አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
መስከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ ሸዋ
ከሰኔ 25 ቀን 2013 ጀምሮ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሌሊት ፌደራል ፖሊሶች ነን በሚል መታወቂያ ባሳዩ አካላት ታፍነው ወደ አዋሽ መልካ ከዛም ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ወደ ገላን የኦሮሚያ ፖሊስ ጣቢያ ተዛውረው በአደራ እስረኛ መልክ ታስረው የቆዩት አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ደራሲና የታሪክ ጸሀፊ ታዲዮስ ታንቱ ዛሬ መስከረም 25 ቀን 2014 ረፋድ ላይ ከእስር ተለቀዋል።
በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 9ኛ ፍታብሔር ችሎት በማቅናት አካልን ነጻ የማውጣት የአቤቱታ መዝገብ በጠበቃ በኩል ተከፍቶላቸው የነበሩት ታዲዮስ ታንቱ የፊታችን አርብ ቀጠሮ እያላቸው ነው ዛሬ የተፈቱት።
ጠዋት 2 ሰዓት ላይ በኦሮሚያ ክልል ከገላን ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ ካሉበት ልዩ እስር ቤት የመጡ አንድ ያላወቋቸው ባለስልጣን ስምና አድራሻ ከጠየቁ በኋላ “ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ ተለቀዋል” እንዳሏቸው ለአሚማ በስልክ ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ አቶ ታዲዮስን እቃቸውን ይዘው ከእስር እንዲወጡ በማድረግ ወደ ገላን መናኽሪያ በመኪናቸው ከወሰዱ በኋላ “ከዚህ ወደ ቃሊቲ ከዛም ሌላ ባስ ይዘህ ወደ አዲስ አበባ ግባ” እንዳሏቸው ጠቁመዋል።
ከተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ወገኖች ባደረጉት ጫና ስለመፈታታቸው የገለጹት አቶ ታዲዮስ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሆነው ድምጽ ለሆኗቸው፣ ለወዳጅ ዘመድ እና ለአድናቂዎቻቸው በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በቃላት ጫና ለመፍጠር እና ለማስፈራራት ከመሞከር ያለፈ በአካላቸው ላይ የደረሰ ድብደባም ሆነ አካላዊ ጉዳት እንደሌለ ነው አቶ ታዲዮስ የተናገሩት።
የጋዜጠኛ እና የደራሲ ታዲዮስን እስር በተመለከተ እንዴት ያዩታል ሲል አሚማ ባንድ ወቅት ያነጋገራቸው ጠበቃ አዲሱ ጌታነህ “ስለ ታዲዮስ እስር ጉዳይ በሕግ ቋንቋ ለማውራት ይቸግራል፤ የመጀመሪያው የህገ ወጥ እስር ቀጣይ ክፍል አሁንም የፍ/ቤቱን ትዕዛዝ ባለመተግበር እየተደገመ ነው” ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።