የኔ ውብ ከተማ (ዘ-ጌርሣም)

October 10, 2020

ገና በልጅነት
በታዳጊው ስሜት
በነበረኝ ምኞት
ካርታዋን በልቤ ቀርጨ የሳልኳት
የኔ ውብ ከተማ የምድራችን ገነት
እንዲህ ትመስላለች
በውበቷ ምህሣሳብ ከሩቅ ትጠራለች
ሁሌም የምመኛት
መምሰል የሚገባት
እንደ አዲስ ሙሽራ ሆ ! በሉ እያሰኘች
በአጃቢ ሚዜዎች እንደተከበበች
ከቤቷ ሳትወጣ ገና ጫጉላ እንዳለች
ታዳሚው ሳይገባ የተሽሞነሞነች
ለሌሎች ከተሞች ትምሳሌት የሆነች
ጣፍጩ ዉኃዋ
የውስጥ መዓዛዋ
አልባብ አልባብ ሲሸት
እንደ ቤተ መንግሥት
በሚያምሩ ተራሮች ዘብ በሚጠብቁ
ምንጮች የሞሉባት የሚፍለቀለቁ
ሁለቱ ጅረቶች ጎን ለጎን ሲፈሱ
ያካባቢን ልማት ህይወት እያደሱ
ከሩቅ ይጣራሉ
ቤት ለእንግዳ ብለው ያስተናግዳሉ
የኔ ውብ ከተማ እንደዚህ ታምራለች
በፍቅር ኑሩብኝ ብላ እየጋበዘች
በመንገዶች ጥራት
በመብራቷ ውበት
ደምቃ የምታይዋት
በአራቱም ማዕዘናት
ለዕድገት በመነሳት
ሰላምን ትራሷ
አንድነትን ልብሷ
ልማትን ብርታቷ
ታሪክን ኩራቷ
አምራቹን አርክታ
ሸማች አስደስታ
አብራ የምታኖር
ያለምንም ችግር
እንደ አንድ ቤተሰብ
እንደ ሚተሳሰብ
ካባ እንደለበሰ
እንደተወደሰ
አምራና ተውባ
ቀዝቃዛውን አየር ከተራራው ስባ
ለቆላማው ምድር እስትንፋስ መግባ
ታስተናግዳለች ሁሉን አስመችታ
እስኪ ዳቦ እንቁረስ ስም ብታወጡላት
ንገሩኝ ልክተበው ማን ብለን እንጥራት
በውበት ላይ ውበት የተሽሞነሞነች
እንደ ንጋት ኮከብ ደምቃ ትታያለች
መጥታችሁ ኑሩብኝ ብላ እየጋበዘች
የኔ ውብ ከተማ ግብዣዋን ልካለች

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

“ላጉርስህ ሥትለው ልንከሥህ ካለህ ምን ትለዋለህ ??… “  መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Next Story

አንድ አፍታ ከኢትዮጵያውያን ወታደሮች ጋር በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል… በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

Go toTop