አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ወደ ራያ ለሚያደርገው መስፋፋት አጋዥ የነበሩ 5 የጥፋት ኃይሎች በጸጥታ ኃይሉ በቁጥጥር ስር ሲውሉ አንዱ ደግሞ እርምጃ እንደተወሰደበት ተገልጿል።
አራቱ በቆቦ ከተማ በተለያዩ ኃላፊነት ላይ ሲያገለግሉ የነበሩ መሆኑም ታውቋል፤ ከዚህ ውስጥ አንደኛው ግለሰብ የሬዲዮ መገናኛ ጭምር ተገኝቶበታል። መረጃ ሲያቀብልበት የነበረው የሬዲዮ መገናኛው በቁጥጥር ስር ሲውል ጁንታው ድንብርብሩ እንደወጣ የቆቦ ከተማ ሰላም እና ደኅንነት ኃላፊ ሃምሳ አለቃ አበበ ደርሶ ተናግረዋል።
ከአሸባሪው ግብረአበሮች በርካታ ገንዘብ፣ የሬዲዮ መገናኛ እና ሌሎችም መረጃዎች ተይዘዋል ነው ያሉት ኃላፊው። ሁለቱ ግለሰቦች ከጁንታው ጋር ሲዋጉ ቆይተው ከወገን ጦር ለመረጃ ተቀላቅለው ተገኝተዋል ብለዋል።
አንደኛው ወዲያው እርምጃ ሲወሰድበት አንደኛው ተማርኮ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በድምሩ አምስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ኃላፊው ገልጸዋል።
የበለጠ በመቀናጀት የሽብር ቡድኑን ድርጊት ማክሰም ተገቢ ነው ያሉት ሃምሳአለቃ አበበ፤ ጁንታው ከመሃል ትግራይ ሕጻናትን እየሰበሰበ ወደ ጦር እየማገደ ነው ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በወልዲያ ከተማ የሽብር ቡድኑ አባላት ሴተኛ አዳሪ መስለው ገብተው ተይዘዋል። ጉዳዮ ሲመረመር የጁንታው የልዩ ኃይል አባላት መሆናቸው የአንዳንዶቹ ተረጋግጧል።
መላው ማኅበረሰብ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ የሽብር ቡድኑን ጥፋት እንዲያመክንም ጥሪ ተላልፏል።
ዘጋቢ:- የሺሐሳብ አበራ
ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ)