ዛሬ በባህርዳር ስታዲየም 0ለ0 የተጠናቀቀውን የባህርዳር ከነማን እና የአዳማ ከነማን ጨዋታ ለማየት የገቡ ተመልካቾች የተከያዩ መፈክሮችን በስታዲየሙ ይዘው በመግባት ሃሳባቸውን ሲገልጹ ውለዋል::
በያዙት መፈክርም መከላከያ ከጎንደር እንዲወጣ የጠየቁ ሲሆን; ለጎንደር ጥቁር እለብሳለሁ; ፍትህ ለጎንደር አማራ ሕዝብ; ክልሉን እያስተዳደረ የሚገኘው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) አማራን አይወክልምና ሌሎችንም መፈክሮች አሳተዋል::
https://www.youtube.com/watch?v=mk2qgm5fFUY
በሌላ በኩል የአማራ ክልላዊ መንግስት የደህንነትና ሰላም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ሰሞኑን በጎንደር ስለተፈጸመው ጥቃት ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ቃል ” ከሰሞኑ በማእከላዊ ጎንደር ጥፋት ያደረሰው ኃይል በሁለት ከፍተኛ ቡድኖች የተደራጀ፤ የታጠቀና ስምሪት የተሰጠው ኃይል ነው፡፡ አንደኛው ቡድን ቤቶችን የሚያቃጥል ሲሆን ሁለተኛው ቡድን ደግሞ የመጀመሪያው ቡድን እንቅፋት ቢያጋጥመው ሊከላከል በሚችልበት ሁኔታ የተዘጋጀ ነበር፡” ብለውታል::
ጀነራሉ አክለውም “የተቀናጀውና የተደራጀው ኃይል በሁለት አቅጣጫ ነው የመጣው፡፡ አንደኛው ቡድን ከ200 በላይ ፤ሁለተኛው ከ70 እስከ 80 ሰው የሚገመት የታጠቀና የተደራጀ ሃይል እንደነበረው ይገመታል፡፡ ብሬንና ድሽቃ የተባሉ የቡድን ከባድ መሳሪያዎችን ተጠቅሟል፡፡ ይሄን መጠቀም የሚችለው የሰለጠነና ፕሮፌሽናል የሆነ ኃይል ብቻ ነው፡፡” ያሉ ሲሆን እነዚህ ወገኖች በድንገት በሰነዘሩት ጥቃት ከ30 በላይ ሰው ሕይወት ማለፉን እና ከ300 በላይ የአርሶ አደር ቤቶች መቃጠላቸውን ገልጸዋል::
“ጥቃቱን የፈጸመው ከሌላ ቦታ በተለይ ከምእራባዊ ጎንደር አቅጣጫ ተጭኖ በተለየ መንገድ ሰርጎ የሚገባ ኃይል ነው፡፡” ያሉት ጀነራሉ ይህ ብቻ ሳይሆን በከሚሴ አካባቢ ከጎንደሩ ጋር በተመሳሳይ ወቅትና በተቀናጀ መንገድ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ የሰው ሕይወት አልፏል፡፡ አውራ ጎዳናዎች ለመዝጋት ተሞክሯል ብለዋል:: ከፍተኛውን አደጋ የመከላከል ስራ የሰራው መከላከያ ሰራዊት ነው፡፡ የተዘጉትን መንገዶች በሙሉ አስከፍቷል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል::