የናዝሬት ከተማ  መሥተዳድር የማፍረስ ዘመቻ ና የጉዳቱ ሰለባዎቹ ቅሬታ ! ! – ሲና ዘ ሙሴ

February 5, 2022

ሰሞኑን በመንገድ ዳር የተገነቡ ና ከመንገድ ዳር ከፕላን ውጪ የተገነቡ የንግድ ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻ በአዳማ አንዳንድ ቀበሌዎች እየተካሄደ ነው ። የማፍረስ ዘመቻውንም እያከናወነ ያለው የከተማው አሥተዳደር ፤ ይሁን እንጂ  ማዘጋጃ ቤቱ ይሁን ፣ የአሥተዳደር አካሉ የትኛው የማፍረስ ሥራውን እንደሚያከናውን ፣ ባለ ንግድ ቤቶቹ አያውቁም ። አብዛኛዎቹም ከግለሰብ ተከራይተው ሥለሚሰሩ ፣ ግርግሩ ግራ አግባቷቸዋል ።  በግልፅ የሚያውቁት ጉዳይም የለም   ። አፍራሽ ግብረ ኃይሎችም ፣  ለፀጥታና መረጋጋት ይበጃሉ ተብለው ከየጎጡ የተመለመሉ እጅግ የበዙ ሥራ አጥ ዜጎች  ናቸው ። ( አንዳንዶቹም የቀበሌ ቤት እናገኛለን ብለው ፣ የቀን ሥራቸውን ትተው ከቀበሌ የብልፅግና ካቢኒዎች ጋር ዘወትር የሚባትሉ ናቸው ።

በእርግጥ ከአፍራሾቹ ውሥጥ   አንዳንድ የመሥተዳድሩ አካላትም በብልፅግና ሥም ራሳቸውን የሚያበለፅጉ ቀምቶ በሎች እንጂ ሠርቶ በሎች እንዳልሆኑ ስለሚታወቅ በዚህ ተግባር ላይ መሠማራታቸው ፈፅሞ አያሥገርምም   ።

እናም እላለሁ ፣ “   ይኽ የማፍረስ ዘመቻ   የሥራ ፈቶች ዘመቻ በመሆኑ አንድ ታታሪ ሰው ፣ ምን ያህል እንደሚለፋ እና ለኑሮዎ መቃናት እንደሚደክም ያልተገነዘበ በመሆኑ በአሥቸኳይ መቆም አለበት ።  በማፍረስ እና መልሶ ጉቦ ተቀብሎ ማሰራት ፣ እንደ ወያኔ ዘመን ልማድ ዜጎችን ማሥከፋት ነው   ይገፀስ  ። ይኼ ፣ ትላንት ያሥተዋልነው ፤ ውሃ ቅዳ ፣ ውሃ መልስ ተግባር ነው  ። ይኽ የማፍረስ ዘመቻ በሥራ ለምናምን ብዙዎቻችን አሥከፊና ግማሽ ልጩ ና ገማሽ ጎፈሬ የሆነ  ድህነትን አሥፋፊ   ዘመቻ በመሆኑ በአሥቸኳይ ይታረም ። “ እላለሁ  ።

ይኽ  ድህነትን የሚያበረታታ ፣ የማፍረስ ዘመቻ ፤ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ያለው   ፣  በየመንገዱ ዳርና ዳር ፣ ከተከራዩበት ቤት ውጪ ፣ ጊዚያዊ  ጥላ ሰርተው ፣ ቤት ገንብተው ፣ የፀሐይ መጠለያ ሰርተው ሸቀጦቻቸውን   ዘርግተው ፣ እየሸጡ ባሉ ግለሰቦች እና እነሱን ከለላ አድርገው ፣ ሲኒ ደርድረው ቡና በመሸጥ ላይ የነበሩትን በእጅጉ የሚጎዳ ና ወደ ድህነት አዘቅት የሚጨምር ነው ና መወገዝም አለበት  ።

በዋና መንገድ ላይ ወንበር ደርድረው ፣ ይኽንን ደሃ ህዝብ ሥጋ እየበሉ ና ውስኪ እየጠጡ  የሚያሥጎመጁትን ፣ “ ወደ ንግድ ቤታችሁ ግቡና ያሻችሁን ፈፅሙ ። ይኽ ነፃ ቦታ የእናንተ በረንዳ አይደለም ና በህዝብ መተላለፊያ ላይ ተቀምጣችው ፣ ህዝብን አታሳቁት ፤ አታሰቅቁት ፣ …  ።”  በማለት የወሰዳችሁት እርምጃ ተገቢና ትክክል ቢሆንም ፣ ሁሉንም ቀበሌዎች በነካ እጃችሁ መዳሰሱን አትዘንጉም ። ይላል ህዝቡ ።

ለውበት አሳማሪ _ ሊስትሮዎችና ለመንገድ ላይ ቡና አፍይዎች የተዋበ መጠለያ በጎዳና ላይ ወይም  ጥገ አላይም በፓርክ ውሥጥ ቦታ ሰጥቶ  ሥራ አጥነትን ፣ ሥራ በመፍጠር ፣ ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የማይጥር ፤ የከተማ አሥተዳደር ፣ ለብልፅግና ቆሜያለሁ ማለት አይችልምና ይኽ የማፍረስ ፣ ህዝብና መንግሥትን የሚያቀያይም ተግባር በነማን ውጥን እና ምክር እንደተከናወነ ይጣራ   ?

ህዝብ የሚለው ፣ “ የከተማው መሥተዳድር ፣ ነገ ከተማው ሲለማ ፣ ፎቅ እየተሰራ ቅርፅ በሚይዘው ከተማ ፣ ምንም ዓይነት እግረኛ የማይጎዝበትን  ፣ በጭርንቁስ ቤት የተሞላን የጎዳና ዳርና ዳር ፣ ዳስና በረንዳ ማፍረሱ ተገቢ ና ፍትሃዊ አይደለም ። “ ነው ። ለዚህ ድህነትን የማሥፋፋት ፣ ድርጊትም የምንጃር ጎዳናንን በዋቢነት ያቀርባል   ።     “ በተለይም  08 እና 07  ቀበሌ ውሥጥ የሞሉት ጭርንቁስ ቤቶች በጊዚያቸው በልማት የተነሳ መፍረስ ላይቀርላቸው ለምን ዛሬ ብዙ ሺ ሥራ አጦችን በውሥጣቸው አካተው ሣለ በዘመቻ መልክ የማፍረስ ተግባር ሊከናወንባቸው ቻለ ?  “ በማለትም ይጠይቃል ።

እነዚህ ሁለት ፣ ቀበሌዎች ያለሙና  እጅግ የበዛ ህገወጥ ግንባታ ያለባቸው ናቸው ። 08 ሙሉ ለሙሉ የህገወጥ ገብያ መናህሪያ ነው ። ሙሉ ለሙሉ ” ጉልት ነው ።” ማለት ይቻላል  ። ዜሮ ሰባትም ከ08 የማይሻል የምንዱባኖች የዕለት እንጀራ ማግኛ  ቀበሌ ነው ።

