። ከብቱ ታርዶ፣ ፈርሱን ሰውነቱን ይቀባል።
አማች የሚሆንና የሚቀብር ሰው ከጠፋ፣ አስከሬኑን በቅጠል ሸፍነው ትተው ይሄዳሉ። ከዚያም፣ የሟቹ ወገኖች የተገዳዩን ወገናቸውን ደም ለመበቀል ይዘጋጃሉ። ሆኖም የገዳዩ ወገን ሁኔታውን በመግለጽ (የአገዳደሉን ሁኔታና ምክንያት) ክሶ ለመታረቅ ይሞክራል። ከደም ካሣ በኋላ፣ የመበቃቀሉ ዝንባሌ ይቀራል።
የቲሽና (የመአነት) ብሔረሰብ
የቲሽና (መኢነት) ብሔረሰብ በማጂ አውራጃ በጉልድያ፣ በጊሽ እና በጠሻሻ ወረዳዎች ይኖራል። ቁጥሩ 45,000 ይደርሳል። አመጣጣቸው ከኦሞ ወንዝ አካባቢ መሆኑ ይታወቃል። ከፊል ነባር፣ ከፊል ዘላን ነው። መኢነቶች በሚኖሩበት አካባቢ ጐሽ፣ ዝሆንና ልዩ ልዩ የዱር አራዊት ሃብት አለ።
ጋብቻቸው ብዙውን ጊዜ በጥልፊያ ነው። የወንድ ወገን የሴቷን ወገን ልጅህን ለልጄ ስጠኝ የሚል ጥያቄ ያቀርባል። ለመጀመሪያ አልሰጥም ይላል። ተመላልሰው እንዲጠይቁ ይሞክራሉ። ይህ ወጉ ነው። ተደጋግሞ ሲጠየቅ ይሰጣል። አሻፈረኝ ካለ ጥልፊያ ይቀጥላል። የጥልፊያ ችግር በካሣና በሌላ ስምምነት ይወገዳል።
አንድ ሰው ሲሞት ዘመድ አዝማድ እስኪሰበሰብ አራት ቀን ድረስ አይቀበርም። የእነሱ ከፍተኛ የሃዘን መግለጫ የቀንድ ከብቶችን በድንጋይ ቀጥቅጦ መግደል ነው። በዚህ ሁኔታ ለሃዘን የሚገደሉ ከብቶች በብዛት ከሟቹ ቤተሰብ ያገቡ ሴቶች ልጆች በኩል የሚቀርቡ ናቸው። የሟቹ ዕድሜ ከ40 ዓመት በላይ ከሆነ ትዳር ይዞ ልጅ የወለደ ከሆነ አልቃሾች የክብር ልብሳቸውን ለብሰው የሟቹን ጀብድ ያወሳሉ። ሃዘኑ እስከ 15 ቀን ይቆያል።ከአራት ቀናት በኋላ፣ አስከሬኑ እየተገለጠ፣ ዘመድ በየተራ እያየ ስሞ ከተገደሉ ከብቶች በአንዱ ቆዳ ተገንዞ በክብ ጉድጓድ ይቀበራል።
የቲሽናዎች ልብስ ቅጠል ወይም ቆዳ ነው። ከቅርፊት ቃጫ የተገመደና የተሸመነ ጉርድ ይታጠቃሉ። ሴቶቻቸው ለቁንጅና ጭቃ ከጉሎ ጋር ቀላቅለው ፀጉራቸውን ይቀባሉ።
የዲዜ ብሔረሰብ
የዲዜ ብሔረሰብ በማጂ በቢሮ፣ በኩሪትና በመሃል ማጂ ወረዳዎች ይገኛል። ቁጥሩ 35,000 ይደርሳል። አመጣጣቸው ከጋሙ ጎፋ፣ ከባኮዎች ነው ይባላል። ግማሾቹ ማጂያውያን ነን ይላሉ።
መኖሪያ ቤታቸው ጣሪያውና ግድግዳው የተመረገ ነው። የከብቶች ግርግም ወለሉ ድንጋይ ነው። ከብቶች የሚታሠሩት ቤት ውስጥ ነው። መኖሪያ ቤታቸው ጣሪያው ዝቅ ያለ ስለሆነ ይሞቃል።
የትዳር ጓደኞች አብዛኛውን ጊዜ የሚተጫጩትና የሚፈቃቀዱት በገበያና በጨዋታ ቦታ ነው። በእነዚህ ቦታዎች ላይ ለትዳር የሚፈልጋትን ልጅ ወንዱ ይቧጭራታል። ፈቃደኛ ካልሆነች ትሸሻለች። ከተስማማች ለአባቷ አንድ ኰርማ ይልካል። አባቷም በዘመድ አጅቦ ባሏ ቤት ያስወስዳታል። የወንዱ ወገን ሙሽራይቱ ስትደርስ ደግሶ የሙሽራይቱን አጃቢዎች ይጋብዛል። በዚህ ጊዜ ዘፈን ይዘፈናል። ሙሽራይቱ በዘፈኑ ተካፋይ በመሆን ትዘፍናለች፣ ትጨፍራለች።
በዲዜዎች ሰው ሲሞት በሟቹ የቀኝ ጆሮ ውስጥ ወተት ይንቆረቆራል። ቀብሩ በዕለቱ አይፈጸምም። ሐዘንተኛ (ዘመድ አዝማድ) ከያለበት እስኪሰበሰብ ይቆያል። አስከሬኑ በከብት ቆዳ ተገንዞ፣ በጎፈርና በልዩ ልዩ ቆዳዎች አጊጦ፣ አልቃሾች ጦርና ጋሻ ይዘው በመንጎራደድ ፎክረው፣ አቅራርተው ይቀብሩታል።
የዲዜዎች ልብስ የከብት ቆዳና የጨርቅ ሽርጥ ነው። ዲዜዎች የበለፀገ ባህልና የማህበረሰባዊ ኑሮ ሥርዓት አላቸው።
Abstract: Submitted 25 years ago this article authored by Mr. Yirga Mengistu Stifanos is published with minimum modification as our editorial board could not find the author and ask for updates. This article contains important and interesting information about the following least known ethnic groups in Ethiopia: Dize, Sheko and Surma.
አቶ ይርጋ መንግሥቱ እስጢፋኖስ
አዲስ አበባ