አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ! (በላይነህ አባተ)

June 14, 2021

 

ዘር ልታጠፋ ልትጨርስ እህል ቡቃያን ስትፈጅ ኖራ፣
አልቅጥ ውጣ ሰልቅጣ ሆዷን እንደ ኳስ ቆዝራ፣
ጉዛሙ በስልት አድፍጦ ጪራሮ ይዞ ሲመጣ፣
ተወጣችበት ጉድጓዷ አይጥ ደንብራ ስትገባ፣
ደብቋት የኖረው ዳዋ ተመጠን በላይ ተመታ፡፡

ዳዋ ተልምድህ ተማር አትደብቅ አይጥና ሌባ፣
እርኩስን መደበቅ ትተህ መግብ በግና ኮርማ፡፡

በእህሎች ቅጥናት ወጥሮህ ተአይጥ ጋር ስትሸርብ ደባ፣
የመከራው ቀን ያልፍና የፍርድ ዘመን ሲመጣ!
አንተ ምን መደበቂያ አለህ አይጥ ጉድጓድ ስትገባ?

አረም ይሉኛል በማለት የእህልን ዘሮች ብትከዳ፣
ተአይጥ ጓጉንችር ተሻርክህ ስታስፈጅ ብትውል አዝመራ፣
በቁናህ መሰፈር አይቀር ዳዋ ሆይ የማታ ማታ!

ባይገባህ እንጅ ባትፈትሽ የአይጦችን የቦካ ሴራ፣
ቡቃያን ምች ሲመታው ቀን ክዶት በልግ ሲጠፋ፣
የአይጦች አፍ ዳዋን ጨርጋጅ ነው ታሪክን ፈትሽ አጣራ፡፡

የዳዋ ራስ ቅል መንፈሱ ተዝቅተኝነት ሳይጠራ፣
እርኩስ በውስጡ ደብቆ እህል አዝመራ ሲያስበላ፣
ጭራሮ አይጥን ሲያባርር አይጥም ጉድጓድ ውስጥ ሲገባ፣
ዘመን ዑደቱን ቀጥሏል አይጥ በበላ ዳዋ ሲመታ፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ሰኔ ሁለት ሺ አስራ ሶስት ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

202206062 10220570568475975 5592884827289968827 n
Previous Story

አስከፊው አድርባይነት ዛሬም ከዋነኛ የፖለቲካ ደዌዎቻችን አንዱ ሆኖ ቀጥሏል ! – ጠገናው ጎሹ

tewedros getachew
Next Story

ልዕለ-ኃያልነት (ያስረካቢ፣ ተረካቢና ያረካካቢዎች ትራጄዲ!!) –   ቴዎድሮስ ጌታቸው-ድሬዳዋ   

Go toTop