እነዚህ ሁለቱ ቀበሌዎች ፣ የሚለወጡት ፣ በአገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ሰፍኖ ፣መንግሥትና ህዝብ ወደልማት ፊቱን ሲመልስ እንደሆነ ይታወቃል ።በወቅቱ  በልማት ፣ ሥለልማት ከተባለ ደግሞ ፣ ለጉልት ቸርቻሪዎች ፣ ሌላ ህገዊ ሆነው የሚሰሩበት ፣ እራሳቸውን ጠቅመው አገሪቱንም በግብር ክፍያ የሚጠቅሙበትን ፣ መንገድ በማመቻመች  ቸርቻሪዎቹን ወደ ሌላ የገብያ ማዕከል መጠለያ ( ሼድ ) ሰርቶ ማዛወር እንጂ ፤  ብት ፈልጉ ዲንጋይ ብሉ ብሎ ፣ ከየጉልቱ ጠራርጎ ማንሳት የሚፈጥረው የራሱ የማይቀለበስ ችግር እንደሚወልድ የታወቀ ነው ።  እናም  ተለዋጭ  ሥፍራ  ሳያዘጋጁ  መነካካት አላሥፈላጊ አይመሥለኝም ። ለራሱ ሰው ኑሮ ጭቅላቱን አዙሮታል ። ተጨማሪ ትንኮሳ ፣ ሆድ ለባሰው ጩቤ ማዋስ እንደሆነም መንግሥት አያውቅም ማለት አይቻልም ።

“ትላንት  ፣ በአማራና  አፋር የደረሰውን መፈናቀል እኛም እንደግመዋለን ! ” ነው እንዴ ነገሩ ? … ።በበኩሌ ፣ “ ይኽ የማፈናቀል ዘመቻ ፣ ህዘብን ለማስቀየም እና የብልፅግና መንግሥትን የድህነት መንግሥት አድርጎ ለመሣል የተወጠነ ነው ። ሌበነት ፣ ለማኝነት ፣ ጎዳና ተዳዳሪነትን  ለማበራከት እና እንደገና በሁከትና በብጥብጥ መንግሥት እንዲተረማመስ  ና ሀገር እንዲፈርስ ለማድረግም በህግ ማሥከበር ሥም የተተኮሰ የመጀመሪያው ሠላም አደፍራሽ ጥይት ነው ። “ ብዬ ለማመን እገደደለሁ ። ይኽ  ድርጊት  መወገዝ ያለበትና በአስቸኳይ መቆም ያለበት ውጉዝ ተግባር  እንደሆነም አሰምርበታለሁ ።

ይኽ ውጉዝ ተግባር ፣  በእግረኛ መንገድ ማፅዳት ሥም ፣  በመሐል ከተማ በጎርፍ መውረጃዎች ውሥጥ የተከማቸውን ግማት ፣ ማዘጋጃ ቤቱ  ሳያፀዳ ፤ በሥራ ፈትነት አልያም ለሥውር ጥቅም ፣ አልያም ለሥውር ሤራ  የገባባት የማፍረስ ተግባር  ከሆነ ደግሞ እጅግ አሣፋሪ ነው ።

( እኔ የለሁበትም የየቀበሌው ካድሬዎችና አጫፈሪዎቻቻቸው ናቸው ካለ ደግሞ ፤  በማዘጋጃ ቤቱ አንፈርድም ። )

እንዴ ! ሆን ብሎ ሠርቶ የሚበላውን ህዝብ ፣ የመሥሪያ ሥፍራውን እያፈራረሱ ፣ መሥለቀሥ ምን የሚሉት ህግና ደንብ ማሥከበር ነው ?  ለሚሰራ ሰው ቀድሞ ቦታ ሳያመቻምቹ   እነሱን ተገን አድርገው የዕለት እንጀራቸውን የሚያገኙትን የመንገድ ላይ ቡና አፍይ እህቶቻችንን እንጀራ መሣጣትሥ  የሚጨበጨብለት ተግባር ነውን ? ¡¡ ከምናፈናቅላቸው በፊት  ለሠራተኛ ዜጎች  ተገቢ መፍትሄ ማሥቀመጥ የአሥተዳደር ነኝ ባዩ ፤ የመንግሥት ሹም ኃላፊነት ነበር ። ይኽ አሥተዳደር የመንግሥት የታችኛው አካል መሆኑንም መዘንጋት አልነበረበትም ።

