ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም በሀገሪቱ የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ ለመምከር እና ገዥ ሐሳቦችን ለመለዋወጥ ለ3ኛ ጊዜ በመከሩበት ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እንደሚገኙ ቀደም ሲል ተገልጾ የነበረ ቢሆንም ሳይገኙ ቀርተዋል::
https://www.youtube.com/watch?v=9_PNwyW18Qg
ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ስብሰባ ላይ ባይገኙም ድርጅቱን ወክለው አቶ ብናልፍ አንዷለም እና የፕሬስ ሴክረተሪያቸው አቶ ንጉሡ ጥላሁን ተገኝተዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ሰብሰባ ላይ በመገኘት እንደተለመደው የለገጣፎውን እና ወቅታዊውን የሃገራችን ጉዳይ በተመለከተ ይናገራሉ ተብሎ ሲጠበቅ ነበር::
በሌላ በኩል ዛሬ የተደረገው ውይይት በፓርቲዎች በኢትዮጵያ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወደ አንድ ምዕራፍ ለማሸጋገር በር የከፈተ መንገድ ነው በተባለው በ3ኛው ዙር ምክክር በአራት ሐሳቦች ላይ ጽሑፎች መቅረባቸው ተሰምቷል::
“ሀገረ መንግሥትና- ብሔረ መንግሥት ግንባታ በኢትዮጵያ ፈተናዎችና የግንባታው ስትራቴጅ ምን ሊሆን ይገባል?” በሚል ጽሑፍ ኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በጽሁፋቸውም ‹‹ጠንካራ ሀገር መገንባት ያልቻለ ሕዝብ ትልቅ ሀገር ሊኖርው አይችልም:: ሀገረ መንግሥትን ከሥርዓተ መንግሥትና ከመንግሥት አስተዳደር ነጥሎ በማየት በኩል ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ አገር ያፈርሳል›› ሲሉ ተናግረዋል::
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ‹‹የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የተማሪዎች ሚና በአንድ ሀገር የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ምን ይዘት ሊኖረው ይገባል›› በሚል ጽሑፍ አቅርበው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰው ኃይል ማፍራት እና ዕውቀት ማስረጽ ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ሥርዓትን የማስረጽ ግዴታም እንዳለባቸው ተናግረዋል::
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር አመራር ዶክተር ዲማ ነገዎ ባቀረቡት ጽሁፍም ‹‹በሀገሪቱ የፖለቲካ አደረጃጃት ውስጥ ሕዝብን አንድ የሚያደርጉ ሥራዎች ሊቀድሙ ይገባል ነው›› ብለዋል:: እንዲሁም የአረና ለትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ‹‹የመናገር ነጻነትና ማኅበራዊ ሚዲያ›› በሚል ባቀረቡት ጽሁፍ ኢትዮጵያ የሐሳብ ነጻነትን ለማረጋገጥ ነጻ የሆኑ ተቋማት ሊኖሩ እንደሚገባ ገልጸዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ከትናንት በስቲያ የአዲስ አበባ አዲሱ ፕሮጀክት ለሕዝብ ይፋ ይሆናል በተባለበት ወቅት እንደሚገኙ ቢገልጽም ሳይገኙ ቀርተዋል::
በሌላ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በጽህፈት ቤታቸው ከኦብነግ አመራሮች ጋር መወያየታቸው ታውቋል:: ኦብነግ እንደገለጸው በለውጡ ዙሪያ በቀጣዩ ምርጫና ሕዝብና ቆጠራ እንዲሁም በሌሎች ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያየተዋል::