ለቸኮለ! መስከረም 4/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

September 13, 2021

1፤ የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ለመግዛት የሚፈልጉ ኩባንያዎች የሃሳብ መጠየቂያ ሰነዱን ወስደው በጨረታው እንዲሳተፉ ገንዘብ ሚንስቴር ዛሬ በድረገጹ ባወጣው ማስታወቂያ በይፋ ጋብዟል፡፡ ፍላጎቱ ያላቸው ኩባንያዎች የሃሳብ መጠየቂያ ሰነዱን ለማግኘት የማይመለስ 20 ሺህ የአሜሪካ ዶላር መክፈል እና ስለ ሚስጢር ጠባቂነታቸው ግዴታ በመግባት ማረጋገጫ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ሚንስቴሩ አስታውቋል፡፡

2፤ የአዲስ አበባ አስተዳደር የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር መሠረታዊ የፖሊስ ሥልጠና የወሰዱ 259 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን አሰልጥኖ እንዳሰማራ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል፡፡ በቀጣይ ሳምንታት ደሞ ተመሳሳይ ሥልጠና የሚወስዱ 27 ሺህ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን አስተዳደሩ እንዳዘጋጀ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች እቤቤ ተናግረዋል፡፡ አማጺው ሕወሃት በከተማዋ ሕዝባዊና ሐይማኖታዊ በዓላት ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት እንዳለው የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ በጎ ፍቃደኞቹ ሰላም አስከባሪዎች የሽብር ድርጊቶችን እንደሚያከሽፉ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

3፤ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የጋራ መርማሪ ቡድን በጸጥታ ችግር ሳቢያ በአክሱም እና በምሥራቅ እና ደቡባዊ ትግራይ ምርመራ ማድረግ እንዳልቻለ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ሚሸል ባቸሌት ትናንት በተመድ ሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ስብሰባ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ምክንያት ቡድኑ በማይካድራ የምርመራ ቆይታውን ለማሳጠር እንደተገደደ ባቸሌት ገልጸዋል፡፡ ግድያ፣ ዝርፊያ፣ የጾታ ጥቃት እና በምዕራባዊ ትግራይ እና አዲስ አበባ የትግራይ ተወላጆች ጅምላ እስር ዛሬም ቀጥሏል ያሉት ባቸሌት፣ ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች በሰብዓዊ መብት፣ የጦርነት ሕግጋትና የስደተኛ መብቶች ጥሰቶችን ፈጽመዋል ብለዋል፡፡

4፤ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ካውንስል በትግራዩ ጦርነት ላይ ያደረገው ውይይት የሉዓላዊ ሀገራትን ራስን ከጥቃት የመከላከል መብት ያላከበረ፣ ሕወሃትን እና ሽብርተኝነትን የሚያበረታታ ነው ሲሉ የኤርትራው ተወካይ በትናንቱ የካውንስሉ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል፡፡ ሕወሃት የኢትዮጵያ መንግሥትን ከገለበጠ በኋላ ኤርትራን ለመውረር ዝቷል ያለችው ኤርትራ፣ ሕወሃት በአማራና አፋር ክልል ለፈጸመው ግፍ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ጆሮውን አልሰጠም ስትል ወቅሳለች፡፡ የካውንስሉ ውይይት በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሠረተና ሕወሃት የችግሩ ዋነኛ ምንጭ መሆኑን ያላገናዘበ ነው- ብላለች የካውንስሉ አባል የሆነችው ኤርትራ፡፡

5፤ ልዩ ኃይሉን ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ የላከው አማራ ክልል ብቻ እንዳልሆነ የክልሉ ጸጥታ ቢሮ ለቢቢሲ አማርኛ ተናግሯል፡፡ ከአማራ ክልል በተጨማሪ፣ ደቡብ፣ ሲዳማ እና ጋምቤላ ክልሎች ልዩ ኃይሎቻቸውን የጸጥታ መታወክ ወዳለበት ቡለን ወረዳ እንደላኩ ቢሮው አረጋግጧል፡፡ ልዩ ኃይሎቹ ጸጥታ የሚያስከብሩት በዞኑ በተቋቋመው የፌደራሉ ወታደራዊ ማዕከላዊ ዕዝ ስር ነው፡፡ ክልሎች ልዩ ኃይሎቻቸውን ያሠማሩት፣ የሕወሃት ታጣቂዎች ከሱዳን ወደ ዞኑ ሰርገው ስለሚገቡ እና የሕዳሴ ግድብን ዒላማ ስለሚያደርጉ እንደሆነ ቢሮው አክሎ ገልጧል፡፡

6፤ የታንዛኒያ ፖሊስ ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን በሕገወጥ መንገድ በማስተላለፍ የጠረጠረውን አንድ ታንዛኒያዊ እንዳሠረ ዥንዋ ዘግቧል፡፡ ግለሰቡ ባለፈው ዕሁድ የታሠረው 16 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን በሕገወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ በመኪና ለማሻገር ሲሞክር እንደሆነ ዘገባው ጠቅሷል፡፡ ፍልሰተኞቹ ከ11 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው ተብሏል፡፡ ፖሊስ ሌሎች 6 ሕገወጥ ሰው አመላላሾችን በማደን ላይ ነው፡፡

7፤ የአሜሪካው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የወባ በሽታን ለመቅረፍ በወባ ትንኝ ላይ ተስፋ ሰጭ ምርምር እያደረገ መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል፡፡ ተመራማሪዎች የወባ ትንኝን ዘር መል በመቀየር በወባ ትንኝ ውስጥ ጥገኛ የሆነችውንና የወባ በሽታ የምታስከትለውን ሕዋስ መግደል ችለዋል፡፡ ዘረ መላቸው የተቀየረላቸው የወባ ትንኞችም ጥገኛ ሕዋሷን የሚገድለውን አዲሱን ዘረ መላቸውን ለሚፈለፍሏቸው ትንኞች እንደሚያስተላልፉ ተረጋግጧል፡፡ በሂደት የተቀየረ ዘረ መል ያላቸው ትንኞች እየተበራከቱ ሲሄዱ፣ ወባ በሽታን ወደ ሰው ማስተላለፋቸው ያበቃለታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

8፤ የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማዔል ኡመር ጌሌ በጽኑ ታመው በፓሪስ ሆስፒታል እየታከሙ ስለመሆኑ የተሰራጨው ወሬ ሐሰት ነው ሲሉ የጅቡቲው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር መሃሙድ የሱፍ በትዊተር ገጻቸው አስተባብለዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ከሥራ ብዛት ድካም ስለተሰማቸው በሕክምና ምርመራ እና ያጭር ጊዜ እረፍት ላይ ናቸው- ብለዋል ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ፡፡ ፕሬዝዳንቱ ወደ ውጭ መጓዛቸውን ያመኑት የሀገሪቱ ባለሥልጣናት፣ በጽኑ ታመዋል ተብሎ የተሠራጨው ወሬ ግን የጅቡቲን ሰላም ለማናጋት የታለመ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

geletaw
Previous Story

ሆሎዶሞር! የስታሊን ፍሬ! – ገለታው ዘለቀ 

241803647 3024971467745312 1690527828246735013 n
Next Story

በሠራዊቱ የጀግንነት ተጋድሎ የአሸባሪው ህወሃት ህልም ከንቱ የሆነበት የማይጠብሪ ግንባር

Go toTop