ዜጎች  ይህ  የታችኛው  የመንግሥት አካል ፣ ፖሊሥን እና ሥራ ፈት የጎጥና የቀበሌ ጭፍራዎቹን ይዞ ” ኃይ በለው ” በማለት በዘፈቀደ ፣ ከጎዳና ላይ ዜጎችን “ቢፈልጉ አፈር ይብሉ ። ምን አገባኝ ። አሥጨንቄ ኋላ ትርፍ አገኛለሁ ። …”በማለት መንቀሳቀሱን ያውቃሉና ፣ ቅሬታቸው አገርን በመምራት ላይ ባለው መንግሥት ላይ መሆኑንን ከፍተኛው የመንግሥት አካል ማወቅ አለበት ። ብዙ መልካም አማራጮችን እና ገቢዎችን ማግኛ መንገድ እያለ ፣ በደቀቀ ኢኮኖማ ፣ ዜጎችን በሥራ አጥነት ማድቀቅም ነውረኝነት ነው ። መሥተዳድሩ ድብቅ ሤራ ባይኖረው ፣ ወይም የዕውቀት ደሃ ባይሆን ኖሮ ፣ ዜጎች ፣ ባልተገነነ ኪራይ ፣ ሰርተው የሚለወጡበትን ፣ የመንገድ ጥግ  ፣ ቡና ማፍያ  ፣ በአማረ መልኩ ሠርቶ በማከራየት ፣ ማዘጋጃቤቱ ገቢ ማግኘት ይችል ነበረ እኮ ! !

ለምሳሌ ፣ ለጫማ ውበት ጠባቂዎች ፣ መንገዱን የሚያሥውብ የፀሐይ መከላከያ ና መቀመጫ ፣ በየመንገዱ በመሥታወቂያ አገልግሎት ፣   በየመቶ ሜትሩ በማሠራት ፣ ለማዘጋጃ አገልግሎት     ፣ በየወሩ በባንክ  እንዲከፍሉ በማድረግ ገቢውን ማሳደግ ይችል ነበር ። ህዝብን ዝቅ ብለው በማገልገል ፣  የዕለት እንጀራቸውን  በማግኘት  ላይ ያሉትን ፣ አገርን ጠቃሚ ማድረግ ሲገባ ፣ ማሳደድ ተገቢ ና ትክክል አይደለም ። በዚኽኛው ዳር መንገድ ላይ ቁጭ ብሎ ሲሰራ ” የእኔ ወገን ነው ። ”  ብሎ መተው ፣ በወዲያ በኩል ተመሣሣይ ሥራ የሚሰራውን በነጋ በጠባ ” መጣሁብህ !  ንብረትህን እወርሳለሁ !! ” ብሎ ማሥፈራራት የሰው ተግባር አይደለም ና ሊወገዝና ባሥቸኳይ እንዲቆም ቀጭን ትዕዛዝ በሚመለከተው ባለሥልጣን ሊሠጥበትም  ይገባል ።  …

( በአዳማ ከተማ ፣ በዋናው ንግድ ባንክ ፊት ለፊት ፣ በፓርኩ  መሐል ፤ በኮብል እስቶን መንገዱ ጥጉን ይዘው የሚሰሩትን ሊስትሮዎች ፣ እንዳይሰሩ መከልከል በበኩሌ ፣ ዘርፋችሁ ፣ ሠርቃችሁ ፣ ለምናችሁ ወዘተ ። ብሉ እንጂ ሠርታችሁ አትብሎ ማለት ነው ።

ሥለ ህገ ወጥ አሠራር መወገድ ከተነሳ   ፣ ከወያኔ አገዛዝ ጀምሮ ህግን መጣሥ የተለመደ እና የሚበረታታ ሆኖ መገኘቱ እየታወቀ ። በዋነኝነት ይህን የህገ ወጥ መድረክም የከፈቱትና ለመላው ከተማ ኗዋሪ ያሥተማሩት  እነሱ መሆናቸው እየታወቀ ፣ ዛሬ ደርሶ ይህንን ውሥብሥብ ህገ ወጥ ድርጊት ፣ ህጋዊ ና ሁሉንም ያካተተ ባልሆነ የጉልበት መንገድ ፣ ቦታ እየለዩ  ማፍረስ ህገ ወጥ አሠራር ነው ። በቅድሚያ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ፣ ለእነዚህ ህገ ወጥ ድርጊቶች ፣ ምን ዓይነት ህጋዊ መፍትሄ በናቅድና ፣ይህንን እቅድ ለመተግበር የሚያሥችል ሀብት ከነማን እናገኛለን ብሎ ማሰብ ሊቀድም ይገባል ። ለሁሉም ነገር ፣ ለከተማ ፅዳቱም ቢሆን በቆሻሻ ለተሞላው አርጂን ዘላቂ መፍትሄ ለመሥጠት ፣ በችግሩና በችግሩ አፈታት ዙሪያ የሚመለከታቸውን ምሁራንን ያካተተ ውይይትና እቅድ እጅግ አሥፈላጊ ነው ።

የከተማ ውበትና ፅዳት የሚመለከታቸው ና የሚቆረቁራቸው ፣ የበኩላቸውን ለማዋጣት ዝግጁ የሆኑ ምሁራን ከተማዋ አላጣችም ።  ደግሞም መታወቅ ያለበት ፣  መላ አዳማ ፣ በአራቱም አቅጣጫ ፣  በጨረቃ ቪላ ቤቶችና ደሳሳ ጎጆዎች  የተሞላች ፣ እና የአካባቢውም ውበት ፣ በእጅጉ የቆሸሸበት ሥፍራ   መኖሩ እንግዳ አይደለም ። እናም  ህገ ወጦች ባለ ጨረቃ ቤቱች ፣  ቢያንስ ግብር የሚገብሩበትን መንገድ መመቻቸት ወይም ወደ ህጋዊ መንገድ ማምጣት እንዲቻል የመፍትሄ አቅጣጫ ሊያሥቀምጡ የሚችሉት እነዚህ ምሁራን እንደሆኑ መገንዘብ ያሥፈልጋል  ።  ቆሻሻ በሚከማችበት የጎርፍ መውረጃም ከአካባቢው ባለሀብት ጋር በመነጋገር ፣ የጎርፍ መውረጃው ፣ ቆሻሻ በማይደፋበት መልኩ ፣ በወጉ  የማገነባበትን መንገድ ሊቀይሱ የሚችሉት እነዚህ ምሁራን ናቸው  ።

ይኽን የከተማዋን ገፅታ ያበላሸ ፣ ማሀል ከተማ ውሥጥ የሚታይ አሥጠሊታ ቆሻሻ ለማሶገድ ፣ መላው የከተማን ህዝብ አሥተባብሮ ወደ መፍትሄ መግባትን ተቀዳሚ ሥራው ከማድረግ ይልቅ ነገ በልማት አሥገዳጅነት የሚሥተካከሉትን እና ከሥራቸው ጋር የብዙ  ሺ ሠርቶ በሌዎችን ጉሮሮ የሚያረጥቡ ፣ የሥራ መድረኮችን መዝጋት በአሁኑ ሰዓት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነውና የብልፅግና መንግሥት ድህነትን ከማሥፋፋት  ና በፀሐይና በቁር አቦራ ለብሰው ጎንበስ ብለው ጫማችንን በማሣመር የሚተዳደሩትን ሊስትሮዎች እና ትኩስ ቡና ለደሃው አዘጋጅተው በርካሽ ዋጋ ጀባ የሚሉንን ወደ ድህነት አረንቋ ተመለሠው እንዲገቡ ከመጫን እንዲቆጠብ በፅኑ እንመክራለን ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

እመኑኝ፣ “ኦሮምያ” የተፈጠረችበትን ቀን ትረግማለች! – ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

Next Story

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘኢትዮጵያ የአፍሪካ አባት (ተረፈ ወርቁ ደስታ

Go toTop