ይህችም ቀን ታልፋለች (ዘ-ጌርሣም)

May 13, 2021

እንዳለፉት ጊዜያት
ለረዥም ዘመናት
ሰው እንደኖረበት
ኖሮ እንዳለፈበት
ገድል አስመዝግቦ
ታሪክን አድልቦ
ደጉንም
ክፉንም
ጥላቻን
ፍቅርን
ማግኘትን
ማጣትን
መጥገብን
መራብን
ከአገር መሰደድን
ተዋርዶ መኖርን
መታመም መሞትን
ታሞ ማገገምን
ሁሉንም በቅጡ
እንድየ አመጣጡ
እንዳስተናገደው
በአግባቡ እንደሸኘው
ይህችም ቀን ታልፋለች
አክብረን ካልያዝናት ታስተዛዝባለች
ትዕግሥቷ ሲሟጠጥ
ስንገፋት ያለቅጥ

መገንዘብ አቅቶን
ስንጋብዝ መከራን
ለጠላት በማገዝ
አገርን ስናወግዝ
በዓይናችን እያየን
ሲያልቅብን ሕዝባችን
ዙሪያውን ተከበን
በጠላቶቻችን
ምጡ ጨክኖባት
የአገራችን ጩኸት
አዋላጅ በማጣት
ድረሱልኝ ብላ ስትጮኽ እያየን
ጆሮ ዳባ ልበስ አልሰማነም ብለን
ጦር አውርድ በማለት መከራ እንጠራለን
ይህችም ቀን ታልፋለች
አክብረን ካልያዝናት ታስተዘዝባለች
ትዕግሥቷ ሲሟጠጥ
ስንገፋት ያለቅጥ
ጨለማው ይበራል
ድፍርሱም ይጠራል
የአገር ጠላት ያፍራል
ጀግኖችን ያኮራል
በጊዜ ዳኝነት
ፍርዱን ቆሞ ማየት
የማይቀር ሐቅ ነው
በቅርብ የምናየው
ሕዝባችን እንደሆን
ለምዶታል መከራን
መፍትሄው አንድ ነው
አማራጭ የሌለው
እንደ አባቶቻችን
እንደ እናቶቻችን
በጋራ አብረው ቆመው
ጠላትን መክተው
መቁሰልን
መሞትን
የመጣውን ሁሉ
የኔ ነው ሳይሉ
እንደየ አመጣጡ ሁሉን አጣጥመው
ክፉ ቀንን ሳይቀር አብረው አሳልፈው
ለእኛ ሲሉ ሞተው
አገር አቆይተው
ትውልድን ተክተው
ለአስረከቡን ሀገር
ልንሆን ይገባናል ጨፈቃና ማገር
የጊዜው ግርግር የትም ላያደርሰን
በታሪክ ተወቃሽ ቆይቶ እንዳያደርገን
ማሰብ ይገባናል መልሰን መላልሰን
ማፈስ ስለሚከብድ የፈሰሰ ውሃን
የእግር እሣት ሆኖ እንዳያቃጥለን
እናስተውል ከልብ መልሰን መላልሰን
ይህችም ቀን ታልፋለች
አክብረን ካልያዝናት ታስተዛዝባለች
ትዕግሥቷ ሲሟጠጥ
ስንገፋት ያለቅጥ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

dembi dollo 1024x576
Previous Story

በዛሬይቷ ኢትዮጵያ መኖር ይቅርና መሞትም አልቻልንም አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)

“እረኛ የሌለው ከብት ሆነናል” የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች ሰቆቃ ግድያና እንግልት
Next Story

“እረኛ የሌለው ከብት ሆነናል” የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች ሰቆቃ ግድያና እንግልት

Go toTop