ወደአንድ ወር ገደማ ይሆናል ጦማሬን ስመለከት፣ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቬርርሲቲ የሕክምና ምሁር የሺዘጠኝ መቶ ስድሳዎቹን ተማሪዎችንና የደቀመዛሙርቶቻቸውን አቋምና ጽሑፎች በምስክርነት በመጥራት ስለአፄ ምኒልክ በሰጠው አስተያየት ከማንኛውም ንግግሩ ይበልጥ ቀልቤን የሳበው የሚከተለው ጥቅስ ነበር።
“Certainly, there is no consensus on king Menelik and his contributions. Some adore him and others hate him. Menelik may have contributed to nation building although the project is not completed. ”
ጥቅሱ አስተያየቴን ዐጠር ምጥን አድርጌ እንድሰነዝርበት አስገድዶኛል። ማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች፣ የተለያየ አሳብ አንፀባራቂ ግለሰቦችን በማካተታቸው ደስ ይላሉ። ይሁንና አንዳንድ አስተያየቶች መስመር ከመሳት ዐልፈው፣ ወዳልሆነ መደምደሚያ መድረሳቸውም ሆነ የሚሰጡት ምክር፣ መረን የለቀቁ ስለመሆናቸው ከዚህ በላይ የተጠቀሰው አስተያየት በምስክርነት ሊወሰድ ይችላል።
አንደኛ፣ አፄ ምኒልክንና አስተዋፅዖአቸውን በተመለከተ ስምምነት የለም ሲሉ ጸሓፊው በምን ጥናት ላይ ተመሥርተው እንደሆነ አልገለጡም። ይሁንና በእማኝነት የሚጠሩት የሺዘጠኝ መቶ ስድሳዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ መሆኑ ያስተዛዝባል ብቻ ሳይሆን ያሳዝናልም። ነገሩ በኻያና በኻያ ዐምስት ዕድሜ ክልል ያለውን ልጄን በሌላ ሳይሆን ረጅም ታሪክ ባለው አገር ግንባታ ጉዳይ ላይ አማክረኝ እንደማለት ነው ብል የተሳሳትሁ አይመስለኝም። ምንም የተማረ ቢሆን እንኳን ልጅ ልጅ ነውና ስሜታዊነትና ግልብነት አያጠቃውም ማለት አይቻልም። ባለጮርቃ አእምሮ እንደመሆኑ በቅጡ የማገናዘብና የማሰብ ችሎታው ምራቁን ከዋጠው፣ በዕድሜ ከቀደመው አባቱ (ፊደል ያልቈጠረም እንኳን ቢሆን) ይሻላል ማለት አጠያያቂ ይመስለኛል። በአገር ቀርቶ በቤተሰብም ጉዳይ ጤናማም ሆነ የሰከነ ምክር ይሰጣል ብሎ ማሰብ ያዳግታል። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎችም ምክንያቶች አሉ። ይፈቀድልኛና ጥቂቶቹን ልጥቀስ።
እዚህ መድረክ ላይ የተሰበሰቡትም ሆኑ የጽሑፌ አንባቢዎች፣ በተለያየ የሥራ ሙያ የተሰማሩ ግለሰቦች ናቸው። በዕውቀታቸው የበቁ፣የመጠቁ፣ ምሁራንም እንዳሉበት አያጠራጥርም። ጸሐፊው የሊቀሊቃውንትንትነትን ማዕርግ የተቀዳጀ በመሆኑ፣ በምሁራኑ ላትኲር።
