ተመስገን እንበል (ዘ-ጌርሣም)

August 15, 2020

ተመስገን ፈጣሪ ሌላ ምን ይባላል
ሰው የሰጠው ቢሆን ዋጋ ያስከፍላል
ከምስጋና በቀር የማትፈልግ ሌላ
በአንድ ላይ ተንሰስተን እንግባ ምህላ

እናመስግን አንተን
ከፍ ከፍ አድርገን
እንባችን ይታበስ
ኢትዮጵያ ትወደስ

ከፍ ብላ በልፅጋ በዓይናችን ልናይ ነው
ችግሮች ሲጠፉ ትውልድ ደስ ሲለው
ውጡ እናመስግነው ወገኖች በሙሉ
የኢትዮጵያ ትንሣዔ ገሃድ ሁኗል አሉ

የአባይ ግድብ አልቆ መሞላት ጀምሯል
ምኞት የነበረው ይኸው በዓይን ታይቷል
የጨለማው ዘመን ሊገፈፍ ተቃርቧል
አኬሩን በእጃችን ቁጭ አድርጎልናል
እወቁበት ይላል የመጣልን ዕድል
ተግባብተን በመኖር እንድንሆን ድል በድል

ደህና ሁን ጨለማ ደህና ሁን ፅልመት
አባይ ሊያበራ ነው ከዓመት እስከ ዓመት
እልል በል ወገኔ በአራቱም ማዕዘናት
ደስታችን ታወጀ ተነገረ ብሥራት
የተጫወተብን ያ ጨለማ ዘመን
ሊገፈፍልን ነው ልናየው በዓይናችን

እንኳን ደስ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ
የአባይ ግድብ ሙሊት ዕውን ሁኗል አሉ
ተመስገን አምላኬ ተመስገን ድጋሜ
ይህን በማየቴ ሳልሞት በአካል ቁሜ
በማለት እንፀልይ እናመስግን ጌታን
ምስጋናም ይግባቸው ለዚህ ድል ላበቁን

በውሃ ሙሊት ብቻ አይቆምም ደስታችን
በአራቱም ማዕዘናት ሳትበራ አገራችን
ልናያት ቅርብ ነው አረንጓዴ ለብሳ
ለችግኝ ተከላው ሁሉም ከተነሳ
በልፅጊ አገራችን በረክተሽ ይሙላ
እኛም እንድንኖር በደስታ በተድላ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የኢትዮጵያ ልክ ከግቢ እስከ ሀገር (የአብይ ቪደኦ)

Next Story

ዝምታ ወርቅ አይደለም – ከአባዊርቱ!

Go toTop