የ40 ዓመት ቂም የቋጠረው የኢጣሊያ ፋሺስታዊው መንግሥት በ1928 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የፈጸመው ወረራ ከአምስት ዓመት የአርበኞች እርመኛ ትግል በኋላ በድል ተደምድሟል፡፡
ይሁን እንጂ በአምስቱ የፋሺስት ወረራ ዘመን ከተፈጸሙት ግፎች አንዱ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመው ነው፡፡
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966›› በተሰኘውና በ1989 ዓ.ም. በታተመው መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ የኢጣሊያ ፋሺዝም ጽልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ነው፡፡
አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት፡፡ ‹‹ጥቁር ሸሚዝ›› እየተባሉ የሚታወቁት የፋሽስት ደቀመዛሙርት መንግሥት አይዟችሁ እያላቸው አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት፡፡ የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ፡፡ ቤቶች ከነነዋሪዎቻቸው ጋዩ፡፡ እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፡፡
የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማይቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ፡፡ ይህ የምሁራን ጭፍጭፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፋ በመሆኑም ባገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሽር ቁስል ጥሎ አለፈ፡፡
በፋሺስት ኢጣሊያ ጭፍራ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ አማካይነት በአዲስ አበባ ከተማ ለሦስት ቀናት በዘለቀው ጭፍጨፋ ሰማዕት ለሆኑት 30 ሺሕ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ እንዲሆን በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎና በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሐውልቶች ቆመዋል፡፡
እነዚህን ሰማዕታት ለመዘከር ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በብሔራዊ በዓልነት እስከ 1966 ዓ.ም. ሲከበር ኖሯል፡፡ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (ደርግ) ሥልጣን ከያዘበት 1967 ዓ.ም. ወዲህ ግን በመሠረዙ እስካሁን ታስቦ እየዋለ ነው፡፡
ባለፉት ሩብ ዘመናት መታሰቢያ በዓሉ ዓመት ካመት እየቀዘቀዘ ጉንጉን አበባ የሚያስቀምጡት ሹማምነት ደረጃም እንደቀደመው ዘመን ከፍተኛ ሹማምንት መሆናቸው ቀርቶ የከተማዋ ተወካዮች የሚገኙበት ሆኗል፡፡
‹‹ዘንድሮ 80ኛ ዓመቱ ከምንጊዜው በበለጠ ሰማዕታቱ የሚታሰቡበት፣ ፕሬዚዳንቱ አበባ ያስቀምጣሉ ብዬ ጠብቄ ነበር›› ያሉት የ75 ዓመቱ አረጋዊ አቶ ዘለቀ በሻህ፣ ‹‹በዕለቱ ቴሌቪዥን ዜናውን ለማየት ብጠብቅ ሽታውም አልነበረም፤ ለምን ዘነጉት?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከ80 ዓመት በፊት ያለቁት የከተማዋ ነዋሪዎች በመሆናቸው በተለየ ዝግጅት ሊያስባቸው ይገባ ነበር፤ ግን አላደረገም፤›› በማለት በቁጭት ትዝብታቸውን ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 14ኛ ዓመት የዘውድ በዓላቸውን ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 1937 ዓ.ም. ሲያከብሩ በተመረቀውና ለአርበኞችም የተጋድሎ ሜዳሊያ ባበረከቱበት አዲሱ ሐውልት ግርጌ በግእዝ ቋንቋ የተጻፈው ጽሑፍ ዘመነ ፍዳውን የሚያስታውስ ነው፡፡
‹‹ዝንቱ ውእቱ ምዕራፈ አዕጽምቲሆሙ ለብዙኃን ኢትዮጵያውያን እለ ተቀትሉ በግፍዕ በእደዊሆሙ በሕዝበ ኢጣሊያ ፋሽስታውያን አመ ፲ወ፪ ለየካቲት በ፲ወ፱፻፳ወ፱ ዓ.ም …››
ይህ የአፅሞች ማረፊያ በኢጣሊያ ፋሽስታውያን እጅ በግፍ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. የተገደሉ የብዙኃን ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ነው፤ በሚል የሚንደረደረው የሐውልቱ ጽሑፍ አገዳደላቸው በድንጋይ በመወገር፣ በዱላ በመቀጥቀጥ፣ በአካፋ፣ በዶማ በመብረቀ ሐፂን/የብረት መብረቅ (መትረየስ)፣ በየቤታቸው ውስጥ በእሳት በመቃጠል፣ ወዘተ እንደሆነ ይዘረዝራል፡፡
የግፍ አገዳደሉ በተፈጸመ በአራተኛው ዓመት ከብሪታኒያ በድል አድራጊነት የተመለሱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የነፃነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ካቆሙ በኋላ በግፍ የተገደሉትን አፅሞች ከየቦታው እንዲሰበሰቡ ሹማምንቱን በማዘዝ ለዝክረ ነገር እንዲሆንም በቅዱስ ስፍራም መታሰቢያውን አቆሙላቸው፡፡
ዝክረ ነገሩ እንደታሰበው ዓመት ታመት በክብር እየዘለቀ እንዳልሆነ የሚናገሩት መምህር መንክር ገብሩ፣ በባሕር ማዶ ያሉ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያውን በማክበር ብቻ ሳይወሰኑ የኢጣሊያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል እየጠየቁ መሆኑ ያስደስታል፤ እኛም የነሱን አርአያ መከተል አለብን፤›› ይላሉ፡፡
አያይዘውም ሰሞኑን የታንዛንያ ፓርላማ ከምታመት በፊት ከ1905 እስከ 1907 በተካሄደው የነፃነት ተጋድሎ በማጂ ማጂ ነገድ አመፅ ላይ ጀርመን ለፈጸመችው ፍጅት፣ ካሳ እንድትከፍል መንግሥት ግፊት እንዲያደርግ እንዳሳሰበው ሁሉ ‹‹እኛስ ለምን አንጠይቅም?›› ይላሉ፡፡
ሔኖክ ያሬድ