አንድ ምሁር በተማረው የሥራ መስክ ከመጠመዱ በፊት በተወሰነ ትምህርት ተቋም ገብቶ የሚገባውን ተምሮ ፈተናውን ካለፈ በኋላ፣ በሙያው መስክ ለመሥራት የሚጠበቀውን ጥናት አሟልቶ ማጠናቀቁን የሚመሰክር ወረቀት ይሰጠዋል። ይሁንና ወረቀቱ ግለሰቡ የሚጠበቀውን ጥናት ተከታትሎና ተፈትኖ በማለፍ፣ በመስኩ የመሥራት ችሎታ እንዳለው ዕውቅና በመስጠት ከመመስከር ውጭ ሌላ ያደረገለት ነገር የለም። ብቃቱ የሚታየው ግን ባጠናው መስክ ተሰማርቶ፣ የተመሰከረለትን ችሎታቸውን በተግባር ሲያሳይ ነው። አፄ ምኒልክንና ብሔራዊ አስተዋፅዖአቸውን እየካዱ ያሉት የሺዘጠኝ መቶ ስድሳዎቹ ወጣት ተማሪዎች፣ መስካቸው ታሪክ እንዳልነበር ሁሉም ያወቀው ሐቅ ነው። አንብቦ ከመረዳት ውጭ ሰፋ ያለ የታሪክ ሕግ ግንዛቤ በፍጹም የላቸውም ማለት ይቻላል። ልክ አንድ ግለሰብ አራቱን አዕማደ ሒሳብ ስላወቀ ብቻ በዚያው ጉዳይ ላይ ቢጽፍ፣ ወይንም ቢለፈልፍ፣ ስለሒሳብ አጠናቅቆ ያውቃል ማለት እንደማይቻል ሁሉ፣ ታሪክንም አንብቦ ስለተረዳና ስለጻፈበት ብቻ ግለሰቡ የታሪክ ዐዋቂ ነው ማለት አያስችልም። ወርዱንና ስፋቱን ጥልቀቱንና ውስብስብነቱን፣ ሕጉንና ሥርዐቱን በቅጡ ይረዳል፤ ሰላ ገደዱን ያውቃል ማለት አይደለምና። በአፄ ምኒልክና በብሔራዊ አስተዋፅዖአቸው የማይስማሙትም የሚጠሉትም እነዚህ ተማሪዎች ወይንም እነሱ በሚያራግቡት ትርክት የተጠለፉ መንጋዎቻቸው መሆናቸው አይካድም።
በሁለተኛ ደረጃ፣ እያንዳንዱ ባለሙያ ብቃት እንዳለው የሚመሰከርለት፣ ሥራውና አስተዋጥፅኦው በጽሑፍ ከሆነ፣ ተቀባይነትና ዕውቅና ባለው አሳታሚ ወይንም ድርጅት ተመርምሮ ታይቶ፣ በአቻዎቹ ተገምግሞና ተዳኝቶ ዕውቅናው በይፋ ሲታወቅለት ነው። በታሪክም አንድ ጽሑፍ አስተማማኝ ነው ማለት የሚቻለው ጽሑፉ ከመታተሙ በፊት መልካም ስም ባለው አሳታሚ ወይንም ተቋም ታይቶ በባለሙያ አቻዎቹ ተገምግሞ ዕውቅና ሲለገሥለት ነው። አፄ ምኒልክንና ብሔራዊ አስተዋፅዖአቸውን እያብጠለጠሉ ያሉት፣ እንደዚህ ዐይነቶቹ ጸሓፊዎች ሳይሆኑ፣ አብዛኞቹ ካልታወቀ ጢሻና ሥርቻ እንደአሸን እየፈሉ እየወጡ ያሉት የውራጅ ወራጅ ወሬን ከሐቅ የመለየት ዐቅሙም ሥልጠናውም የሌላቸው በገዛ ገንዘባቸው የቆጡን የባጡን የሚያሳትሙት ግለሰቦች ናቸው። አብዛኞቹ የአገራችን የጐሣ ታሪክ ደራሲዎች የሚመደቡት ከነዚህ መካከል ስለሆነ፣ ሥርዐቱንና ደምቡን እንዲሁም መስፈርቱን ሳያሟሉ፣ በመስኩ ደኅና ዕውቀት ወይንም ዕውቅና ባላቸው ሳይገመገሙ በታተሙት፣ አሉባልታውንና ሐቁን አበጥረው ማየት በማይችሉ ጽሑፎች ተመሥርቶ አፄ ምኒልክንና ብሔራዊ አስተዋፅኦአቸውን እጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ምሁር ትርፉ ትዝብት እንጂ ሌላ ፋይዳ አይኖረውም።
ከአፄ ምኒልክ በፊት ባላባቶችና ጐሣዎች ጊዜያቸውን፣ ሀብታቸውንና ጉልበታቸውን በማያባራ በርስበርስ ፍጅት፣ በአካባቢው ውድመት አገሪቷን የጦርነት ዐውድማ አስመስለዋት ነበር። ዛሬ ባንዳንድ የጐሣ ሥርዐት አድናቂዎች ዘንድ እየተወደሱ ያሉት አንዳንድ መንግሥት ቢጤ የነበሩት እንደከፋው አባጅፋርና በጊቤ ዙርያ ያቈጠቁጡት የኦሮሞ ባላባቶች መንግሥታት ከባርያ ቸርቻርነትና ፈንጋይነት ያለፈ የሚሻል የመንግሥትነት ባሕርይ መግለጫ ነበራቸው ማለት ያዳግታል። ስለነዚህ መንግሥታትና ኅብረተሰብ ከፍተኛ ምርምር ያካሄደው ሊቀጠበብት ሙሐመድ ሐሰን አሊ እንደዚህ ሲል ይገልጥልናል።
“ኦሮሞቹ ከእረኝነት ወደግብርና እንደተሻገሩ፣[የሌሎቹን]ከብታቸውን ሊዘርፉና ነዋሪዎቹን በባርነት ሊሸጡ ሲሉ፣ አካባቢያቸውንና ጐረቤቶቻቸውን የመውረር ተግባር እንደዋና ሙያቸው አድርገውት ነበር። [ለነዚህ]የባርያ ጥቅሙ ሁለገብ ነበር። በባርያ ጋማ ከብትና ጠመንጃ ይሸመትበታል፤ መድኀኒትና የክት ልብስ ይገዛበታል፤ እንደስጦታ ዕቃም ይሰጣል። ስለዚህ ባርያ ከማንኛዉም ሀብት በላይ የሚፈለግ ብርቅ ዕቃ ነበር። በጐጃም፣ በበጌምድር፣ በምፅዋና በቀይ ባሕር ዙርያና እንዲሁም በሸዋና በሐረር ከዚያም ባሻገር ባሉት አገሮች የሚሸጡት ባሮች፣ ዋናው ምንጫቸው ከነዚሁ አካባቢዎች [በምዕራብ ኢትዮጵያ ከ፲፱ኛ ዘመነምሕረት መግቢያ እስከመኻሉ ድረስ ከጐጃም በታች አቈጥቊጠው የነበሩት የጊቤ ባላባቶች ግዛቶች በመባል የሚታወቁት እነጉማ፣ ጐማ፣ ሊሙ፣ ጌራና ጅማ] መሆኑ ይታወቃል።”
አፄ ምኒልክ ናቸው እንግዴህ “የሰው ባርያ የለም፤ ሁላችንም የእግዜር ባሮች ነን” ብለው በማሳሰብ፣ በመገሠፅና በመደንገግ ይኸንን አጸያፊና ኢሰብኣዊ የሰው ልጅ ችርቻሮና ንግዱንም ለማስፋፋት ሲባል በባላባቶቹ መካከል ይካሄድ የነበረውን የርስበርስ ጦርነት ያከተሙት።
እሳቸው ጠበኞቹን በአንድ ኢትዮጵያ በምትባል እናት አገር ጐጆ ሥር በማምጣት፣ እያንዳንዱ ጉልበቱን፣ ሀብቱንና ጊዜውን ርስበርስ በመተላለቅ ሳይሆን፣ በፈለገበት የዕውቀት ውድድር ሜዳ ገብቶ ድርሻውን ለአገሪቷና ለመላው ዓለም መክፈል እንዲችል፣ ከባዕድ ቀንበር ሥጋት አድነው፣ ነፃነቱን አቀናጅተው፣ መንፈሱን አደራጅተው፣ አገሩን አደላድለው፣ የዘመናዊ ሥልጣኔ መሠረት ጥለው አመቻችተውና የማይደመሰስ አሻራቸውን አስፍረው፣ ዐደራችሁን ቀጥሉበት ብለው ከተማፀኑ በኋላ ወደማይመለሱበት አገር ሂደዋል።
የጐሣዎችና የባላባቶች ዓለም ምን ያህል አጸያፊ፣ ኢሰብኣዊና አሬመናዊ መሆኑን ለመረዳት ብዙም ሩቅ መሄድ አያስፈልግም። አሁን በአገራችን እየሄደ ያለውን ሁናቴ ማየት ብቻ ይበቃል። ወያኔ የተባለው ድርጅት በትግሬዎች ስም፣ በሸኔ ስም ደግሞ ጥቂት ናቸው የማይባሉ የኦሮሚያ ባለሥልጣኖች በሕዝቡ ስም በመነገድ እያካሄዱ ያሉት አሬመናዊ ተግባር ብዙዎቻችንን ሰው ሁኖ መፈጠር እስከሚያስጠላን ድረስ ያንገፈግፈናል፤ ይሰቀጥጠናልም። እነዚህ ፅንፈኞች ተብለው የተሰየሙት ዘመናዊ ባላባቶች በጐሣቸውና በቀዬአቸው ስም እየፈጸሙ ያሉት ግፍና ዕልቂት ከቅድመ ምኒልክ የነበሩት ያደርጉ ከነበሩት ጋር ሲነጻጸር ኢምንት ነው ማለት ይቻላል። ይህንን እውነታ እያየ ማንኛውም ኅሊና አለኝ ባይ፣ የአፄ ምኒልክን ተግባር ቢወቅስ ፋይዳው ትዝብት ብቻ ይሆናል።
የአፄ ምኒልክ ብሔራዊ አስተዋፅኦ በጥያቄ ውስጥ የሚገባ ወይንም ምናልባት (may have contributed ) በማለት የሚታለፍ አይደለም። እንደጠራራ ፀሓይ ግልጥና ጥርት ያለ የማያከራክር፣ የማያወላውል ሐቅ እንደሆነ መላው ዓለም የመሰከረው ተግባር ነው። የኛ “ምናልባት”፣ “ግን”፣ “ይሁንና”፣ የሚሉት መስተፃምሮች ዋጋ የላቸውም። የሚጠራጠር ካለ፣ የአእምሮውን ጤንነት መመርመር ይኖርበታል። የሚያስፈልገን ዐይናችንን በትንሹም ቢሆን ከፍተን ራሳችንን መመርመርና አካባቢያችንን በቅንነት መንፈስ መቃኘት ብቻ የሚበቃ መሰለኝ። ለምሳሌ ያህል፣ የኦሮሞ ሕዝብ በኬንያም በኢትዮጵያም አለ። በኢትዮጵያ ያለው በሥነልቦናው፣ በኑሮው፣ በጠባዩ የኬንያውን የማይመስለው አፄ ምኒልክ ባመጡለት እሴትና ጸጋ ስለታነጸና የትሩፋቱ ተቋዳሽ ስለሆነ ብቻ መሆኑ አያጠራጥርም። ኢትዮጵያም ከመላው አፍሪቃ የምትለየውና ሕዝቧም ከማንም አገር ነዋሪ በሚጻረር መልኩ ባህሉን ጠብቆና ኰርቶ፣ አንገቱን አቅንቶ፣ ደረቱን ነፍቶ፣ ትከሻውን ደርበብ፤ ሰውነቱን ሰፋ አድርጎ የሚሄደው፣ ጉንጩን ሞልቶና ነፍቶ የሚናገረው አፄ ምኒልክ ባጎናፀፉት ድል ምክንያት እንደሆነ የማይካድ ሐቅ ነው።
ይኸንን የአፄ ምኒልክን ሥራቸውን መመስከርና ማድነቅ ለእውነት መቆም እንጂ ማምለክ አይባልም። ምክንያቱም አሻራቸው በያንዳንዳችን ላይ እንደጠራራ ፀሓይ ጩራ ያንፀባርቃል። በምንም መልክ ሊፋቅ፣ ወይንም ሊጠፋ የሚችል ነገር አይደለም። ትሩፋታቸው ከኛም ተንዘግዝጎ ዐልፎ በቀረው ዓለም ለማንቦግቦግ በቅቷል። ወደድንም ጠላንም ሐቁ ግን ይኸ ነው።